>

የዳኛቸው ወርቁ 24ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ  (ልኡል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የዳኛቸው ወርቁ 24ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ 
ልኡል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል
ደራሲ፣ የሥነ-ጽሑፍ መምሕር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ የነበሩት ዳኛቸው ወርቁ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት (ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም) ነበር፡፡

📖ዳኛቸው ወርቁ  የካቲት 16 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ፣ በይፋትና ጥሙጋ፣ በደብረ ሲና ከተማ አቅራቢያ ከአቶ ወርቁ በዛብህና ከወይዘሮአሰገደች ሀብተወልድ ተወለዱ። ከ1936 ዓ.ም. እስከ 1942 ዓ.ም. ድረስ በተወለዱበት አካባቢ በደብረ ሲናው አብዬ ትምሕርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ተከታተሉ። እዚያ ሳሉ ገና በ13 ዓመት እድሜያቸው «ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ» የተሰኘች ተውኔት ደርሰው በመተወን ታዋቂነት ማትረፍ የቻሉ ሰው ነበሩ።

በ1943 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ሄደው መጀመሪያ ሊሴ ገብረማርያም፣ በኋላ ደግሞ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምሕርት ቤት ይሰጥ የነበረውን የመምሕርነት ኮርስ ለአንድ ዓመት ተከታትለው በመምሕርነት ተመርቀዋል።
ከምርቃት በኋላም በሐረር መድኃኔዓለም ለሁለት ዓመታት፣ በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል ግዕዝና አማርኛ ያስተማሩ ሲሆን፣ «ሰቀቀንሽ እሳት» የተሰኘ ተውኔት በመድረስ ተሰጥዖዋቸውን የገለፁ፤ «ሰው አለ ብዬ» የተውኔት ድርሰታቸውን ደግሞ በማሳተም ያበረከቱ የፈጠራ ሰው ናቸው።
ዳኛቸው በ1953 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምሕርታቸውን እየተከታተሉ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ በረዳት መምሕርነት ጭምር በዩኒቨርሲቲው ያገለገሉ ሲሆን፣ ተመርቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በወቅቱ የተማሪው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጁ ገጣሚዎች ከነታምሩ ፈይሳ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ አበበ ወርቄ፥ ይልማ ከበደ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ መስፍን ሀብተማርያም፣ … ጋር እንደ «ወጣቱ ፈላስማ» በመሳሰሉ ግጥሞቻቸው የለውጥ ሐሳቡን ያስተጋቡ ገጣሚም ነበሩ።
በ1956 ዓ.ም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው፣ ከ1957 ዓ.ም. እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ እዚያው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምሕርነት ያገለገሉ ሲሆን «ትበልጭ» የተሰኘ ተውኔታቸውን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ለመድረክ ያበቁ ጸሐፌ-ተውኔት ናቸው። በ1962 ዓ.ም. በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የፈጠራ ሥነ ጽሑፍ አጥንቶ በመመረቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ›› የሚል ማዕረግ ያገኙና የመጀመሪያዎቹንም አጫጭር ልብ ወለዶች ደርሰው የታተሙላቸው ድንቅ ሰው ነበሩ።
ወደ ሀገራቸው ተመልሰውም እስከ 1965 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ መምሕርነት አገለገሉ፡፡ ዳኛቸው ከነጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደመወዝ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ኃይሉ ፉላስ … ጋር በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል››ን ያደራጁ፣ ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በማደራጀት አስተዋጽዖ ያደረጉ … ምሁር ናቸው፡፡
ባነሷቸው በሳል የለውጥ ሐሳቦችና የተራቀቀ ሥነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ ስልት የተደነቀውን፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊ ልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ በእድገት ምዕራፍ ያሸጋገረውንና «አደፍርስ» የተሰኘውን ልብ ወለድ መጽሐፋቸውን በ1962 ዓ.ም. በማሳተም ታላቅ ጠቢብነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩት ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› እና ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጦችም የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ የተመለከቱ ስራዎችን በማቅረብና የወጣት ደራሲያንን ሥራዎችን በመሔስ ለሀገሪቱ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ምሁራዊ ኃላፊነታቸውንና ተልዕኳቸውንውን ተወጥተዋል፡፡
«አደፍርስ» የተሰኘው ልብ ወለዳቸው ከዩኒቨርሲቲው የሥራ ባልደረቦቻቸውና የአስተዳደር አካላት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያደፈረሰባቸው ዳኛቸው፣ ዩኒቨርሲቲውን ለቀው በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት እንዲሁም በፈረንሳይ ኮሌጅ እስከ 1966 ዓ.ም. የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ አስተምረዋል። ኋላም «በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ድርጅት» በትርጉም አዋቂነት፣ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና በኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት ሹምነት ለ15 ዓመታት አገልግለው፣ በ1983 ዓ.ም. ጡረታ ወጡ።
ዳኛቸው የዛሬዎቹን ወጣት ኢትዮጵያውያን በጥበቡ ዘርፍ የሚታደጉ የሥነ ጽሑፍ ጥበብ መመሪያ እና የአማርኛ ፈሊጦች መጽሐፍትን ያሳተሙ ምሁር ናቸው፡፡ ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» የመሳሰሉ ጥልቅና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታቸውን የተወጡ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
የሀገራቸውን እምነትና ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ለሥራ ነገን የማያውቁ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ አገር ወዳድ፣ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁልጊዜ የሚቆረቆሩ፣ ማጎብደድንና አድርባይነትን የማይወዱ፣ ፊት ለፊት ተናጋሪ … ባጠቃላይ በ«አደፍርስ» ልብ ወለድ ድርሰታቸው ጠጣርና ምጡቅ ሐሳቦችን በድንቅና ውብ የአጻጻፍ ስልት … የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዕልናን ልዩ በሆነ የቋንቋ ኃይል ያሳዩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ከስራዎቻቸው መካከል … 
1. አደፍርስ (ልብወለድ)
2. እምቧ በሉ ሰዎች (ግጥምና ቅኔ)
3. ሰቀቀንሽ እሳት (ተውኔት)
4. ሰው አለ ብዬ (ተውኔት)
5. ትበልጭ (ተውኔት)
6. ያላቻ ጋብቻ ፥ትርፉ ሐዘን ብቻ (ተውኔት)
7. ማሚቴ (ልብወለድ)
8. The Thirteenth Sun
9. የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ (ምርምር)
10. Shout It From the Mountain Top (ያልታተመ – ልብ ወለድ) … ይጠቀሳሉ፡፡

 

Filed in: Amharic