>
10:01 am - Saturday November 26, 2022

ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና ለደጋፊዎቹ !!!  (አፈንዲ ሙተቂ)

ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና ለደጋፊዎቹ !!!
 አፈንዲ ሙተቂ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንባሩ ከህወሓት ጋር ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት መስርቷል እየተባለ እየታማ ነው። ይህ ትክክል ያልሆነ የጠላት ወሬ ነው እያልን ስናስተባብል ቆይተናል። በእርግጥም ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነትና መብት ለአርባ አምስት ዓመታት በጽናት ሲታገል የቆየው ኦነግ በአጭበርባሪነቱ ከሚታወቀው ወያኔ ጋር ተስማምቶ ራሱን ወደ ተላላኪነት ደረጃ ያወርዳል ብሎ ማሰብ በጣም ይከብዳል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶሻል ሚዲያው ላይ የምናየው ነገር በጣም እያደናገረን ነው። በተለይ ወያኔ በፌስቡክ ላይ ያሰማራቸው ተላላኪዎቹ ኦነግንና መሪውን ከልክ በላይ እያደነቁ የኦዴፓ መሪዎችን ሲወነጅሉ ማየት ብዙዎችን ለጥርጣሬ የሚጋብዝ ሆኗል። በተጨማሪም አሉላ ሰለሞንን የመሳሰሉ በወንጀል የሚጠረጠሩ ማጅራት መቺዎች ONN በተሰኘው ጣቢያ በተደጋጋሚ ጊዜያት መቅረባቸው ነገሩን እያወሳሰበው ይገኛል።
እኛ ኦነግን የኦሮሞ ብሄርተኝነት አባት ነው ብለን ስንከራከርለት የነበረው አባቶቻችን የመሠረቱትና የታገሉበት ግንባር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ትግልን በሚጎዱ ተግባራት ላይ ይሰማራል ብለን ስለማንጠብቅ ጭምር ነው። በተለይ ግን በ1992 (እኢአ በ1984) በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ወንጀል በፈፀመው እና የኦነግን ስም ለማጥፋት ሲል በበደኖ እና በአርባ ጉጉ ከባድ የጦር ወንጀሎችን ከፈፀመው ወያኔ ጋር ስውር የሆነ ግንኙነት ይፈፅማል ብለን በፍጹም አንገምትም።
ወያኔ በኦነግ ጦር ውስጥ ሰርጎ ገብቶ የፈፀማቸው ወንጀሎች እስከ አሁን ድረስ አልተረሱንም። ገመቹ፣ መቶ አለቃ ቦንሳ እና በከልቻን የመሳሰሉት የወያኔ የውስጥ አርበኞች ለኦሮሞ ህዝብ የሚታገሉ እየመሰሉ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላትን ያለ ጥፋታቸው ሲረሽኑ እንደነበር እስከ አሁን ድረስ እናውቃለን። ኤባ የተባለው የወያኔ ድርብ ሰላይ (double agent) የሰራው ግፍ ከገለምሶ እስከ ፊንፊኔ ድረስ የተነገረለት ነው። ፎዚያ (ከዶ) የተባለችው ድርብ ሰላይ ደግሞ ለኦነግ መረጃ የምታቀብል መስላ ለኦነግ ጦር የተሳሳተ መረጃ እየሰጠች ብዙዎችን ካስጨረሰች በኋላ ተነቅቶባት ኦነግ ራሱ እርምጃ ወስዶባታል። በቅርብ ዘመን እንኳ ግርማ ጥሩነህ የተባለው የወያኔ ምንደኛ የኦነግ አባል ነኝ እያለ ምን ዓይነት ጥፋት ሲፈፅም እንደነበረ በደንብ እናውቃለን። እነዚህን ሁሉ ጥፋቶች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የፈፀመው ህወሓት የተባለው አሸባሪ ቡድን ነው።
ታዲያ ይህ ሁሉ ጥፋት ተረስቶ ኦነግ ከህወሓት ጋር የጋራ ግንባር ይፈጥራል ማለት ለእኛ የማይታመን ነው። ኦነግ እንዲህ ይለከሰከሳል ብሎ ማሰብም በፍፁም የማይቻለን ነው። ነገሩ እውነት ነው ብለንም አናምንም። በመሆኑም ነበር ባለን አቅም ሁሉ ነገሩን “ውሸት ነው” እያልን ስናስተባብል የቆየነው።
ከዚህ በኋላ ግን ኦነግ ራሱ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጠን እንሻለን። ግንባሩ ከወያኔ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በይፋ ማስታወቅ አለበት ብለን እናምናለን። ONN የተባለው ሚዲያም እንደሚባለው በኦነግ ባለቤትነት ስር የሚገኝ ከሆነ አሰራሩን ማስተካከል አለበት። በተለይም የኦሮሞ ህዝብ ጥቅምን የሚጎዳ ማንኛውንም ዘገባም ሆነ ሪፖርታዥ ማቅረብ የለበትም።
እኔ አፈንዲ “የኦነግ ጦር ትጥቁን ይፍታ” የሚል ዘመቻ በሶሻል ሚዲያው ላይ በተከፈተበት ወቅት “Kabajaan Shiftaaf godhaamaa ture WBO hanqachuu hinqabu” የሚል ጽሑፍ ጽፌ ለጦሩ ያለኝን ክብር ገልጬ ነበር። ONN የተባለው ሚዲያም ጽሑፉን አስተላልፎታል። ታዲያ ያንን ጽሑፍ ያቀረብኩት WBO ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ሲታገል የኖረ ሐቀኛ ጦር ነው ብዬ ከልቤ ስለማምን ነው። የወያኔ ተላላኪዎች ግን ይህንን ጦር “አሸባሪ ነው” ሲሉት ነበር የኖሩት።
ዛሬ እነዚያ ተላላኪዎች 180 ዲግሪ ተገልብጠው አሸባሪ ሲሉት የነበረውን የኦነግን ጦር ማድነቅ ሲጀምሩ ሁሉም ነገር ተደነጋግሮብናል። ስለዚህ ግንባሩ ከህዝብ የሚቀርበውን ቅሬታ ተቀብሎ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 8/2011
Filed in: Amharic