>

ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው? (ኤርሚያስ ቶኩማ)

ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?
ኤርሚያስ ቶኩማ
በአክሱም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በሃይማኖት መነፀር ብቻ መመልከት ተገቢ አይደለም፡፡ በጋራ በምንኖርባት ሀገር ላይ መስጂድ ለመገንባት ፈቃድ ሰጪና ፈቃድ ከልካይ ማነው? ይህቺ ሀገርስ የማን ነች? ሙስሊሙ ከሀገሩ የት ሄዶ ይስገድ?
የአክሱም ሙስሊሞች ለበርካታ አመታት ሲጠይቁት የነበረው የመስጂድ ግንባታ ጥያቄ ሳይመለስ በዛሬው እለት ደግሞ የጁምዓ ስግደት አትሰግዱም ተብለው ተከልክለዋል፤ ሙስሊም ወገኖቻችን ሶላት እንዳያደርጉ የከለከሉ ባለስልጣናትን ለመቃወም ግዴታ ሙስሊም ልንሆን አይገባም፡፡ እኔ ሙሉ ክርስቲያን ነኝ፤ እኔ የማምነው ክርስትና ከተገፉት ወገን እንድቆም የሚያስገድድ እንጂ ከእኔ በእምነት የተለዩትን ሰዎች እንዳሳድድ የሚያስገድድ አይደለም፡፡
አንዳንድ ሰዎች አክሱም ላይ መስጂድ መገንባት እንዳለበት ስታጫውታቸው መካ ላይ እኮ ቤተክርስቲያን የለም ይሉሃል፡፡ መካ የኢትዮጵያ ንብረት አይደለም፤ መካ ላይ ቤተክርስቲያን ይገነባ ዘንድ መጠየቅ ያለበት ሳውዲ ያለ ክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ አክሱም ግን የኢትዮጵያውያን ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የሁሉም እምነት ተከታዮች ሀገር ነች በመሆኑም አክሱም ላይ መስጂድ እንዳይገነባ መከልከል ፍፁም ህገወጥነት ነው፡፡
አክሱምን ከአንድ እምነት ጋር የማያያዝ አመል መቆም አለበት፡፡ ኢትዮጵያን በንብረትነት የያዘ የሃይማኖት ተቋም የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተከታይ ያሏቸው ሃይማኖቶች በሙሉ ከውጭ ፈልሰው የመጡ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ በዚህ ሀገር ማንም እንግዳ ማንም ቤተኛ አይደለም፤ ሀገራችን የሁላችንም እንጂ የጥቂቶች አይደለችምና ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊስ ሀገሩ የት ነው? ኢትዮጵያ አይደለምን?
በትግራይ ክልል ባለስልጣናት አማካኝነት አክሱም በሚገኙ የእስልምና ተከታይ ወንድሞቻችንን ላይ የሚደርሰውን በደል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእምነት ሳይለያይ መቃወምና ከሙስሊም ወገኖቹ ጎን መቆም አለበት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ዶክተር አብይ ስልጣን ይሰጣቹህ ዘንድ አራት ኪሎ ድረስ እየሄዳቹህ ከምትልከሰከሱ ከእነዚህ ወገኖቻችን ጎን ልትቆሙ ይገባል፡፡ ዛሬ መብቱ ሲገፈፍ አለሁልህ ያላልከውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ነገ በምን ድፍረትህ ነው ምረጠኝ ብለህ ፊቱ የምትቆመው?
Filed in: Amharic