>
1:48 am - Saturday December 10, 2022

የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ!!! (ዘውድአለም ታደሠ)

የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ!!!
ዘውድአለም ታደሠ
እውን የዚህ ሁሉ ግፍ ፈጻሚዎች ከአንድ ብሔር ብቻ የተውጣጡ ናቸው??? ይህን  ለማመን ይቸግራል!
ሰላም ሰላም ሰላም አንተ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የተፈጠርህ ማህበረሰብ? አማን ነህ ወይ? ለነገሩ ዝም ብዬ ነው እንጂ ህዝቤ በሰላምታ አንደኛ ሰላም በማጣትም አንደኛ እንደሆነ አይጠፋኝም።
ለማንኛውም ይሄ ሳልፈልግ የለመደብኝን የመጥፋት ሱስ ሰብሬ የተከሰትኩት የትናንቱን የስቃይ ዶክመንተሪ አይቼ የሆነ የሆነ ነገር ብዬ ለማምለጥ ነው!!
ባይ ዘ ዌይ አሰቃቂውን ዶክመንተሪ እያየሁ ፖትልኮ አዳሪ ለጥቂት ቀን ጉዳዩን የብሔር ካርታ እየመዘዘ ሲጨቃጨቅበት እንደሚውል ገምቼ ነበር። የሆነውም እንደዚያው ነው። ዘንድሮ መቼም ይሄ ከሆነ ቦታ መጥቶ የሰፈረብን የዘር ጋኔን የማያደርገን የለም! ዘንድሮኮ ጌታዬ ህዝቤ “አንድ ሰው መንገድ ሲሻገር በመኪና ተገጭቶ ሞተ” የሚል ወሬ ቢሰማ ሰውዬውን ትቶ “ሟቹ ብሔሩ ምንድን ነው? የገዳዩ ዘርስ ምንድን ነው? መንገዱን የሰራው ሜቴክ ነው ወይ” ብሎ መጨቃጨቅ ነው ሚጀምረው። የሆነ የሰፈረብን ጋኔልማ አለ ጎበዝ! (ወጋሁት! አለ እስራኤል ዳንሳ)
እሺ ወደሃሳቤ ሳልፍ … የትናንቱ የሰቆቃ ዶክመንተሪ ለኔ አዲሴ አይደለም። ለአመታት በየወህኒው የሚፈፀመውን የሚዘገንን በደል ሰምቻለሁ። በኔ እምነት ትናንት የቀረበው ዶክመንተሪ ባለፉት ሃያሰባት አመታት ከተፈፀመው ጥቂቱ ነው። በየስርቻው የተገደሉ፣ ስቃያቸው ሳይነገር እስከወዲያኛው ያሸለቡ፣ የተደፈሩ፣ ሰዋዊ ክብራቸው ተሸልቶ ህይወታቸው እስከወዲያኛው የተበላሸ፣ አካላቸው የጎደለ፣ እልፍ አእላፍ የቃየል መስዋእቶች ፣ እልፍ አእላፍ አቤሎች ደማቸው በአራቱም አቅጣጫ ይጮሃል! በህይወት ለተረፉት ፍትህና መፅናናትን እመኛለሁ!
እውነት መውጣቱ፣ በደል ባደባባይ መነገሩ ትክክል ሆኖ ሳለ ዶክመንተሪው የቀረበበት መንገድ ግን ትክክል አልመሰለኝም። (ይሄ የግሌ አመለካከት ስለሆነ ጓ እንዳትሉብኝ አደራ)
በደል የደረሰባቸው ሰዎች የተናገሩትን እረዳለሁ። ብልቱ የተኮላሸና አካሉ የጎደለ ሰው በዳዩን ካሻው ብሔር እየጠራ፣ ካሻው ስም እያነሳ ቢናገር አልፈርድበትም። እሱ ያሳለፈውን መከራ ባሳልፍ እኔም ምን እንደማደርግ አላውቅማ! በነሱ ጫማ ውስጥ ሆኜ ሳላየው እንዴት እነሱን እንዲህ አውሩ እንዲህ አታውሩ የማለት አቅም ይኖረኛል?
ነገር ግን ይሄን ያዋቀሩት የሚዲያ ሰራተኞች ጥንቃቄ መውሰድ ይገባቸው ነበር። ህዝቡ እንዲህ በሰበብ አስባቡ ካራ በሚማዘዝበት ወቅት ዶክመንተሪውን በዘርና በብሄር ብቻ የተቃኘ አድርጎ ማቅረቡ ውጤቱ የከፋ ነው! ተጠቂዎቹ በሃዘን ተሰብረው የተናገሯቸውን ነገሮች ሁሉ በዚህ ሰአት እንደወረደ ማቅረብ በእሳት ላይ ቤንዚንና ጭድ ማርከፍከፍ አይሆንም ወይ? ዛሬ ሐገር ምድሩ በጥላቻ ሰክሮ የሌላ ብሔር ተወላጅ ከቀበሌዬ ይውጣ እያለ በሚያፈናቅልበት ወቅት ሁለት ብሔርን ብቻ ተጠቂ አንድ ብሔርን ብቻ አጥቂ አድርጎ የሚስል ዶክመንተሪ ማቅረብ ነባራዊውን እውነታ ያላገናዘበ ሃላፊነት የጎደለው ስራ አይደለም ወይ?
ጎበዝ! ይሄን ቪዲዮ አይቶ ምን ያህሉ ሰው ህዝብና እነዚህን ነፍሰገዳዮች ለይቶ የማየት አቅም አለው? በጠቅላላው ትግሪኛ ተናጋሪዎች እየተባለ ተደጋግሞ ሲገለፅ ንፁሃን የቋንቋው ተናጋሪዎችን ስነልቦና አይጎዳም ወይ? ዛሬ ሳያጣራ ሰው ሚሰቅልና በድንጋይ ወግሮ የሚገድለው ግራና ቀኙን የማያውቅ ወጣትስ ይህን ቪዲዮ ካየ በኋላ ባካባቢው የሚኖረው ንፁሃን ላይ በደቦ እንዲዘምት አይገፋፋውም ወይ? አሁን በስልጣን ላይ ያሉና የሃገሪቱን እጣ ፈንታ ከሞላ ጎደል በመወሰን ላይ ያሉ ባለስልጣኖችን ስም እያነሱ በመንግስት ሚዲያ መጥቀሱስ ከህግ አንፃር ተገቢ ነው ወይ? ከዶክመንተሪው በፊት በሰሩት ወንጀል ፍርድቤት ቀርበው ብይን ሊሰጥባቸው አይገባም ነበር ወይ?
ባጭሩ የተበደለ ሁሉ ባደባባይ ሊናገር፣ በዳዩም ለፍርድ ሊቀርብ፣ ድርጊቱም ለትውልድ መማሪያ ሊሆን አስፈላጊ ከሆነ ሙዚየም ውስጥ ሊቀመጥ ግድ ሆኖ ሳል በዚህ አስጨናቂ የሽግግር ወቅት በዚህ መልኩ የፖለቲካ በደልን ወደብሔር ጥቃት ብቻ አውርዶ ማቅረቡ ተገቢነቱ አልታየኝም።
ባለፉት አመታት ኢህአዴግ ለፖለቲካው ያልተመቸውን ሁሉ ሲያስርና አሰቃይቶ ሲገድል ነበር። አማራውን አማራነቱን እንዲጠላ፣ ኦሮሞውን ኦሮሞ መሆኑ ወንጀል እንዲመስለው አድርጓል! ሁሉንም እንደማንነቱ በተለያየ መንገድ እንዳፈነ ሁሉ ትግራዋይ ሆኖ የተቃወመውንም አፍኖ በማምጣት ገድሏል! ከማህበረሰብ እንዲገለልና እንደከሃዲ እንዲቆጠር ሰርቷል። ቤተሰቡ ትግራይ ውስጥ መኖር እስከማይችል ድረስ ግፍ ሰርቷል! ይሄ ማውቀው ሃቅ ነው!
በደሉ እንደህዝቡ ቁጥርና እንደተቃዋሚው ብዛት ቢለያይም ህውሃትም ሆነ ኢህአዴግ ላለፉት ብዙ አመታት የተጋፈጠውን ሁሉ ከትግል ወቅቱ ጀምሮ በእሾሃማ ብትር ሲገርፍ ነው የኖረው! የማን ስቃይ ይበዛል? የስቃዩ ክብደት ምን ያህል ነው? የሚል ሂሳብ መስራት አስፈላጊ አይደለም! እንደሐገር በድለናል! እንደሐገር ተበድለናል! እንደሐገር መጠየቅ እንደሐገር ፍትህ ማግኘት፣ እንደሐገር ንስሃ መግባት እንደሐገር ታርቀን ወደፊት የምንመኛትን ሐገር ለመገንባት መስዋእት መሆን አለብን!
የትኛው ብሔር በደለ? የቱ ብዙ ተበደለ ብሎ በደልን በብሔር ግዜ ቤት እያሰላን ጣት መጠቋቆምና ለማስተባበል እየሞከሩ የወል ስም መሰጣጠቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል! ከብሔርም ሆነ ሳንመርጥ ተወልደን ከተሰጠን የወል ስም በፊት ሰዎች ነን! እንደሰው እንዘን! እንደሰው እንቆጭ! እንደሰው እንፀፀት! የእገሌ ብሔር ለምን ይሄን አደረገ? ማለቱን ትተን ሰው ሰው ላይ እንዴት እንዲህ ጨከነ? ብለን እንደሰው ከወደቅንበት የአስተሳሰብ ዝቅጠት እንደሰው ለመውጣት እንሞክር! ከፍ ስንል ሰው ዝቅ ስንል ኢትዮጵያዊ ነን! ከዚያ በታች አንወርድም! ሙሾ አውራጇ እንዳለችው «የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ» ነው ነገሩ! በተፈፀሙት ሁሉ ግፎች እንደማህበረሰብ ገዳይ ወይም ሟች የሚባል ነገር የለም!
ዘንድሮም አንድን ማህበረሰብ በጥቅሉ ዘርና አጥንት እየቆጠርን ኮንነን አንዱን ደግሞ ምንም እንዳላጠፋ ካፀደቅንማ ብሔርና አጥንታችንን ቆጥረው ሲያሰቃዩን ኖሩ ከምንላቸው ሰዎች በምን ተሻልን? ያጠፋ ዘሩና የፖለቲካ አቋሙ ሳይመዘን ይጠየቅ! በደል የደረሰበት የፍትህ ፅዋ ትድረሰው! የዘርና የብሔር ካርታ እየመዘዙ መጠቋቆሙ ግን ቢያንስ ይሄን ዘመን አይሻገር!
Filed in: Amharic