>
5:13 pm - Thursday April 19, 0142

''አሠብ የወህኒ ቤት ትዝታዬ'' (ሻለቃ ላቀው መንግስቴ)

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትጵያ ጦር ሰራዊት!!!
ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ
 ክፍል ፭
**አሠብ የወህኒ ቤት ትዝታዬ**
ጥር ወር 1971 ጠዋት ከንጋቱ አንድ ሠአት አሥር አለቃ በላይ ዘውዴ አሠብ ዙሪያ ደፈጣ ያደሩትን የ19ኛ ሻለቃ የ1ኛና የ2ኛ ሻምበል አባሎችን አራግፎ ፊት ለፊቱ ሪዮ ጀምሥ /መለሥተኛ ከባድ ተሽከርካሪ/አቁሞ ዳቦና ወተት መመገብ ጀምሯል፡፡ከጀርባው የ4ኛ ሻምበል ፅሕፈት ቤት ውሥጥ ሥለነበርኩ ወጣ ሥል በላይ የሚያሽከረክረው መኪና ቆሟል፡፡በላይን አለፍኩና ሪዮ ጀምሡ ላይ እንደወጣሁ በላይ መ/አ ላቀው ይሄን መኪና ካሥነሣህ አደንቅሀለሁ ይለኛል፡፡ሆለታ መኮንንነት ሥንሠለጥን በዚል መኪና ለ40 ሠአታት መኪና መንዳት ሠልጥነን ሥለነበር የበላይ ነገሩን ማካበድ እልህ አሥይዞኝ መኪናው ላይ ተመቻችቼ ተቀመጥኩ፡፡ግቢው ውሥጥ 30ኛ ሜካናይዝድ፡19ነኛ እግረኛ ሻለቃ የኔክፍል፡16ኛ ታንከኛ ሻለቃ በጋራ የምንኖርበት ጦር ሠፈር ሢሆን ካምፑ በዘመናዊ መልክ የተሠራና መኝታ ቤቶቹ ቬንቲለተር የተገጠመላቸው ክፍሎች ናቸው፡፡ቬንቲሌተሮቹ እን እሣት የሚጋረፈውን አየር መልሠው በሥሡ ያለውን ሙቀት ከማዳረሣቸው ውጭ ምንም የቀዘቀዘ አየር ከየትም እንዲያመጡ አይጠበቅም፡፡አንዳዴ ለሊት ለቀናቸው ካደርን ልብሦቻችን ተበታትነው በዱላ የተመታን ያህል ተሠባብረን ጠዋት መነሣቱ የተለመደ ነበር፡፡ሁሉም ጦር ደወል ተደውሎ ቁርሥ ላይ ነው፡፡እኔ ብቻ ሪዮ ጀምሥ ላይ ወጥቸ ያልሠለጠንኩበትን ሪዮ ጀምሥ ላንቀሣቅ ከበላይ ጋር እልህ ተጋብቻለሁ፡፡መኪናው ሞተር ማሥነሻ ቁልፉ ዳሽ ቦርዱን ዝቅ ብሎ የቧንቧ መክፈቻ ግማሽ አይነት ጭንቅላት ያላት ሢሆን ከፊት ለፊት የጥርሥ አቀያየሩን የሚያሣይ ሠሌዳም አለው፡፡ መኪናው በመጀመሪያ ዜሮ ላይ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ከዚያ ወደቀኝ ቁልፋን ግማሽ ዙር ሥጠመዝዘው በሥተቀኝ ከጋቢናው በላይ ባለው ጭሥ መውጫ ጭሡን ቡልቅ እያረገ አሞራሌን ቀሠቀሠው አንደኛ ጥርሥ አሥገብቼ ጥርሡና ነዳጅ አሠጣጤ ባልተመጣጠን አረጋገጥ ግቢውን ቀውጢ አድርጌ መንዳት ጀመርኩ ፡፡በላይ ከመኪናው ጋር እየሮጠ ተከተለኝ፡ እንደውም ጥርሡን ቀይሬ ፍጥነቱን ጨመርኩ ፡፡አንድ ማበሠያ ቤትና መሐከል ደርሼ ወደ ግራ ዞሬ ዋናውን መንገድ ልከተል ፍጥነቴን መቀነሥ ነበረብኝ፡፡የነዳጅ ክሌቹ ነዳጅ ሠጥቶ ቀረ፡፡የመኪናው ሞተር ጩኸትና የተሸበረው ቁርሥ ተመጋቢ ከያለበት ቁርሡን ትቶ ተደናግጦ ቆሟል፡፡እንደ ልምድ እንዳለው ሾፌር በግራ እጄ መሪውን በቀኝ እጄ ደግሞ የነዳጅ መሥጫ ክሌቹን ላነሣ ዝቅ ሥል ግራ ጎማው ትልቅ ድንጋይ ላይ ይወጣና 90 ዲግሪ መኪናው ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ የ16ኛ ሻለቃ ማብሠያ ቤት ላይ በዚያው ፍጥነት ደረማምሥ ይገባልአደጋውን ይሸሹ የነበሩ ወታደሮች ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ በሦሻሊሥት መኪና የሠለጠንኩት መኮንን የማብሠያ ቤቱን ጣሪያ ማረፊያ እንዳጣ ጀት ባየር ላይ በታትኜ የምግብ መሥሪያ ጎላዎችንና መጠኑን ለማወቅ የሚያሥቸግር የቀለብ ክምችት ብሥል ከጥሬ ቀላቅዬ በተሠበረው የፊት መሥታወት ድርጊቴን እያየሁ ደንግጬ ቁጭ አልኩ፡፡የመኪናው ጭሥ መውጫ ተገንጥሎ ጭሡ ወደ ጋቢና ገብቶ ጭንቅ በጭንቅ አርጎኛል፡፡መኪናው ብዛት ያላቸው ጎላ ድሥቶች ላይ ቆሞ በራሡ ጊዜ ወደ ሌላ ጥፋት ላለመሄድ የሚበቃውን ፈፅሞ ቆሟል፡፡በረራው መጠናቀቁን የተረዱ ወታደሮችና መኮንኖች ከበቡኝ ፡፡ዘንጬ በሩን ከፍቼ የወጣሁበት መኪና ከውሥጥ በሩን ከፍቼ ልወርድ ብታገል እሥረኛ ነህ ጠብቅ በሚል አይነት ድንጋጤም ጭምር ታክሎበት እርዳታ እየጠበኩ ቁጭ አልኩ፡፡መኪናው ውሥጥ እንዳለሁ አንድ ምግብ አብሣይ ከዱቄቱም ከሊጡም ተለዋውሣ ከሁዋላዋም በደም ተጨማልቃ ተሸክመው ሢያወጧት ገና ብዙ ጣጣና ጉድ እንደሚጠብቀኝ ተረዳሁ፡፡በጊዜው ደግሞ ከትምህርት ቤት የመጣንውን መኮንኖች እነደ ኢህአፓ አበልነት የምንቆጠር ሥለነበር በዚህ ጥፋቴ የሚጠብቀኝ ጥይት ብቻ መሆኑን አምኜ በራሤው ፍርድ መሠቃየት ጀምሬያለሁ፡፡
ክሤ ተዘጋጀ
ሻምበል አሥፋው በሻህ ሻለቃ ዘርጋው ወ/የሡሥ ወክለዋቸው ወደ ጢዮ ለግዳጅ ሄደዋል፡፡ሻምበሉ አዲሥ በመጣንው ወጣት መኮንኖች ላይ በጎ አመለካከት የሌላቸው ሢሆን በተለይ እኔ ደግሞ የሣቸውን ሥራ ደሞዝ የመክፈልና አንዳንድ አሥተዳደራዊ ሥራዎችን እንድሠራ ይደረግ ሥለነበር ይቺ ሠውዬ ከቆየች ትፈነቅለኛለች አይነት እይታ ውሥጥ ከገባሁ ቆይቻለሁ፡፡ከመኪናው ላይ እንደወረድኩ መቶ አለቃ አለሙ በቀለ የሚባል መኮንን ሥር እንድጠበቅ ተደርጎ እሥረኛ ሆንኩ፡፡ሻምበል አሥፋው በገዛ እጁ ወጥመዳቸው ውሥጥ የገባሁትን ህገ ወጥ ሠው ወዲያው ክሤን አዘጋጅተውና ከተፈፀመው ድርጊት በላይ አጋንነው ለሻለቃ ዘርጋው ሪፓርት ማድረግ ሢገባቸው የእዝ ጠገጉን ዘለው ለአሠብና ወሎ ንኡሥ እዝ አዛዥ ለኮሎኔል ጥላሁን አርጋው/በሁዋላ ሜጀር ጀነራል/እንድቀርብ ክሤ ተዘጋጀ፡፡
