>

የዘመናችን ኤልዛቤል - ህወሓት!!! (አሸንጌ ማይጨው)

የዘመናችን ኤልዛቤል – ህወሓት!!!

 

አሸንጌ ማይጨው

 

ኤልዛቤል የአክዓብ ሚስት ናት። ሚስት ብቻ አይደለችም የባሏም ጌታ ናት። ጌታ ብቻ አይደለችም እንደፈለገች ባለቤቷን የምታሽከረክረው ነች።አክዓብ የእርሷ ባል ሳይሆን ልጇ ነው።

አንድ ቀን አክዓብ ናቡቴ የሚባለውን ሰው መሬቱን እንዲሸጥለት ጠየቀው። ናቡቴ ግን “የአባቶቼን ርስት አልሸጥም” አለው። አክዓብ ይህን ዓይነት መልስ በማግኘቱ አዘነ። ባለቤቱ ፊቱ ጠቁሮ ተክዞ አገኘችው። የገጠመውን ነገር ከነገራት በኋላ ንጉሥ ሆኖ በተራ ሰው እንዲህ  መሆኑ ስላናደዳት ገሰጸችው። ለዚህ መልስ አለኝ አትቸገር አለችው።

የጾም አዋጅ እንዲታወጅ አደረገች። ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ አስደረገች። በዚህም ጊዜ ናቡቴ እንዲገኝ አስደረገች። በስፍራውም  ምናምንቴ የሆኑ ሰዎች እንዲገኙ አዘዘች። እነዚህ ምናምንቴ ሰዎች “ናቡቴ እግዚአብሄርንና ንጉሡን ሰድቧል” ብለው እንዲመሰከሩ አስደረገች። ናቡቴም በዚህ ተወንጅሎ ተወግሮ እንዲገደል ተደረገ። የናቡቴ መሬትም ለአክዓብ ያለገንዘብ ተሰጠ። አክዓብ ደስ አለው፤ እንዲህ ያለች ሚስት ስላለችው የሚፈልገውን ማግኘት ቻለ።

እግዚአብሄር አክዓብና ኤልዛቤል በናቡቴ ላይ ያደረጉትን ተመለከተ። እግዚአብሄር ነቢዩን ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከ። እንዲህም በላቸው:-

”ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል” ፩ኛ ነገሥት ፳፩፡፲፱።

ሰዎች በዘመናት በስልጣናቸው ተመክተው ግፍ ፈጽመዋል። ግፍ የፈጸሙ ሁሉ ማንም እንደማያያቸውና ሁሉም ነገር ተድበስብሶ እንደሚቀር ያስባሉ። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ኤልዛቤል የዋሁን ናቡቴን ባልፈጸመው ወንጀል እንዲገደል አስደረገች። ሁሉ በስልጣኗ ሆኖ ስለተሰማትና በትዕቢት ግፍ ፈጸመች። የሚገርመው ግን ግፉ ሲፈጸም ያዩ ሰዎች የሚደረገው ነገር ተገቢ አለመሆኑን ባይናገሩም ሁሉንም የሚመለከትና የሚፈርድ አምላክ ፍርዱን ሰጠ።

እግዚአብሄር የራሱ የሆነ ንጉሥ አዘጋጀ።በሕዝቡ ላይ አነገሠው።ይህም ንጉሥ ኢዮ ይባላል።

”የነቢያትን ደም፤ የእግዚአብሄር ባሪያዎችን ሁሉ ደም ከኤልዛበል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ…”፪ ነገሥት ፱፤፯

አዎን እግዚአብሄር ይበቀላል። በግፍ የተጋዙትን፤የ ተሰቃዩትን፤ የተገደሉትን ብድራት ይመልሳል። በኤልዛቤልና በአክዓብ ላይ ብቻ ሳይሆን በልጃቸው በኢዮራም ላይ ተፈጸመ። ኢዮራም ተገደለ አባቱ በግፍ በወሰደው በናቡቴ እርሻ ላይ ተጣለ። ይህ ብቻ አይደለም ኢዩ ኤልዛቤል ወደምትገኝበት ሄዶ ስታስት የነበረችውን ኤልዛቤል፤ ዓይኗ እያየ፤ በመስኮት ተወርውራ እንድትሞትና የናቡቴን ጽዋ እራስዋ እንድትጠጣ ተደረገች። የናቡቴን ደም የላሱ ውሾች ደሟን ላሱ።

ይህ የረጅም ጊዜ ታሪክ ነው። ታሪክ ግን ይደጋገማል፤አሁንም እናየዋለን። የዘመናችን ኤልዛቤል የሆነው ህወሓት ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሟል። ሰዎችን እየገደለ እያስገደለ እርሻቸውን የቀማቸው ቁጥራቸው ብዙ ነው። ለዘመናት ከሚኖሩበት ቦት፤ እርሻ እያፈናቀል ያሳደዳቸው፤ የአውሬ እራት እንዲሆኑ ያደረጋቸው ቀላላ ቁጥር አይደለም። የዘረፋቸው፤የገደላቸው፤ያዋረዳቸው ብዙዎች ናቸው።

ስልጣን ያባልጋል፤ያሳውራል። የኢትዮጵያ ኤልዛቤል ህወሓት የሚያይ አምላክ፤ሰው ከሕዝቡ መካከል አስነስቶ ፍርድ እንደሚሰጥ፤ የደነደነው ልባቸው ስላሳወራቸው አሁንም ይህንኑ ተግባራቸው እያከናውኑ ነው።

ኤልዛቤል ኢዩ ወደእርሷ ሲመጣ “ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሆይ ሰላም ነው?አለችው።”ምን ሰላም አለ።በየቦታው ደም ታፈሻለሽ፤ሰው ታስለቅሻለሽ። አሁን ግን ተራው የአንቺ ነው። ትወረወሪያለሽ ፤የዋሃንን በግፍ ደም እንዳፈሰስሽ የአንቺም ደም ይፈሳል አለ ኢዮ። በመስኮት ወርወሯት ፤ተከሰከሰች፤የፈረደችው ዓይነት ፍርድ በእርሷ ላይ ተከናወነ። መኳኳሏ አላዳናትም። መልካም ቃላት ብትደረድርም ከፍርድ ልታመልጥ አልቻለችም።

የግፈኞች የመጨረሽ ዕጣ ፋንታቸው ይኸው ነው። ግን በመጨረሽ ይኳኳላሉ። ይዘፍናሉ፤ይጮኸሉ። ማቅራራት ፤መፎከር ፤ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት አይቀሬ ነው።የሠሩት ሥራ ወደ እግዚአብሄር ጆሮ ደርሷልና የሚያስጥል ነገር የለም።የምትተማመንባቸው ጋሻ ጃግሬዎች ማስጣል ሳይሆን እጆቻቸው ሊወረውሯትን ሊፈጠፍጧት ፈጠኑ።

ኤልዛቤል ህወሓት በሰዶምና በገሞራ ድርጊትሽ ፍርድ እበርሽ ደርሷል።ቀረርቶ አያድንም።አክዓብን ያዳነው አንድ ነገር ብቻ ነው።ንስሐ መግባትና ሐጢአትን መናዘዝ ነው።ኢዮዎች ተዘጋጅተዋል። ወደበርሽ፤ወደምትተማመኝበት ምሽግሽ እየተቃረቡ ነው። የኑዛዜ ጊዜ ተሰጥቶሽ አንቺ ግን ልብሽን አደነደንሽ። ይባስ ብለሽ በየቦታው ደም ማፋሰስሽን ገፋሽበት።አሁን ግን ጽዋው ሞልቶ ፈሷል። ልትወረወሪ ቀናት ቀርተውሻል።ኢዩ በበር ነው።ኢዮ መሳሪያ አያነሳም የራስሽ የሆኑትን ሰዎች ይወረውሩሽ ዘንድ ያዛቸዋል በውርደት ዘመንሽን ትጨርሻለሽ።

Filed in: Amharic