>

 ፕሮፌሰሩን ለቀቅ አድርጉት !!! (አፈንዲ ሙተቂ)

 ፕሮፌሰሩን ለቀቅ አድርጉት !!!
አፈንዲ ሙተቂ
 
*  “ከዶክተር አቢይ መንግስት ጋር መስራት እንፈልጋለን” በማለት ወደ ሀገር ቤት የገቡትን አቶ ሌንጮ ለታን “የኦሮሞ ህዝብ ትግልን የሸጠ ከሃዲ ነው” እያሉ የምናከብራቸውን ሰውዬ እንደ መንደር አለሌ ወረዱባቸው። ከዚም ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በሚዲያ የተናገሩትን ነገር እንዳሻቸው እያጣመሙ “ዳውድ የወያኔ ምንደኛ ነው” በማለት ሌላ ታሪክ አመጡብን። አሁን ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የሚያውቀውን ሁሉ ሳይሰስት ያስተማረንን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እንደ መንደር ጎረምሳ እያንጓጠጡት ነው።
እኛ ቀለም የቀመስነው ኢትዮጵያዊያን ሰልጥነናል እንላለን። ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ከስልጣኔ ጋር ሆድና ጀርባ ነን። ይህንን ከሚያስረዱት ዓይነተኛ አብነቶች አንዱ ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንደ ጠላት የምንፈርጅ መሆናችን ነው።
ያለፉት መንግስታት በዚህ አቋማቸው ሺዎችን ጨርግደው ጨረሱ። “መንግስት ነኝ” የማይለው ክፍልስ በየዘመኑ የእንዲህ ዓይነቱ በሽታ ተጠቂ ሆኖ ሲገኝ ምን ይባላል? ይሄኔ “እምቦጭ እንዘጭ” ማለት!
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ “የአርበኞች ግንቦት ሰባት” ንቅናቄ ሊቀመንበር ነው። ፓርቲው የሚታገልበት የፖለቲካ መስመርም በግልፅ ይታወቃል። ሚሊዮኖች የእርሱንና የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም ይደግፋሉ። የፓርቲውን አመለካከት የሚቃወሙም እንደዚያው ሚሊዮኖች ናቸው። በአመለካከትና በአቋም መለያየት የተፈጥሮ መብት ነው። ይህ መብት በየትኛውም ጊዜና ስፍራ መከበር አለበት።
—-
ታዲያ በአመለካከት መለያየት ለጠላትነት ይዳርጋል እንዴ? እንዲህ ዓይነት ነገር ሀገራችንን የባሰ ያተረማምሳታል። አሁን የተገኘውን ድል እና እፎይታ ለመቀልበስ ለሚራወጡት ማጅራት መቺዎችም ሃይለኛ ዱላ ማቀበል ነው የሚሆነው።
—–
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጣም የምናውቀው ሰው ነው። እዚህ ፌስቡክ ላይ ስለእርሱ የሚጻፈው አሉታዊ ነገር ሁሉ ለእኛ ባዳ ነው። አብዛኛው ሰው ደግሞ ልብ ወለድ ተረት እየፈጠረ ነው እርሱን የሚያወግዘው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ዛሬ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ እርሱን ባወቅኩበት ዘመን እንኳ አሁን የሚራምደውን የፖለቲካ አመለካከት ነው የሚያንፀባርቀው። በዚህ ላይ የተለየ ለውጥ አላሁበትም።
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዩኒቨርሲቲው ካስተማሩኝ ምሁራን መካከል በተሻለ ሁኔታ ዲሞክራት እና ለሌሎች አመለካከት ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን አውቃለሁ (ከዩኒቨርሲቲው ደመወዝ ሳይቀበል በነፃ የሚያስተምር መሆኑም ሳይነዘጋ ማለት ነው)። ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ካለው ፅኑ እምነት የተነሳ የፈተና ወረቀት ለተማሪ መመለስ የጀመረው እርሱ ነው። በዚያ ወቅት እርሱ ከሚያስተምራቸው ኮርሶች በስተቀር ሌሎች ትምህርቶችን የተፈተንባቸውን ወረቀቶች አናገኘም ነበር። እኛ በ1992 ከተመረቅን በኋላ ነው ዩኒቨርሲቲው ያንን አሰራር እንደ መመሪያ ወስዶ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ያዘዘው።
በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበሩ ብዙ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች “በኢትዮጵያ ውስጥ ጎሳ እና ነገድ እንጂ ብሄር እና ብሄረሰብ የለም” በሚሉበት ዘመን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኢትዮጵያ የብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ሀገር እንደሆነች ይናገር ነበር። የጉራጌ ብሄረሰብ ተወላጅ መሆኑንም የሰማነው ከራሱ አንደበት ነው።
እኔ እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ የማንግባባው በሁለት ነገሮች ነው። አንደኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በብሄር ተደራጅቶ መታገልን ይቃወማል።  ሁለተኛ “ብሄርና ቋንቋን መሠረት ያደረገው የክልሎች አወቃቀር የግለሰቦችን መብት ይደፈጥጣል፣ ለግጭት እና ለብተና ይዳርጋል” የሚል እምነት አለው። በዚህ ላይ ከእርሱ ጋር ከፍተኛ ልዩነት አለኝ። ነገር ግን ለአንድም ቀን እንደ ጠላቴ አይቼው አላውቅም።
—–
ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ወጣ ስንል ደግሞ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ወያኔን ሲታገሉ በኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚደነቁለት በርካታ ነገሮች አሉት። በምርጫ 97 ወቅት ወያኔን ለከባድ ቀውስና ድንጋጤ የዳረገውን “ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ” በመመስረት ሂደት በግለሰብ ደረጃ የአንበሳ ድርሻ የነበረው እርሱ ነው (ከቅንጅቱ ምስረታ በፊት መኢአድና ኢዴፓ በከረረ ጥል ላይ ነበሩ። ሁለቱን አስታርቀው ወደ ቅንጅቱ የቀላቀሏቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ነበሩ)። ፕሮፌሰር ብርሃኑ የቅንጅቱ የምርጫ ዘመቻ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እጅግ ውጤታማ የሆነ ስራ መስራቱም በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል።
በተለይ ግን በሬድዮና በቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፉት የምርጫ ክርክሮች ላይ የኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣኖችን እንዴት ሲያዋክባቸው እንደነበር ዛሬም ድረስ በአብነት እየተነገረ ነው።
በምርጫው ማግስት ለእስር የተዳረገው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ የጻፈው ቃሊቲ ሆኖ ነው። ያ መጽሐፍ እኛ  የማናውቃቸውን በርካታ የወያኔ ሚስጢሮችን ያጋለጠ መሆኑ ይታወቃል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ውጪ ሀገር እንደተሻገረ ሁሉንም ሰው ያነቃ አንድ ትልቅ እውነታ ተናግሮ ነበር። ይህም “ወያኔ በህዝባዊ ምርጫ የሚወዳደርበት ተፈጥሮ የለውም። ይህ ሀገር አጥፊ ቡድን በህዝባዊ አመጽ፣ አሊያም በትጥቅ ትግል ካልሆነ በስተቀር በምርጫ ከስልጣን አይወርድም” የሚል ነበር።
 ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያኔ የተናገረው ነገር ብዙዎች ለትግል እንዲነሳሱ አድርጓል። እሱና ጓዶቹም “ግንቦት ሰባት የነፃነትና የፍትሕ ንቅናቄ” የተሰኘውን ድርጅት በመመሥረት ወደ ህዝባዊ ትግሉ ገብተዋል።
—–
