ሳሙኤል ገዛህኝ
”Red Indians” ወይም ”ቀያይ ህንዶች” በመባል የሚታወቁት የዛሬዋ USA ነባር ህዝቦች የዛሬ 500 ዓመት ገደማ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፖውያን አሳሾች እና ስደተኞች እንደተወረሩ ታሪክ ይነግረናል:: ቀያይ ህንዶቹ Native American በመባልም ይታወቃሉ::
እነዚህ በዋራሪዎች ለሺህዎች ዘመናት በኖሩበት አገራቸው ግፍና ወረራ የተፈፀመባቸ ባህል እና ቋንቋቸው የጠፋባቸው red Indians ዛሬ ቁጥራቸው ስለመነመነ: ቋንቋቸው ስለጠፋ: ማንነታቸው ስለተበረዘ: አገሩ የእናንተ አይደለም: ለብቻችሁ ክልል ያዙ አልተባሉም ይልቁንም የምድሪቱ ነባር ህዝብነታቸው ታውቆላቸው በአንድ አንድ ሁኔታም ልዮ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ህግ ተደንግጎላቸዋል በክብር ይኖራሉ::
በተመሳሳይ ሁኔታ በኢትዮጵያችን በ16ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የግራኝ አህመድ ውጊያ እና የኦሮሞዎች የመስፋፋት ዘመን በደቡብ በመካከለኛው እና በሰሜን ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ነባር ህዝብች በሰፊው የተፈናቀሉበት: ቋንቋቸውና ባህላቸው እንዲጠፋ የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር::
በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ወረራ ሞጋሳ በሚባለው የማዋሃድ ስራና በማስገደድ ብዙ ነገድ እና ቋንቋ ጠፍቷል: ማንነታቸው ተበርዟል: ቁጥራቸው ተመናምኗል::
ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ የተሰየመው ክልል በአብዛኛው ነባር ህዝቦች ይኖሩበት የነበረ አካባቢ ነው:: ለምሳሌ አማራዎች አብዛኛውን ሸዋ: ጉራጌዎች: እናርያዎች: ሃድያና: ሲዳማዎች ሰፊውን ደቡብ ይኖሩበት ነበር:: በምእራብ ኦሮሚያም እንደዚሁ በርካታ ነባር ህዝቦች ይኖሩ ነበር::
አሁን በኦሮሚያ የሚኖሩ የጥንት ነባር ህዝቦች እንደመጤ መቆጠራቸው: የክልሉ ባለቤት እንዳልሆኑ መነገሩ በምንም አይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም:: ይልቁንም እንደ ነባር የአካባቢው ነዋሪነታቸው ታሪካቸው ታውቆ ልዮ እውቅና ሊደረግላቸው ይገባል::
በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ በተመሳሳይ በሌሎችም ክልሎች እና ክፍለ ሃገሮች ያለው የህዝብ ታሪክ ታውቆ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእኩልነት በነፃነት የምንኖርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት::
ጥንት እድሜው ስንት ነው?
በባለፉት 27 ዓመታት በህወኃት የከፋፍለህ ግዛው ዘመን ሁለት ዘመናት የታሪክ ማጣቀሻቸው እና የአገር ታሪክ መጀመሪያ ሲያደርጉት ኖረዋል:: አንደኛው ከአፄ ሚንሊክ ንግስናና አስተዳደር ዘበን ጀምሮ ያለውን ሲሆን ሌላው ወያኔ ወደ ስልጣን የመጣበትን ከ1983 ጀምሮ ያለውን ጊዜ ነው::
በመሰረቱ እነዚህ ዘመናት እጭር እና የአንድ ሰው እድሜ ርዝማኔ ያላቸው ናቸው:: እነዚህን ቁንፅል ጊዜያት እያጣቀሱ ገናና እና ታላቅ ባለትሪክ ህዝብን ለማስተዳደር መሞከር ስላቅ ነው :: ነውርም ነው::
ለአገራችን እና ለህዝቧ ሁሉ የሚበጀው በፋሽስት ህወሓት የከፋፍለህ ግዛው አስተዳደር በወረራና በሴራ የተጫነብንን የውሸት ታሪክ እና የጎሳ አስተዳደር አፍርሰን የዜጎች እኩልነት የሰፈነበት ፍትሃዊ አስተዳደር መመስረቱ ነው::
ሌላው ቁም ነገር እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ የተዋሃደ እና የተዋለደ ህዝብ ሌላ ብዙም አይገኝም:: ቋንቋ እና ባህሉን ከማንፀባረቁ ባለፈ ማንም በዘር ምርመራ እኔ የእገሌ ነኝ ብሎ ሊኩራራ እና በዘር ሊቧደን አይቻለውም:: ስለዚህ በጎሳ መቧደኑን ትተን በዜግነት ክብር አብሮ መኖሩ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው::