>
9:28 am - Saturday December 10, 2022

ወንጀለኞችና ዘራፊዎች በ«ብሔራቸው» እየተጠቁ እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበው ትርክት . . .

 ወንጀለኞችና ዘራፊዎች በ«ብሔራቸው» እየተጠቁ እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበው ትርክት . . .
አቻምየለህ ታምሩ
[ክፍል ፩]
የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ቁንጮ በነገድ  ግቢ ውስጥ የታሰረው «የብሔር» ፖለቲካ ነው። የ«ብሔር» ፖለቲካ  ዋጋ እንዲያጣ ተደርጎ እስካልተወገደ ድረስ  ወንጀለኛና ዘራፊ በ«ብሔሩ» እንደተጠቃ ተደርጎ መቅረቡና በ«ብሔሩ» አባላነት ዘንድም ይህ ቅቡል መሆኑ አይቀሬ ነው።  ለዚህ ማሳያ የሚሆነን  እነ ጌታቸው አሰፋ በትግሬነታቸው እንደተጠቁ ተደርጎ በትግራይ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ያለው ትዕይንተ ሕዝብ ነው።
ሲጀመር የአገራችን ፖለቲካ የተገነባው ወንጀለኛና ዘራፊዎችን በብሔራቸው እንደተጠቁ ተደርጎ ትርክት በመፍጠር ነው።  ሕወሓት የሚባለው የግድያና የቅሚያ ድርጅት ጫካ የገባው የ«ብሔር»  ጭቆና ተፈጽሞብኛል ብሎ ነው። ይህ የቅሚያና ግድያ ድርጅት ወያኔ የሚል ስም ይዞ  የብሔር ፖለቲካን  የጀመረው በ1935 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን የወያኔ ንቅናቄ «ቀዳማይ ወያኔ» የሚል ስያሜ በመስጠት የቀዳማይ ወያኔ ንቅናቄ የተጀመረው በትግሬ ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና የ«ብሔር» ጭቆና  ስለተፈጸመ ነው የሚል ትርክት በመፍጠር ነው። እውነታው ግን  በ1935 ዓ.ም.  የተቀሰቀሰው የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ የዝርፊያና የሽፍትነት አመጽ ነበር።
ቀዳማይ ወያኔ እንዴት ተመሰረተ? 
ፋሽስት ጥሊያን በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎና በእንግሊዝ መንግሥት እርዳታ  በተለይም በአሜዲዮ ዲ አኮስታ የሚመራው ብርጌድ  በአምባላጌው ጦርነት ድል ከሆነ  በኋላ በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ሌላ መልክ እየያዘ መምጣት ጀመረ። ከተማረኩ  የጥሊያንና የባንዳ ወታደሮች የተገኘው የነፍስ  ወከፍ የጦር መሣርያ በግዥም በዘረፋም በአካባቢው ገበሬዎች እጅ ገባ። አንዳንድ አርበኞችም የማረኩትን ቀላል የጦር መሣሪያ በርካሽ ዋጋ ቸበቸቡት። በዚያን ጊዜ በእንደርታ  የዘመናዊ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን የማይገኝ እድል ነበር። የእንደርታ ገበሬ ከብቱን እየሸጠ መሣሪያ መሸመት ጀመረ። ወቅቱ በተለይም በእንደርታ አውራጃ በዋጅራት ለሚኖረው  ገበሬ  ሰርግና ምላሽ ሆነለት። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ነው። ዋጅራት አንድ ለየት ያለ መጥፎ ልማድ ነበረው። ይህም  በየ ዓመቱ እየዘመተና እየወረረ የመዝረፍ ባሕሉ ነው። ይህ የመዝረፍ ባሕል የወንዶች ጉብዝና መለኪያም ተደርጎም  ይቆጠር ነበር።
ይህ ዘመቻ ወይንም ዘረፋ «ጋዝ» ተብሎ ይጠራል። በተጠጋጋ አባባል የዘረፋ ዘመቻው ባሕላዊ የዘመቻ ወረራ ሊባል ይችላል። እንግዲህ! ፋሽስት ጥሊያን ሲጠቀምበት የነበረውን ዘመናዊ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ እንደልብ መታጠቅ ለጋዝ ወይንም ለወረራ ዘመቻ ማን ያህል ኃይል እንደሚሰጥና አስፈላጊ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ዋጅራት  ከአፋር ጋር ላለበት የጋዝ ዘመቻ የታጠቀው አውሮፓ  ሰራሽ መሣሪያ በወረራው ብልጫ እንደሚያመጣ ዋና ጉዳይ ሆነ።
የፋሽስት ጥሊያን  ከኢትዮጵያ መደምሰስ እየወረረ ያሻውን ይዘርፍ  ለነበረው የጋዝ ጦረኛ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር አልተመቸውም ነበር። ከፋሽስት ጥሊያን ጋር በነበረው የመጨረሻው ከአሜዲዮ ዲ አኮስታ ጋር በተደረገው  የአምባላጌ  ጦርነት መጨረሻ  ላይ የተማረከው የጦር መሳሪያ   ዋጅራት በያመቱ ወደ አፋር  የሚያደርገውን የጋዝ ወረራ ከበፊቱ በከረረና በተባባሰ ሁኔታ እንዲያካሂድ አድርጎታል። በወቅቱ በአንድ አመት ብቻ  አይሙት ኪዶ በሚባል የወረራ አለቃ መሪነት ዋጅራት  ሰባተኛ ወረራውን   ወደ  አፋር  አካሂዷል።
በአይሙት ኪዱ መሪነት የተካሄደው የጋዝ ወረራ በአፋር ላይ ባደረገው ዘረፋና ግድያ ድል እየተጎናጸፈ የዘረፋው ጠቃሚነት በወራሪው በኩል እየጎላ በመሄዱ በወቅቱ የአገሬው አቀንቃኝ እንዲህ ብሎ ዘፎኖ  ነበር፤
ሶሞ አይሙት ኪዱ፣
ዝሞተ ይሙት፣
አይሙት ኪዱ፣ አይሙት ኪዱ፣
ኮርቻ እርዱ፣
ሕሩስ መንገዱ፣
ቀኝ መንገዱ ጎራ መንገዱ፤
 
ይህ የዘረፋ  ዘፈን ትርጉሙ  ወደ አማርኛ ሲመለስ እንደሚከተለው ነው፤
 
ከአይሙት ኪዱ ጋር ዝመት፣
የሞተው ይሙት፤
አይሙት ኪዶ፣ አይሙት ኩዶ  
ኮርቻ ምሽጉ፣
መንገዱ ይታረስልህ፣
ቀኝ ይሁልህ ግራው ይቅናልህ፤
ይህ ዘፈን በሚዘፈንበት ጊዜ ጎረምሳውና ጎልማሳው የጥይት ባሩድ  ለማሽተትና ሾተሉን ደም ለማቅመስ ጥማትና ወልፍ እየያዘው ስለተነሳ ዋጅራት  በአፋር ላይ የሚያካሂደውን የግድያና የዝርፊያ ወረራ ከቀድሞው በበለጠ የከረረና ውጊያውንም በባሰ ሁኔታ እንዲካሄድ ሊያደርገው ችላል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ወረራውን የፈጸሙትና በአፋር ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ፣ ሰለባና ዘረፋ ያካሄዱት ለሕግ እንዲቀርቡ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ዴሬክተር የነበሩት ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ ታዘዙ። ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲም ትዕዛዙን በተዋረድ በወቅቱ የጠቅላይ ግዛቱ የጦር አበጋዝ ለነበሩት  ለአድዋው ተወላጅ ለደጃዝማች ዓባይ ካሳ አስተላለፉ።
በጦር አበጋዙ  በደጃዝማች ዓባይ ካሣ የአካባቢው የአውራጃና የወረዳ ገዢዎች የአገሬውን ነጭ ለባሽ አስከትለው ከዋጅራት በሚያዋስነው አካባቢ ግንቦት ሁለትና ሶስት ቀን 1935 ዓ.ም. ተሰበሰቡ።  በሌላ በኩል ደግሞ የዋጅራት ሕዝብ የጎበዝ አለቆች ሕዝቡን በየአምባው አሰልፈው ከመንግሥት ጋር ለሚያደርጉት ውጊያ ቦታ ከአስያዙ በኋላ በነደጃዝማች ዓባይ ካሳ አማካኝነት ከመንግሥት የተላከውን ልዑክ በሚያነጋግርበት ወቅት ሁለት ዘዴ ይዞ በመነሳት ግባቸው ለመጨበጥ  አቀዱ፤
አንደኛው  አነስተኛ ጉዳት በመቀበል ጉዳዩ በሰላም እንዲያልቅ በማለት ከካህናት፣ ከወንድና ከሴት ሽማግሌዎችና ባልቴቶች የተውጣጣ የጥምር የሽምግልና ቡድን ወይንም በአካባቢው አጠራር «ዱበርቲ» የሚባለውን መርጠው በማውጣት ወደ አባጋዙ ወደ ደጃዝማች ዓባይ ካሳ ለልመና ሲልኩ  የጠየቁትም «ሕዝቡ ጥቂት ጀብደኞች እንዳሉ ስለሚያምን እነሱን መርጦ እስከነመሳሪያቸው ለመንግሥት እንዲያስረክብ፣ መንግሥት ደግሞ በበኩሉ አስተያየት አድርጎ ቅጣቱን እንዲያቀልላቸው» የሚል ነበር።
ሁለተኛው የዋጅራት ዕቅድ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣኖች የተላኩትን የአገር ሽማግሌዎች ልመናና ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ባይቀበሉ  ወደ አካባቢው የተላከውን የከተት ጦር ለመውጋት ጦሩን በየአምባውና  በየጎበዝ አለቃው አማካኝነት ለውጊያ ማሰለፍ ነበር። የመንግሥት ባለሥልጣኖች  በኩል የተፈለገው የዋጅራት  ጋዝ የሚለውን የወረራ ልማድ እንዲያቆምና አጥፊዎችም ለሕግ እንዲቀርቡ ስለነበረ ሕዝቡ ራሱ ለማመልከት በላካቸው ሽማግሌዎች ይህንን ለማድረግ ከጠየቀ ከዚህ የተሻለ መፍትሔ እንደሌለ በመገመት እስከነመሣሪያቸው ይዞ እንዲያስረክብ ለልመና ከመጡ ሽማግሌዎች ጋር ስምምነት ተደርጎ ለማመልከት የመጡትም ሽማግሌዎች የቁርስና የቡና ግብዣ ግራዝማች ኃይሌ ተድላ በሚባሉ ሰው ጊቢ ተደርጎላቸው ሲመለሱ ለከተት በመጣው ጦር በኩልም ከእንደርታ የመጣው ብቻ አገሩ ቅርብ በመሆኑ በየሰፈረበት ሲቀር ሌላው አርሶ አደር ወደ እርሻው እንዲመለስ ተደረገ።
ሁኔታው በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ከልብ እንደሚከበር ታምኖበት ሳለ ቀድሞውንም  የዋጅራት የጎበዝ አለቆች  ጥፋተኞቹን ለፍርድ እናቀርባለን በሚል ያቀረቡት የእርቅ ሀሳብ ጊዜ መግዣ ስለነበር  ከጋዝ ዘማቾች መካከል ፊታውራሪ ኪሮስ አምባዬ የሚባሉ ሽፍታ እርቁን ተቀብሎ በፋንታው ወደ አምባው ሲለመስ በነበረ ደጃዝማች አለማየሁ በሚባሉ አርበኛ ይመራ በነበረው ተመላሽ የክተት ጦር ላይ ግንቦት 11 ቀን 1935 ዓ.ም. ሙጃ የሚባል ቦታ ሲደርሱ የዋጅራት ጦር በእሪታና በጡሩምባ ጥሩ ዳር እስከዳር ተቀስቅሶ እንደ ድንገተኛ ደራሽ ጎርፍ ወደየአገሩ እየተመለሰ ባለና በመንግሥት ጥሪ ለሰላም ማስከበር በከተተ ጦር ላይ  ውጊያ ከፍቶ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማርኮ ወደተለያዩ አካባቢዎች ወስዶ በማሰር ጥፋተኞችን ለመንግሥት ላለማቅረብ ፍቃደኛ አለመሆኑን አሳየ።
በዚህ ድንገት በተከፈተ ውጊያ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለእርቅ ተቀምጠው የነበሩ የሕዝብ ሽማግሌዎች ጭምር ተቀላቅለው የተፋፋመ የእጅ በእጅ ውጊያ በመደረጉ የመንግሥት   አስተዳዳሪዎች፣ የጦር መሪዎና ለክተት የተሰበሰበው  ለጦር ያልተዘጋጀ አርሶ አደር አለቀ። ከዚህ በኋላ ዋጅራት  ከመንግሥት ጋር ለመደራደር እንዲያመቸው ምርኮኞችን በእስር ይዞ በከባድ ቁጥጥር እያስጠበቀ ከአምባ ወደ አምባ እያዘዋወረ በማስቀመጥ ጥበቃውን ቀጠለ።  በመቀጠልም  ዋጅራት  በሙሉ በየጎበዝ አለቃው ለውጊያ ተደራጅቶ በምርኮ የተወሰዱትን እነ ደጃዝማች ዓባይ ካሣና ሌሎችን የመንግሥት ምርኮኞች ለማስለቀቅ ከሚመጣው የመንግሥት ጦር ጋር ውጊያ ለመግጠም መዘጋጀት ጀመረ።
ይህን የዋጅራት የድንገት  ጦርነት  ተከትሎ የዋጅራት ሕዝብ በድንገት ጦርነት ከፍቶ በማረካቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት የጎበ መዡና  ቀደም ሲል ከጭቃ ሹምነት በራስ ስዩም መንገሻ የተነሱ እነ ብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ  ወቅቱን ጠብቀው  «ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም»  በማለት ይህንንም ለማሳመን አጎዛና ቆዳ የለበሱ፣ ብረት ሰንሰለት በወገባቸው  የታጠቁ አስመሳዮችን  ባሕታውያን ናቸው በማለት ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም የሚለውን ክሳቸውን በሕዝቡ ዘንድ እንዲቀሰቅሱ በማዝመት   በመንግሥት ላይ አመጹ። ይህ አመጽ ነው እንግዲህ ቀዳማይ ወያኔ እየተባለ የሚጠራው። እነዚህ አመፀኞች «አረና ሐረና» በማለት በእንጣሎ ዋጅራት ውስጥ ልዩ ስሙ ማይደርሁ በተባለ ሥፍራ በሐምሌ ወር  1935 ዓ.ም. ተማምለው አመጹ።
ቀዳማይ ወያኔ «ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም» በማለት የእንደርታን ሕዝብ ለማሳመጽ ይጠቀሙበት ከነበረው ስልት በተጨማሪ ሕዝቡን ለማሳመጽ እንግሊዝም የሚያካሂደው ቅስቀሳ ነበር። ይኸውም ቅስቀሳ ፋሽስት ጥሊያን ኤርትራ ብሎ ከሰየመው የቅኝ ግዛቱ ተሸንፎ ከተባረረ በኋላ ኤርትራ ትተዳደር የነበረው በእንግሊዝ ስለነበርና ኢትዮጵያ ደግሞ ግዛቷ የነበረችው ባሕረ ነጋሽ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በተዋዋሉት የአዲስ አበባ ስምምነት መሰረት ከጥሊያን መባረር በኋላ ትመለስልኝ የሚል ጥያቄ አቅርባ እየተከራከረች ስለነበር እንግሊዝ ኤርትራን ከቅኝ ግዛቷ ሱዳን ጋር ልታስተዳድርና በኢትዮጵያም ውስጥ ተሰሚነት እንደያዘች ለመቆየትና የሚፈልገውን ለማግኘት አስፈላጊውን ተጽዕኖ ለማድረግ ወይንም የኢትዮጵያን ባሕረ ነጋሽ ትመለስልኝ ሀሳብ ለማሰናከል ካልሆነም ኢትዮጵያን በሥጋት ወደ መከላከል ደረጃ እንድትገባ አማራጭ ብላ የወሰደችው ዘዴ ኤርትራንና ትግራይን በመቀላቀል «ትግራይ ትግርኝ» የሚል ስያሜ አስይዛ  ራሱን የቻለ መንግሥት ለማቋቋም  አንዳንድ የትግራይ  መሳፍንቶች ፈቃደኛ ሆነው ከቆሙ ኤርትራውያን ለዚህ ዓላማ እንዲተባበሩ ለማድረግ እንረዳለን» የሚል  ቅስቀሳ ይዛ ነበር።
ይህ የእንግሊዝ እቅድ በተወሰኑ መሳፍንቶች  በኩል ፍሬ አፍርቶ ጀግኖች የተዋደቁለት የኢትዮጵያን አንድነት ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይ አፈር ድሜ በልቶ የትግራይ ትግርኝ ሀሳብ በሕዝቡ ዘንድ እንዲታወቅ ውስጥ ውስጡን በመቀስቀስ እርምጃውን ተቀላቀሉ። ይህ በእንግሊዝ መሰሪነት፣ በትግራይ አንዳንድ መሳፍንቶች ፊት አውራሪነት ይካሄድ የነበረው የትግራይ ትግሪኝ ቅስቀሳም ለአመጹ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።
እንግዲህ! የቀዳማይ ወያኔ አመጽ መነሻዎች የዋጅራት የጋዝ ወረራና  «ንጉሠ ነገሥቱ እውነተኛ የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አይደሉም» በሚል  የተከተለው  የነ ብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ  አመጽና የእንግሊዝ እቅድ የሆነው የትግራይ ትግሪኝ ፕሮጀክት ነው። ከእነዚህ ምክንያቶች በቀር ከሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የተለየ አስተዳደራዊ በደልም ሆነ ጫና ስለነበረ አይደለም የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ የተፈጠረው። ልብ በሉ! የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ እየተባለ የሚወራለት ሽፍትነት የተቀሰቀሰው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአምስት አመታት ተጋድሎ በኋላ ወደ መንበረ መንግሥታቸው ከተመለሱ ገና ሁለት ዓመት ሳይሆናቸው ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የተለየ  ምን ተበድሎ ነው የ«ብሔር» ጭቆና ተካሄደበት ተብሎ ትርክት ሊፈጠር የቻለው? የበደሉ አይነትስ ምንድን ነው? ወይንስ ቀዳማይ ወያኔ የተፈጠረው ከጥሊያን ወረራ በፊት የደረሰ በደል ስላለ ያንን በመቃወም ነው? ተብሎ ጥያቄ ቢነሳ መልስ የሚሰጥ አንድ ሰው አይገኝም።
የቀዳማይ ወያኔ ወራሽ ነኝ በማለት የቆዬ በደልና  የ«ብሔር» ጭቆና  ወልዶኝ  የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ጫካ ገባሁ ያለው  ፋሽስት ወያኔም  ዱር ቤቴ ያለበትን ተጨማሪ ትርክት ሲያስቀምጥ ደርግ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደርስ በነበረው ጭፍጨፋና በደል ነው ሲል ታሪክ ቀቅሏል።
ይታያችሁ! ወያኔ ጫካ የገባው ደርግ ሥልጣን በያዘ በአምስት ወር ውስጥ ነው። ደርግ ስልጣን በያዘበት በአምስት ወር ውስጥ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰ አንዳች የተለየ ነበር የለም። በነዚህ አምስት ወራት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ እንኳን የተለየ በደል ሊደርስበትና ወያኔ የሚወልድ ብሶት በሕዝቡ መካከል ሊፈጠር ደርግ ስልጣን በያዘበትና ወያኔ ደደቢት በረሀ ወርዶ የትጥቅ ትግል በጀመረባቸው አምስት ወራት ውስጥ በወቅቱ በርሀብ የተጠቃው የትግራይ ሕዝብ ርዳታ እንዲደርሰው ልጅ አዋቂ ሳይል ሁሉም  ኢትዮጵያዊ ለርዳታ ይረባረብበት የነበረበት ወቅት ነበር። ቀዳሚውም ሆነ የዛሬው ወያኔ የኢትዮጵያ መንግሥታት በትግራይ ላይ በተለየ መልኩ ባደረሱት ጭቆናና በደል የተወለዱ አይደሉም። ቀዳሚው ወያኔ  በአፋር ላይ የጋዝ ወረራ ለማድረግና የእንግሊዝን የትግራይ ትግርኝ አለማ ለማሳካት የተፈጠረ ነው፤ የኋለኛው ወያኔ ደግሞ በዐማራ  መቃብር ላይ  ታላቋን የትግሬ ሪፑብሊክ ለመመስረት የተፈጠረ ነው እንጂ የሁለቱም ውልደት ከሕዝብ መከራና ጭቆና ጋር የሚያያይዛቸው ገመድ የለም።
ባጭሩ ሕወሓት የሚባለው የግድያና የቅሚያ ድርጅት ጫካ የገባው የነገድ  ጭቆና ተፈጽሞብኛል ብሎ ነው። ለመታገያነት የመረጠው ወያኔ የሚለው ስያሜ ግን ዋጅራት  የአፋርን  ነገድ  በመውረር ጭቆና፣ ግድያና ዘረፋ ፈጽሞ በፈጠረው የአመጽ ስም ነው። በሌላ አነጋገር ሕወሓት የወረሰው «ወያኔ» የሚለው ስያሜ የነገድ  ጭቆና ለማድረግ ወደ አፋር የዘመቱ የጋዝ ወራሪዎች በፈጠሩት የአመጽ ስም ነው። የነገድ ጭቆና የተካሄደበትን የአመጽ መጠሪያ ስያሜው አድርጎ የነገድ ጭቆና ተካሂዶብኛል በማለት የነገድ ጨቋኞችን ስያሜ በመያዝ በረሃ የወረደው ብቸኛው የአለማችን ነውረኛ ድርጅት ቢኖር ሕወሓት ብቻ ነው።
የወያኔ እንቅስቃሴ ትግራይ  በአፋር ላይ የፈጸመችው የነገድ ጭቆና ስለመሆኑ የወቅቱ የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን በበላይነት ይዞ ለመቆየት  በተባበሩት መንግሥታት ፊት ካቀርባቸው ሰበቦች አንዱ መሆኑን ማየቱ በቂ ነው። የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን በበላይነት ይዞ ለመቆየትና የተባበሩት መንግሥታት አባል ለመሆን ያቀረበችው ማመልከቻ ውድቅ እንዲሆን ካቀርባቸው ሰበቦች አንዱ «የኢትዮጵያ  መንግሥት አንዱ ነገድ ሌላውን ለመውረርና ለመጨቆን የሚያደርገውን ዘመቻ ማስቆም አልቻለም» በማለት እንደ አብነትም ቀዳማይ ወያኔን የወለደውን የጋዝ ዘመቻ እንዳስረጂ በማቅረብ ነበር።
ሕወሓቶች  በነገድ ጨቋኝነት የሚከሱት የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እነሱ የትግላቸው ስያሜ ባደረጉት በወያኔ ስም አመጽ የጀመሩ የቀዳማይ ወያኔ ወራሪዎች በአፋር ሕዝብ ላይ ያካሂዱት የነበረውን ነገድ ጭቆናና ወረራ ያስቆም የነበረውን አስተዳደር ነው።  እንግዲህ! ወያኔዎች አማራ «የብሔር ጭቆና አካሄደብን» ብለው ከሚያቀርቡት ክስ መካከል ዋነኛው የሆነው ይህንን የወቅቱ ኢትዮጵያ መንግሥት በአፋር ነገድ ላይ  የዋጅራት የጋዝ ወራሪዎች ያካሂዱት የነበረውን የነገድ ጭቆና ለማስቆምና በተባረሩት መንግሥታት ጭምር የተቀመጠለትን መንግሥታዊ ግዴታውን በመፈጸሙ ነበር።
በ1935 ዓ.ም. ፖለቲካው የ«ብሔር» ባለመሆኑ  በእንደርታ የተነሳውን የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ ያስቆሙት  አብዛኛዎቹ የአድዋ ተወላጅ ዘማቾች ነበሩ።  ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ፖለቲካችን የ«ብሔር» መሆን ሲጀምር    በ1935 ዓ.ም. በአፋር ሕዝብ ላይ የተካሄደውን  የጋዝ ወረራ ለማስቆም የዘመቱ የአድዋ ዘማች ልጆች  አባቶቻቸው ስርዓት ለማስከበር  የወሰዱትን  እርምጃ ትርክት ፈጥረውለት  ዳግማይ ወያኔ ብለው ሕወሓትን ወለዱ።  ዛሬ  ግን ፖለቲካው የ«ብሔር» ስለሆነ   ወንጀለኞቹ እነ ጌታቸው አሰፋና  የተቀሩት ፋሽስት ወያኔዎች ይጠየቁ መባሉ በአንድ «ብሔር» ላይ እንዳነጣጠረ ዘመቻ ተቆጥሮ ሳልሳይና ራብአይ ወያኔን  ለመፍጠር ሰላሳ አመት አይፈጅም! እንዴውም እነ አረና፣ ደምህትና ታንድ ተቃዋሚነታቸውን ትተው ወደ ሳልሳይ ወያኔነት ለመቀየር እያኮበኮቡ ነው።  የ«ብሔር» ፖለቲካ ከሰብዓዊነት፣ ከነጻነትና ከዲሞክራሲ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም። በብሔርተኞች እምነት የ«ብሔራቸው» አባላት ሌሎችን  የሚሰርቁትና የሚገድሉት የ«ብሔራቸውን» ልዕልና ለማስጠበቅ ነው። ለዚህም ነው ለብሔርተኞቹ  የ«ብሔራቸው» አባላት የሆኑ ሰዎች  በሌሎች ላይ የፈጸሙትን  ግድያና ዘረፋ  ደግፈው ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት!
በቀጣይ ክፍል የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ትርክት ይቀርባል. . .
Filed in: Amharic