በአለማየው ገላጋይ
“ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ አይደል? እንደ አብዛኛው…..አዲስ አበቤ እግሬ እንጂ ህልሜ አልታሰረም። ምናቤ ነፃ ተጓዥ ነው። በራሪ ህልም አለኝ። በመንፈስ ስከንፍ የክልል ቀርቶ የአገር ድንበር አያነቅፈኝም። ወገንተኝነት አይዘኝም፣ ብሔርተኝነት አይገድበኝም። የፍቅር እጄ በየአቅጣጫው እንደ ጨረር ይበተናል። ያገኘሁት ወገኔ ነው። “እኛ” ለማለት ቦታና ጊዜ አይገስፀኝ። እኔ አዲስ አበቤው ለማቅረብ ስል የማርቀው የለኝም።
ምን ላድርግ? የተወለድኩት ከአንድ እናትና አባት ይሁን እንጂ ያደግኩት በብዙዎች ነው። ወላጅ እናት ለንዴቷ ስትጨክን፣ የምትመክር ሌላ እናት ከጎረቤት አለች። ያቺ የጉርብትና እናት ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከሐረሪ….መሆኗ ልብ አይባልም። ወላጅ እናት በእልህ የነፈገችው እህል ከጉርብትና እናት ይገኛል። ማን መርጦ ይወለዳል? እንዲያ ነው!
…አባት ሲያመር፣ ፀባዩ ሲገርር የሚመክር ሌላ የጉርብትና አባት ይነሳል። “እኔን ግደል!” ብሎ በጉርብትና ልጅ ገመድ ይገባል። ልጅ ከወላጅ የሚፈራውን፣ የተጎራባች አባትን ይጠይቃል፤
“እስክሪብቶ ገንፍሎብኝ አባዬ ከሰማ ይገድለኛል” ይባላል።
እንዲህ ነው ያደግኩት…..
ተጎራባች አባት ከየት? ከሲዳማ? ከኩናማ? ከድሬ? ከቡሬ? ከኤርትራ? ከጎርጎራ፣ ከጎንደር፣ ከሐረር?….ምን ለውጥ ሊፈጠር?
…እኔ አዲስ አበቤው ያደግኩት በደቦ ነው። የሴቶች ቀሚስ ተጋርዶ፣ ካንዱ ቤት ወደ ሌላ ቤት የተመላለሰው እንጀራ ህያው መረብ ሰርቶ፣ ህይወቴን ለዝንታለሙ አጥምዶታል። የበላሁት የብዙ ብሔሮችን ወዝ ነው። ከተማዬ እንጂ ህይወቴ በሚለያይ “ተራራ” አልተከበበም። ከተማዬ እንጂ ኑሮዬ ደረቅ ደሴት አይደለም። አንድ ኪሎ በርበሬ በ “ቅመሱ” ስም ስንት ደጃፍ ታንኳኳለች? ሽሮዋስ ለስንቱ ጎጆ ትሞሸራለች?
እትብቴ አንድ ጉድጓድ አጥቷል። በየቦታው ተዘርቷል። ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ እዚያ እትብቴ የተቀበረበት ይሆናል። ወገንተኝነቴ ተቀይጧል፤ አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አንጠልጥሎ መሆን አይሆንልኝም። የአባቴ ትውልድ አገር፣ የእናቴ ትውልድ አገር በተጎራባች ወላጆቼ ሲሳከር፣ ምን ይፈጠር?
እራሴን ልፈትሽ፣ ልቤን ልበርብር…….
ኡፍፍፍፍፍ……! መሰልቸት ሳይሆን ህመም አለበት። የአዲስ አበባ ድንበር ለአይን እንጂ ለምናብ ተራራ የለውም። በሁሉም አቅጣጫ እንዲያ ወዲያ…. ወዲያ…. ወዲያ፣ ወገን፣ ዘመድ፣ ሥጋ….አለ። እትብቴ የተቀበረው የተወለድኩበት ቤት ጓሮ አይደለም። ሁሉም ቦታ ተሰራጭቷል። በአስተዳደጌ ውስጥ የሁሉም “እጅ እላፊ” አለብኝ – በማጉረስም በመቆንጠጥም።
ትግራይ ብቻ፣ አማራ ብቻ፣ ኦሮሞ ብቻ፣ ጉራጌ ብቻ፣ ሐረሪ ብቻ፣ ጋምቤላ ብቻ፣ ቤኒሻንጉል ብቻ፣ አፋር ብቻ፣ ሶማሌ ብቻ፣ ወላይታ ብቻ፣ ሲዳማ ብቻ፣….. መሆን ለኔ የተሰጠ አይደለም። ትግራይነትን ብቻ፣ አማራነትን ብቻ፣ ኦሮሞነትን ብቻ፣ አፋርነትን ብቻ፣ ወላይታነትን ብቻ…… በሚያስቡ መገዛት ለኔ ማነስ ነው። ማነስ ብቻ ሳይሆን ውርደት ነው። እንዴት ሁሉን ጥቂት ይበልጠዋል? እንዴት ባሕርን ወንዝ ይውጠዋል? በቀዬ ውስጥ አገር እንዴት ያድራል? ብዙ በጥቂት ይታሰራል?……..”
መለያየት ሞት ነው።