>
3:44 am - Wednesday May 18, 2022

~ የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ  ደቀመዛሙርት ዐመፅ ላይ መሆናቸው ተነገረ!!!

 ~ የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 
ደቀመዛሙርት ዐመፅ ላይ መሆናቸው ተነገረ!!!
 ዘመድኩን በቀለ 
አስተዳደራዊ ጥያቄም በድፍረት  ማቅረብ መጀመራቸው ተነግሯል!
                  
~ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርት ካቆሙ ሳምንት አልፏቸዋል!
 
~ ጥያቄአቸው አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ነው ተብሏል!
 
~ የሚገርመው ነገር ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በከባድ የሙስና ወንጀል የተወገደው ጎይቶም ላይኑም በ13 ሺህ ብር ደሞዝ በኮሌጁ መልሶ ተቀጥሯል። 
 
~ በአንጻሩ ደግሞ የትምህርተ መለኮት ሊቁ ዶክተር #ዘሪሁን_ሙላቱ የሰሜን ሸዋ #ዐማራ በመሆኑ ብቻ በትግርኛ ተናጋሪው ሊቀጳጳስ በአቡነ ጤሞቴዎስ ተባርሮ ጉዳዩን በፍርድ ቤት በመከራከር ላይ ይገኛል። መራራ ሀቅ።   
~ አዲስ አበባ ። ★ ተማሪዎቹ በእንጀራው አረረ፣ ወጡ ገረና ጥያቄ ላይ ብቻ ተንጠላጥለው ካልቀሩ እንደ አያያዛቸው ከሆነና ተጠናክረው ከገፉበት አጠቃላይ የቤተክርስቲያኒቱን ችግር የመፍታት አቅም እንዳላቸው ይታመናል። አማኙም ከጎናቸው ይቆማል። ካልሆነ ግን ወጥና እንጀራውን አስተካክለው በሆዳቸው እንዳይገዟቸው ያሰጋል።
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሰረተ ጀምሮ እንደ ግልርስታቸው የኮሌጁ ኃላፊ ተደርገው በመንግሥት ትእዛዝ እንደተሾሙ የሚነገርላቸው አረጋዊው ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ ናቸው። ሊቀጳጳሱ በእርጅና ምክንያት ማየትና መስማት ተስኗቸው አብዛኛውን ጊዜ ከቤታቸው የሚውሉ ቢሆንም ባለ ብዙ ሚልየን በጀትና ባለ ብዙ ሚልየን ገቢ ያለውን የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን ለመልቀቅ አይፈቅዱም።
አሁን ግን የሚረዳቸው ያለ አይመስልም። ህወሓት መቀሌ ከገባች በኋላ ጭንቀት በቤተክህነቱ አካባቢ መፈጠሩም ይነገራል። እስከዛሬ ትግሬ ነን እያሉ የሚፎክሩ አስተዳዳሪዎች በሙሉ አሁን የራያ ሰዎች ነን ማለት መጀመራቸውም ይነገራል። እናም በስመ ትግሬ እያስፈራሩና እየዘረፉ መኖር ያበቃለት ይመስላል የሚሉ አሉ።
ደቀመዛሙርቱ ኮሌጁ በተማረ ሰው ይመራ፣ አጠቃላይ የኮሌጁን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለው የዘመድ አዝማድ ጥርቅም በመሆኑ እነዚህ ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ የሊቀጳጳሱ ዘመዳ አዝማዶች በሙሉ ተነስተው ቦታውን በሚመጥኑ አካላት ይተካና ኮሌጁ በዕውቀት ይመራ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ነው አመፁን የጀመሩት።
