>

የመቀሌው ትዕይንት !!!  (መሳይ መኮንን)

የመቀሌው ትዕይንት !!!
መሳይ መኮንን
 መቀሌ ሰልፍ ብርቋ ሆና ዘመናትን ከቆየች በኋላ ሰሞኑን ተንበሽብሻለች። ፊተኞች ኋለኞች ሆነው፡ ህወሀቶችም ጊዜ ክድቷቸው ሰላማዊ ሰልፍ የነፈጉትን ህዝብ ለተቃውሞ ሰልፍ መጥራት የክልሉ መንግስት ቀዳሚ የስራ ተግባር ሆኗል። በህገመንግስት ይከበር መጠቅለያ ተሸፋፍኖ የተጠራውና የህወሀትን ህይወት ለማቆየት ያለመው ትዕይንተ ህዝብ እውን የትግራይ ህዝብ ፍላጎት የተንጸባረቀበት ነውን? በፍጹም!!!
መቀሌ ዛሬ የሰሜን ኮርያዋን ፒዮንጊያንግን መስላ ውላለች። እንደዚያ የመሰለኝ የህወሀት ዓርማ ከሰሜን ኮርያው ጋር ተቀራራቢነት ስላለው ብቻ ይሆን? የሟቹ መለስ ዜናዊና የደብረጺዮን ፎቶግራፎች በቲሸርት ላይ ታትመው መቀሌን ያጥለቀለቁበት ሁኔታም የሰሜን ኮርያው ሟቸ መሪ ኪም ጆንግ ኢልና አሁን በስልጣን ላይ ያለው ልጃቸው ኪም ጆንግ ኡን ፎቶግራፋቸውን ሰሜን ኮርያውያን እንደማህተብ አንገታቸው ላይ ሳይቀር እንዲያንጠለጥሉ የተደረጉበትን አሳፋሪ ክስተት የሚያስታውሰን ሆኗል።
ህወሀት ዕድሜ ከሰጠው መለስ ዜናዊን  ከመላዕክት ወይም ቅዱሳን አንዱ ተደርጎ እንዲመለክ ሊያስገድድ ይችላል ብሎ መጠበቅ ስህተት አይሆንም። የባለፈውን የደብረጺዮንን እንደጳጳስ ቆብ ደፍቶና ካባ ደርቦ ላየው ሰው ህወሀቶች ክንፍ የሌለን መላዕክት ነንና ስገዱልን የማይሉበት የሞራል ገደብ የለባቸውም። በእርግጥ ህወሀቶች መለስን የሚፈለጉት የትግራይን ህዝብ እንደሙጫ አጣብቆ እስከመጨረሻው መከለያ መደበቂያ ያደርግልናል በሚል ስሌት መሆኑ አይጠፋንም። የማታገያ አጀንዳ ሲያልቅ መቃብር የወረደን መሪ አንስቶ ሙሾ ማውረድ የህወሀት በህይወት መቆያ ብቸኛ አማራጭ ሆኗል ማለት ይቻላል።
ለነገሩ የአልባኒያን አብዮት ኮርጆ፡ በስታሊን አስተምህሮት ተገንብቶ፡ ያደገውና ለአቅመ መንግስት የበቃው ህወሀት አመል አይለቅ ሆኖበት በ21ኛው ክፍለዘመንም የኮሚኒስት መፈክሮችን ከመቃብር ቆፍሮ በማውጣት ህዝብን ለአደገኛ አብዮት ይቀሰቅስበት ተያይዟል። መቀሌ ሰልፍ ብርቋ ሆና ዘመናትን ከቆየች በኋላ ሰሞኑን ተንበሽብሻለች። ፊተኞች ኋለኞች ሆነው፡ ህወሀቶችም ጊዜ ክድቷቸው ሰላማዊ ሰልፍ የነፈጉትን ህዝብ ለተቃውሞ ሰልፍ መጥራት የክልሉ መንግስት ቀዳሚ የስራ ተግባር ሆኗል። በህገመንግስት ይከበር መጠቅለያ ተሸፋፍኖ የተጠራውና የህወሀትን ህይወት ለማቆየት ያለመው ትዕይንተ ህዝብ እውን የትግራይ ህዝብ ፍላጎት የተንጸባረቀበት ነውን? በፍጹም። ባለፈው በዝርዝር ስለሄድኩበት አልመለስበትም።
ዶ/ር ደብረጺዮን በቅርቡ አንድ ላይ መሆን ካልቻልን መለያየቱ ይሻለናል ብለው ነበር። ለነገሩ እስከዛሬም ‘አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል’ ነበር አብሮነታችን:: እነሱ ሲገደሉ እኛ ስንሞት: እነሱ ጥጋብ ሲያሰቃያቸው እኛ የረሃብ ጉንፋን ስንስል: መቼ አንድ ሆነን እናውቅና? ዛሬ ደርሶ በግልፅ  ቋንቋ፡ የፖለቲካ መተሻሸት ያልተጫነው፡ በልብ የተቀመጠውን የህወሀትን እቅድ ይፋ አድርገውታል። ”የትግራይ ወጣቶች ለሁሉም አይነት ሁኔታዎች ዝግጁ ሁኑ” ብለዋል። ግልጽ መልዕክት ነው። ማድበስበስ የለበትም። መሽኮርመም አይታይበትም። አካፋን አካፋ ብለው ጠርተዋል ዶ/ር ደብረጺዮን። ዛሬ በይፋ የትግራይ ክልልን የሚመራው ህወሀት ከፌደራሉ መንግስት ጋር በጓዳ ሲፋጠጥበት የነበረውን ጉዳይ ለአደባባይ አብቅቶታል። ”የገነባናት ሀገር ካላስከበረችን፡ የምታስከብረን ሀገር ለመመስረት እንገደዳለን” የዛሬው የመቀሌው ትዕይንት ዋንኛ መልዕክት ነበር። ይህ መልዕክት እኛ ዘንድ ሲደርስ ትርጉሙ ”የህወሀትን የበላይነት ያልተቀበለች ኢትዮጵያ እንጦሮጦስ ትውረድ” የሚል ነው።
እንግዲህ ህወሀት ካልደፈረሰ አይጠራም በሚለው መስመር ላይ ወጥቷል። ሌቦቼን አትንኩ ከነካችሁ ሀገር አነዳለሁ፡ ኢትዮጵያን በቁሟ አጬሳታለሁ ሲል በገደምዳሜ ነገሮናል። በእርግጥ ህወሀቶች እኛ ከሞትን ሰርዶ አይብቀል ዓይነት ፉከራቸውን የጀመሩት ዛሬ አይደለም። የጸረ ህወሀት ትግሉ ተጧጡፎ፡ እሳቱ ሰውነታቸውን ማጋል በጀመረበት ሰሞን አባይ ጸሀዬና ስዩም መስፍን ፋና ሬዲዮ ላይ ወጥተው ” እንተላለቃታለን” ብለው እንደሰፈር ጎረምሳ ማስፈራራታቸውን አንዘነጋውም። ሰሞኑን ደግሞ ብሶባቸዋል። የትግል ዘመን ትዝታቸውን እየቀሰቀሱ ”ዓወት ንሓፋሽ” እያሉ ናቸው። አዋራ የጠጡ፡ የሸረሪት ድር የሸፈናቸው የቆዩ ዜማዎች ከየሸልፉ አቧራቸው ተራግፎ እየተቀነቀኑ ነው። ”ተጋዳላይ፡ ናይ ወያነ፡ አጆሀ!” እየተደለቀ ነው።” ህወህቶች የተሳሳተ ስሌት ላይ የወጡት እንደትላንቱ የደደቢት ጫካ ጠርቶት የሚሸፍትላቸው ህዝብ ያለ መስሏቸው ነው። ትላንት ዛሬ አይደለም።
ይሄ ነገር ጥሩ አይደለም፡ በደል በደልን ይጠራል፡ ዛሬ የምትሰሩት ግፍ ተራው ደርሶ ወደ እናንተ ይመጣል፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፡ ለሰው ጉድጓድ ስትቆፍሩ አታርቁት የሚገባበት አይታወቅምና፡ የሚሉና ሌሎች ምክሮችና ማሳሰቢያዎች በፊት ለፊትና በጀርባ ሲሰጣቸው የከረሙት ህወሀቶች የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለው ሲዘርፉ፡ ሲገድሉና ሀገር በቁሟ ሲያፈርሱ ቆዩ። ዛሬ የተመከሩት ሲደርስባቸው፡ ቀን ደርሶ በሰፈሩት ቁና በሚሰፈሩበት ዘመን ”ህዝብን” ሰብዓዊ ጋሻ አድርገው ለዕልቂት እየጋበዙት ነው። ቀድሞ ነው እንጂ መጥኖ መደቆስ፡ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ?!
በመቀሌው ሰልፍ የሱዳን ሰንደቅዓላማ በብዛት ተውለብልቧል። ለሱዳን ምስጋና የሚያስተላልፉ መልዕክቶች ከፍ ብለው ታይተዋል። በቅርቡ ዶ/ር ደብረጺዮን ተናገሩት የተባለውንና ህወሀቶች ያስተባበሉት ንግግራቸውን የሚያረጋግጥ ትዕይንት ነው- የመቀሌው። ከትምህክተኛ ሱዳኖች ይሻሉናል ያሉት ደብረጺዮን የህወሀት መጨረሻ፡ ወይም የቀብር ቦታ የት እንደሆነም እየነገሩን እንዳይሆን? መቀሌ እስከመቼ የህወሀቶች ምሽግ ሆና ትዘልቃለች? መንጌ እንዳለው ህወሀቶችም ”አንድ ጥይት እስኪቀር” ከዮሀንስ ቤተመንግስት ባንከር ውስጥ እየተፋለሙ ይዘልቁ ይሆን? ወይስ ወደ ነፍስ አባታቸው ሱዳን ሸሽተው መጨረሻቸውን በሱዳን አፈር ላይ ያደርጉታል? ዛሬ መቀሌ ላይ ህወሀቶች እንዲታይ ያደረጉት መፈክር ”የመጨረሻ እስትንፋሳችን የሚያልፈው በሱዳን እጅ ላይ ነው” የሚል ስውር መልዕክት ያለው ይመስላል።
የመቀሌው ትዕይንት የህወሀትን የበላይነት ለማረጋገጥ የተጻፈው ህገመንግስት ይከበር የሚል ዓላማ እንዳለው ተነግሯል። ሀገርን በህገ አራዊት ሲመሩ የከረሙ፡ ለጻፉት ህገመንግስት ታማኝ መሆን አቅቷቸው በህገመንግስት ስም ታላላቅ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ ኖረው ዛሬ ለህገመንግስቱ መከበር ሰልፍ ሲወጡ አለማፈራቸው አያስገርመንም። በአደባባይ ጌታቸው አሰፋ የዋህ፡ የህዝብ ጠበቃ፡ አዛኝ፡ ሆደ ቡቡ፡ ህይወቱን በሙሉ ለህዝብ ጥብቅና የቆመ ብሎ የሚናገር የህወሀት ባለስልጣንን የሰማ በመቀሌው ትዕይነተ ህዝብ አይደነቅም። ሰሞኑን አንድ የትግራይ የሃይማኖት አባት እነጄነራል ክንፈ መታሰራቸው አንገብግቧቸው ”ከውጭ ለመጡ ምህረት እየተደረገ የልማት ጀግኖች እንዴት ይታሰራሉ?” ብለው የተናገሩን ላዳመጠ መቀሌ ዛሬ በሆነችው አይገረምም።
ህዝብን የሌባና ወንጀለኛ ጠበቃ አድርገው ”ልጆችህ ስላንተ ታስረዋልና ታደጋቸው” የሚለው የእነ ደብረጺዮን የከሰረ ስትራቴጂ ጊዜያዊ መንገጫገጭ ሊፈጥር ይችላል። በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች እሳት ጭረው፡ ቤንዚን ያርከፈከፉባቸው ግጭቶች ግን መብረዳቸውና መስከናቸው አይቀርም። ትግራዮችም አስክሬን ማቆያ ደጃፍ ላይ የቆመን ስርዓት ሸሽገው ብዙ ጊዜ ሊያቆዩት አይችሉም። የመጣው ለውጥ ህወሀትን አደብ ሊያስገዛ፡ ከነኮተቱ የታሪክ ድሪቶው ሊያሰናብተው እንጂ በትግራይ ህዝብ ላይ የተነጣጠረ እንዳልሆነ ለመረዳት የሚቸግራቸው እንዳልሆኑ ይገባናል። የያዘ ይዞአቸው እንጂ።
ለትግራይ ህዝብ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። የግማሽ ክፍለ ዘመን የህወሀት ማደንቆሪያ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ የሆነው የትግራይ ህዝብ ለጊዜው በህወሀት ዜማ እየደነሰ ሊሆን ይችላል። ህወሀት ላለመሞት የሚያደርገውን መፈራገጥ በሰላማዊ ሰልፍ ስም ”የትግራይ ህዝብ አቋም” እንዲሆንለት ላቀደው የመጨረሻ ሙከራው አጃቢ እንዲሆንለት አድርጓል። የትግራይ ህዝብ መረዳት ያለበት ግን ኢትዮጵያ ላይ የሚታየው ለውጥ ወደ ኋላ የሚመለስ አይደለም። በድፍን ትግራይ ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ ቢደረግ እንኳን የሚቆም ለውጥ ኢትዮጵያ ላይ አልተጀመረም። በሰልፍ ጋጋታ፡ በፉከራና ቀረርቶ የሚበርድም አይደለም። ይህ ለውጥ ለትግራይ ህዝብም ትንሳዔ ይዞ የመጣ ለውጥ ነው።  በፍጹም ይቀለበስም። ዶ/ር አምባቸው መኮንን እዚህ አሜሪካ መጥተው የተናገሩትም ይህንኑ ”ለውጡ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም። ለውጡ ግን ወደኋላ ከማይመለስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።” እናም የትግራይ ህዝብ ዛሬ የያዛችሁትን መፈክር ገልብጣችሁ በሚቀጥለው ሳምንት ሰልፍ ውጡና ህወሀትን አሳፍሩት። ”ትግራይ የሌባና የወንጀለኛ መደበቂያ አትሆንም” ብላችሁ እቅጩን ንገሩት።
በተረፈ ፌደራል መንግስቱ መሽኮርመሙን ማብቃት ያለበት ይመስለኛል። ዓይነ አፋር ሆኖ ሀገር መምራት ዋጋ እያስከፈለ ነው።  የቀን ጅቦች፡ ለውጥ አደቃፊዎች፡ ጥቅማቸው የቀረባቸው እየተባለ ድፍን እያደረጉ በመግለጽ እስከመቼ ይዘለቃል? የትግራይ ቴሌቪዥኖችን ከፍቶ በየዕለቱ የሚደልቁትን ፕሮፖጋንዳ ለተመለከተ ሰዎቹ አካፋን አካፋ እያሉ ነው። በግልጽ ጠላት ብለው ያሉትን እየጠሩ የእርግማን መዓት እያዘነቡ ነው። እነሱ ለእኩይ አላማቸው በሚጓዙበት ፍጥነት የፌደራል መንግስቱ እንደዔሊ እየተራመደ ሀገር መታደግ አይቻለውም። ፍጥነታቸውን የሚያቀዘቅዝ ቢቻል የሚያስቆም እርምጃ መውሰድ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። ህወሀቶች ብቻቸውን አይደሉም። የጥፋት ጋብቻ ከፈጸሟቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ያለውን ገመድ የመበጠስ እርምጃም ከፌደራል መንግስቱ የሚጠበቅ አፋጣኝ ተግባር ነው። መንግስት የጀመረውን የእርቅና የይቅርታ መንገድ በማያደፈርስ መልኩ፡ ህወሀቶችና ሸሪኮቻቸውን ማስታገሱና ለፍርድ ማብቃቱ መቀጠል አለበት።
Filed in: Amharic