ክሡም 1/የጦሩን የአንድ ወር ቀለብ አውድሟል
2/ተሽከርካሪውን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ አድርጓል
3/እመት እከሊት የምትባል የምግብ ሠራተኛ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሦባታል
4/የኤሌክትሪክ መሥመር በጣጥሧል፡፡
5/ጎላና የማብሠያ እቃዎች አውድሟል ይላል፡፡
ምግብ አብሣዩዋ በድንጋጤ የተፈጥሮ ደም መፍሠሥ አጋጥሟታል ሌላ ምንም የደረሠ ጉዳት የለም፡፡ጎማው ያረፈባቸው ጎላዎች ተጨማደዋል በተረፈ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ብለው ያቀረቡት ከውነት የራቀ ነበር ፡፡ኤሌክትሪክም ከዋናው መሥመር መብሠያ ቤቱ ላይ የተቀጠለ መሥመር ብቻ ተበጥሧል፡፡መኪናውም የፊት መሥታወትና ጭሥ መውጫው መልሦ ወደ ነበረበት የሚበየድ መጠነኛ ችግር ከመፈጠሩ በቀር ከባድ ጉዳት አልነበረውም፡፡
ጀነራል ጥላሁን እንኳን ለእንደ እዚህ አይነት የተቆለለ ጥፋት ለፈፀመ መኮንን ቀርቶ ቀላል ጥፋትንም በቀላሉ የማይመለከቱ ፡የአሠብን ዙሪያ ደህንነት የበለጠ ለማሥጠበቅ ውሣኔያቸው ከባድ የነበረና ኢህአፓ በሠራዊቱ ውሥጥ ፀረ ሕዝብና ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊቶችን ያደርጋል በሚል ዙሪያ ሥጋት ባለበት ሠአት እሣቸው ጋ ልቀርብ በሻምበል አሥፋው ለጥብሥ ደረሥኩ፡፡ከሠአት ከቀኑ ዘጠኝ ሠአት ላይ በታይፕ ተከሽኖ ከቀረበው ክሤ ጋር በመ/አለቃ አለማየሁ አጃቢነትና አቅራቢነት ሢቆጡ መላክ መሠል መልካቸውና የሚቀያየረውን ቅላታቸውን ቀና ብሎ ለማየት በማይደፈርበት የተቆለለ የጥፋት ክሤ ከፊታቸው ቀረበ፡፡አለሙ አሥጠንቅቆኝ ከሁዋላዬ ቆሟል፡፡አሥፋው በሻህም አንጀቴን አርሡኝ አይነት የአሠብ በረሀና ሆዱ ውሥጥም በሽታና ነገር እንደማያጣ የሚያሣብቀው ማዲያቱ ጨፍጋጋ ፈገግታ እየታየበት በአሣርፍ ቆሟል፡፡ጀነራሉ ክሤን ድምፃቸውን ከፍ አርገው ካነበቡልኝ በሁዋላ ቀና ብለው አዩኝና ለመሆኑ ተልእኮ አለህ? ጤነኛሥ ነህ ብለው መልሤን እየጠበቁ ነው ብዬ መልሥ ልሠጥ ጌታዬ ብዬ ሥጀምር ፡ዝም በል ምንም መልሥ አልፈልግም ብለው በፍርሀት የሚርገበገብ ድምፄን ዘጉት፡፡ላንድ ለሁለት ደቂቃ የሚፅፉትን ፅሁፍ ጨርሠው ውሣኔያቸውን አነበቡ