የተማሪዎች መማክርት በመጀመሪያ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ለኮሌጁ ዲን ለራሳቸው ለአቡነ ጢሞቲዎስ ነበር። አቡነ ጢሞቴዎስም ጆሮአቸው ችግር ስላለበትና ዐይናቸውም ስለማያይ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለውን ነገር ካለማወቅ ይመስላል እንደድሮው መስሏቸው ለተማሪዎቹ መማክርት “ከተማርክ ተማር ያለዚያ ግቢውን ለቀህ ውጣ” የሚል የትቢትና የንቀት እንዲሁም የምን ታመጣላችሁ ዓይነት ምላሽ ይመልሱላቸዋል። ” ሃሎ ተክላይ ቧይ ናአሞ ” ብለው እንደድሮው በአንዲት የስልክ ጥሪ ልክ የሚያስገቡ መስሏቸው ነው የሚሉም አሉ። ዘመን መቀየሩን እስካሁን ያለሰሙት ብፁዕነታቸው ብቻ ናቸውም ይላሉ። አሁን ፌደራል ፖሊስ ስልክ ቢደውሉ የሚያገኙት ቶሌራን እንጂ ተክላይን እንዳልሆነም አልገባቸውም።
ከዚያ በኋላ ተማሪዎቹ ያደረጉት ነገር ቢኖር ሕጋዊ መስመሩን ተከትለው የትምህርት ቤቱ የበላይ ጠባቂና ባለቤት ወደሆነው ወደ ጠቅላይ ቤተክህነቱ መሄድ ነበር። በዚያም የጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ዲዬስቆሮስ አናግረዋል።
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም ለተማሪዎቹ መማክርት “ኮሌጅን እኛ አናውቀውም። እኛም አናዘውም። ከአቅማችን በላይ ነው። እኛ 10 ሚሊየን ብር እንበጅታለን በጀቱን የት እንደሚያደርሱትም አናውቅም። ሪፖርትም አይደረግም ” እና ስለ ኮሌጁ ቅዱስ ሲኖዶሱ መፍትሄ ካልሰጣችሁ በቀር እንዲህ በቀላሉ ምላሽ የሚኖረው አይመስልም ” በማለት መልሰዋቸዋል።
ተማሪዎቹም ተስፋ ሳይቆርጡ ከብዙ መከራና እንግልት በኋላ ወደ ፖትርያርኩ ለመግባት ከቤተክህነቱ ጥበቃዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻ ወደ ግቢ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። ተማሪዎቹ ከጠዋቱ 2:00 ስዓት የገቡ ቢሆንም ከብዙ ጥበቃና ደጅ መጥናት በኋላ ከረፋዱ 5:45 ላይ ቅዱስ ፓትሪያርኩ በስንት ምጥና በስንት መከራ ወጥተው ተማሪዎቹን ማናገራቸው ተነግሯል።
አቡነ ማትያስን መርጠው ያሾሟቸው ተከሳሹ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በመሆናቸው አቡነ ማትያስ ከእግዚአብሔር በላይ አቡነ ጢሞቴዎስን እንደሚያከብሩና እንደሚፈሩ ይነገራል። እናም ተማሪዎቹ የፓትሪያርኩ አለቃ የሆኑትን አቡነ ጢሞቴዎስን ነው እንግዲህ ለመክሰስ የመጡት። ተማሪዎቹ እንደ ፈለጉት በዝርዝር ጥያቄዎችን ለማቅረብ አልቻሉም። እሳቸውም ለማዳመጥ ፍቃደኛ አልነበሩም። እንዲያውም ሰኞ እመጣና ችግሩን አብረን በጋራ እንፈታለን በማለት ተማሪዎችን አሰናብቷቸው።
ተማሪዎቹ በቀጠሮአቸው ቢጠብቋቸውም ፖትርያርኩ የውኃ ሽታ ሁነው ቀሩ። ተማሪዎቹ ያለፈው ሳምንት ማክሰኞ በድጋሚ ወደ ፖትርያርኩ ቢሮ አመሩ። ነገር ግን ወደ መንበረ ፓትሪያርኩ ግቢ መግባት ቀላል አልሆነላቸውም ነበር። ዘበኞቹ እንደ ድሮው ቧይ!  ዋይ!  እያሉ ሊያስፈራሩአቸው ቢሞክሩም ወይ ንቅንቅ አሉ የኮሌጁ ተማሪዎች። ተማሪዎች በቀላሉ የሚበገሩ አልነበሩምና ጥበቃዎችን አቸንፈው ገቡ።
አሁንም በስንት ጣርና ምጥ ቅዱስ ፓትሪያርኩም ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ተማሪዎችን ወጥተው ለማናገር ተገደዱ። አግአዚ የለ፣ ፌደራል የለ የጨነቀ ለት ሆኖባቸው ተማሪዎቹ ፊት የምንተእፍረታቸውን ለመቆም ተገደዱ።
ተማሪዎቹም ጥያቄያቸውን አንድ በአንድ ለማቅረብ ቻሉ።   በኮሌጁ ውስጥ እና በኮሌጁ ህንፃ ላይ የአህያ ሥጋ አርዶ ከመሸጥ እስከ በገና ጾም ከሚቆረጥ ቁርጥ። ከመንዙማ ካሴት እስከ ቡናቤት ድረስ መከፈቱን ችግሮችን ከነ መፍትሔ ሀሳቡ አቀረቡ። የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ከአቡነ ጢሞቲዎስ እስከ ፖስተር ሶሎሞንና አይተ ፖስተር ብርሃኔ ድረስ ያሉትና  ሌሎች የተሃድሶ አቀንቃኞች በኮሌጁ ላይ የሚሠሩትን ሴራ አንድ በአንድ አቀረቡ። የፓትሪያርኩ መልስ ግን ያው የተለመደው መከረኛ አጣሪ ቡድን ይቋቋማል፣ እሱ መጥቶ እስኪያጣራ እናንተ ትምህርታችሁን ተማሩ በማለት ተማሪዎችን መሸኘት ነበር።
ተማሪዎቹም ፓትሪያርኩ የሾሟቸውን አቡነ ጢሞቴዎስን እንደማይደፍሩ ይታወቃል። እናም ተማሪዎቹ ጉዳያችን ካልተፈታ “ትምህርት በእኛ ይብቃ፤ ቀጣዩ ትውልድ ያልተበረዘ ንፁህ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ያግኝ፣” የሚል ጠንካራ አቋም በመያዝ ትምህርት መማር አቆሙ።
የሚገርመው ኮሌጁ “ክርስቶስ አማላጅ ነው” ብሎ የጻፈ ፤ “ክርስቶስ የአብ የግብር ልጅ ነው” ብሎ ያስተማረ መምህር ያለ ድንግል ማርያም ዓለም አይድንም እና ከአብራከ መንፈስ ቅደስ ከማህፀነ ዩርዳኖስ ተወለድን ብሎ ማስተማር ክህደት ነው” እያሉ የሚያስተምሩ መምህራንን የያዘ ኮሌጅ ነው፡፡
ይሄም ብቻ አይደለም አሁን በምንፍቅና የተባረሩ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ኮሌጁ እንዲመለሱ ተደርገዋል። ከሁሉም ከሁሉም ግን የሚያስደንቀው ይላሉ ተማሪዎቹ ” የአቶ በረከት ስምዖን የወንድም ልጅ ነኝ የሚል ሱራፌል የሚባል የ4ኛ ዓመት የኮሌጁ ደቀመዛሙር የነበረ ኤርትራዊ ወጣት የክህደት ትምህርቱ በድምፅ እና በምስል በማስረጃ ሲገኝበትና በፀረ ተሀድሶ ኮሚቴው ተረጋግጦ ከትምህርት ቤቱ ከተባረረ በኋላ፤ ሊቀጳጳሱና አስተዳደሩ የልጁን የትምህርት ማስረጃቸዎች በድብቅ ወደ መቀሌ በመላክ በዚያ በከሳቴ ብርሃን እንዲማር አድርገዋል፡፡ ይሄ የአቶ በረከት ወንድም ልጅ በዚህ ዓመት መቀሌ ላይ ይመረቃል። ከዚያም ወይ ጎንደር ወይ ጉደር ተመድቦ የስብከተ ወንጌል መምህር ሆኖ ከች ይላል።
አሁን ተማሪዎቹ የኮሌጁ ችግር እስካልተፈታ ድረስ አንማርም በማለት በአቋማቸው ፀንተዋል፣ ኮሌጁም ተማሪዎቹ ካልተማሩ ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ማስታወቂያ አውጥቶባቸዋል። ተማሪዎቹም ከማስታወቂያው በኋላ ባነር አሠረተው መፈክር በማሰማት እዚያው በኮሌጃቸው ግቢ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል።
የነገሩን ፍጻሜ እየተከታተልኩ አቀርብላችኋለሁ።
ሻሎም !  ሰላም !
ነኝ።
ታህሳስ 4/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic