>

የወለጋው ገዳይ ማን ነው ? 

የወለጋው ገዳይ ማን ነው ? 
 
ሀብታሙ አያሌው
በማያሻማ ሁኔታ በወለጋ ኦነግ በህወሓት ሸበጥ እየረገጠ ነው። በቅርቡ የአቶ ለማ መገርሳ አስተዳደር በፀጥታ ማስከበር ጉዳይ የፌደራል መንግስት በክልሉ ጣልቃ እንዲገባ ማዘዙ ይታወሳል።  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በንግግራቸው ደግሞ ወደ ወለጋ ሳይሄዱ የቀሩት የሞት መልዕክተኞች ለግድያ የመዘጋጀታቸው መረጃ የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረው እንደነበረ የታወቀ ነው።
መከላከያ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በአገር ውስጥ ትጥቅ ሳይፈቱ በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን ማለቱ አይዘነጋም። ይህ የአገር መከላከያ ሰራዊት አንድም ኃይል ሊከፋፍል የሚችል የውጭ ጦርነት ስጋት በሌለበት ሁኔታ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ታጥቀው ሰላማዊ ህዝብ የሚዘርፉ የታጠቁ ሽፍቶችን ማስቆም አለመቻሉ ለሁላችንም እንቆቅልሽ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
ከትላንት ምሽት ጀምሮ በኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ አንገር ጉቲን አካበቢ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ቡድን “በአማራን አጥቃ”  ዘመቻ  በይፋ አፍና እና ዝርፊያ እየፈመ ነው።  ከህዝቡ ላይ መሳሪያ ይነጥቃል፤ የክልሉ መንግስት ያስታጠቃቸውን  የአካባቢ ሚንሻ ወታደሮች ሳይቀር ትጥቅ እያስፈታ ይገኛል።  እያፈነ የሚሰውራቸው ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ ሲሆን፤  እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ መከላከያም ሆነ የክልሉ ፖሊስና ልዩ ኃይል ከዛቻ የዘለለ እርምጃ ሊወስዱና ለዜጎች ደህንነት ዋስትና ሊሰጡ አልቻሉም።
አስገራሚው ነገር  ህወሓት የተባለው የወንበዴዎች ቡድን 27 ዓመታት የግፍ ቀንበር ሲጭንብን አስመራ ከተማ ሜሎቲ ከመጠጣት የተሻገረ አንድም ጊዜ ድምፁ ተሰምቶ የማያውቀው ቡድን ዛሬ ህወሓት ከአገር ከዘረፈው ሃብት ደራጎት እየተቀበለ አገር ማመሱን ዋነኛ ስራው አድርጓል።
ወለጋ ላይ በህወሓት ሸበጥ የሚረግጠው ገዳይ ቡድን ዶክተር አብይንም ሆነ አቶ ለማ መገርሳን በሞት ሰይፍ ለመቅጠፍ እያደባ እያደባ መሆኑ የታወቀ ነው። ሰኔ 16 ጠቅላዩን ለመግደል በጋራ የወረወሩት ቦንቦ ከከሸፈ በኋላ እነ ደም ምሱ ባልተቋረጠ ጥረት በየቀኑ የሞት ዜና እያስነገሩ ነው።
የኦሮሚያ ፖሊስም ሆነ ልዩ ኃይል ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ጥሪ አቅርበው እያለ በወለጋ በይፋ ሽፍቶች ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጡ ከህዝብ መሳሪያ እየነጠቁ ሲደራጁ በዝምታ ተመልክቶ የዜጎች ህይወት ሲቀጠፍ በመግለጫ መፎከር  ተቀባይነት የለውም።
አባ ገዳዎች የአገር ሽማግሌዎች እና የሐይማኖት አባቶች የዚህን ሽፍታ ቡድን እንቅስቃሴ በይፋ በማውገዝ ከመንግስት ጎን መቆማችሁን በመግለፅ ጥርብቅ እርምጃ እንዲወሰድ በማሳሰብ ከዚህ በላይ ሳይረፍድ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንደ አንድ ዜጋ እማፀናለሁ።
Filed in: Amharic