>
10:49 am - Sunday May 22, 2022

ከካባው በስተጀርባ ያሉ ለሚመስሉኝ ሸፍጦች!!! (ዮሀንስ መኮንን)

ከካባው በስተጀርባ ያሉ ለሚመስሉኝ ሸፍጦች!!!
ዮሀንስ መኮንን
ዶክተር ደብረጽዮን በአክሱም ጽዮን በዓለ ንግሥ ላይ አባ ማትያስ በደረቡላቸው ካባ እና በደፉላቸው አክሊል ዙሪያ ውይይቱ ደርቷል:: ጉዳዩን ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን እና ከተገቢነት አንጻር ከማየት ይልቅ “እኛ እና እነርሱ” ወደሚል መቧደን እና ብሽሽቅ ማዘንበሉ ደስ አይልም::
እኔ ግን ከካባው በስተጀርባ ያሉ ለሚመስሉኝ “ሸፍጦች” ግምቶቼን ላስቀምጥ!
1) የአባ ማትያስ “ዋሻ ፍለጋ” ይሆን?
አንደኛው መላ ምት አባ ማትያስ የቤተክህነቱ ንቅዘት እና መዝረክረክን የማይታገሱ ለውጥ ጠያቂዎች ምእመናን በየአድባራቱ እየተበራከቱ በመምጣታችው ህወሓትን እንደመደበቂያ ዋሻ እያዩዋት የመጡ ይመስላል:: የካባውም ሽልማት “ለመደበቂያ ዋሻው” እንደ “ቀብድ” የተከፈለ ይሆን?
2) የድጺ “የሞራል ድጋፍ” ፍለጋ ይሆን?
ህወሓት እና ደጋፊዎቿ ሀገሪቱ በማካሄድ ላይ ያለችው ሁለንተናዊ ለውጥ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል:: ይህ ደግሞ በአብዛኛው የለውጥ ደጋፊ ዘንድ ህውሓትን “የለውጥ እንቅፋት” ተደርጎ የመሳል ዝንባሌ እያስተዋልን ነው:: ከዚህ የተነሳ ህውሓት እና ግብረ አበሮቿ ከሥልጣን ብቻ ሳይሆን ከሞራል ልእልናም ቁልቁል ተንሸራተዋል:: አባ ማትያስ የደረቡላቸውን ካባ የፈለጉት ለሙቀቱ ወይንም ለድምቀቱ ሳይሆን ለወደቀው ሞራል “ክሪክ” ፍለጋ ይሆንን?
3)  የትግራይ ቤተክህነት ዳርዳርታ ይሆን?
ከሰሞነኛ የህወሓት አስጨፋሪዎች (አክቲቪስቶች ማለትስ ይከብዳል) ትርክቶች አንዱ “አክሱም ጽዮንን ማዕከል ያደረገ የተጋሩ ሲኖዶስን እንመሠርታለን” ሽለላ ላይ ናቸው::  ስለዚህ የካባው ድብብቆሽ ህውሓት ጥርሷን የነቀለችበትን “የጎሳ ፖለቲካ” ወደ ቤተክህነቱ አስርጎ የማስገባት አካል አድረገው ያዩም አልጠፉም:: የካባው ሽልማት “የትግራይ ቤተክህነት” ዳርዳርታ ይሆን?
4)ከዶክተር ዐብይ ጋር ፉክክር ይሆን?
ጠሚዶ ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኇላ ካሳኳቸው አስደናቂ ለውጦች አንዱ ለሁለት የተከፈለውን ሲኖዶስ የማስታረቅ እና የማዋሀድ ሥራ ዋንኛው ነው:: ለዚህም ድጋፋቸው ቤተክርስቲያኒቱ የክብር ካባ (በእውደ ምህረት ንግስ ላይ አይደለም) አበርክታላቸዋለች:: ይገባቸዋልም:: የህውሓት አስጨፋሪዎች “ለዐብይ ሲደረግ ለምን አልተቃወማችሁም?” ሙግትም መነሻው ይሄው ፉክክር ነው:: ዝርዝሩን ብንተወው “ለአታራቂው የተሰጠን የካባ ሽልማት ላጋጨውም ይሰጠው” ማለት በራሱ ግን የጤና አይደለም:: ከዚህ ተነስተን ጉዳዩን ስንመረምረው እንዲህ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን:: ሀገራዊ ለውጡን በስጋት የምትመለከተው ህውሓት “የእውቅና” ፉክክር ውስጥ ገብታ ይሆን?
5)የህወሓት ንሰሀ መግባት ፈልጋ ይሆን ?
ህውሓት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ያላት ጥላቻ መጠን አልባ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው:: አንዴ “የትምክህት ኃይሎች መሰብሰቢያ” ስትል ሌላ ግዜ ደግሞ “አከርካሪዋን ሰብረናታል” እያለች በጀብደኝነት መፎከሯ የቅርብ ጊዜ ትዝታነው::
ግፎቿን እናስታውስ ከተባለም የዋልድባ አብያተክርስቲያናት እና የአጽመ ቅዱሳን ፍልሰት, የመናንያን መነኮሳት እስር እና እንግልት, የፓትርያርክ ስደት, የካድሬዎች ሲመት, … ወዘተ ህውሓት በበረኪና ብትታጠበው የማትጠራው ኃጢአቶቿ ናቸው:: ምናልባት በካባው ጀርባ ለዚህ ሁሉ በደሏ ንሰሀ መቀበሏ ይሆን? እንደኔ ንደኔ የመጨረሻው መላምቴ እውነት እንዲሆን እመኛለሁ:: ህውሓት ከራሷ ከታረቀች ከቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ከምእመናን ለመታረቅ እዳው ገብስ ይሆንላታል::
እስኪ እጃችሁን ዘርጉና እንጸይ! 
“አምላክ ሆይ የህውሓትን በደሏን አትቁጠርባት:: ንሰሀዋንም ተቀበላት!!!”
Filed in: Amharic