>
5:44 am - Tuesday July 5, 2022

ይድረስ ለኢንጅነር ታከለ ኦማ (አብዱራህማን አህመዲን - የቀ/የፓርላማ አባል)

ይድረስ ለኢንጅነር ታከለ ኦማ

አብዱራህማን አህመዲን (የቀ/የፓርላማ አባል)

አዲስ አድማስ

“አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች የመኖር መብት አላቸው፤ የከተማዋ ባለቤት ግን አይደሉም…” ታከለ ኦማ

* በኔ አተያይ… ኦሮሞው መጤ ነው፤ አማራው መጤ ነው፤ አገውም ፤ ትግራዩም መጤ ነው። ጉራጌው – ሐረሪው – ስልጤው… መጤ ናቸው። ኛንጋቶሙ – ሱርማው – መዠንገሩ – ጉሙዙ – ሽናሻው – አኙዋኩ… ከየአቅጣጫው ተገፍቶ የመጣ ነው፡፡ ሌላውም እንዲሁ፡፡ ስለሆነም፤ በዚህ ዘመን ሰንጎ የያዘንን ይህንን የ“መጤ ነህ” ንትርካችንን እዚህ ላይ ቆም አድርገን ስለ ጋራ ቤታችን በጋራ እንስራ!!

—-

ክቡር ሆይ!
የአክብሮት ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡ ዛሬ ይህቺን ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በዚህ ወቅት ባለዎት ስልጣን ለከተማችን አዲስ አበባ መስራት የሚገባዎትን በተመለከተ የማውቃትን ሃሳብ ለመወርወር በማሰብ ነው – ‘ያለውን የወረወረ ከንፉግ አይቆጠርም’ እንዲሉ አበው!
ስልጣን ከያዙበት እለት ጀምሮ ሶሻል ሚዲያውና “ፀረ-ለውጥ ኃይሎች” ስም የማጥፋት ዘመቻ ቢያካሂዱበዎትም ሁሉንም ነገር በመሪነት (Leader) መንፈስ ቻል አድርገው፤ በእርጋታ ይዘው ሥራ ለመስራት ለሚያደርጉት ጥረት ያለኝን አድናቆት ከሁሉ አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ይህ ማለት ግን እስከ አሁን እያደረጉት ባለው ነገር ሁሉ እስማማለሁ ወይም ደስተኛ ነኝ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ፤ ዴሞክራሲ ማለት የማይፈልጉትንም ቢሆን የመስማት ግዴታ በመሆኑ የማልፈልጋቸውንም ሃሳቦች ሲናገሩ በጽሞና ሳደምጥ ቆይቻለሁ፡፡ በእርስዎም በኩል ከዚህ ቀጥሎ የምጽፋቸውን ሃሳቦች በእርጋታ እንዲያነቡና አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት በሰለጠነ መንገድ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ አደራ እላለሁ፡፡
ክቡር ሆይ!
“አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች የመኖር መብት አላቸው፤ የከተማዋ ባለቤት ግን አይደሉም…” የሚል መንፈስ ያለው ሃሳብ በቅርብ ጊዜያት ሲናገሩ እንደሰማሁ አስታውሳለሁ፡፡ ለዚህ ሃሳብ ማጠናከሪያ ተደርጎ የሚቀርበው ሃሳብ ደግሞ የኦሮሞ ቤተሰብ የሆኑት የጉለሌ፣ የገላን፣ የየካ፤… ጎሣዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ መስፈራቸው ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ የመከራከሪያ ሃሳብ ብዙ ርቀት የሚወስደንና የሚያግባባን ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ወደ ምክንያቶቼ ከመሄዴ በፊት የተወሰኑ ጥያቄዎች ላንሳ፡፡
በአንድ ሥፍራ የሚኖር ማህበረሰብ የሰፈረበት መሬት ባለቤት ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ ማረጋገጫ መስፈርቱ ምንድነው? በዚያ መሬት ላይ ምን ያህል ጊዜ ሲኖር ነው ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው? ለምን? ማረጋገጫ ሰጪውስ ማን ነው? አንድ ከንቲባ የሚያስተዳድረውን ማህበረሰብ የመሬቱ ባለቤት አይደለህም የማለት ስልጣን አለው? መሬት አልባ ህዝብ ማስተዳደርስ ይቻላል? … ለአንድ ማህበረሰብ ማንነቱን የሚወስንለት ማን ነው? ለምን? …የአዲስ አበባ ህዝብ “ቅይጥ ማንነት” አለኝ፣ መሬቱም የራሴ ነው ቢል የሚከለክለው ድንጋጌ በየትኛው የሀገሪቱ ህግ ውስጥ ነው ያለው?
እነዚህ ጥያቄዎች ተራ ጥያቄዎች ይመስሉ ይሆናል። ላይ ላዩን ሲታዩ በርግጥም ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ በበኩሌ፣ ከእነዚህ ጥያቄዎች በስተጀርባ ያለው ፖለቲካዊ ፍልስፍና፣ እነዚህ ጥያቄዎች ተራ ጥያቄዎች እንዳልሆኑ ይናገራል ብዬ አስባለሁ፡፡ በማንነቱና በርስቱ ቀልድ ለማያውቀው ኢትዮጵያዊ፤ እነዚህ ጥያቄዎች “ተራ” እንደማይሆኑም ከፍ ያለ ግምት አለኝ፡፡
ከላይ ለዘረዘርኳቸው ጥያቄዎች በግሌ መልሶች አሉኝ፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ስራ እንደሚበዛብዎ እገነዘባለሁ፡፡ ጊዜ ካለዎት የእርስዎን መልስ ባነብ ደስታዬ ነው፡፡ መልስ ጻፉም አልጻፉ በጥያቄዎቹ ዙሪያ ሃሳብ ለማውጠንጠን ይረዳዎት ዘንድ ወደ እኔ መልስ የሚያንደረድሩ አንዳንድ ታሪካዊ ዳራዎችን እንደሚከተለው ለማቅረብ ወደድሁ፡፡
እርስዎም እንደሚያውቁት “ደብተራ” የጻፈው የሀገራችን “ታሪክ” ሁላችንም አምነን የምንቀበለው አይደለም፡፡ የዚህ ዘመን ጭቅጭቃችን መነሻና መድረሻም ይኸው የተዛባ የታሪክ ትርክት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚሁ በተዛባው የታሪክ ስንክሳር ውስጥ ግን አንዳንድ ሊያስማሙን የሚችሉ ወይም ሊያስማሙን የሚገቡ እዚህም እዚያም ጣል ጣል ያሉ እውነታዎች መኖራቸውም የሚታበል አይሆንም፡፡ ሀቀኛውና ሁላችንም የምንቀበለው ታሪካችን በታሪክ ባለሙያዎች በአግባቡ እስኪሰነድ ድረስ ሁላችንም የምንቀበላቸውን ሀቆች ተቀብለን፣ በየወቅቱ የሚገጥሙንን ማነቆዎች ፈተንና ተግባብተን፣ ሰላማዊ ህይወታችንን ማጣጣም የሰለጠኑ ሰዎች ተግባር ሊሆን ይገባዋል በሚለውም ላይ ልዩነት የሚኖረን አይመስለኝም፡፡
ክቡር ሆይ!
“ፍቅርና መደመር” ሀገር ለማረጋጋት እንደሆነ እንጂ፤ ሀገር ለመመስረት (Nation Building) ብቻውን የሚሰራ መርህ ሆኖ አይታየኝም – የሰው ልጅ ባህሪ በፍቅር ብቻ የሚገዛ አይደለምና! የዓለም ታሪክ የሚነግረንም ሀገራት በጉልበት፣ በማስገበር፣ በመገዳደል፣… ጭምር መመስረታቸውን ነው፡፡ በጣም የሩቁን ዘመን ትተን በቅርብ ዘመን ጣሊያንን ጋርባልዲ፣ ጀርመንን ቢስማክ፣… እንዴት እንደመሰረቷቸው ብናይ ሂደቱ የሚነግረን ቁም ነገር አለ፡፡ የእኛም አያቶችና ቅድመ አያቶች ኢትዮጵያን በመመስረት ሂደት በቀስት፣ በጦር፣ በአንካሴ፣ በመጥረቢያ፣ በጎራዴ፣ በዱላ፣ በጠመንጃና በናዳ ጭምር… ሲገዳደሉ፣ ሲያሸንፉና ሲሸነፉ፣ ሲሸሹና ሲያሳድዱ፣ ሲማርኩና ሲማረኩ፣ ግዛታቸው ሲሰፋና ሲጠብ፣ ሲጣሉና ሲታረቁ፣ ሲኳረፉና ሲፋቀሩ፣ ሲጋቡና ሲፋቱ፣… ኖረው… ኖረው… በመጨረሻ የህይወትም የአካልም መስዋእትነት የከፈሉባትን ኢትዮጵያ ሀገራችንን አስገኝተውልናል፡፡
ወላጆቻችን በግጭትና በጦርነት ሀገር መስርተው፤ በወጉ ያልተጻፈ የመገዳደል የታሪክ ቁስልና ኢትዮጵያ የምትባል ዓለም ያወቃት ሀገር ለእኔና ለእርስዎ አስረከቡን፡፡ እኔና እርስዎ ያለን አማራጭ ሁለት ይመስለኛል፡፡ ወይ የግጭትና የፍጅት ታሪካችንን እያነሳን፣ “ያንተ ቅድመ አያት እንዲህ አድርጓል፤ የለም ያንተ ነው እንዲህ ያደረገው…” እየተባባልን ጉንጭ አልፋ ንትርክ ማድረግ፤ አሊያም የሆነውን ሁሉ ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ መፈተሽ፣ የጥፋቱን ዓይነትና የጥፋቱን መጠን መለየት፣ መወያየትና ለዘመናት በ“ስማ በለው” የመጣውን የመጠፋፋትና የመናናቅ የታሪክ ምዕራፍ እውቅና ሰጥተን በመዝጋት፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጀመር። የእርስዎም የእኔም ምርጫ ሁለተኛው አማራጭ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
እንደኔ እንደኔ፤ ኢትዮጵያ በምንላት ሀገራችን ውስጥ ያሉ ብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉም “መጤዎች” መሆናቸውን አምነን መቀበል ከሚገቡን መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉት የክርስትና፣ የእስልምናም ሆነ የአይሁድ ሃይማኖቶች እንዲሁ ሀገር በቀል አለመሆናቸው የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ቀድሞ የመጣው በኋላ የመጣውን “አንተ መጤ ነህ” ሊለው አይገባም፡፡ ቢልም ትርፉ ትዝብት ነው እንጂ እውነታውን አይቀይረውም፡፡
እናም፤ በኔ አተያይ… ኦሮሞው መጤ ነው፡፡ አማራው መጤ ነው፡፡ አገውም – ትግራዩም መጤ ነው። ጉራጌው – ሐረሪው – ስልጤው… መጤ ናቸው። ኛንጋቶሙ – ሱርማው – መዠንገሩ – ጉሙዙ – ሽናሻው – አኙዋኩ… ከየአቅጣጫው ተገፍቶ የመጣ ነው፡፡ ሌላውም እንዲሁ፡፡ ስለሆነም፤ በዚህ ዘመን ሰንጎ የያዘንን ይህንን የ“መጤ ነህ” ንትርካችንን እዚህ ላይ ቆም አድርገን፣ ሀገሪቱ በሁላችንም አያት – ቅድመ አያቶች መስዋእትነት (በመግደልም በመሞትም) ተፈጥራ በጋራ መስዋእትነታቸው ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ አሁን ላለነውም ወደፊት ለሚመጡትም የምትበቃ፣ የሁላችንም እናት ናት የሚለውን ብንይዝ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡
ክቡር ሆይ!
ለግንዛቤ ያህል የእኔን የ“መጤነት ታሪክ” ላቅርብልዎ፡፡ (ከእርስዎ የተለየ ሊሆን እንደማይችል አስባለሁ) ወላጆቼ እንደነገሩኝ፤ የተወሰኑት ቅድመ አያቶቼ ላኮመልዛ (አሁን ወሎ) ከሚባለው አካባቢ ከ“ማመዶ” ቤተሰብ የተገኙ አማራዎች ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ከግራኝና ከኦሮሞ ማህበረሰብ ወደ መሀል አገር መምጣት በኋላ አንጎት (አሁን የጁ) ከሚባለው አካባቢ ከ“ወረ-ሼህ” ቤተሰብ የተገኙ የየጁ ኦሮሞዎች ናቸው። በኋላ ላይ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ከትግራይ ወደ መሀል አገር የመጡት የ“አደ ከቢሬ” ቤተሰቦቼም ቀድመዋቸው ከመጡት “ማመዶዎች” እና “ወረ-ሼህዎች” ጋር ተጋብተውና ተጋምደው መጡ መጡና እኔን ወለዱ፡፡ እኔ ከአማራ፣ ከኦሮሞና ከትግራይ አያት፣ ቅድመ አያት የተገኘሁ ብሆንም አፌን የፈታሁት ግን በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከእነዚህ አያት፣ ቅድመ አያት መወለድም ሆነ በአማርኛ ቋንቋ አፍ መፍታት በፍፁም የእኔ ፍላጎት አልነበረም። ምርጫዬም አልነበረም። (እርስዎም ኦሮሞ ሆኖ መወለድን እንዳልመረጡት አምናለሁ)
የሆነ ሆኖ ወደ መጤነቱ ትርክት ልመለስ… በቀድሞው አጠራር በየጁ አውራጃ የተገናኙት እነዚህ ሦስት ቤተሰቦቼ፤ አንዳቸውም እዚያች መሬት ላይ የበቀሉ አልነበሩም፡፡ “መጤዎች” ነበሩ፡፡ ልዩነቱ የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው፡፡ አማራዎቹ በጥንት ዘመን ከደቡብ ዓረቢያ የመጡ ናቸው ይባላል፡፡ ኦሮሞዎቹ ከግራኝ ጋርና በኦሮሞ እንቅስቃሴ ወቅት ወደ የጁ የመጡ ሲሆኑ፤ ከትግራይ የመጡት በአፄ ዮሐንስ ዘመን ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲሰደዱ፣ የጁ ላይ ቆም ብለው ከቀዳሚዎቹ ጋር የተገናኙና የተጋቡ ናቸው፡፡
መቼም እነዚህ አያት – ቅድመ አያት – ምንጅላቶቼ ቀስት ሳይወራወሩ፣ በሽመል ሳይፈናከቱ፣ በጎራዴ ሳይከታከቱ፣ በናስ ማስር ሳይታኮሱ፣… በፍቅር የተደመሩና የተጋመዱ እንዳልሆኑ መንፈሴ ይነግረኛል። ግና… አብሮ በመኖር ሂደት ደመኝነትን ትተው፣ በጋብቻ ተሳስረው፣ በፍቅር ተጣምረው እኔን ወለዱ፡፡ እኔ ትምህርት ልማር ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ይኸው አዲስ አበባንና ሀገሬን እያገለገልኩ መሐል ሸዋ ላይ 33 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ግን “መጤ ነህ” እየተባልኩ ነው። ወደተወለድኩበት መንደር ብመለስ ወላጆቼ የሉም፣ የሚያውቀኝም የማውቀውም ሰው የለም፣ መንደሯም ፈርሳለች፡፡ እዚያም “መጤ ነህ” መባሌ አይቀሬ ነው። “መጤ ነህ” የማልባልበት ምድር የት እንደሆነ አላህ ይወቅ! (እርስዎ በአዲስ አበባ 25 ዓመታት መኖርዎን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ከእርስዎ ቀድሜ ስለመጣሁ “መጤ ነህ” አልልዎትም!)
ልጆቼ አዲስ አበባና ለገጣፎ ነው የተወለዱት፡፡ እንደ እርስዎ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ማቀላጠፍ ጀምረዋል፡፡ ወደፊት መቀሌ ዩኒቨርስቲ ከተማርን ትግርኛ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ከተማርን ሶማልኛ ወይም ሌላ ቦታ ያለ ዩኒቨርስቲ ከተማርን 3ኛ ቋንቋ እንጨምራለን እያሉኝ ነው፡፡ የፈለጉትን ቋንቋ ቢማሩ እዚህም እዚያም “መጤ ነህ” መባላቸው ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ያለ ጥርጥር የወደፊት እጣ ፈንታቸው “መጤ ነህ” ከመባል የዘለለ አይሆንም፡፡
ክቡር ሆይ!
የመጤነትን ጉዳይ እዚህ ላይ ገታ ላድርግና ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ ልመለስ፡፡ አዲስ አበባ የተቆረቆረቺው በ1879 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚያ በፊት በነበረው ዘመን አሁን አዲስ አበባ ባለቺበት አካባቢ ሰዎች ይኖሩ እንደነበርም ታሪክ ይነግረናል። አዲስ አበባ በተቆረቆረቺበት ወቅት እዚያ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ኦሮምኛ ተናጋሪ እንደነበሩ መገመት ለእውነት የቀረበ ሀቅ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም እዚያ ይኖሩ የነበሩት ማህበረሰቦች ጉለሌ፣ ገላን፣ የካ፣… የሚባሉ የኦሮሞ የዘር ግንድ ጎሣዎች እንደነበሩም ታሪክ ይነግረናል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚያ ጉለሌ፣ ገላን፣ የካ፣… የሚባሉት ማህበረሰቦች እዚያች ምድር ላይ የበቀሉ ሳይሆኑ፤ ከ1540ዎቹ ጀምሮ ባሉት ዓመታት በኦሮሞ እንቅስቃሴ አማካይነት ከባሌና ከቦረና አካባቢዎች አሁን አዲስ አበባ ወደምንለው አካባቢ እንደመጡም ብዙዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ እርስዎም በዚህ የሚስማሙ ይመስለኛል፡፡
ከኦሮሞ እንቅስቃሴ (በአንዳንዶች አባባል ከኦሮሞ ፍልሰት) አስቀድሞ ወደ መሀል አገር በተለይም አሁን አዲስ አበባ ወደተመሰረተቺበት አካባቢ የመጣው ከምስራቅ ኢትዮጵያ የተነሳው የኢትዮጵያ ጦረኛ መሪ ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጛዚ (ግራኝ) እንደነበር ልዩነት የሚኖረን አይመስለኝም፡፡
ዐረብ ፋቂህ የተባለው የመናዊ “ፍቱህ አል-ሀበሻ” በተባለው መጽሐፉ ላይ በጻፈው ታሪክ መሰረት፤ ግራኝ ከአፄ ልብነ ድንግል ጋር ጦርነት ካካሄደባቸው ስፍራዎች ውስጥ ሽምብራ ኩሬ (በአሁኑ አጠራር ሞጆ) አካባቢ፣ ባዶቄ (በአሁኑ አጠራር ዱከምና ቢሾፍቱ) አካባቢ፣ እንዶጥናህ (በአሁኑ አጠራር አዲስ አበባ) አካባቢ፣… የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በተለይም በእነዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ “ማያ” የተባሉ ቀስተኛ ህዝቦች አስቸግረውት እንደነበር ዐረብ ፋቂህ ዘግቧል፡፡ ይህ ታሪክ የሚነግረን ከኦሮሞዎች በፊት በእነዚህ አካባቢዎች ሌሎች ማህበረሰቦች ይኖሩ እንደነበር ነው፡፡
