>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7098

የክብር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ 15ኛ የሙት  ዓመት መታሰቢያ!!! (ልኡል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የክብር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ 15ኛ የሙት  ዓመት መታሰቢያ!!!
ልኡል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል
✍️📖

ደራሲ፣ መምህር፣ ፖለቲከኛ፣ አርበኛ፣ ባለቅኔ፣ … የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ያረፉት ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት (ኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም) ነበር፡፡ 

የክብር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም ከአባታቸው ከቄስ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ በደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በጎዛምን ወረዳ፣ በእንጾር ኪዳነ ምኅረት ቀበሌ ተወለዱ። ገና በለጋ  እድሜያቸው በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት በቤተሰባቸው አጠገብ ሆነውና ወደአባታቸው አገር፣ ደብረኤልያስ ሄደው የግእዝ ትምሕርት ቤት ገብተው ቅኔ ተቀኝተዋል።
የቤተክርስቲያን ስርዐታትንና መንፈሳዊ ትምህርትን በጎጃም ገዳማት በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ ከቀሰሙ በኋላ በ1918 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን ሚሽነሪ ት/ቤት፤ በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ከዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል በአስተማሪነት ሥራ ተሰማርተው እንዳገለገሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ።
የኢጣልያ ወረራ ሲከሰት ከልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴ ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በመያዛቸው ጣሊያን ከልዑል ራስ ዕምሩ ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት በፖንዞ እና በሊፓሪ ደሴቶች ታስረው ቆይተዋል። ከእስር ቤት ወጥተው በትምህርታቸው ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተለይም በትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜያት አገልግለዋል።
‹‹ሀበሻና የኋላ ጋብቻ››፣ ‹‹ተረት ተረት የመሰረት››፣ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››፣ ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ››፣ ‹‹የልም ዣት››፣ ‹‹ትዝታ›› በሚሉትና በሌሎችም ስራዎቻቸው ተወዳጅነትንና ታዋቂነትን ያተረፉት የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ፣ በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ላይ ያሳረፉት አሻራና ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከሁሉም የዘርፉ ሰዎች ላቅ ያለ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው በሥነ ጽሑፍ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ለመሆን የበቁ ሰው ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የዶክተርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic