>

ገነት ዘውዴ እና ሙሉ ሰለሞን እንደ አናቃቂ ተናጋሪ (Inspirational speakers) [ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ]

ገነት ዘውዴ እና ሙሉ ሰለሞን እንደ አናቃቂ ተናጋሪ (Inspirational speakers)

 

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ኮተቤ  ሜትሮፖሊን  ዩኒቨርስቲ

 

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ህዳር 28፣ 2011ዓ.ም. (Ensuring sustainable development through empowering women academicians) በሚል ርዕስ በግዮን ሆቴል የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት መድረኮች ወጣት ሴት ተማሪዎችን፣ መምህርትን እና ሴት ተመራማሪዎችን የሚያበረታታ ስለሆነ ጉዳዩ ወቅታዊና ተገቢ ነው፡፡ በጉባኤው ላይ አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ፣ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ ፕሮፌሰር አለምፀሀይ እና ዶ/ር አስቴር ፀጋዬ አናቃቂ  ተናጋሪዎች ሁነው ተጋብዘው ነበር፡፡ሁሉም ተናጋሪዎች ግሩም የሆነ የህይውት ተሞክሮዓቸውን ለወጣት ሴት ተማሪዎችና ሴት መምህራን አካፍለዋል፡፡

በተለይወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን እጅግ ግሩም የሆነች ተናጋሪ ከመሆንዋ በላይ ለሴት እህቶቻችን ጥሩ ምሳሌ መሆን የምትችል እህት ነች፡፡ የማትሰለች፣ አንደበተ-ርቱዕ፣ ድንቅ ኢትዬጲያዊ ነች፡፡ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በተለያዩ መድረኮች በየክፍለ-ሀገሩ እና በየ-ትምህርት ተቋማት እየተዘዋወረች ንግግር ብታደርግ የበርካታ ኢትዬጲያዊ ሴቶችን ግንዛቤ የመቀየር እምቅ አቅም ያላት ፍቅር የሆነች ሴት ነች፡፡ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን የመምህርትን ባህሪ የተላበሰች፣ አቀራረብ የምትችል፣ ለዛ ያላት አስተማሪ ነች፡፡

አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴም ንግግር ካቀረቡ ምሁራን አንዷ ነበሩ፡፡ አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴን ለመጠየቅ ዕድል አግኝቸ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የበፊቱ የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ስመ-ጥር የሆነ የመምህራን ማፍለቂያ ተቋም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ መስተዳድር ስር ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ግን እንደ ሌሎች የፊዴራል ዩኒቨርስቲዎች በሚጠበቅበት ደረጃ አለማደጉ የዶ/ር ገነት ዘውዴ የፖለቲካ ውሳኔ እንደ ነበር እና በኢትዮጲያም ለሚታየው የትምህርት ስርዓት ውድቀትም እንደ ሚኒስተር የዶ/ር ገነት ዘውዴ አስተዋፅዎ ከፍተኛ እንደነበረ እና ለነዚህ ጉዳዬች በምን ያህል መጠን እንደሚፀፀቱ ጥያቄ አንስቸላቸው ነበር፡፡  ዳሩ ግን ዶ/ር ገነት ዘውዴ የሚፀፀቱ ሰው እንዳልሆኑ ከንግግራቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡

የዶ/ር አብይ አስተዳደር ሁሉንም ነገር በይቅርታ እና በፍቅር ለማለፉ የሚያደርገውን ጥረት ከባንዳዎች ጋር ሁነው አገርን የዘረፉ፣ ትውልድን ያመከኑ፣ የበፊቱ ስርዓት ባለሟሎች ያጠፉት ጥፋት ሊታያቸው አለመቻሉን በዶ/ር ገነት ዘውዴ መልስ ለመረዳት ችያለሁ፡፡በህግ መጠየቅ እና እስር ቤት መግባት የነበረባችው የበፊቱ ስርዓት አጋፋሪዎች የመልካም ስራ ተምሳሌት ሁነው መቅረባቸው ምን ያህል የሞራል ልዕልናቸው እንደወረደ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የበፊቱ አስተሳሰባቸው ምን ያህል ወደ ኃላ እንደሚጎትታቸው የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ሰው ባጠፋው ጥፋት ተፀፅቶ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ይቅርታ መጠየቅ ሰብዓዊ ባህሪነው፤ ባጠፋው ጥፋት መታበይ ግን አላዋቂነት ነው፡፡አጥፊ ከሆነ ስርዓት ጋር ወይም ህዝባዊ ድጋፍ ከሌለው መንግስት ጋር ህዝቡን ሲበድሉ፣ ሲያሳዝኑ፣ሲዘርፉ፣ሲገሉ እና በትውልድ ህይወት ላይ ሲያፌዙ የነበሩ ግለሰቦችን እንደ ምሳሌ አድርጎማ ቅረብ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት ተጠያቂነት ከሌለው ስርዓት ጋር መወገን ምንም አይነት ዋጋ  እንደማያስከፍል እና የአድርባይነትን ሰብዕና እንዲላበሱ ነው የሚያደርጋቸው፡፡ የመልካም ነገር ተምሳሌት መሆን የማይችሉ ዜጎችን ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ የግለሰቦችን ደካማ ባህሪ ዕውቅና መስጠት እና ሌሎች እንዲጋሩት መጋበዝ ነው፡፡

ምሳሌ መሆን የሚችሉ ድንቅ ሴት ኢትዮጲያውያን ባልጠፉበት ሀገር የጥፋት ተልዕኮ ከያኒያንን የሆኑ ምሁራን እንደ አናቃቂ ተናጋሪ አድርጎ መጋበዝ የፖሮግራሙ አዘጋጆች ችግር ቢሆንም ለወደፊት መታረም ያለበት ክፍተት ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ዜጋ መመዘን ያለበት በደረሰበት የትምህርት ደረጃ እና በነበረው ስልጣን ልክ ሳይሆን ለወገን፣ ለሀገር፤ ለትውልድ ብሎም ለምድሪቱ ባበረከተው አስተዋፅኦ መሆን አለበት፡፡

Filed in: Amharic