>

በዘመኔ ያየኋቸው ድንቅ ኢትዮጵያውያን!!!  (አሳዬ ደርቤ)

በዘመኔ ያየኋቸው ድንቅ ኢትዮጵያውያን!!!
 አሳዬ ደርቤ
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ፡-
 ከልጂነታቸው ጀምሮ የሃይማኖት አባት ለመሆን የታጩ፣ መቻችልን ይሰብኩን ዘንዳ አቻችሎ ከሚያኖረው የወሎ አፈር የተሰሩ፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በስስት እንዲያያቸውና መወክሉ እንዲያደርጋቸው…. በበረሐ ውስጥ ዘምዘም ውሃን የሚያፈልቅ አንደበት፣ ከማንነታቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ተክለ-ሰውነትና ለአገር የሚጠቅም ሸጋ አመለካከት የተሰጣቸው፣ ከእምነት መጽሐፎች ውስጥ ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ያስተምሩን ዘንዳ የተቀቡና ትልቅትነትን ከአላህ እጅ የተቀበሉታላቅ ኢትዮጵያዊ አባት ናቸው፡፡
አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ፡-
ሹመትና ታላቅነት ከማፊያዎች እጅ በሚገኝበት ዘመን… መስሎ በማደር ፈንታ ራሱን በመሆን ከትግል ወደ ትግል የተሸጋገረ፣ የዘመኑ ባለስልጣኖች በሀገር ሀብት ላይ ሲቆምሩ… ቆማሪ ከመሆን ይልቅ ተቆርቋሪ በመሆን ከቁማርተኞቹ ጋር እየተላተመ ብቻውን ሲንገላታ የኖረ፣ ስልጣን የሰጡት ሰዎች በዝርፊያ ስራ ላይ ሲሰማሩ የሚወርዱበትን ቀን በመጠባበቅ ፈንታ አቤቱታውን በማርቀቅ ወንጀለኞቹን የከሰሰበትን ማመልከቻ ለወንጀለኞች ሲሰጥ የኖረ፣ በበሽተኞች ከመከበቡ የተነሳ የራሱን ጤንነት እስኪጠራጠር ድረስ የማያስቆመውን የግፍ ስራ እያዬ ቆሽቱ ሲበግን የኖረ ታላቅ ሰው ነው፡፡
ዶክተር መረራ ጉዲና፡-
ህዝብን ከማባላት ይልቅ ህዝብን ለማግባባት ጽኑ ፍላጎት ያለው፣ ዶክትሬቱን ወደ ቢዝነስ ከመቀየር ይልቅ የአቶ መለስን መንግስት ለመቀየር ጥቅም ላይ ያዋለ… በአስተማራቸው ሰዎች ሲተች፣ ሲከሰስና ሲብጠለጠል የኖረ፣ በተማሪዎቹና በልጆቹ ከዩኒቨርስቲ መምህርነቱ የተባረረና የታሰረ፣ ከዘመኑ ጋር የማይለዋወጥ ጠንካራ አቋም ያለው፣ ለአንዱ ምቾት ሲል ለሌላው ስጋት መሆንን የማይመርጥ፣ ለህዝብ ከመታገልና አገሩን ከማገለግል የዘለለ የስልጣን ጥም የለለው፣ አላዋቂው ሁሉ ያለፈን ታሪክ እያነሳ ህዝብን በህዝብ ላይ ሲያነሳሳ ያለፉ መሪዎችን ከመውቀስ ይልቅ የዘመኑን ገዳዮች ማስወገድ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ የኖረ…
– ኦቦ ለማ መገርሳ፡-
ቅንነቱና መልካምነቱ ከፊቱ ገጽታው ላይ የሚነበብ፣ እንደ እርጎ የተረጋጋ ማንነት ያለው፣ እንቅፋት የሚሆኑበትን ሰዎች በዛቻው ሳይሆን በዝምታው የሚያሸንፍ፣ አንድን ነገር ለመፈጸም ሲነሳሳ በብሔር ጭንብል ሳይሆን በአገራዊ መነጽር የሚያስተውል፣ በተናጠል ከመሮጥ ይልቅ በቲም መስራትን የሚመርጥ፣ በኢትዮጵያዊነትና በመልካምነት ሱስ የተለከፈ፣ ምድር ላይ ለመስራት እንጂ መድረክ ላይ ሪፖርት ለማቅረብ የማይጋፋ….
ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፡–
ከዚያ ትውልድ ጋር አብሮ የታሰረ፣ የተማረውን ፍልስፍና ሲያስተምርና ሲተገብር የኖረ፣ በነጻ አስተሳሰቡ በመሃይም ባለስልጣኖች ውሳኔ ከዚህ ትውልድ ጋር ተገፍትሮ የነበረ፣ ባገኘው መድረክ ሁሉ ለአገራችን ይጠቅማል የሚለውን ምክር ያለ ስስት በመለገሱ የሚታወቅ፣ የተማረው ሁሉ ገንዘብን በሚያባርርበት ሰዓት እራሱን በመጽሐፍቶች በመሙላት ጭንቅላቱ ውስጥ ላይብረሪ ያቋቋመ….
-አቶ ኦባንግ ሜቶ፡–
ኢትዮጵያዊነት ከማይሰበክበት የጠረፍ ስፍራ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የተወለደ፣ ከተገለለ ህዝብና ምድር ላይ ተኸልቆ ለእኛ ለመሃል አገሮቹ ኢትዮጵያዊነትን ያስተምር ዘንዳ ከጋምቤላ ወደ ሸዋ የተላከ፣ እኛ የጣልነውን የኢትዮጵያዊነት ካባ ከመሬት ላይ አንስቶ በጥቁር ሰውነቱ ላይ በመጎናጸፍ በእራሳችን ቋንቋ የአባቶቻችንንና የአገራችንን ታሪክ እየሰበከን የሚገኝ ጥቁር መሲህ፣ ልንለግሰው የሚገባውን ክብርና አድናቆት ሳይጠብቅ ወደ አርሶ አደሩ በመሄድ እርሻቸውን እያረሰ፣ በጭቃ እየተለወሰ አንድነትንና ፍቅርን በማስተማር ላይ የሚገኝ ጥቁር ብርሐን…
ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴክሳ፡
አሳሪውም፣ ከሳሹም፣ ምስክሩም፣ ፈራጁም ኢህአዴግ በነበረበት ሰዓት የሙያ ግደታዋን የተወጣች፣ ‹‹በህግ እንጂ በሰው አልመራም›› በማለት ስራዋን የለቀቀች፣ ፖለቲካ ክስረት በነበረበት ሰዓት በፓርቲ ታቅፋ አምባገነኑን ስርዓት የታገለች፣ ይቅርታ አልጠይቅም በማለቷ የተነሳ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ የእድሜ ልክ እስር የተፈረደባት፣ በወህኒ ቤት ውስጥ የሚፈጸመውን ግፍና ጥቃት ተቋቁማ አልሸነፍ ባይነቷን ያሳየች፣ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከከፈለች በኋላመ የሰላም አየር እየተነፈሱ ከመኖር ይልቅ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ ተመድባ በሙያዋ ህዝቧን ለማገልገል ወደ ሃገሯ የተመለሰች…
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፡–
ጋዜጠኝነትን በእውቀት የጀመረች፣ ተወዳጅነትን ያተረፈ ሚዲያ መገንባት የቻለች፣ የምትጋብዘውን እንግዳ ጠንቅቃ የምታውቅ እና ስለ ተጋባዧ ማንነት ከባለቤቱ በላይ በቂ መረጃ ያላት፣ የሐገሪቱ ሬድዮ ጣቢያዎች ሁሉ ስፖንሰር በሚያገኙበት የኳስ ትንታኔ ላይ ሲሰማሩ በገነባችው ሚዲያ ላይ ብዙ አይነኬ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ ስታደርግ የኖረች…
-ጋሼ አብዱ (ሸገር ካፌ)፡-
በተለያዩ ዘርፎች ላይ በቂ እውቀትን ያከማቸ የመረጃ ቋት፣ ከመአዛ ብሩ ጋር ተቀናጅቶ በሚያቀርበው አስደማሚና አስገራሚ የሸገር ካፌ ፕሮግራሙ ጎታታውን የሰንበት ጧት በጉጉት እንዲንጠብቀው ሲያደርገን የነበረ፣ መንግስት የሚሰራቸውን ህጸጾች ከእውነትና ከህግጋት አንጻር እየተመለከተ እስከጫፍ ድረስ በድፍረት ሲናገር የኖረ፣ ቀኑን ሙሉ ቢናገር የማይሰለችና የማይጠገብ የህግ ሙህር…
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ፡-
ኪነት አስመሳይና ቀፋይ በነበረችበት ዘመን ራሷን ችላ እንዲትሄድ ማድረግ የቻለ፣ የጥበብን ከፍታ ማንም እንዳይደርስባት አድርጎ ከዳሽን ተራራ ጫፍ ላይ የሰቀለ፣ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ እንደ ባልንጀሮቹ መሬት በመቀበል ፈንታ ከህዝብ ጎን ወግኖ እስራትን ለመቀበል የመረጠ፣ እንደ እሱ ብዙ ተስፋ ያለው ቀርቶ የሚበላው ምሳ የሌለው ዜጋ መንግስትን በፍራቻ በሚመለከትበት ሰዓት በሁለት ስንኝ ግጥም የህውሓቶችን ቅስም የሰባበረ፣ በዚህም የተነሳ ‹‹ኮንሰርት ማዘጋጀትን፣ ሙዚቃ ማስመረቅን፣ በፈለገው ጊዜ ወደ ውጭ አገር መሄድን፣ በፈለገው ቦታ መገኘትን›› የሚከለክል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎበት እንዲኖር ሲደረግ ከፍታውን አስጠብቆ መዝለቅ ያላቃተው፣ በገንዘብ ሳይሆን በጥበብ በመመራት እራሱን የህዝብ ሃብት፣ ህዝቡን ደግሞ የራሱ ሐብት ማድረግ የቻለ….
