>
10:49 pm - Tuesday July 5, 2022

በመቀሌ የዋንጫ ጨዋታው ተጀምሯል!!! አሮጊቷ ህወሓት Vs ወጣቱ ዓረና!!! (ዘመድኩን በቀለ)

በመቀሌ የዋንጫ ጨዋታው ተጀምሯል!!!
አሮጊቷ ህወሓት Vs ወጣቱ ዓረና!!!
ዘመድኩን በቀለ
• በትግራይ መጪው ጊዜ ለዓረና ብሩህ ይመስላል!
 
• በመቀሌው ደርቢ ህወሓት በገዛ ሜዳዋ ነጥብ መጣል ጀምራለች!
አሮጊቷ የጁቬ ዶቼ የልጅ ልጅ ባንዳዋ አጅሪት ህወሓት በንፁሁ የትግራይ የፖለቲካ ተጫዋች ክፉኛ መጠብጠቧ ተነግሯል። 
ወዳጄ ልቤ ፦ 
• ነገሮች ሁሉ ከሸማኔ መወርወሪያ በላቀ ፍጥነት ወደ ፍጻሜ እያመሩ ይመስላል። አንድ ሰው ይረገዛል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ በመጨረሻም ይሞታል። የፖለቲካ ፓርቲም እንደዚያው ነው። በመጀመሪያ በተወሰነ ሰው አእምሮ ይጠነሰሳል። ብዙ መሳይ ጓደኞቹን ያስረግዛል። ከዚያ ፓርቲው ይወለዳል። ያድጋል። አርጅቶ ይሞታል።
ህወሓትም ይሄ እጣ እየገጠማት ያለ ይመስላል። ህወሓት  በአንድ ዐማራና በ7 የኢትዮጵያ ትግሬና የኤርትራ ትግሬ በሆኑ ጥቂት ትምህርት ጠል በነበሩ የ60ዎቹ አጋማሽ ጎረምሶች፣ ደደቢት በተባለ የትግራይ በረሃ ውስጥ ተፀንሶ በሻአቢያ አዋላጅነት ተወለደ። የህጻንነቱን ወራትም በዚያው በበረሃ አሳልፎ ለአቅመ አዳም ደረሰ። በበረሃ ሳለ የበረሃ ሰይጣን አግኝቶት እንደሁ አይታወቅም የወጣትነት ዘመኑን የመንግሥት ባንኮችን፣ የልማት ድርጅቶችን፣ የትግሬ ገበሬዎችን ሃብትና ንብረት በዘርፍ አሳልፏል። የተንቤንና የወልቃይት፣ የራያን እንዲሁም የኢሮብ ተወላጆችን እያረደም ጊዜውን አሳለፈ።
ለአቅመ አዳም በደረሰ ጊዜም በህገወጥ ጋብቻ፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን፣ የተባሉ የምርኮኛ ልጆችን አግብቶ ወለዳቸው። በአሜሪካና በዐረቦች እርዳታም በሻአቢያ ፊትአውራሪነት ደርግ የተባለ የኢትዮጵያ ባል የነበረን ወታደር አስወግዶ የአባወራነቱን መንበር ተቆናጥጧል።
ህወሓት መንበረ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረም በኋላ በህገወጥ መንገድ በርካታ ልጆችን ከህጋዊ ጋብቻ ውጪ ሲፈለፍል ኖሯል። ሶህዴፓ፣ አህዴፓ፣ ቤኒዴፓ፣ ጋህዴፓ፣ ከሃደሬው፣ ከስልጤው እየተኛ ፈልፍሏል።
ህወሓት መንበሩን ከተቆጣጠረች በኋላ አብሮ ያደገ አጋንንትና ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንደሚባለው በበረሃ የጀመረችውንና የኖረችበትን ዝርፊያ እና ግድያ አጠናክራ በሰፊው ቀጥላበታለች። ስግብግብ ስለነበረች በዝርፊያው ልጆቿን እንኳ አታሳትፍም ነበር። እናም ይህቺ ስግብግብ አሁን በስተመጨረሻ ነውሯ ተገልጦ፣ አቅምም አጥታ በስተመጨረሻ ወደ ነበረችበት ወደ ቀደመ ቤቷ ወደ ምድረ ትግራይ ተመልሳ በዚያም የቁም እስር ታስራ የተራሰ ልጧን፣ የተማሰ መቀበሪያ ጉድጓዷን እየተመለከተች በስጋት ተቀምጣ አለች።
