>

ህገ መንግስቱ የመጥፊያችን ዶሴ ነው የምለው ለዚህ ነው (ሀብታሙ አያሌው)

ህገ መንግስቱ የመጥፊያችን ዶሴ ነው የምለው ለዚህ ነው
ሀብታሙ አያሌው
ይህ የሞት ደብዳቤያችን የተሰነደበት ህገ መንግስት የሰው ልጅ እንደ ሰው መቆጠርን (ዜጋ)  የመሆንን መብት ክዶ በብሔርና በጎሳ ይደለድላል። ይህ ህገ መንግስት በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አጠራር ህገ አራዊት ይህው በየቀኑ የሚያሳየን እውነት የአራዊት መተዳደሪያ መሆኑን እንጂ የመራሄ መንግስት መተዳደሪያ መሆኑን አይደለም።
የዛሬውን ዘግናኝ ግድያ  የፈፀሙት አካላት የጭካኔ አፈፃፀም ብቃታቸውን ለማሳየት ድርጊታቸውን በቪዲዮ ጭምር አስደግፈዋል። ድርጊቱ የተፈፀመው በኦሮሚያ እና በሶማሌ መካከል የፖለቲካ እሳት በሚራገብበት ቦታ ነው።
ከዚህ ቀደም በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች በሚሊዬን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ለሞት እና ለሰቆቃ ተዳርገዋል።
የዛሬውን ለየት የሚያደርገው ለተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ እና እሬሳን በገመድ እየጎተቱ በቪዲዮ የእዩልኝ ጥሪ ማቅረብ ጉዳይ እንደወትሮው የገዳዬችን ማንነት በብሔረሰብ ደረጃ የኔ ለማለት ድፍረት ያገኘ ያለመኖሩ ነው።  ይህ በራሱ ጥሩ ጎንም አለው። ገዳይ ብሔር ተነፍጎ ጎሳ ከተሰጠው ቀጥሎ ደግሞ ጎሳንም ይነጠቅና መደበቂያ ጫካ ያጣል።
ለዛሬው ጭካኔ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል እየተባሉ ያሉት “ገሪ” የሚል መጠሪያ ያላቸው ጎሳዎች እንደሆኑ እየተነገረ ነው።  ስለዚህ ጎሳ እናውቃለን የሚሉ አካላት እንዳህ ሲሉ ያስረዳሉ…
                        ————-
“ገሪ ከቦረና አዋሳኝ ያለ ጎሳ ነው። የዚህ ጎሳ አባላት ራሳቸውን እንደ ሱማሌ ነው የሚቆጥሩት። ሱማሌዎች ደግሞ ”እናንተ ሱማሌ አይደላችሁም ኦሮሞ ናችሁ” ይሏቸዋል። ገሪዎች የሚናገሩት ቋንቋ በአመዛኙ ኦሮምኛ ነው። አኗኗራቸውም ልክ እንደ ቦረና ኦሮሞ ሁሉ በኬኒያም በኢትዮጵያም ውስጥ ሲሆን በዋናነት በከብት እርባታ ይተዳደራሉ። “
                      —————
እንደሚባለው ከሆነ “የገሪ”  ጎሳ የሚናገሩት ኦሮሚኛ ከሆነ አኗኗራቸው እንደ ቦረና ኦሮሞዎች ከሆነ፤  የሰፈሩትም ልክ እንደ ቦረና ኦሮሞ ኢትዮጵያም ኬንያም ከተባለ፤  ሶማሌ ነን ሲሉ አይደላችሁም ኦሮሞ ነን ሲሉ ክልክል ነው ከተባሉ፤ የቦረና አዋሳኝ በሚል ብቻ ከተጠሩ ክልላቸው የት ነው ? በኬንያ ያሉት ኬንያ ነውና አያከራክርም። በኢትዬጵያ ያሉት የገሪ ጎሳዎች ክልላቸው የት ነው ? እስከ ዛሬ በሶማሌና በኦሮሚያ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሁሉ በክልል ሲጠሩ ኑረው አሁን ለምን ጎሳ ተባለ ? የጎሳው ክልል የት ነው ?
በአካባቢው በቅርቡ በተደጋጋሚ በትጥቅ ላይ የተመሰረተ ተደጋጋሚ ግጭት ሲፈጠር ነበር። ሁሉም እልቂቶች እንደሰው የተፈፀሙ ሳይሆን ብሔረሰብን መሰረት ባደረገ ፖለቲካ የሚጫወቱ የፖለቲካ ኃይሎች የሚለኩሱት እሳት ነበር።  እነዛ ኃይሎች ደግሞ የታወቁ ናቸው።
ያም ሆነ ይህ ህግ የማስከበር ኃላፊነት የፌደራል መንግስቱ በመሆኑ በአፋጣኝ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።  የችግራችን ሁሉ ምንጭ የሆነው አብሮነታችንን ንዶ በጎሳ እና በብሔረሰብ እያቧደነ ህዝብን እና አገርን የጥቂት የፖለቲካ ኃይሎች መጫወቻ ያደረገ ህገ መንግስት ካልተሻሻለ ጠብ ሲል ሲደፍን መሆኑ አይቀሬ ነው።
    ህገ አራዊት ይሰረዝ ህገ መንግስት ይፃፍ !!
 የመለስ ድርሰት የሆነው የህወሓት ሰነድ ይወገድ !!
Filed in: Amharic