ግራኝ እ.ኤ.አ ከ1529 – 1543 ድረስ ተመሳሳይ ጦርነቶችን እያደረገ ወደ ደቡብም፣ ወደ ምዕራብም፣ ወደ ሰሜንም በመዝመት በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጣር ለአሁኗ ኢትዮጵያ መሰረት የሆነውን ግዛተ መንግስት በጉልበት አስፋፋ፣ አጠናከረ፡፡ ዋና ከተማውን በጎንደር ደንቢያ በማድረግ መላዋን ኢትዮጵያ ለ15 ዓመታት ሲመራና ሲያተራምስ ከቆየ በኋላ ሞቶ እዚያው ደንቢያ አቅራቢያ ተቀበረ፡፡ ግራኝ ከሞተ በኋላ የግራኝ ጦር አባላትና ከእርሱ ጋር ወደ መሀል አገርና ወደ ሰሜን የሄዱት ተከታዮቹ ከፊሉ የያዘውን ይዞ ወደ መጣበት አካባቢ ሲመለስ፤ ከፊሉ እዚያው ተጋብቶ መኖር እንደቀጠለ ይነገራል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከባሌና ከቦረና የተነሳው የኦሮሞ ማህበረሰብ ግራኝ የሄደበትን ዱካ ተከትሎ ወደ ደቡብ ምዕራብ፣ ወደ ምዕራብም፣ ወደ መሀል አገር (አሁን ሸዋ የሚባለው አካባቢ) እና ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተንቀሳቀሰ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴው በርካታ አካባቢዎችን የተቆጣጠረው የኦሮሞ ማህበረሰብ፤ በየአካባቢው ከነበሩ ማህበረሰቦች ጋር በውድም በግድም እየተጋመደና እየተዛመደ መኖሩን ቀጠለ። የኢትዮጵያን ግዛተ-መንግስት በደም አስተሳሰረ። በዚህ ሂደት ወደ መሐል ሀገር የመጡት ኦሮሞዎቹ እነ ጉለሌ፣ ገላን፣ የካ፣… ከእነሱ ቀድመው በእንዶጥናህ (በአሁኑ አጠራር አዲስ አበባ) አካባቢ ይኖሩ የነበሩትን ማህበረሰቦች በመግፋት ወይም በጉዲፈቻና በሞጋሳ በመዛመድ መኖር እንደጀመሩ መገመት ይቻላል፡፡
በዚህ መልኩ ሲኖሩ … ሲኖሩ… በርካታ ዓመታት ከተቆጠሩ በኋላ እነ አጤ ምኒልክ ወደ አካባቢው መጡና እንዶጥናህ (በእነ ምኒልክ ዘመን አጠራር ዲልዲላ/እንጦጦ፣ በኋላ አዲስ አበባ) ላይ ሰፈሩ። የአሁኗን አዲስ አበባ የመንግስት መቀመጫ፣ ዋና ከተማ አድርገው መሰረቱ። ከዚያም ንጉሱን ተከትለው ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በስፍራው የነበሩትን እነ ጉለሌ፣ ገላን፣ የካ፣… ወደ ዳር እየገፉ የአሁኗን አዲስ አበባ አስፋፏት፡፡ …ከዓመታት በኋላ እኔም እርስዎም ወደ አዲስ አበባ መጥተን ተደመርን። እርስዎም እነሆ ከንቲባ ለመሆን በቁ! – እናስ አዲስ አበባ የማን ናት? የኦሮሞ እንዳይሉኝ አደራ! ምክንያቱም የአዲስ አበባ ከንቲባ የሚሆኑት የከተማዋ ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ሲመርጥዎት እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ስለመረጠዎ ሊሆን አይችልምና!
ክቡር ሆይ!