ለክፉ ቀን ብላ ያስቀመጠቻቸው በሙሉ እየከዷት መምጣታቸው ታይቷል።
* ቁጥር አንድ ትመካበት የነበረው የሶማሌው የመብራት ግንድ ተሸካሚ የነበረው አብዲ ኢሌ ድራሽ አባቱ ጠፋባት።ብዙ ጮኻ ተንፈራግጣም ልታስጥለው ብትሞክርም አልቻለችም። አልሆነላትምም።
* በብአዴን ውስጥ ያስቀመጠቻቸው፣ በኦህዴድና በደኢህዴንም ውስጥ የሰገሰገቻቸው ተመንጥረው እየተለቀሙ አጎደሏት።
* ጋምቤላን በቁሙ ተነጠቀች።
*  ውርውር ዊኒጥ፣ ዊኒጥ ያለችበት ቤኒሻንጉልም ተነፈሰ።
* የመጨረሻ ምሽጓ የነበረው የዐፋር ፓርቲም ሰሞኑን ሙሉ ለሙሉ ተፐወዘ። አከተመ።
የመጨረሻ ዕድሏን ለመጠቀም ቅማንትን ብትጠቀምም በጥቂት የዐማራ ሚኒሻና የገበሬ ጦር አፈር ከደቼ በልተው አሳፈሯት፣ ብሯንም አቀለጡት። አሁን ህወሓት መቀለ ከትማለች። አክሱም ሆቴል ውስኪ እየጠጡ ሱሪያቸው ላይ በሚሸኑ መሪዎቿ የመጨረሻ የሞት ሽረት ለማድረግ እየጣረች ያለ ይመስላል።
አብርሃ ደስታ የዐረና ሊቀመንበር ነው። መቀሌ ሳለ የአዲስ አበባን የለውጥ አየር ስላልተመለከተ ዳግማዊ ህወሓት መስሎ መንበጫበጭ አብዝቶ ነበረ። ብዙ የዓረና ጀግና ወጣቶች የህወሓት ፎቶ ኮፒ መስለው ለተመልካች አስቸግረው ነበር። ብዙ የህወሓት ካድሬዎችም ዓረናና ህወሓት የተዋሃዱ እስኪመስላቸው ድረስ ተጭበርብረው ድጋፋቸውን ለዓረና መስጠት ጀምረውም ነበር።
የዓረናው አብርሃ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት ለስብሰባ ተጠራ። ከአቢቹም ጋር ረዘም ላሉ ሰዓታት መከረ። አብርሃና አቢቹ ምን እንደተባባሉ ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ አንድም ሰው የለም። ብቻ አቢቹ ለአብርሃ ደስታ ምን እንዳሳየው፣ ምንም ቃል እንደገባለት፣ ምንም እንዳስነካው የታወቀ ነገር ሳይኖር አብርሃ ገና እግሩ ከቤተመንግሥት እንደወጣ ወዳጁ ህወሓት ላይ የጭቃ ጅራፉን ያዘንበው ጀመር። ብዙዎችም ደነገጡ፣ ተቆጡም። አብርሃ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ ሆኖ አረፈው።
አሁን በመቀሌ ዙሩ ከርሯል። የትእምት ተቀጣሪ ትግሬዎች የእንጀራ እናታቸው የህወሓት ሞቷ ታይቷቸዋል። መቀበልና ማመኑ ብቻ ነው የቸገራቸው። ለቅሶ ያበዛሉ፣ ይነጫነጫሉ፣ ይሳደባሉ። ያለፈውን ዘመን ሰርተው ሳይሆን ሰርቀው በነፃነት ይበሉ የነበረበትን ዘመን እያስታወሱ እንደ እብድም ያደርጋቸው ጀምሯል። ሂልተንና ሸራተን ናፍቆታቸው ከሆኑ ሰነባበቱ። ድሮ እኮ ይሄን ጊዜ እያሉ መተረት ከጀመሩ 8 ወር እየሆናቸው ነው። ወይ ጊዜ ደጉ ስንቱን አስተነፈሰ?
