>

የፋሽስት ወያኔንም የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ አገዛዝንም የሚያስንቁ  «ጎበዞች» እየመጡ ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የፋሽስት ወያኔንም የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ አገዛዝንም የሚያስንቁ  «ጎበዞች» እየመጡ ነው! 
አቻምየለህ ታምሩ
 
* የፋሽስት ወያኔን የአፓርታይድ ሥርዓት ታግለን ከፋሽስት ወያኔ የከፋ የአፓርታይድ አገዛዝ ከፊታችን ተደቅኗል።  በፋሽስት ወያኔ ጭካኔ ተማረን ጨካኙን መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን «መንጌ ናልን» እንዳልን  እስኪያንገሸግሸን የመተረንን  የወያኔን የአፓርታይድ ስርዓትም  የምንናፍቅበት   ቀን መምጣቱ አይቀሬ ነው!!!
— 
ሕዝቡ ተደብቀው  የልባቸው የሚያወሩትን ሳይሆን ባደባባይ ባማርኛ የሚያወሩትን እያየ  ለውጥ የመጣለት መስሎት በባዶ ሜዳ  ጉም  በመዝገን በፈንጠዝያ አለሙን ሲቀጭ  «ጎረቤቶቻችን» የሚሉን እነ እንተና ግን ካሁን በኋላ ኦሮምኛ የማይችል የኢትዮጵያ መሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና የአዲስ አበባ ምክር ቤት እንደራሴ መሆን አችልም የሚል ሕግ እንዲወጣ እየጠየቁ ነው።
ባልጋው ላይ  ያሉት ልክ  በአኖሌው ሐልውት ግንባታና  በቴሌቭዥን አስነብበውን  በነበረው የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ረቅቅ አዋጅ  እንዳደረጉት ሁሉ ይህ ጉዳይ  ተጠንቶ  ረቂቅ ይቀርብላቸው ዘንድ  ሰዎችን አሰማርተው እያሰሩ መሆኑን ዛሬ እየተቀባበሉ በፌስቡክ የጻፉ ጎበዞች ከመጻፋቸው ከቀናት በፊት    በውስጥ መስመር ካለኝ ግንኙነት ለማወቅ  ችዬ ነበር። ይህንን እንደሚያደርጉ  ብዙ ሰው ሊጠራጠር ይችላል። ለነገሩ  የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ በሚከፍለው ገንዘብ  ያልተመረጠው ታከለ ኡማ ማንምም ሳያማክር የአዲስ አበባ ከተማን የትምህርት ቋንቋ በተሾመ በቀናት ውስጥ  መቀየሩንና ወደ ተግባርም እንደገባ  የማያውቅ  ያ ቀን እንደሚመጣ ቢጠራጠርና በአማርኛ የሚናገሩትን ብቻ እያመነ ቢታለል አይገርመኝም!
ወያኔ የዘረጋው  መዋቅር የአፓርታይድ አገዛዝ ከሆነባቸው አንዱ  ስርዓቱ የተዋቀረው ኢትዮጵያን ኦሮሞ ፣ አማራ፣ ትግሬና ደቡብ  ብሔር፣ ብሔረሰቦች ከሚባሉት ውጭ  በመሪነት እንዳያስተዳድራት መመሪያው  በማድረጉ ነው። ዛሬ እየተተገበረ ባለው የአፓርታይድ ስርዓት ከሶማሌ፣ ከጋምቤላ፣ ከአሶሳ፣ ከአፋር፣ ወዘተ  ነገዶች የሚወለድ ጎበዝ  ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መሆን አይችልም። ኢሕአዴግ ከሚባለው  የአራቱ ድርጅቶች አባል  ውጭ የሆነ ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያን ማስተዳደር እንደማይችል ልብ ይሏል!
ዛሬ ያለው የአፓርታይድ መዋቅር ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርነት መታጨት የሚችለው   ከአሮሞ ፣ ከአማራ፣ ከትግሬና ከደቡብ  ብሔር፣ ብሔረሰቦች ከሚባሉት ብቻ ነው ብለናል።  የዛሬ ባለጊዜዎቹ ደግሞ ይህንን የወያኔ የአፓርታይድ ስርዓት  እጅግ ፍጹም በማድረግ [ከወያኔም  በመጥበብ]  ካሁን በኋላ ለኢትዮጵያ መሪ መሆን ያለበት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሊሆን የሚገባውና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ምክር ቤት መወዳደር የሚገባው   ኦሮሞ ብቻ ነው እያሉን ነው።
እንደ እውነቱ  ከሆነ የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ስርዓት እንደነዚህ ሰዎች እሳቤ እጅግ የከፋ ስርዓት አልነበረም! ከእንግሊዝ፣ ከደችና ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ዝርያ ያላቸው የደቡብ አፍሪካ መሪ መሆን ይችሉ ነበር። ባለጊዜዎቹ ግን ከኛ ውጭ ካሁን በኋላ መሪ መሆን ብቻ ሳይሆን ከንቲባና የምክር ቤት እንደራሴ መሆን አይችልም እያሉን ነው። በቀለ ገርባ «የኦሮምያ ጦር ሊመሰረት ይገባል፤ የኦነግ ጦር መጣልን፤ የኦሮምያ ጦር አካል መሆን አለበት እያልን ስንጠብቅ እስካሁን ይህ አልሆነም፤ ወደፊት እንዲሆን እንፍጠን» ሲል  የጋራ ፎረም በመጠሩበት መድረክ  ከሰሞኑ መናገሩን አንድ ወዳጄ  ፎረም የመሰረቱት ፓርቲ አመራሮች የተናገሩትን ልኮልኝ አስደምጦኛል።  በሕዝቡ ዘንድ «ነብይ» የተደረገው ዐቢይ ያመጣው «ለውጥ» እዚህ ደርሷል!  ማን ያውቃል ወደፊት በበቀለ ገርባ የሚመራ «የኦሮምያ ጦር» ይኖረን ይሆናል!
እንግዲህ ምን ቀረን! የፋሽስት ወያኔን የአፓርታይድ ሥርዓት ታግለን ከፋሽስት ወያኔ የከፋ የአፓርታይድ አገዛዝ ከፊታችን ተደቅኗል።  በፋሽስት ወያኔ ጭካኔ ተማረን ጨካኙን መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን «መንጌ ናልን» እንዳልን  እስኪያንገሸግሸን የመተረንን  የወያኔን የአፓርታይድ ስርዓትም  የምንናፍቅበት   ቀን መምጣቱ አይቀሬ ነው። ወደፊት  የፋሽስት ወያኔን የአፓርታይድ ስርዓት የምንናፍቅበት ቀን ባይመጣ ዛሬ የጻፍሁትን በመናገሬ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
Filed in: Amharic