በየትም ሀገር ያሉ ከተሞች የተመሰረቱት በዚያ ከተማና በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን በመግፋትና በማፈናቀል ነው፡፡ የእርሻ መሬቶችን ሳይቀማና አርሶ አደሮችን ሳያፈናቅል የተመሰረተና ያደገ ከተማ በዓለም ላይ ሊገኝ አይችልም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ወደፊትም ልናቆመው የማይቻለን ሀቅ ነው የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ይልቁኑ ልንጋፈጠው የሚገባ እውነታ ነው፡፡ እንዴት? በሚለው ላይ ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
እዚህ ላይ “እና ገበሬው ከመሬቱ ላይ ዘለዓለም እየተፈናቀለና እየተጎሳቆለ ለማኝ ሆኖ ይኑር ነው ወይ የምትለው?” የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን (Sociologists) እንደሚሉት “Urbanization is all about civilization, industrialization and development” ይህንን አባባል በቀላል ቋንቋ ስንተረጉመው፤ “ከተማ ተመሰረተ ማለት ስልጣኔ መጣ፣ ኢንዱስትሪ ተስፋፋ፣ እድገትና ልማት እውን ሆነ” ማለት ነው የሚል አንደምታ ይሰጠናል፡፡
ይህቺ ሃሳብ አንድ ነገር የሚጎድላት መሆኑ ይታየኛል፡፡ ይኸውም “ከተማ ተመሰረተ ማለት ገበሬ ከመሬቱ ላይ ተነቀለ ማለት ነው” የሚል ሃሳብ ይጎድላታል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮችን ሰብስበው ‘ከእንግዲህ ወዲያ ከመሬታችሁ ላይ የመፈናቀልና የመነቀል ችግር አይደርስባችሁም’ ያሏቸው፡፡ ይህንን ሃሳብዎን እኔም እጋራለሁ፣ እደግፋለሁ፡፡ ለዚህም ነው ‘አዲስ አበቤዎች የቤት ችግር ቢኖርብንም ገበሬ አፈናቅለው ግን አንድ ክንድ መሬት አይስጡን!’ የሚል ርእስ የመረጥኩት፡፡ (እና ምን ይደረግ? በሚለው ላይ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ)
በርግጥ የከተማ መመስረት እድገትና ልማትን አስከትሎ መምጣቱ እውነት ነው፡፡ በዚያው መጠን የገበሬ መፈናቀልም እውነት ነው፡፡ …እኔም ከአርሶ አደር ቤተሰብ የወጣሁ ከተሜ ነኝ፡፡ እናም የአርሶ አደር ህይወት ያሳስበኛል፡፡ እንቅልፍ ይነሳኛል፡፡ አርሶ አደሩ ከመሬቱ ላይ ሲነሳ መሬቱን ብቻ አይደለም የምንቀማው፡፡ የምንቀማው ሙያውን ጭምር ነው፡፡ የምንቀማው ለዘመናት የኖረበትን፣ ልምድ ያካበተበትን ገበሬነቱን ጭምር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አርሶ አደርነቱን ቀምተን ተራ ዋርድያ፣ ቤት ጠባቂ ዘበኛ እያደረግነው ነው፡፡ ሙያውን ቀምተን ጠጪ፣ እብድ፣ ወፈፌ፣ ለማኝ፣… እያደረግነው ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ አዲስ አበባ ባልወለድባትም አሳድጋኛለች። አስተምራኛለች፡፡ ሥራ ሰጥታኛለች፡፡ ድራኛለች፣ ኩላኛለች። ከእድሜዬ ሁለት ሦስተኛውን ጊዜ ኑሬባታለሁ፡፡ እናም ከመሬቱ የተነቀለው ገበሬው ብቻ ሳይሆን የምወዳት አዲስ አበባ ሁኔታ ያሳስበኛል። የነዋሪዎቿ ቤት አልባነት፣በረንዳ አዳሪነት ሰላም ይነሳኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ የወላጆቻቸውን “የትውልድ መንደር” የማያውቁ ወጣቶች መውደቂያ ማጣት ልቤን ይሰብረዋል፡፡
እናም የእርስዎ ትልቁ የቤት ስራ የእነዚህን ሁለት ማህበረሰቦች (የተፈናቃይ ገበሬውንና የቤት አልባ ከተሜውን) መብት፣ ጥቅምና ፍላጎት ማሟላት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ‘ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም’ እንዲሉ ከምር ካሰብንበት፣ የሁለቱንም የህብረተሰብ ክፍሎች ችግሮች (ማለትም፤ በአንድ በኩል የከተሜውን የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ በሌላ በኩል የገበሬውን መፈናቀል መግታት) ሙሉ ለሙሉም ባይሆን ደረጃ በደረጃ መፍታት ይቻላል፡፡ እንዴት? ቀጥለን እንየው!
ክቡር ሆይ!