አሁን ህወሓት እንደቃሪያ ተሰንጋለች። እነ አቦይ ፀሓዬ ሻአቢያን ማሪን እያሉ በአደባባይ ቢያለቅሱም አይተ ኢሳያስ ክላ ብሎ ዘግቷቸው የስኳር መጠናቸውን ጨምሮባቸዋል።
 ኦነግንና ጀዋር መሃመድ እግር ላይም መደፋት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በአባዱላ በኩል ጃዋር በኃይለኛው ተይዞላቸዋልም ይባላል። ሱዳንም ከዐቢይ ጋር አዲስ ፍቅር ውስጥ መሆኗ ይታወቃል። ሐራ መሬቶቿን በሙሉ ተነጥቃ መቀሌ በሆቴል ውስጥ ከመሸገች ሰንበትበት ብላለች። ቢቸግራት በትግራይ ቲቪ ትጠየፈው በነበረው የአማርኛ ቋንቋም ፕሮግራም ጀመረች። ወፍ ግን የለም።
አሁን ጨዋታው እዚያው መቀሌ ሄዶላታል። ባለፈው ሳምንት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የግጥሚያ ሜዳ ላይ ግሩም የሆነ ጨዋታ ለማየት በቅተናል። በዐማራ ክልል የኤርትራ አምባሳደር የነበረውና ለህውሓት ፈርሞ በዐማራ ማልያ ዐማራ ላይ ግብ በማስቆጠር ይጫወት የነበረው አይተ በረከት የመሃል ዳኛ ነበር። የቀኝ ዳኛው የራያ ዐማራውና ህወሓትን ዶግ አመድ አድርጎ ቀስበቀስ የሚያፈራርሳት “የእኔ የብቻዬ ያልተዘመረለት ጀግናዬ ” ጌታቸው ረዳ ነበር። ” ደንቆሮዎች ” እያለ የሚገዛቸው ምርጥ የራያ ዐማራ እኮ ነው ጌች። ዛሬ ላይ ክብሩ ባይገለጥ ነገ የጌታቸው ረዳ ክብር መገለጡ እንደሁ አይቀር።
ጨዋታው ተጀመረ። ዳኛው አይተ በረከት ” ትግራይን ጠባብ ብሔረተኞች በአንድ ድንኳን የተሰባሰቡባት ” ናት ብሎ የጭቃ ጅራፉን ዘረገፈባቸው። የራያው ዐማራ ጌታቸው ረዳም ” ኢህአዴግ ምሑር የሚባል አልነበረውም ” በማለት የእነ ዶክተር ደብረ ጽዮንን ዶክትሬት አፈር ከድሜ አስግጦ አረፈው። በጨዋታው ላይ እንደእነ አቶ አየለ ጫሚሶ ዓይነት የማደጎ ልጆችም ነበሩ። የተቋረጠባቸውን የጡረታ ገንዘብም ለመቀበል የሄዱም ይመስላል።
አረጋዊው አይተ ስብሃትም ተናገረ። አቢቹን መርጠው የሾሙት አማሪካኖቹ ናቸውም አለ። አቶ አያ ያማማቶ የአቢቹ ዋነኛ ሿሚ እንደነበሩና አቶ በረከትም ተቃውመው እንደነበር አስረግጠው ተናገሩ። እኛ ስለሌለን ኢትዮጵያ ትፈርሳለችም ብለው ሟርታቸውን አሟረቱ። ሞርቱ ወዪ አለ ኦሮሞ።
በመጨረሻም የህወሓትን ዙፋን በቅርቡ የሚረከበው የዓረናው ተመላላሽ አጥቂ ከነ ሙሉ ትጥቁ ወደ መጫወቻ ሜዳ ገባ። የቡድኑ መሪም ራሱ ወጣቱ ዓምዶም ገብረሥላሴ ነበር። ዓምዶም ንግግሩን ከስደተኛውና መቐሌ የስደተኞች ጣቢያ ከተጠለለው ከአይተ በረከት ጀመረ። እንዲህም አለ።
