>
11:06 pm - Wednesday November 30, 2022

የዶ/ር አብይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን የሚገባው....!!!! (ስዩም ተሾመ)

የዶ/ር አብይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን የሚገባው….!!!!
ስዩም ተሾመ

ላለፉት 27 አመታት ህወሓት አማራና ኦሮሞን አስከፊውን የታሪክ ገፅታ እያጎላና ከፋፋይ የፖለቲካ ቁማር እየተጫወተ ማዶ-ለማዶ አራርቆ የለያያቸው፣ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብን ውስጡን በብሔርና ጎሳ ሸንሽኖ በአንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ጠቅልሎ ጠፍሮ ያሰራቸው፣ በሦስቱ ክልል ሕዝቦች መካከል በጋራ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይኖር ለማድረግ ነው። የዚህ መሰረታዊ ዓላማ ደግሞ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር እንዲያስችለው ነው። ምክንያቱም የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ማዶ-ለማዶ ቆሞ አተካራ ይገጥማል፣ ደቡቦች ደግሞ ጎን ከጎን ቆመው በጥርጣሬ የጎሪጥ ይተያያሉ።

በዚህ መልኩ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል እርስ-በእርስ መግባባትና መተማመን ከተሳነው የጋራ አጀንዳ እና የተቀናጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችልም። በኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት ኦዴፓና አዴፓ እርስ በእረስ ተባብረው፣ ከደቡብ የፖለቲካ መሪዎች ጋር ተመካክረው፣ የህወሓትን የበላይነት ማስወገድ ችለዋል። ስለዚህ የዶ/ር አብይ እና የአቶ ደመቀ አመራር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ወደዬት ይሆናል? አሁን ላይ የህወሓት የስልጣን የበላይነት ከሞላ-ጎደል አከርካሪው ተመትቶ ወድቋል። ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት ለመለየት የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ማስወገድ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ተመልሶ መጠየቅ ያስፈልጋል።

በእርግጥ ህወሓት አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ልሂቃንና አመራሮችን በጋራ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው እንዳይሰሩ ያደረገበት መሰረታዊ ምክንያት የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ ሀገራት የፖለቲካ ስልጣንን የበላይነት መሰረታዊ ፋይዳ በቀጥታ የሀገሪቱን ውስን የኢኮኖሚ ሃብት በበላይነት በመቆጣጠር ኢፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው።

እንደ ዶ/ር አለማየሁ ገዳ ያሉ የሥነ-ምጣኔ ባለሞያዎች እንደሚገልጹት፣ በተለይ በብሔር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ የመጨረሻ ግቡ ውስን የሆነውን የኢኮኖሚ ሃብት በበላይነት ለመቆጣጠርና ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ባለፉት 27 አመታት ህወሓት በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሲፈፅም የነበረው ፖለቲካዊ በደልና ጭቆና ነው።

ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ምክንያት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የህወሓት የስልጣን የበላይነት አደጋ ላይ የሚወድቀው ከእነዚህ ክልሎች በሚነሳ ፖለቲካዊ ንቅናቄ አማካኝነት ስለሆነ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አናሳ ብሔሮች፥ ህዝቦች ወይም ነዋሪዎችን አብላጫ ድምፅ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም የፖለቲካ ቡድኖች ለመነጠል ነው። ስለዚህ ህወሓት በተለይ በኦሮሞና አማራ ህዝቦች ላይ የሚያደርሰው በደልና ጭቆና በዋናነት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ በደል ነው። አናሳ ድምፅ ባላቸውና ከብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል በተነጠሉት ላይ ደግሞ ከፖለቲካዊና አስተዳደራዊ በደል በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ ይፈፅማል።