እነሆ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ወያኔ ተንኮታኩቷል። ፕሮፌሰር ብርሃኑና ጓዶቹም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። የእርሳቸው ፓርቲ፣ በዶክተር መረራ የሚመራው ኦፌኮ፣  በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ኦዴፓ እና አዴፓ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በቀጣዩ “ምርጫ 2012” ዋነኛ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከህዝብና መንግስት የሚጠበቀው ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን መወጣት ነው።
—-
ታዲያ በየመንደሩ እንደ አሸን የፈሉ ወጀላቴዎች የማያውቋቸውን እንደ ሰማይ የራቋቸውን ግለሰቦች በቅንጭብጫቢ መረጃ ብቻ እንደ ሀገር ጠላት ሊፈርጇቸው የሚነሱበት ድፍረት ይደንቃል። እነዚህ ወጀላቴዎች በቅድሚያ “ከዶክተር አቢይ መንግስት ጋር መስራት እንፈልጋለን” በማለት ወደ ሀገር ቤት የገቡትን አቶ ሌንጮ ለታን “የኦሮሞ ህዝብ ትግልን የሸጠ ከሃዲ ነው” እያሉ የምናከብራቸውን ሰውዬ እንደ መንደር አለሌ ወረዱባቸው። ከዚም ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በሚዲያ የተናገሩትን ነገር እንዳሻቸው እያጣመሙ “ዳውድ የወያኔ ምንደኛ ነው” በማለት ሌላ ታሪክ አመጡብን። አሁን ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የሚያውቀውን ሁሉ ሳይሰስት ያስተማረንን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እንደ መንደር ጎረምሳ እያንጓጠጡት ነው።
እነሱ ምን ያደርጉ! ይህ ፌስቡክ የሚባል በርና መስኮት የሌለው በረንዳ ባይኖር ኖሮ በማይመጥናቸው ሰው ላይ እንደ ውሻ አፋቸውን አይከፍቱም ነበር።
—–
በነገራችን ላይ፣
የሚከተሉትን ድንቅ መጻሕፍት ለማንበብ የቻልነው በፕሮፌሰር ብርሃኑ አነሳሽነት መሆኑን ታውቃላችሁ? አዎን! እውነት ነው።
1. ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የጻፈው “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር”
2 Das Kapital ( Karl Marx)
3 How Europe Underdeveloped Africa (Walt Rodney)
4 ሌሎች በርከት ብዙ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መጻሕፍት
ታዲያ መጻሕፍቱን በማንበብ ብቻ አልታቀብንም። በአንዳንዶቹ ላይ የኢኮሚክስ መነፅርን ተንተርሰን ሂስ እንድንጽፍባቸው በፕሮፌሰር ብርሃኑ እንታዘዝ ነበር (ለምሳሌ በካርል ማርክስ መጽሐፍ ላይ ባለአምስት ገጽ ሂስ መጻፌን አስታውሳለሁ)። እንደዚያ ዓይነቱ የትምህርት አሰጣጥ ጠቃሚነቱ የታየን በኋለኛው ዘመናችን ነው።
—-
በመጨረሻም:
ባለፉት አራት ወራት በዚሁ ግድግዳ ላይ ስለ ኦቦ ሌንጮ ለታ፣ ዶክተር መረራ ጉዲና፣ ስለኦቦ ዳውድ ኢብሳ እና ስለአክቲቪስት ጀዋር መሐመድ አዎንታዊ ነገሮችን ስጽፍ ነበር። ታዲያ ዛሬ  ስለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ስጽፍ ያየኝ ሰው ከኦሮሞ ታጋዮች ካምፕ ኮብልዬ ወደ ሌላ ካምፕ የገባሁ ሊመስለው ይችላል። አልተገናኝቶም!!
እኔ ሁልጊዜም የምወግነው ከእውነት ጋር ነው። ሰዎች የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሲሆኑ “እውነት ነው” ብዬ የምቀበልበት ህሊና የለኝም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለህዝባቸው መብትና ነፃነት የታገሉ ጀግኖቻችን በሙሉ የሚገባቸውን ክብር ማግኘት አለባቸው ብዬ አምናለሁ።
እነዚህ ሰዎች የሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት ላይጥመን ይችላል። ሆኖም ወያኔ ህዝቡን በቅኝ ግዛት ይዞ የደም እምባ በሚያስለቅስበት ዘመን የብዙኃን ድምፅ ሆነው በዓለም ዙሪያ ሲጮኹልን የነበሩ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም።”
Filed in: Amharic