• እርስዎ (አቶ በረከትን መሆኑ ነው) ከስብሐት ነጋና ከአቶ መለስ ጋር ሆነው ” ትግራይ ብቻዋን እየለማች ነው!” ብለው ጽንፈኝነት አምጥተውብናል፡፡ የትግራይ ወጣት ቁጭት አለበት፡፡ ዛሬ ላይ ህወሓት ከፌደራል /ከአዲስ አበባ/ ሲባረር ነው፣ ትግራይ እንደሚጠፋ፣ የትግራይ ህዝብ እንዳለቀለት፣ በጠላት እደተከበበ በኃይለኛው እየተቀሰቀሰ ያለው፡፡ ነገር ግን በአንጻሩ ከኤርትራ ጋር ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡ በማለት በመቐለ ከተማ ታይቶም ተሰምቶም የማያው የአጨዋወት ስልት በማሳየት ተጫዋቾቹንም፣ ዳኞቹንም፣ ተመለካቾችንና ታዛቢዎችን ጭምር ማስደመም ጀመረ።
ቀጠለና እንዲህ አለ። “ ሕገ መንግሥት ”መከበርን በተመለከተ፡- ኢህአዴግ ተመርጦ ያውቃል እንዴ? ኮረጆ ሲዘርፍ እኮ ነው የኖረው። በኃይል ነው እስካሁን የቆየው፡፡ አሁን ከፌደራል ስልጣን ስለተባረረ ነው፤ በራሱ ሲደርስ ነው ይሄ ሁሉ ጫጫታ የበረታው፡፡ ምርጫ ሲጭበረበር ነው የኖረው፤ በዳኝነት ላይ ጣልቃ ሲገባ ነበር፡፡
እንኳን ሕገ መንግሥት፣ ህወሓት የራሱን ሕገ ደንብ አክብሮ አያውቅም፡፡ ልዩነቱ፣ አሁን በትግራይ ያለው የህወሓት አመራር ከፌደራል ስልጣን ስለተባረረ፣ እንደ አዲስ ነገር ተደርጓል፡፡ እዚህ ያለው አመራር፣ “#አንጃ! #አሸባሪ!” ሲል የነበረ ነው፡፡ እንጂ በዚህ 27 ዓመት ሕገ-መንግሥት አልተከበረም፤ ዴሞክራሲ አልነበረም፡፡ በማለት የጫዋታውን ዙር በሽማግሌዋ ላይ አጦዘው።
ቀጠለናም ትንታግ የሆነው ወጣቱ ዓምዶም “የትግራይ ሕዝብ እና ህወሓት አንድ እንደሆኑ ይገለጻል፡፡ እንዴት ሆነው ነው አንድ የሚሆኑት? ድኻ ኅብረተሰብ፣ የሚበላ የሚጠጣ የሌለው ሕዝብ እና በትግራይ ህዝብ ስም በቢሊየን ብር የሚያንቀሳቅስ ባለስልጣኖች እየተጠቀሙበት እንዴት ብሎ ነው አንድ የሚሆኑ? አሁንም ትግራይ ሕዝብ በድህነት ላይ ነው ያለው፤ አሁንም በስደትና በጉስቁልና ላይ ነው ያለው።” በማለት ለዘመናት ብዙዎች በትግራይ ስም ሆነው ለትግራይ ህዝብ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩበት የነበረውን ጫማ አጥልቆ ኳሷን መሾር ጀመረ።
አሁን የእነ አቦይ ስብሃት ቡድን ትእግስቱ ተሟጠጦ ማለቅ ጀመረ። እናም በማያውቁት የጫወታ ስልት ብዙ ጎል ተቆጥሮባቸው ጌሙን በዝረራ ከመቋጨታቸው በፊት ከልጅነት ጀምሮ በለመዱት የጨዋታ ስልት ተከሰቱ።
• የአቦይስብሐት ቡድን፡- ጨብጭበጭ…ብብብ… በማለት ዓምዶምን አስደንብሮ ለማስቆም ሞከረ። ዲሞክራሲን በአፍ እንጂ በተግባር የማያውቀው የህወሓት ገመና መገላለጥ ጀመረ። ህወሓት አዲስ አበባ እያለ ከሚሳኤል ይልቅ ብዕር የሚፈራ ድንጉጥ ነበረ። እስክንድር ነጋን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ ውብሸት ታዬን ክላሽ ታጥቀው አይደለም ያሰራቸው። ብዕር ስለጨበጡ እንጂ። ያለ ልማዱ በ1997 ዓም በንግግር ልሞክር ብሎ እነ ብርቱካን ፣ እነ ዶር ብርሃኑ፣ እነ ዶር መራራ ውኃ ውኃ አስብለው አፈር ከደቼ ሲያስግጡት ጊዜና ደንግጦ የሞት ፍርድ እንዳስፈረደባቸው ይታወሳል። አሁን ያ ጨዋታ መቐለ ከተማ ከሳሎናቸው ድረስ በዓረናዎች አማካኝነት ሰተት ብሎ ከተፍ አለላቸው።
• ስደተኛው ዳኛ አይተ በረከትና ጌችዬ፣ ጌችነት፣ ጌቾ ፡- አንዴ! አንዴ! ቆይ ይጨርስ… አንዴ ይጨርስ… አለ። በተለይ ጌቾ ህወሓትን ልኳን የሚያገባለት ሲያገኝ ደስታው ነው። ህወሓት ከመለስ ሞት በኋላ ምላሳም ሰው ማጣቷ እንደጎዳትና ችግር ላይ እንዳለች ጌታቸው ረዳ ጠንቅቆ ያውቃል። አቶ መለስ ምላሱን እንኳ ሳያስቀምጥላቸው እኮ ነው ወደ አፈር የወረደው።
• የዓረናው አይተ ዓምዶም ፤ ቆይ እንጂ ሃሳቤን ላጠቃልል… አስጨርሱኝ….
• እነ አይተ ስብሐት፡-ጨብጨብጨብብብብ…ጨብጨብ… ቡኡኡኡኡ … …
• አብዛኛው ህዝብ ግራ ተጋባ። ገልመጥመጥ ዞር ዞር፣ እያለ ማየትም ጀመረ።  የሌባው ቡድን ጉዱ ፈላ። በትግራይ ህዝብ ስም ቆማሪዎቹም ጨነቃቸው። ሳቅቅቅ…ቂቂቂቂ…ሃሃሃሃ…
• የዕለቱ ምርጥ ተጫዋች የዓረናው አጥቂ ቀጠለ እንዲህም አለ። “እኔ እኮ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኮንፈረንስ መስሎኝ ነበር፤ የህዋሓት ወሬ እንዳለው አልገባኝም ማለት ሲጀምር ማይኩ ተቋረጠ። የደጋፊዎች ረብሻ ቀጠለ። በመቀሌ ግጥሚያ ብዙ ጊዜ ረብሻ ቢኖርም በካሜራ እንዲቀረጽ ግን አይደረግም ነበር። አዲግራቶች መቀሌ ሄደው አፈር ከደቼ ግጠዋል። ባህርዳር ከነማ፣ ፋሲል ከነማም የጦርነቱ ዕጣ ገጥሟቸው ያውቃል። የዛሬው የዓረናና የህወሓት ግጥሚያ ግን ከፉጨትና ከማጉተምተም፣ ከጭብጨባ በቀር ተነስቶ የተደባደበ የለም።
ህወሓት እንዲያ ለማድረግ አሁን ዕድሜዋ አይፈቅድላትም። አርጅታለች። ድሮ ቢሆን ሲጀመር ቀድሞ ነገር ዓምዶምንም አይጠሩትም። አይጋብዙትምም። መጥቶ ግን እንዲህ ቢናገር ባዶ ሽድሽተ ዕጣ ፈንታው ይሆን ነበር።
ህወሓት አሁንም በ84 ዓመቱ ሽማግሌ አምበልነት ነው ለግጥሚያው ወደ ሜዳ የገባችው። አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና ዶር ደብረ ጽዮንም የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው። እናም ህወሓት በዚህ ስብስብ በቅርቡ ትሸነፋለች።
