>
2:06 pm - Thursday December 8, 2022

ሌባ በካቴና ተጠፍሮ ይቀርባል እንጅ ዘሩ "ከወርቆቹ" ስለሆነ "ጉሮ ወሸባየ" አይባልለትም!!! (ሻምበል ካሳ)

ሌባ በካቴና ተጠፍሮ ይቀርባል እንጅ ዘሩ “ከወርቆቹ” ስለሆነ “ጉሮ ወሸባየ” አይባልለትም!!!
ሻምበል ካሳ 
* ለደብረፂዮን አድርሱልኝ :-
ሀገር እና ህዝብ የመዘበረ በየትኛውም የአለም ዳርቻ ይሁን መጨረሻው ካቴና ጠልቆለት ዘብጥያ መውረድ ነው – ብሃሬ ተጠቃ የሚል ተረት ሰሚ የለውም!
አቶ ደርበው ደመላሽ፣ አቶ ተሾመ ኃይሌ፣ አቶ ነጋ ካሴ፣ አቶ አሸናፊ ተስፋሁን፣ አቶ ደርሶ አያና ወዘተ ሌሎች በርካታወች የታሰሩ የደህንነት ሹመኞች አማራ ናቸው፤ ሲታሰሩ ግን በአማራነታቸው ነው የታሰሩት ያለ ሰው የለም። እነ አቶ አዲሱ በዳሳ፣ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣ አቶ ጌታቸው ወ/ጊዮርጊስ ወዘተ የታሰሩ የደህንነት ሹሞች ኦሮሞ ናቸው፤ ሲታሰሩ ግን በኦሮሞነታቸው ነው የታሰሩት ያለ ሰው አላጋጠመኝም።  አቶ ያሬድ ዘሪሁን ወላይታ ነው፤ ሲታሰር በወላይታነቱ ነው ያለ ሰው አላጋጠመኝም።ዶ/ር ሀሺም ቶፊቅ አደሬ ነው፤ የእስር ማዘዣ ሲወጣለት በአደሬነቱ ነው ያለ የለም።
ታዲያ የክንፈ ዳኘው መታሰር እንዴት በትግሬነቱ ነው ያስብላል??? በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የወጣው የእሰር ማዘዣ እንዴት ትግሬ በመሆኑ ነው ያስብላል? እንዲህ የሚሉ ሰወች እነዚህ ወንጀለኞች የወጡበትን ጎሳ በሰወቹ ወንጀል ልክ እንዲጠየቅ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው ብየ አስባለሁ። ትግራይ ክልል እንደ ሌሎቹ ዘጠኙ ክልሎች በፌደራሉ መንግስት ስር የምትተዳደር ክልል ነች፡፡ አስራ ሰባት አመት ታግለው ሃያ ሰባት አመት ሃገሪቱን እንደ ብረት ቀጥቅጠው የገዙ ሰዎችም የወጡት ከትግራይ ነው፡፡ አሁን ዘመን ተቀይሮ ሌላ ኢትዮጵያዊ ቡድን የፌደራል መንግስትን ስልጣን ተቀብሏል፡፡
ይህ እውነት ነው እና የመረረውም የጣፈጠውም ሊቀበለው ይገባል፡፡አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ደስ እያለው የሚቀበለው እውነት ነው! የነፃነት ታጋይነን ባዮቹ ህወሃቶችም ከማዕከል ወርደው የወጡበትን ምድር እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡  የፌደራል መንግስቱን የተረከበው መንግስት ደግሞ አንዱ ስራው ወንጀለኛን ለህግ ማቅረብ ነውና ስልጣንን ተተግነው ሌብነቱን ሲያስኬዱ የነበሩ በሚል የተጠረጠሩ ሰዎችን ከያሉበት እያደነ  ለፍርድ ለማቅረብ እየሞከረ ነው፡፡
ይህን ሲያደርግ ጥፍር እየነቀለ፣እያመከነ፣ሰው በማይደርስበት ስውር ቦታ አስሮእያሰቃየ፣ግብረ-ሰዶማዊነትን እስኬደ፣የሰው ልጅ ደም እና ፈርስ በአፉ እስኪመጣ ዘቅዝቆ ሰቅሎ እየገረፈ፣እንጨት ላይ አንጠልሎ እየሰቀለ፣ተረባርቦ ሴት ልጅ ላይ እየሰፈረ እንደ ዱር አውሬ ሆኖሳይሆን መንግስትን በሚመጥን መንገድ የፍርድቤት ትዕዛዝ ይዞ፣በአርባስምንት ሰዓት ሳያልፍ ፍርድቤት አቅርቦ ነው፡፡