እንደሚታወቀው አዲስ አበባ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች፣ በፋብሪካ የሚሰሩ ወዛደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ በግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ሙያተኞች፣ በግል ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች፣… ተማሪዎች፣ ሥራ ፈላጊዎች፣ ህፃናትና አረጋውያን… ይኖራሉ፡፡ ከተማዋ ከተለያዩ አካባቢዎች ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡና የሚሄዱ እንግዶችንም በየእለቱ ታስተናግዳለች፡፡
ከአዲስ አበባ ችግሮች ዋነኛው ነዋሪዎቿንና እንግዶቿን የምታስተናግድበት መጠለያ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት ውስን ነው፡፡ አሁን ካለው መጠን የምትጨምረው አንድ ክንድ ወርድም ሆነ ስፋት የለም፡፡ ስለሆነም ከተማዋ ያላትን የመሬት ሀብት በውስጧ ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር ማጣጣም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የሀገራችን የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በአግባቡ ተፈትሾ፤ የተለያዩ ስልቶች ተቀይሰው ያለፉ ስህተቶች የሚታረሙበትና ቀጣይ ተግባራት በህግና በስርዓት የሚመሩበት አቅጣጫ መቀመጥ ይገባዋል፡፡
ቅድም እመለስበታለሁ ወዳልኩት የመፍትሄ ሃሳብ ላምራ… በ1992 በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ከከፍተኛ 17 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል ሆኜ በተመረጥኩበት ወቅት በከፍተኛ 17 ውስጥ አራት የቀበሌ ገበሬ ማህበራት እንደነበሩ አስታወሳለሁ። በዚያ ወቅት በአዲስ አበባ ደረጃ 23 የቀበሌ ገበሬ ማህበራት እንደነበሩም ትዝ ይለኛል፡፡ እነዚህ የቀበሌ ገበሬ ማህበራት አሁንም እንዳሉ አስባለሁ፡፡ ይህም ማለት በእነዚህ ቀበሌዎች ያሉ ገበሬዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሆነው ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
በከተማዋ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታም ሆነ ፋብሪካዎችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት መሬት ይወሰድ የነበረው ደግሞ ከእነዚህ አርሶ አደሮች ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መደዳውን ተቸምችመው የተሰሩ ነባር መንደሮችን በማፍረስ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመስራት ተነሺዎችን ወደዚያ የማዛወር ስራ መስራትና ተነሺዎች የነበሩበትን መሬት በሊዝ በመሸጥ የመሬት ፈላጊዎችን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ሲደረግም ቆይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በዘላቂነት መቀጠል የሚችል አይደለም፡፡ እናም፤ “እና ምን ይደረግ?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በክቡርነትዎ በኩል የሚከተሉት ተግባራት መከናወን ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አንደኛ፡- በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ጥርት ያለ፣ ከአድርባይነት የራቀ አቋም መያዝና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ ነው። እንደኔ እንደኔ በዓለም ላይ አንድም መሬት የጠፈጠፈ ብሔር/ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የለም፡፡ መሬት፤ የሞቱ፣ በሕይወት ያሉ እና ገና የሚወለዱ ሰዎች የጋራ ሀብት ነው፡፡ ከአጠቃቀም አኳያ መሬት የሞቱት ሰዎች ዘላቂ ማረፊያ፣ ያሉት መስሪያና መኖሪያ፣ የሚወለዱት መወለጃ፥ መቦረቂያ፥ መማሪያ፥ መስሪያና መኖሪያ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ብሔር/ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የሚባለው “ነገር” ሃሳባዊ ነው፡፡ ብሔር/ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የሚባል ልክ እንደ “ሰው” የሚታይ ወይም የሚዳሰስ፥ ግዝፈት ያለው፥ ቁስ አካል የለም፡፡ የሌለ ነገር ደግሞ ባለ መብትና የንብረት ባለቤት ሊሆን አይችልም። የንብረት ባለቤት መሆን የሚችለው ሰው ብቻ ነው፡፡ እናም የምናወጣው የመሬት ፖሊሲና ስትራቴጂ እነዚህን ፍሬ ሃሳቦች ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይገባዋል፡፡
ሁለተኛ፡- ከአጭር ጊዜ አኳያ በአዲስ አበባ ያሉ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው ላይ ማፈናቀል መቆም አለበት። ይሁን እንጂ እነዚህ አርሶ አደሮች በረጅም ጊዜ ሂደት ውጤታማ በሆነ ዘመናዊ የከተማ ግብርና ሥራ እንዲሰማሩ በማድረግ ለከተማው ነዋሪ የሚቀርቡ ምርቶችን (ማለትም፡- በእንስሳት እርባታ፣ ከብት ማድለብ፣ ወተት፣ ዶሮና እንቁላል፣ የጓሮ አትክልት፣ ማር፣ ወዘተ.) እንዲያመርቱ በማድረግ ከከተማ አኗኗር ጋር አብሮ በሚሄድ የእርሻ ስራ (Urban Agriculture) እንዲሰማሩ እገዛና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን፣ የአርሶ አደሩ ልጆች እንዲማሩ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ በማድረግ ከወላጆቻቸው በተለየ የስራ መስክ ማለትም በጎጆ ኢንዱስትሪና አግሮ ፕሮሰሲንግ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረግ፡፡