በሰፊ ሜዳ ላይ ዶሮን አባርሮ ለመያዝ ያስቸግራል። በሰፊ ሜዳ ላይ ዶሮን አባርሮ ለመያዝ መሞከር ትርፉ ድካም ነው። ዶሮን ለመያዝ ቀስ እያሉ እያሳሳቁ ወደ ኮርነር ጥግ መግፋት ነው። ያን ጊዜ ዶሮን በቀላሉ መያዝ ይቻላል። ይሄ እኔ የምወደው የነበረው የሌብሮ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጁ የአቶ ገነነ መኩሪያ ፍልስፍና ነበር። ከኢትዮጵያ ቡናው ካሳዬ አራጌ ጋር የፈለሰፉት አዲስ የአጨዋወት ስልትም ነበር።
ለእኔ አሁን ህወሓት እንደ ዶሮዋ ነው የምቆጥራት። በሰፊው በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ ያውም የአብዲ ኢሌን ነዳጅ እየጠጣች፣ የዐማራንና የጋምቤላን ጤፍና ስንዴ እየበላች። በቤኒሻንጉል ወርቅ አጊጣ፣ በኦሮሞ ቅቤ፣ በደቡብ ክትፎ ተወጥራ፣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ላይ ተኝታ፣ በአፋር ጨው እየታሸች እሷን መያዝ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ግን ወደ ኮርነር እየገፏት እንደዶሮ አስጨንቆ መፈናፈኛም አሳጥቶ ለመያዝ የሚደረገው ሙከራ የሚሳካ ይመስለኛል። ኢሱም ህወሓትን ጌም ኦቨር ያለችው ይኸው ገብቷት ነው።
ህወሓትና ዓረና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው የሚሉ ቢኖሩም። መጪው ጊዜ ግን ከዓረና ጋር ለትግራይ ብሩህ ነው የሚሉቱ ይበዛሉ። ቢያንስ ቢያንስ ስለ ህወሓት ክፋት ሌላው ኢትዮጵያዊ ከሚናገረው ራሱ የትግራይ ህዝብ በሚገባው ቋንቋ መነጋገሩ ተመራጭ ነው ባይ ነኝ። አሁን በህወሓት ካድሬዎች አማካኝነት በዓረና ላይ የተከፈተውን ፕሮፓጋንዳ ስትመለከት ደግሞ የሆነ ነገር እንዳለ መጠርጠር ትጀምራለህ። አከተመ።
የዛሬ ወር አብርሃ ደስታና ዓረና ለህወሓት ካድሬዎች ጀግና ነበረ። አሁን ግን ባንዳ ተደርጓል።
የዛሬ ወር በረከት ስምኦን ለህወሓት ካድሬዎች የጀግና ጀግና ነበረ ። ከቅዳሜ ጀምሮ ግን ከትግራይ ይውጣልን ብለው ዘመቻ ጀምረዋል።
ከዛሬ ወር በፊት ዓረና የህወሓት ብርቅዬ ልጅ ተደርጎ ተቆጥሮ ነበረ። ከቤተመንግሥቱ የአብርሃና የአቢቹ የብርቱካን ውይይት በኋላ ግን እንደ ጠላት የተቆጠረ ሆኗል። የሆነ ሆኖ ትክለኛውን ሥዕል በጥራት ለማየት ነገን መጠበቅ የግድ ይሆናል።
ሻሎም !  ሰላም ! 
ታህሳስ 9/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic