>

ያባቶቻችን ታሪክ የሚያስተምረን የሀገር አንድነትን እንጅ በየቀጠናዉ አጥርና ክልል መከለልን አይደለም!! (ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት)

ያባቶቻችን ታሪክ የሚያስተምረን የሀገር አንድነትን እንጅ በየቀጠናዉ አጥርና ክልል መከለልን አይደለም!!
 
ዶ/ር  ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት
የቅማንት ነገር ከተነሳ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁሌም አብሮ ይነሳል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘር በተቧደኑ ግለሰቦች ተሞልቷል ይባላል፡፡ ሰሞኑንን በቅማንት ስም በአማራ ሕዝብ ላይ ከተፈፀመውን ወንጀል ጋር ተያይዞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እጃቸው እንዳለበት በስፋት በማህበራዊ ሚዲያዎች ተወርቷል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ ጎንደር ከተማ ተወልደው በአማረኛ አፋቸውን ፈትተው ያደጉና የተማሩ፣ የቅማንት የዘር ሀረግ እንዳለቸውም፣ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ከደም ይልቅ ሥነ-ልቦና የማንነት መገለጫ አርገው እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
በቅማንትና በአማራ መካከል ለተፈጠረው ችግርም “ምሁራንን” እና ስልጣን ፈላጊዎችን ወቅሰዋል፡፡  ዶ/ር ደሳለኝ እንዲህ ይላሉ፡-
“ የቅማንትን ብቻ ሳይሆን የማንኛዉም ብሄር/ብሄረሰብ ጥያቄንም የማክበር ግዴታ አለብኝ። አከብራለሁም። እጅግ የሚያሳዝነኝ ግን የቅማንትና የአማራ ወንድማማች ህዝቦችን እዚህ ያደረሱት ”ምሁር” ተብየዎችና እኛ እናዉቅልሀለን የሚሉ ሳይማሩ ራሳቸዉን ታሪክ ፀሀፊ ያደረጉ እርጉማን ናቸዉ። እነሱን ተከትለዉ በሀሳባቸዉ ወሰንና ግዛት ያሰመሩ ተከታዮቻቸዉም ባሰቡት መዋቅር ውስጥ ራሳቸዉን በመሰግሰግ በየደረጃዉ በነቀዘ ህሊናቸዉ ራሳቸዉን ለዘረፋና ለስርቆት ሲያመቻቹ የተከተሉት መንገድ በማንኛዉም ወገን ለሽዎች ሞትና ስደት እንደሚዳርጉት ጠፍቷቸዉ አይደለም።
ለህዝብ ጥቅም የሚቆም ትክክለኛ የህዝብ ወኪል ህዝብ ሲሰደድና ሲጨፈጨፍ የራሱን ምቾትና ደህንነት አይጠብቅም ነበር። እስካሁን በአራቱም የሀገሬ ማዕዘናት በታዘብኳቸዉ ቦታዎች ልዩ ወረዳም ይሁን ልዩ ዞን በራሳችን እናስተዳድራለን የሚሉ ‘እንደራሴዎች’ እንደ መዥገር ተለጥፈዉ ህዝብን ሲበዘብዙ እንጅ አንዳችም የህዝብ ኑሮ ሲለዉጡ አላየሁም። የመዋቅር ብዛት ያገሬን ገበሬ ከበሬዉ ስር ስር አየተከተለ ከከብትና ከአህያ ጋር በጨለማ እያደረ ብርሀን ባለበት ከተማ እየሄደ ግብር ሲጠፈጥፍ እንጁ ኑሮዉን ሲለዉጥለት አልተመለከትኩም።
በእድገቴና በኑሮየ ሁሉ የኖርኩት እዉነታ ጎንደር ላይ የቅማንት ማህበረሰብ ከአማራ ወንድሙ ጋር በፍቅር ሲኖር ነበረ። አሁን እንደሰርገኛ ጤፍ የማይነጣጠሉ ህዝቦችን ችግር ያራራቁ ተዋናዮችን ህዝብ ሊያወግዛቸዉ ይገባል። ፈጣሪም ምስኪን ህዝቦችን በቃችሁ ሊላቸዉ ይገባል።
በመጨረሻም ለአማራና ቅማንት ወገኖቸ ያለኝ ምክር ህዝቡን ችግር ውስጥ እየከቱት ያሉት የዉስጥና የቅርብ ሩቅ ህሊና ቢሶች እንጂ ሁለቱ ህዝቦች የፈጠሩት እንዳልሆነ በመረዳት ወደቀድሞ አብሮነት እንዲመለሱ እንደ አንድ ሀላፊነት እንደሚሰማዉ ኢትዮጵያዊ እመክራለሁ። የሀይማኖት አባቶች፣ መንግስት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶች በሰከነ ልቦና ቢያስቡበትና ቢነጋገሩበት ወደ ቀደመዉ ሰላም ሊመለስ ይችላል።
ዘረኝነት ከሀይማኖት በላይ አይሁን።ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ናት። ያባቶቻችን ታሪክ የሚያስተምረን የሀገር አንድነትን እንጅ በየቀጠናዉ አጥርና ክልል መከለልን አይደለም። ሽህ ዘመን ለማንኖርባት ምድር ፍቅርና ሰላምን እንጂ ጦርነትና ጥላቻ አንዝራባት። የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችም ቀለም እንጅ ዘር መቁጠር  አናስተምራቸዉ።
እዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።”
Filed in: Amharic