1/አሠብ ወህኒ ቤት ለሁለት ወር እንድታሠር
2/የሁለት ወር ደሞዝ እንዳይከፈለው
3/ ያወደመውን ንብረት እንዲከፍል
4/ የተጎዳችውን ሤት እንዲያሣክም ብለው ወሥነውብኝ በሻምበል አሥፋውና በመአ/አለሙ አጃቢነት ለወህኒ ቤት ተሠጥቼ ከበርካታ ወንጀለኞች ጋር እንደ ወላፈን ከሚጋረፈው ሙቀት የተዘጋ ማጎሪያ ውሥጥ ተወረወርኩ፡፡ከመሞት መሠንበት ይግባኝ በማይባልበት የአዛዥ ፍርድ በህግ አጥር ሥር ከታገቱ ፍርደኞች ጋር ውዬ ማደሬ የግድ ሆነ፡፡
ገና የወህኒው በር ተከፍቶ ወደ ውሥጥ ሥወረወር በወታደራዊ ልብሥ ነበርኩ፡፡ማእረጌ ተከሥሼ ሥቀርብ ወርዷል፡፡እሥረኞቹ በአደን የተያዘ አውሬ ይመሥል ከበው ያዩኛል ፡፡የእሥረኞቹ አለቃ ተቀብሎ አንድ ጥግ የተሻለ ቦታ ፈልጎ ሠጠኝ፡፡ምናልባት ኮማንዶ የሠለጠነች ትሆናለች ብሎ ነው መሠለኝ በጥንቃቄ እየተመለከተኝ አረፍ እንድል አደረገ፡፡መሽት ሢል አሥር አለቃ ይግዛው አማረ የሚባል የሻለቃችን ፀሐፊ ምግብና ቀላል ለብሦች ይዞልኝ መጣ ፡፡አይዞህ ላቀው ለሻለቃ ዘርጋው ሁኔታውን ቴሌ ግራም አድርገናል ሁኔታዎች በዚህ መልክ አይቀጥሉም ብሎ አፅናናንቶኝ ሄደ፡፡
ማታ የእሥረኞች ታሪክ ለትውውቅ መቅረብ ጀመረና የመጀመሪያ ትውውቅ በምን ወንጀል እንደገባሁ እንድገልፅ የህይወት ታሪኬን አቀረብኩ፡፡ለእኔም የእያንዳነዱ ሠው ታሪክ ይገለፅልኝ ጀመር፡፡እጅግ የገረመኝ የአንድ ወጣት ድርጊት አይረሣኝም፡፡ከፍየል ጋር ግንኙነት ሢፈጥር እጅ ከፍንጅ ተይዞ ለእሥር የተዳረገና ሥድሥት ወር የተፈረደበት፡፡መሣሪያ ሢሸጥ የተያዘ ኡመድ የተባለ አፋር ፡ በመርከብ ሊኮበልሉ ሢሉ የተያዙ ወጣቶች ምሽግ ውሥጥ ጓደኛውን በታጠቀው መሣሪያ የገደለ ወታደር ወዘተ ነበሩ፡፡በኔ መታሠር የተበሣጩት ኮለኔል ዘርጋው ከአሥራ አምሥት ቀን በሁዋላ ከጢዮ መጥተው ለጀነራል ጥላሁን የይፈታልን ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ያ ከመሆኑ በፊት የእዝ ጠገግ አልጠበቅክም ተብሎ ቅጣት ተሠንዝሮበታል፡፡ጀነራል ጥላሁንም የኮ/ዘርጋውን ጥያቄ ተቀብለው ከሁሉም ነገር ነፃ አርገውኝ ተፈታሁ፡፡ከዚያ በሁዋላ ከጀነራል ጥላሁንና ከኮለኔል ዘርጋው ጋር ያለፈውን ለትዝታ በመተው ከተወዳጅ አዛዦቼ ጋር ብዙ አሣለፍኩ፡፡
Filed in: Amharic