የህዝብ አደራ ሳይከብደው ከሌብነት እስከ ውንብድና ድረስ የዘለቀ ወንጀል በመስራቱ የተጠረጠረ ሁሉ በፍርድ አደባባይ ይቆማል፡፡ ይህን ትግሬነት ወይም አደሬነት ሊከለክለው አይችልም፡፡ የሌባ ዘር ሌብነቱን አይቀይረውም፡፡ የህግ ጉዳይ ከወንጀል እንጅ ከሌባው ዘር አይደለም፡፡ሌባ ደግሞ ሌባ ነው፤በካቴና ተጠፍሮ ይቀርባል እንጅ ዘሩ ከወርቅ ወይ ከጨርቅ ስለሆነ “ጉሮ ወሸባየ” አይባልለትም፡፡
“ከተጠርጣሪ ውስጥ ትግሬ መብዛቱ ትግራይን ለማዳከም ነው” የሚለው ተልካሻ የተሸናፊ ምክንያት ሌላ በርካታ ጥያቄ ያስነሳል እንጅ ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ሌባ ስለተያዘ ትግራይ የምትዳከመው ድሮ የበረታቸው በሌባ ብዛት ነው ማለት ነው? ሌባ ስለተያዘ የሚዳከም ክልል ካለ ድሮም የቆመው በሌባ ተደግፎ ነበር ማለት ነው፡፡ ሌላው እሪ እያስባለ ያለው  ጉዳይ “የትግሬ እስረኛ በዛ” የሚለው ነው፡፡ የትግሬ እስረኛ የመብዛቱ ምክንያት ግልፅ ነው- ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ከዋነኛ እስከ ንዑስ የስልጣን እርከን ላይ ተጠራርቶ ተሰይሞ ሃገር ሲግጥ  የነበረው በአብዛኛው ትግሬ ስለነበረ ነው፡፡ ትግሬ በሰረቀው ደግሞ ለብሄረሰብ ስብጥር ተብሎ ኮይራ ወይ ያንጋቶም ሊታሰር አይችልም፡፡  “ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ሌላ ሰው በሃገሩ የሌለ ይመስል ትግሬ ስልጣን ላይ በዛ” ሲባል ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ አካል ዛሬ በብዛት መታሰሩንም ሊጠላው አይገባም፡፡ ተሰባጥሮ መጠየቅ የፈለገ ስልጣኑንም ተሰባጥሮ መቀራመት ነበረበት፡፡ የእስሩ የብሄር ስብጥር  የሃያ ሰባት አመቱ የስልጣን ክፍፍል መዛባት ነፀብራቅ ነው!!
ይህ ማለት ከትግሬ ሌላ ሌባ አልነበረም አሁንም አልታሰረም ማለት አይደለም፡፡ ጌታቸው አሰፋ ያዘምታቸው የነበሩ እንደነ ያሬድ ዘሪሁን እና ተስፋየ ኡርጌ ያሉ ሰዎችም ታስረዋል፡፡ጌታቸው ሲያዘምታቸው የኖረው ትዕዛዝ ተቀባዮቹ ታስረው ጌታቸው የማይታሰርበት ምድራዊ ሃቅ የለም -ሰውየው ራሱ ሰማያዊ ነው ካልተባለ በቀር!!  እሱ ያዘመታቸው ሰዎች ታስረው ዋናው ወንጀለኛ  ጌታቸው ይታሰር ሲባል ትግሬን ለማዳከም ነው የሚያስብለው የተለመደው የእበልጣለሁ ባይነት  በሽታ  ነው፡፡
ስለ ዘር እናውራ ከተባለ ያሬድም ተስፋየ ኡርጌም ዘር አላቸው የነሱ ዘር ክልል መሪዎች ግን እንደ ትግራይ ክልል መሪ በየ ደቂቃው የሚቀያየር መግለጫ አላወጡም፡፡ ሁሉም ሰው፤ሁሉም ሌባ እኩል ነው፡፡ ስልጣን ይዘው ሞክረውትም ያልሆነ እበልጣለሁ ባይነት ዛሬ ሊሰራ አይችልም፡፡ ከእብሪት አየር ላይ ወረድ ብሎ መሬት መያዝ ጥሩ ነው!!!
Filed in: Amharic