>

“መቸም፣ የትም እንዳይደገም!” (እዮብ ብርሀኑ)

“መቸም፣ የትም እንዳይደገም!”
`Never, Ever Again`
እዮብ ብርሀኑ
ሃውልቱን ያቆመው – መፈክሩን የጻፈው ህወሃት ነው፡፡ ሃውልቱ የቆመው በደርግ ዘመን ለተፈጸመ ግፍ ማስታወሻነት ነው፡፡ ደርግ በሰብዓዊነት ላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸሙን በመጻሕፍት ተጽፎ አንብቤለሁ፤ ከዓይን እማኞችም ሰምቻላሁ፡፡ የደርግ ወንጀል  ወያኔ ህወሃት በ27 ዓመታት ከፈጸመው ወንጀል ጋር ሳነጻጽረው ግን ኢምንት ይሆንብኛል፡፡ ደርግ ያን ሁሉ ግፍ የፈጸመው በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ ነበር፡፡ “አቢዮት ልትቀለብስ ነው” በሚል ነበር፡፡ ወያኔ የፈጸመው ግፍ ግን “ለምን አማራ ሁነህ ተወለድክ? ለምን ኦሮሞ ሆንክ? ለምንስ ሱማሌ ሆንክ?….” በሚል ኢ-ተፈጥሯዊ እሳቤ ነው፡፡
ግን . . .
ምን ያህል ቢጠሉን ነው? ምን ያህል ኢ – ሰብዓዊ ቢሆኑ ነው? ምን ያህል ሰይጣናዊ ቢሆኑ ነው? ይሄን ሁሉ ግፍ የፈጸሙት፡፡ እውነቱን እና የልባቸውን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ የትግራይ ተወላጆች በተለይም በአማራ ላይ የፈጸሙት ግፍ ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ተነስቶ እስከ የአሜሪካ ጓንታናሞው ማሰቃያ ድረስ ተምሳሌት ቢፈለግ የማይገኝለት አረመኒያዊ ድርጊት ነው፡፡ . . . በጣም አረመኒያዊ ድርጊት ነው፡፡ ጉዳዩን በጣም አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ አሁንም እንደዚህ ኢ-ሰብዓዊና ሰይጣናዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዎች ለምን ተነኩ የሚል ወገን መኖሩ ነው፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙት በአስቸኳይ በሕግ ይቀጡ ወይም ለመግባባት ሲባል ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው ሕዝብ ይወስን እንደማለት ዓይንን በጨው አጥቦ በአደባባይ በተሰው፣ በየእስር ቤቱ ሰቆቃ በተፈጸመባቸው እና ደብዛቸው በጠፋ ኢትዮጵያዊያን ላይ ያፌዛሉ፡፡
ሦስት ነገር ለጊዜው መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡
1.  አካላቸው ጎሎ እና ሥነ-ልቦናቸው ተጎድቶ ከእስር ቤት ለወጡ ወገኖች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከእለታዊ ምግብ ጀምሮ መጠለያ እና አፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኙ መረባረብ ይኖርብናል፡፡ የከፈሉት ዋጋ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ በተለይ አካላቸው የጎደለ እና ሥነ-ልቦናዊ መቃወስ የደረሰባቸው ወገኖቻችን እርዳታችንን በአፋጣኝ ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝቡ የሚያስተባብረው ካገኘ ከጅብ አፍ የተረፉ ልጆቹን ለመርዳት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡
2.   አጥፊዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ይገባል፡፡ በአንድ የሕግ ታራሚ ላይ አይደለም ሰቆቃ የፈጸመ በጥፊ የተማታ አካል ሁሉ ባጠፋው መጠን ሳይቀጣ ከሕብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ አይገባም፡፡ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለመፋረድ እየተሄደበት ያለው መንገድም የሚደገፍ ነው፡፡
3.  ባሕር ዳርን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ማሰቃያ ቤቶች መዘጋት ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡ  ክፍት እንዲሆኑ እና ምንም ዓይነት ሰቆቃ የሚፈጸምበት ዜጋ እንደሌለ መታየት መቻል አለብን፡፡ አሁንም በኢሚግሬሽን ጽ/ቤት የሚገኙ እስረኞች አሉ ይባላል፡፡ በየወረዳው ያሉ ማሰቃያ ቤቶችን ሕዝቡ በዓይነ ቁራኛ በመከታተል ከዚህ በፊት የተፈጸመው ግፍ ይብቃ ሊል ይገባል፡፡
Filed in: Amharic