>
5:13 pm - Thursday April 18, 4712

አዲስ አበባና  የነታከለ ኡማ ፖለቲካ?!? (ሀብታሙ አያሌው)

አዲስ አበባና  የነታከለ ኡማ ፖለቲካ?!?
ሀብታሙ አያሌው
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከከተማው አርሶ አደሮች ጋር ተወያየሁ ይልሃል።  ይህው የገበሬዎቹ ፎቶም ተለጥፏል። ይህ ሰው አዲስ አበባ ላይ ምን እየሰራ እንደሆነ በጥንቃቄ ለሚከታተል ሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እየሄደ እንደሆነ በቀላሉ ይገባዋል።  አዲስ አበባ ገበሬ አላት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ከሳምንት በፊት ጀዋር የአዲስ አበባ ኮንደሚኒየሞች ቅድሚያ ካልተሰጡን ብሎ ቄሮን እያሳመፀ ነው ሲል ወሬ አሾልኮ ነበር።  ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ  አልገባኝም የሚሉ ነገር ግን ተሽቀዳድመው “ታኬ ያራዳልጅ ኢትዬጵያዊነት ከፍታዬ ነው አለ” እልል በሉ የሚሉን ሺዎች ናቸው።
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል በህዝብ የተመረጠ ሌጅትሜት መንግስት ያስፈልጋል ብለው እንደነበረ ታስታውሳለህ ብዬ እገምታለሁ።  የአዲስ አበባን ነዋሪ በህገወጥ ስም ዛሬም ድረስ እያፈናቀለ የፈለገውን ለመትከል ለሚሰራው ዴሞግራፊ ቅየራ እውቅናም ይሁን ሽፋን መስጠት በፍፁም ሊያግባባ አይችልም።  በግሌ ኢትዮጵያ ብሎ ማንም ሲጠራ ክብር እና ደስታ ይሰማኛል።  እያቆላመጠ ጠርቶ ልንሰማ የምንፈልገውን እየነገረ በተግባር አዲስ አበባን ለብሔር  ፖለቲካው የበላይነት መፈናጠጫ ሲያደርጋት ግን ህሊና እና እውነት አለኝና ሽፋን አልሰጥም።
በግልፅ የሚታይ ብሔር ተኮር ስራ እያጣደፈ ነው።  ቅሬታው በአዲስ አበባ በዙሪያ ላለ ገበሬ በቂ ባልሆነ ካሳ ክፍያ  ተፈናቅሎ ነበረ ከሆነ።  አፈናቃዮቹ ኩማ ደመቅሳ ፤ ድሪባ ኩማ የክልል መሪ የነበረውም አባዱላ ገመዳ ነበር።
አዲስ አበባ በመንገድ ስራ  ስም፤  በኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ ስም፤  በባለሃብቶች የልማት ግንባታ ስም፤ ታሪካዊ መንደሮቿ ፈራርሰው ነዋሪዎቿ ሜዳ ሲወድቁ ኑረዋል።  ይህ ተለይቶ መብት ይጠበቅ ጫወታ እና ጥድፊያ “የጊዜው የኛነው”  ባዬች አጀንዳ እንደሆነ ግልፅ ነው። ስለዚህ በገበሬ ተፈናቅሏል ስም እነማን ተቀናጅተው አዲስ አበባ ላይ የዲሞግራፊ ቅየራ እየሰሩ እንደሆነ ከመቼም ጊዜ በላይ ግልፅ እየሆነ መጥቷል።  እወድሻለሁ እያሉ መግደል ኢትዮጵያ እያሉ በተግባር ብሔር ተኮር ስራ ማጣደፍ በዝምታ ሊታለፍ አይገባም የሚል እምነት አለኝ። የኔ ሃሳብ ይሄው ነው !!
(ፎቶ  1)  በዚህ ሳምንት ታከለ ኡማ ሜዳ ላይ የጣለቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
(ፎቶ  2) ጥቅማቸውን ለማስከበር ስብሰባ የጠራቸው   (ጸሃፊው)
Filed in: Amharic