ህወሓት በፌደራሊዝም ስርዓቱ ክልሎችን ሲያዋቅር ወደፊት ለሚፈፅመው የኢኮኖሚ ብዝበዛ አመቺ እንዲሆን ታሳቢ አድርጎ ነው። በዚህ መሰረት በተለይ የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላና አፋር ክልል፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳደሮች የተመሰረቱት ለኢኮኖሚ ብዝበዛ እንዲያመቹ ተደርጎ ነው። የደቡብ ክልል፣ ትግራይ፣ ሶማሌና ሀረሪ ክልሎችም ከላይ እንደተጠቀሱት አይሁን እንጂ ለህወሓት የኢኮኖሚ ብዝበዛ ተጋላጭ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በአማራና ኦሮሚያ ክልልም ቢሆን የኢኮኖሚ ብዝበዛ የለም ማለት አይደለም።

በእርግጥ ህወሓት ዛሬ ካለበት የውድቀት ደረጃ ላይ ያደረሰው ከላይ በተጠቀሱት ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች የሚፈፅመው ብዝበዛና ዘረፋ አልበቃ ብሎት ቀስ በቀስ ወደ ኦሮሚያና አማራ ክልል እጁን በመዘርጋቱ ምክንያት ነው። በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ዘርፈው ሲጨርሱ በማስተር ፕላን አማካኝነት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ የእርሻ መሬት ለመቀራመት ሲያሰፈስፉ ቄሮ ማንቁርታቸውን ይዞ ለዚህ ያበቃቸው።

ይሁን እንጂ ላለፉት 27 አመታት በዋናነት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላና አፋር ክልልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳደሮች ውስጥ የፈጸሙትና የዘረጉት የኢኮኖሚ ብዝበዛ መረብ በሌሎች ክልሎች ካለው ፍፁም የተለየ ነው። የተወሳኑ ማሳያዎችን ለመጥቀስ ያህል፤ የአዲስ አበባ መሬትና ህገውጥ ግንባታዎች፣ የድሬዳዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ የአፋር ክልል የማዕድን ማምረቻዎች፣ የጋምቤላ የእርሻ መሬት፣ እንዲሁም የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ የንግድ እንቅስቃሴና ተቋማት በአብዛኛው በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በደልና ጭቆና ሲፈጽሙ የነበሩት በዋናነት የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይነሳ ስለማይፈልጉ ነው። ዛሬ ላይ በአፋር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይነሳ የሚፈልጉት የክልሉን የጨው ማዕድን ለመዝረፍ ነው፥ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የጋምቤላን ህዝብ የጨፈጨፉት የክልሉን ለም የእርሻ መሬት በኢንቨስትመንት ስም ለመዝረፍ ነው። በ1998 ዓ.ም የአዲስ አበባ ወጣቶችን እንደ ጠላት በጥይት የገደሉት የከተማዋን መሬት ለመዝረፍ እንደሆነ በተግባር ተመልክተናል።

በኦሮሚያና አማራ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ሲነሳ በእነዚህ አከባቢዎች ተመሳሳይ ንቅናቄ ያልተጀመረበት ዋና ምክንያት በፖለቲካዊ በደልና ጫና ላይ የብዝበዛ ቀንበር ስለተጫነባቸው ነው። በእነዚህ አከባቢዎች ላይ የብዝበዛ ቀንበር መጫን የቻሉት ደግሞ አብላጫ ድምፅና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መፍጠር ከሚችለው ከኦሮሞና አማራ ህዝብ ለብቻቸው በመነጠል ነው። ስለዚህ እንደ ኦሮሞና አማራ ህዝብ ፖለቲካዊ መብትና ነፃነታቸው ሊከበር ይገባል። እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ደግሞ ከኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ ነፃ ሊወጡ ይገባል። በመሆኑም በአራቱ ክልሎች፤ ኦሮሚያ፥ አማራ፥ ደቡብና ትግራይ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ከላይ የተጠቀሱትን ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች ከፖለቲካዊና አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና፣ እንዲሁም ከተጫነባቸው የኢኮኖሚ ብዝበዛ ነፃ ማውጣት የዶ/ር አብይ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል።

Filed in: Amharic