ዶክተር አረጋዊ በርሔ፡–
እንደ ጓዶቹ ሐብት በማከማቸት ፈንታ ራሱን በእውቀትና በትምህርት ሲገነባ የኖረ፣ ለድጋፍ በሚያገለግለው ቋንቋ ነቀፌታውን ሲገልጽ የተሰማ፣ አብሮ አደጎቹ ወደ ውጭ መውጣት በሚፈልጉበት ሰዓት ለውጡን ለመደገፍ ወደ አገሩ የተመለሰ፣ አብዛኞቹ የትግራይ ሙህራን፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አገር ወዳዱን የትግራይን ህዝብ ከራስ ወዳዱ ህውሓት ጎን ለማሰለፍ ሲፍገመገሙ… ከጥቂት ጓዶቹ ጋር ተነጥሎ በመውጣት የሚወደውን ህዝብ በትክክለኛው መንገድ ለማስገባት ጥረት እያደረገ የሚገኝ፣ ተነጥሎ መቃወምም ሆነ ተነጥሎ ድጋፉን መግለጽ የሚያስችል ግዙፍ የራስ መተማመን የተሰጠው…
ቴዎድሮስ ጸጋዬ፡-
 
 በFM 97.1 ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሚሰራቸው ፕሮግራሞቹ ብዙ ርዕዮቶችን የገለጠ፣ በብቃትና በመክሊት ሳይሆን በገጠመኝ ታዋቂ የሆኑትን ገለባዎች በጠንካራ ሙግቱ ያስጎነበሰ፣ ታላቅ ሆነው ሳለ የተረሱትን እንደ ጋዜጠኛነቱ እያስታወሰ በሚችለው ልክ ያሞገሰ፣ ወደ ብሔር አሮንቃ ሊከቱት የሚፈልጉትን ሰዎች ከአሮንቃቸው በመምዘዝ አገራቸውንና አገሩን ያመላከተ፣ እኛ ዐይናሞቹ ማየት የማንችለውን ሙላትና ጉድለት የሚመለከት ታለቅ ብርሐን በልቡ ውስጥ የተለኮሰለት….
 
-ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፡-
ሚዛናዊ፣ ሁሌም ከእውነት ጋር የቆመ፣ በእውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ የሙያ ግደታውን የሚወጣ፣ ብዙ የማያወራ፣ ከስሜታዊነት የጸዳ፣ እንደ ጋዜጠኝነቱ ሁሉንም ነገር ከመተቸት ይልቅ እንደ አገር ወዳድነቱ በቁጥብ አንደበቱ በጎውን የሚያወድስ፣ ሕሱሙን የሚነቅስ….
-ከዚህ ባለፈ ደግሞ የእናንተ ስልቹ መንፈስ ቢገድበኝም…. የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በየነና የሶማሊያ ክልል አዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ኡመር ምርጥ ኢትዮጵያዊያን የምላቸው ሰዎች ናቸው፡፡
በመጨረሻም የእነዚህ ምርጦች ‹‹ጠርናፊ›› በማድረግ ዶክተር አቢይን ከራስጌ በኩል አስቀምጡልኝ፡፡ ‹‹አደናቃፊ›› የምትሏቸውን ደግሞ እናንተ ዘርዝሯቸው፡፡
Filed in: Amharic