>
5:13 pm - Monday April 19, 3813

ትግራይ እና እስረኞቿ 3231 እስረኞችን ፈታሁ እያለች ነው!!! (ዘመድኩን በቀለ)

የኔታስ ተፈተው ይሆን? 
ትግራይ እና እስረኞቿ 3231 እስረኞችን ፈታሁ እያለች ነው!!!
ዘመድኩን በቀለ
ትናንት ከወደ መቀሌ”ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቲ ትግራይ 3231 ተሃነፅቲ ብይቅሬታ ክፍትሑ ወሲኑ።” የሚል ደስ ዝብል ዜና ሰምቼ እጅግ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር የዋልኩት፣ ያመሸሁትም። ህውሓት ልብ ገዝታ ይሁን ወይም ደንገጧ ብቻ ለጊዜው ባይገባኝም ትናንት አደረገች የተባለው የእስረኞችን የመልቀቅ ዜናዋን ግን ወድጄላታለሁ። ይበል የሚያሰኝም ነው!!!
መጣ የተባለው ለውጥ ከመጣ በኋላ እንኳን ሌሎች ክልሎች በገፍና በግፍ ያሰሯቸውን እስረኞች ሲፈቱ እንቢኝ ብላ እስረኛ ሳትፈታ የቆየችው የአጅሬ ህውሓቷ ትግራይ ብቻ ነበረች። 18 ዓመታት የተፈረደባቸው የዓረና ፓርቲ አመራሮች እንኳ እስከ ትናንት ድረስ ስለመፈታታቸው መረጃዎች አልወጡም። የዐማራው፣ የኦሮሞው፣ የደቡቡና የሶማሌ ብሔር መንግሥታት እግር ቆርጠው፣ ዐይን አፍርጠው፣ ብልት አኮላሽተው፣ ኩላሊት አፍርሰው፣ ትዳርና ቤተሰብ በትነው መለመላቸውን ያስቀሯቸውን እስረኞች በይፋ ሲፈቱ ትግራይ ብቻ ነበረች እስረኞቿን ከምድር በታች እንደ ወይን ቀብራ፣ እንደ ቋንጣ አድርቃ አከማችታ የቀረችው። ምድረ ሳዲስት ሁላ።
እንዲያውም የፌደራል መንግሥቱ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ እነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታቱ ጭምር “ሕገ መንግሥት ተጣሰ፣ አሸባሪዎችም ተፈቱ ” በማለት ትግራይ ብቻዋን ነበር ጭርጭር ብላ ፀጉሯን እየነጨች ደረቷንም እየደቃች ሙሾ ስታወርድ የከረመችው። ኮሎኔል ደመቀ ለምን ይፈታል? ብልት ላይ ሃይላንድ አንጠልጣዩ ሕጋችን ተጣሰ፣ ሰዶም የምንፈጽምባቸው እስረኞች ለምን ይፈታሉ? ዓይነት ልቅሶ ነበር ከወደ ህወሓት መንደር ይሰማ የነበረው የሐዘን እንጉርጉሮ።
ለወትሮው እስረኞች የሚፈቱት አዲስ ዓመትን በማስመልከት የነበረ ቢሆንም “የጨነቀለት” በመምጣቱ ግን አጅሬ ህወሓት “#በህዳር_ገብርኤል_ዋዜማ ” ህዳር ጽዮንን እንኳ ሳትጠብቅ ከ3 ሺ በላይ እስረኞችን ለመፍታት መገደዷንና መወሰኗን ነው ስታወጅ የዋለችው።
የእኔ ጥያቄ ግን ወዲህ ነው። ትናንት ከወደ ትግራይ በተሰማው “ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቲ ትግራይ 3231 ተሃነፅቲ ብይቅሬታ ክፍትሑ ወሲኑ።” በሚለው ዜና ውስጥ ከ1986 ዓም ጀምሮ አጅሪት ህወሓት ለተከታታይ 25 ዓመታት በትግራይ ምድር በግፍ ያሰረቻቸውን የጎንደር ዐማራውን የደብረታቦሩን ሊቅ የኔታ እንደሥራቸው አግማሴ ከሚፈቱት እስረኞች መካከል ይኖሩ ይሆን ወይስ አሁንም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ለሚቀጥሉት ዓመታትም እዚያው በትግራይ ምድር ወኅኒ ቤት ይቆለፍባቸው ይሆን? ተፈቱ የተባሉት የዓደዋ፣ የሽሬና የአክሱም ትግሬዎች ብቻ ናቸው ወይንስ የራያና የወልቃይት ዐማሮች፣ የአገው ዐማሮቹ ተንቤኖች፣ የሰብዓ እንደርታዎቹ መቀሌዎች፣ እና ምስኪኖቹን ኢሮብ ተወላጅ ምስኪን እስረኞችን ያካትታል?
እኔ ግን እላለሁ ትግራይ ሰላም እንድታገኝ፣ በረከትና ረድኤትም እንድታገኝ፣ በእንቅልፍ ልቧም አስሬ ስትባትት ከማደር እንድትገላገል ከፈለገች ሁለት ዓበይት ተግባራትን በአስቸኳይ ብትፈጽም ሸጋ ይሆንላታል ባይ ነኝ።
፩ኛ፦ በሚሊዮኖ ዜጎችች ላይ ግፍ የፈጸሙ፣ ሀገር የሠረቁ፣ ሰዶምና የሰዶም ተግባር በእስረኞች ላይ የፈጸሙ ቆሻሻና በከዘራ የሚንቀሳቀሱ ግፈኛ ሽማግሌ ወንጀለኞቿን ከሸሸገችበት ጉያ አውጥታ በአስቸኳይ ለፍርድ ብታቀርብ፤ በረከትና ታደሰ ጥንቅሹን ይጨምራል።
፪ኛ፦ ያለምንም በደል ለ25 ዓመታት በግፍ ያሰረቻቸውን የደብረ ታቦሩን የአቋቋም መምህርና ሊቁን የዜማ ደራሲ መምህር እንደሥራቸው አግማሴን ጨምሮ በግፍ የታሠሩ የወልቃይት፣ የራያና የተንቤን ተወላጆችን ብትፈታ ለትግራይ ለምድሪቱ ራሱ ስርየት ይሆንላታል።
ያለበለዚያ ግን ጥቂቶች እየፎከሩ ሚሊዮኖች እየተጨነቁ እንቅልፍ እና በረከት ጤናም አጥተው የሚኖሩባት ምድር  ሆና ነው የምትቀረው። በግፍ የታሰረው የአንዱ ጻድቅ ሰው እንባ ገና ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላዋን ኢትዮጵያን ጭምር ዋጋ ሳያስከፍል የሚቀር አይመስለኝ።
እናም እኔ ግን እላለሁ። ” ፍቱ እንድትፈቱ ” ።
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic