>

የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው ቸኩለዋል!  (አበበ ቶላ ፈይሳ)

የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው ቸኩለዋል! 
አበበ ቶላ ፈይሳ
የአቶ በቀለ ገርባ “ህዝቡ መንግስትን አይፈልገውም… ህዝቡ አዲስ መንግት ይፈልጋል” የሚል አገላለፅ ከምርጫ መቻኮሉ ጋር ተያይዞ የምርጫ ውጤቱ አቶ በቀለ ካሰቡት በተቃራኒው ቢሆን አደጋ ያለው ይመስለኛል… 
—-
የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ቶሎ እንዲደረግ የፈለጉ ይመስላሉ… እንደው ነገር ይጠናብናል ብለን እንጂ ለምርጫ ተጣድፈዋል ብንል ይበልጥ ይገልፀዋል።
ባለፈው አቶ ዳውድ ኢብሳ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩ ግዜ እንዲሁም ትላንት ደግሞ አቶ በቀለ ገርባ ፋና ቲቪ ላይ ስለ ምርጫው ያደረጉት ውይይት ላይ ያየሁት ምርጫውን እንደ ጥሩ ዘመድ አብዝቶ የመናፈቅ አዝማሚያ ከምን የተነሳ እንደሆነ በቅጡ ሊገባኝ አልቻለም።
ምናልባት ምርጫውን የፈለጉት ባለፈው ጃዋር መሃመድ እንደተነበየው ኢህአዴግ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አያሸንፍም እንዳለው እነርሱ በሚወዳደሩበት ኦሮሚያ በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉት እነ አቶ ለማ መገርሳ አይመረጡም ብለው አስበው ይመስለኛል፤ አቶ በቀለ ገርባ በትላንቱ የፋና ውይይት ላይ ደጋግሞ “ህዝቡ ይሄንን መንግስት አይፈልገውም… ህዝቡ የታገለው መንግስት ለመለወጥ ነው…” ሲል ስሰማው ተገርሜ ነበር። ህዝቡ የታገለው የመንግስት ክፉ ፀባይ እንዲለወጥ ነው ወይስ መንግስት እንዲለወጥ የሚለው ጥናት ይፈልጋል።
የሆነው ሆኖ እነ አቶ በቀለ እና አቶ ዳውድ ለምርጫው የቸኮሉት እናሸንፋለን በሚል ስሜት ይመስለኛል። ህዝቡ ቅሬታዎቹ ሳይፈቱ ቶሎ ወደ ምርጫ ከሄድን የማሸነፍ እድል አለን ብለው ያሰቡ ይመስለኛል። እሺ ይሁን ተብሎ ምርጫውን ቢያሸንፉት በኦሮሚያ ላይ ብቻ ምርጫን ማሸነፍ ምን ይረባቸውል? ሲጀመር አሁን ራሱ ምርጫ ቢደረግ እውነት እነ ኦቦ ለማ ኦሮሚያ ላይ ሙሉ በሙሉ ድምፅ ያጣሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው…
ነገር ግን ኦነግ እና ኦፌኮ ከODP የበለጠ ድምፅ አገኙ ቢባል እንኳ የተወሰኑ አባሎቻቸውን ፓርላማ ከማስገባት በዘለለ መንግስት ለመመስረት በሌላ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ህብረት ወይም ግንባር መፍጠር ግድ ይላቸውል… በኦሮሚያ ብቻ የሚገኝ ድምፅ መንግስት ለመመስረት አያስችልም። ለምሳሌ ከአማራ ክልል አብን ጋር ስምምነት እና ግንባር ወይም ህብረት መፍጠር ከትግራይ አረና ጋር እንዲሁም ከሌሎች ጋር ትብብር ሳይፈጥሩ ወይም የትብብር አዝማሚያ ሳያሳዩ ለምርጫው መቻኮል ምንም ውጤት አያመጣም ባይ ነኝ።
እርግጥ ነው ኦፌኮ የመድረክ አባል ድርጅት ነው… መድረክ ግን ከለውጡ በኋላ አንድም ቀን ተሰባስቦ እንኳን አላየነውም። በህይወት መኖሩንም እንጃ…
ከሁሉ በላይ ግን ያሳሰበኝ… የአቶ በቀለ ገርባ “ህዝቡ መንግስትን አይፈልገውም… ህዝቡ አዲስ መንግት ይፈልጋል” የሚል አገላለፅ ከምርጫ መቻኮሉ ጋር ተያይዞ የምርጫ ውጤቱ አቶ በቀለ ካሰቡት በተቃራኒው ቢሆን አደጋ ያለው ይመስለኛል… እና ከአሁኑ ጋዜጠኞችም እነ አቶ በቀለም ይሄንን አይነት አገላለፅ ቢያስተካክሉ መልካም ይመስለኛል! አለበለዛ ጦስ አለው…
Filed in: Amharic