>

ህንድን ምሳሌ አድርጋችሁ ስትመክሩን ምነው የደቡብ ሱዳንን ደበቃችሁን!!! (መሳይ መኮንን)

ህንድን ምሳሌ አድርጋችሁ ስትመክሩን ምነው የደቡብ ሱዳንን ደበቃችሁን!!!
መሳይ መኮንን
 
“ሲዳማና ወላይታ ሲለያዩ እንዲመካከሩ ለሲዳማ ወጣቶች አስረድቼአለሁ”
 
“ህንድ ስትነሳ ዘጠኝ ክልሎች ነበራት። አሁን ሰላሳ ደርሰዋል። እኛም ጋ ቢበዛ ጤናማ ነው።”
እንግዲህ ጆሮ አይደክመውም። አፍ መናገር አይሰለቸው፡ ጆሮም መሰማቱን ይቀጥላል። ይሄንኑ ቀድመን ብለናል። ጭራሽ በአደባባይ በግልፅ ደረት ተነፍቶ እየተነገረን ነው። አቋም እንደየመድረኩ መቀያየሩን ለምደነዋል። የትኛዋ ከደም ጋር የተጣበቀች፡ የትኛዋ አቋም ደግሞ ለሽርደዳ የምትወረወር እንደሆነች ይገባናል። “የእኔ ግዛት” ከሚሉት ተሻግሮ ሌላውንም ልዩነትን መስበክ ስትራቴጂው ወዴት ለመድረስ እንደሆነ ጡጦ ያልጣለ ህፃን እንኳን የሚረዳው ነው። እየተበራከተ የመጣውን ”የክልል” ጥያቄ ቤንዚን በማርከፍከፍ እያቀጣጠለ ያለውን አካል ማወቃችንም አንድ ነገር ነው።
ቀድሞውኑ ግን መለያየቱን ምን አመጣው? ለምን ተፈለገ? የሲዳማ ወጣቶችን ብቻ ማስረዳቱ ምን ማለት ነው? እንደዛም ከሆነ ሀዋሳ ሄዶ ”ስትለያዩ ተመካከሩ” ሲባል ወደ ወላይታ ሶዶም ጎራ ተብሎ ተመሳሳይ መልዕክት ለወላይታ ወጣቶች ያልተመከረበት ለምን ይሆን? የተሰበከው የ”ተለያዩ” መልዕክት በሰላም የሚጠናቀቅ ልዩነት ወይስ ካራ የሚያማዝዝ፡ ደም የሚያፋስስ? ውስብስብ ከሆነው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የወሰንና የመሬት አሰፋፈር አንጻር ምን ዓይነት ”የተለያዩ” ስብከት ነው በሰላም የሚቋጨው?
ህንድ ሰላሳ መድረሷ በአወንታዊ ጎኑ ተጠቅሶ ችግር የለውም ስንባል፡ ደቡብ ሱዳን ከ2 ወደ 32 የመጡበት መጨረሻቸው ምን መዘዝ እንዳስከተለስ ማን ይንገረን? የጎሳና የዘር ክልል ያልተከተለችው ህንድ ለእኛ እንደምን በምሳሌነት ትነሳለች? ይልቅስ የደቡብ ሱዳኑ የሚቀርበንም የሚመስለንም ምሳሌ በሆነ ነበር። ለራስ ክፉ ዓላማ ያልሆነን ምሳሌ መደንቀር ድፍረት ነው። ለምን? ብሎ የማይጠይቅንና በስሜት የሚከተልን ደጋፊም መናቅ ነው።
Filed in: Amharic