ሦስተኛ፡- የከተማዋ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ በኩል፤ ከተማዋ ለቤት መስሪያ የሚሆን መሬቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ነው። በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ከመሬቱ መነቀል የለበትም እያልን ነው፡፡ ታዲያ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዴት ይፈታ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሦስት ተግባራትን ማከናወን አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፡፡ ይኸውም፡-
(ሀ) አሁን በከተማው አስተዳደር የመሬት ባንክ ውስጥ ያለውን መሬት ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ፣ በኃላፊነት መንፈስ፣ ችግሮችን በቅደም ተከተል (Priority) በማስቀመጥ ሥራ ላይ ማዋል፡፡ በሪል እስቴቶችና በጋራ ቤት ግንባታ ሂደት ረጃጅም (ባለ20፣ 30፣ 40፣… ወለል) ፎቆች እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጥና ማስፈጸም፡፡
(ለ) የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የደቡብ ክልሎችን በማነጋገር ከአዲስ አበባ እስከ 150 ኪሎ ሜትር ዙሪያ መለስ (Radius) ርቀት ባሉ ትንንሽ ከተሞች ወይም ምንም ዓይነት መንደር በሌለበት ስፍራ አዳዲስ ከተሞችን ለመመስረት የሚረዳ መሬት ከክልሎች በሊዝ በመግዛት የኮንዶሚኒየምና የሚከራዩ ቤቶችን መስራት፣ አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላትና ከአዲስ አበባ የሚነሱ የባቡር ሐዲዶችን በመዘርጋት የቤት ችግርን መቅረፍ ይቻላል፡፡ የመሬት ሊዝ ዋጋውን ለክልሎቹ በጥሬ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ከተሰሩት ቤቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለክልሎች በመስጠት በዚያ የሚሰፍሩትን ሰዎች ማሰበጣጠር፡፡ በአዲሶቹ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች በፈጣን ባቡር ጧት አዲስ አበባ ሄደው፣ ሲሰሩ ውለው ማታ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣
(ሐ) የአዲስ አበባን የመኖሪያ ቤት ችግር ያባባሰው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ዜጎች ናቸው፡፡ የሀገሪቱን ዜጎች ወደ ዋና ከተማችሁ መጥታችሁ መኖር አትችሉም ማለት ደግሞ አይቻልም። ስለሆነም፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ሁለት ነገሮች ቢደረጉ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኸውም፡- 1ኛ) የክልልና የዞን ከተሞች አዲስ አበባ ያላት ነገር ሁሉ እንዲኖራቸው በማድረግ ለየአካባቢያቸው ህብረተሰብ ምቹና ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆኑ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ፣ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሰውን ዜጋ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ፣ 2ኛ) አዳዲስ በሚመሰረቱት ከተሞች ልክ እንደ ቫቲካን ሲቲ በአነስተኛ ዋጋ (በ100፣ 200፣… ብር) የሚከራዩ የድጎማ ቤቶችን በመስራት ማከራየት፡፡ ይህም ብዙ ሰዎች በአነስተኛ ገንዘብ ዘላቂ መጠለያ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ቤት የመስራት ፍላጎትን ይቀንሳል፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ህይወት ዋስትና ያገኛል፡፡
ክቡር ሆይ!
በመጨረሻ አንድ ነገር ልበልና ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነዋል፡፡ ይህንን ስልጣን ከያዙ በኋላ የኦሮሞነት ኮፍያዎን አውልቀው የአዲስ አበቤነትን ካባ መደረብ ይጠበቅብዎታል፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት…” ማለት አንዳንድ የጨፌ ሰዎችን ለማስደሰት ካልሆነ በስተቀር አግባብነቱ አይታየኝም፡፡ ቀን ቀን “ከንቲባ” ማታ ማታ “ኦቦ” መሆን ጠንካራ አቋም እንዳይኖርዎት ያደርግዎታል፡፡ ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት እንደማይቻል ሁሉ፤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ የኦሮሚያ ጠበቃ መሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሁለት አንዱን መምረጥ ግድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ሀገራዊ ገጽታ ይዞ እንዲጠናከር ማድረጉ ቀዳሚ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ ኦቦ ለማ እና ዶ/ር ዐቢይ እየሄዱበት ያለው መንገድም ይኸው ይመስለኛል፡፡
በከንቲባነት ዘመንዎ ዋና ተግባርዎ መሆን ያለበት የአዲስ አበባና የአዲስ አበቤው ጠበቃ መሆን ነው፡፡ እናም፤ ከላይ የጠቃቀስኳቸውንና ሌሎች አማራጮችን ሥራ ላይ በማዋል የአዲስ አበቤውን መብት፣ ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እንዲያደርጉ ልመናዬን አቀርባለሁ፡፡
አዲስ አበቤው ደግሞ የሰለጠነ የከተሜነት ባህሪውን ጠብቆ፤ ለመንግስት ፖሊሲዎች ተፈጻሚነት እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ልምዱን ሳይሰስት ሥራ ላይ ማዋል ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባው መገንዘብ አለበት እላለሁ፡፡ በእኔ በኩል ለከተማችን እድገትና ልማት ያለኝን እውቀት፣ ልምድና ጊዜ ጭምር መስዋዕት ለማድረግ ቃል እገባለሁ! ምንጊዜም አክባሪዎ!

Filed in: Amharic