>

በርግጥም ሌባ «ብሔር» አለው! (አቻምየለህ ታምሩ)

በርግጥም ሌባ «ብሔር» አለው!
አቻምየለህ ታምሩ
ሌባ «ብሔር» አለው። ሌብነትን ሕጋዊ ለማድረግ  ደግሞ «ብሔርተኛነት» የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው የቅሚያ ፖለቲካ አለ። ብሔርተኛነት የሚባለው  የጎሰኛነት  ፖለቲካ ወደ አገራችን የገባው  ከ«ብሔሩ» ውጭ  ባለ ኪሳራ የራስን «ብሔር» ትርፍ የማካበቻ መሳሪያ ተደርጎ ነው!
«ብሔሬ» በሚሉት ተደራጅተው ጥሬ ቢሊዮን ዶላሮችን ብቻ ሳይሆን ጥሬ    አውሮፕላኖችና መርከቦችን ሳይቀር የሰረቁ አገር ገፋፊዎችን  እስር ለማስታመም  ሲባል ከሰሞኑ ሌባ «ብሔር» የለውም የሚል ነጠላ ዜማ  እየሰማን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። ለሌብነትና ለቅሚያ «ብሔሬ» በሚሉት  ተደራጅተው አገር ሲያራቁት የኖሩ ሌቦች ሲታሰሩ «ብሔር» የላቸውም  እንዴት ሊባል ይችላል? ሲጀምር የጎሳ ብሔርተኞች በ«ብሔራቸው» የተደራጁት «የራሳችን» የሚሉትን በክልል አጥረው እያስጠበቁ  የሌላውን ድርሻ  ተሻግረው ለመንጠቅ ነው።
በሌላ አነጋገር  የ«ብሔር» ፖለቲካ «የራሴ» ወይንም «የብሔሬ» የሚሉትን የግል ለማድረግ፤ «የሌላ» ወይንም «የጎረቤት» የሚሉትን ደግሞ  ለመጫረት ወይንም ለመንጠቅ የሚደረግ ቡድንተኛነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት የበለጸገው  የ«ብሔር» ፖለቲካ ከነጻነት፣ ከሕግ የበላይነትና ከዲሞክራሲ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው የ«ብሔር» ፖለቲካ ከነጻነት፣ ከሕግ የበላይነትና ከዲሞክራሲ የሚገናኝ ነገር ቢኖረው ኖሮ አንዱ  ብሔርተኛ ከ«ብሔሬ» ውጭ  ነው ያለውን  ሌላውን «ብሔር» ነጻነቱ ገፎ፣ ከሕግ በላይ ሆኖና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ጥሶ  «ውጣልኝ» እያለ ሊያባርረው፣ ሊገድለው፣ ሊዘርፈውና ሊያሳድደው አይችልም ነበር።
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት ሲካሄድ ያየነው «ብሔር» ፖለቲካ ከአገር በላይ የመግዘፍ ወይንም ከአገር ጋር የመፎካከር እንቅስቃሴ ነው። የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች «ኦሮምያ» የሚሏት አገራቸው ከኢትዮጵያ የምትበልጥ እንጂ የምታንስ፤ የምትሰፋ እንጂ የምትጠብ አድርገው አይቆጥሯትም። ለዳዎድ ኢብሳም ሆነ ለሌንጮ ለታ ኦሮምያና ኢትዮጵያ  ሁለት  የተለያዩ ናቸው።
ለወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞችም ትግራይና ኢትዮጵያ ሁለት ናቸው። ሲናገሩ ከሰማችኋቸው ኢትዮጵያና ትግራይ ነው የሚሉት። እንዴውም ከሰሞኑ ከወደ መቀሌ በጎረቤት አገር ኢትዮጵያና ጋና መካከል የሚደግ ጨዋታ እናሳያለን የሚል የDSTV ማስታወቂያ አይተናል። ሌንጮና ዳዎድም ኦሮምያና ኢትዮጵያ ነው የሚሉን።  የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞችም አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር «ትግራይን እንገነጥላለን» የሚሉን ታላቋ ትግራያቸውን ከጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ተልቃ ስለምትታያቸው  ትግራይ ይዘው ስለተነጠሉ አገር የሚፈርስ  ስለሚመስላቸው ነው።
የ«ብሔር» ፖለቲካው እውነታ ይህ ስለሆነ   በ«ብሔራቸው» ተቧድርነው
የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽ የሚል የወያኔ የቅኝ ግዛት የቢዝነስ ኩባንያ አቋቁመው ኢትዮጵያን ሲዘርፉ  የነበሩት እየዘረፉ የነበሩት  ከራሳቸው  ሳይሆን ከሌላ አካል  እንደሚሰርቁ  ስለሚያስቡ ነበር። እንዲህ እንዲያስቡ ያደረጋቸው  ሰዎቹ በተፈጥሮ ሌቦች ስለሆኑ ሳይሆን የ«ብሔር» ፖለቲካ እንደዚያ እንዲያስቡ ስለሚያስገድዳቸው ነው። በ«ብሔር» ፖለቲካ የተጠመቀው  ተከታዩም የ«ብሔሩ» አባል የሆነ  አንድ ሰው በሌብነት ቢታሰር «የኔ ብሔር  ላይ ያነጣጠረ ጥቃት» ተፈጸመ ሲል እንጂ  አገር ስለዘረፈ ታሰረ የሚል መቆርቆር ሲሰማ ታይቶ አይታወቅም።
 በ«ብሔር» ፖለቲካ ለተጠመቁት  ምዕመናን ከአገር መዘረፍ በላይ የሚያሳስባቸው  የ«ብሔራቸው» አባል መታሰር ነው። በንጹሐን ዜጎች ላይ ግብረ ሰዶም የፈጸሙ፣ ሴቶችን እየተፈራረቁ የደፈሩ፣ መርከብና አውሮፕላን የዘረፉ፣ ከኢራቅ የጦር መሳሪያ እየገዙ በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ ላይ ተሰማርተው ምናልባትም ለአልሸባብ አይነት አሸባሪ  ቡድኖች የጦር መሳሪያ ሲሸጡ የነበሩና አገራችንን ገፈው ባጽሟ ያስቀሩ ዓለም አቀፍ ወንጀለኞች መታሰራቸውን በመቃወም በትግራይ ክልል በትግሬዎች ላይ ያነጣጠረ እስራት እየተካሄደ እንደሆነ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ያለው የነ ክንፈና ግብረ አበሮቹ ወንጀል ለብሔርተኞቹ ወንጀል ስላልሆነ ነው።
ባጭሩ ሌባ «ብሔር» አለው። ሌብነትን ሕጋዊ ለማድረግ  ደግሞ «ብሔርተኛነት» የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው የቅሚያ ፖለቲካ አለ። ብሔርተኛነት የሚባለው  የጎሰኛነት  ፖለቲካ ወደ አገራችን የገባው  ከ«ብሔሩ» ውጭ  ባለ ኪሳራ የራስን «ብሔር» ትርፍ የማካበቻ መሳሪያ ተደርጎ ነው።  በሌላ አነጋገር የ«ብሔር» ፖለቲካው የተዋቀረው አንድ የአንድ «ብሔር» አባል  የሆነ ሰው  በሌላ የ«ብሔር»  አባል  በሌብነት ቢያዝ  የ«ብሔሩ» አባላት  በ«ብሔር» አማካኝነት ጥቃት እንደተፈጸመበት እንጂ ጥፋት ስላጠፋ ታሰረ ወይንም ተጠያቂ ተደረገ ብለው እንዳያስቡ ተደርጎ ነው።
በተግባርም የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኝ የሆኑ ብሔርተኞች አንድ የጎሳቸው አባል የሆነ የትግራይ ሰው ከኢትዮጵያ ቢዘርፍ ትግራይን ለመጥቀም  እንጂ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ነው ብለው አያስቡም፤ የብቻቸው የሆነችዋ ትግራይ  መጠቀም እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ አያሳስባቸውም። ለዚህም ነው ከ«ብሔሩ» ውጭ ባለ አካል አንድ ሌባ ቢታሰር  በ«ብሔሩ» ምክንያት ጥቃት የደረሰበት እንጂ ሌላ ስለሆነ ታሰረ ብሎ የብሔር ፖለቲካ አያስብም። ለዚህ ምሳሌ ከነ ክንፈና  ዳኘውና የደኅንነት መስሪያ ቤቱ ሰውች  እስር ዙሪያ በሰላማዊ ሰልፍ እየተስተጋባ ካለው ጩኸት በላይ  አስረጂ ሊኖር አይችልም።
የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ የሆኑ ብሔርተኞችም  አንድ ሰው ከኢትዮጵያ ቢሰርቅና ቢታሰር  ኦሮምያን ለመጥቀም  ስለሰራ እንጂ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ወንጀል ስለፈጸመ  ነው ብለው አያስቡም፤ ሰልፉም ይወጡለታል፤ መንገድም ይዘጉለታል። እነ ኦቦ በቀለ ገርባ ኢትዮጵያውያን በገንዘባቸው መሬት እየገዙ ሀብታቸውን አፍስሰው  ተወልደው ያደጉበትን ርስታቸው የሆነችውንና የጋራ ከተማችን የሆነችዋን  አዲስ አበባን  ለመንጠቅ «ፊንፊኔ የኛ ብቻ ነች፤ ወደኛ ክልል ሳትመለስ እህል አንቀምስም» የሚል የዘረፋ መግለጫ  ሲያወጡ  የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች  በሙሉ ኦሮምያን ለመጥቀም ያወጡት መግለጫ አድርገውት ለዘረፋ መግለጫው ያልሰጡት ድጋፍ አልነበረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን  ከተግብራዊነቱ በመለስ  ኢትዮጵያውያን በሙሉ አንጡራ ሀብታቸውን አፍስሰው የገነቧትን የጋራ ከተማ «የኛ ብቻ ነች» በሚል የዘረፋ መግለጫ ባወጡ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞችና  አውሮፕላኖችና መርከቦችን በሰረቁ የሜቴክ ዘራፊዎች መካከል ልዩነት የለም።
ስለዚህ  በወያኔም ሆነ  በኦነግ  ፕሮግራም አቀንቃኝ  ብሔርተኞች መካከል ሌባ «ብሔር» አለው። ሲዘርፍ በ«ብሔሩ» ተደራጅቶ የሰረቀና የዘረፋ መግለጫ ያወጣ  የዘራፊዎች ስብስብ  ሲያዝ  ወይንም ተጠያቂ ሲደረግ «ብሔር» አልባ ሊሆን አይችልም። ሌባ ብሔር የማይኖረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ deethnicize  ከተደረገ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic