አማራ የፈላታ (Fellata) ማኅበረሰብ በአልጣሽ ፓርክ፤ቋራ
ውብሸት ሙላት
ኢትዮጵያ ዉስጥ ስለሚኖሩት የናይጀሪያ ዘላን አርብቶ አደሮች ለማዉጋት በቀጠሯችን መሠረት መጥተናል፡፡ ይህ ነገር ለሰሚዉ ግራ እንደሚሆን ይገባኛል፡፡ እኔም በአንድ ወቅት ግራ ገብቶኝ ምን ትኩረት ሳልሰጠዉ አልፌዉ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነበር፡፡ ኤልቲቪ ላይ ሰፊዉ ምህዳርላይ ዉይይት እያደረግን ሳለ በመካከል አንዱ፣ እግረ መንገዱን “ኢትዮጵያ ዉስጥ እኮ ናይጀሪያዊ ከብት አርቢዎች መጥተዉ ሲኖሩ መንግሥት ምንም እርምጃ አልወሰደም” አለ፡፡
እኔ ደግሞ በልቤ ይቃዣል ወይስ ካርታ አያውቅም አልኩ፡፡ በእኔ ቤት መቼም እዉነት ሊሆን ይችላል ብዬ ማሰብም አልፈለግኩም፤ለማጣራትም አልሞከርኩ፡፡ ምክንያቴ ደግሞ በናይጀሪያና በኢትዮጵያ መካከል ቢያንስ ቻድና ሱዳን፤ሲበዛ ካሜሩን፣ቻድ፣ማዕከላዊ አፍሪካ ከዚያም ሱዳንን ማቋረጥ ያስፈልጋል፡፡ እንዴት ይህ እውነት ይሆናል ብዬ ልገምት? ለማንኛዉም እውነት ነዉ፡፡ ከወራት በኋላ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 18ኛ ፎረም ወሎ ዩኒቨርሲቲ ላይ ሲካሔድ እኔም ታዳሚ ነበርኩና በመድረኩ ላይ ስለ አልጣሽ ፓርክ አንድ ጥናት ቀርቦ ስለነበር በዚያ ምክንያት ከእንደገና ሰማሁ፤አጣራሁ፡፡ መረጃዎቹንም ይዠ ትንሽ ኢንተርኔት ላይ ፍተሻ አደረግኩ፡፡ እነሆ!
ፈላታ ዘላን ከብት አርቢዎች በኢትዮጵያ
******************
ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በኋላ፣ በአካባቢዉ የፈላታ ማኅበረሰብ በነጻነት እንዲገቡም እንዲኖሩም ተፈቀደላቸዉ፡፡ ይባስ ብሎም በ1984 ዓ.ም. ከቋራ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተስማማተዉ እንዲኖሩ ተፈቀደላቸዉ፡፡ የቋራ ሕዝብ ተገድዶ እንደ ዐይኑ ብሌን በሚጠብቀው አልጣሽ ደን ዉስጥ በነጻነት መኖር ጀመሩ፡፡ ፈላታ ድንበር ዘለል ዘላን ከብት አርቢዎች ናቸዉ፡፡
የፈላታዎቹ በዘመነ ኢሕአዴግ
ፈላታዎቹ ከቋራ ሕዝብ ጋር ድሙር በምትባል ቦታ ላይ በ1984 ስምምነት ሲያደርጉ ከብት ላይዘርፉ፣በደኑ ዉሥጥ የሚኖሩ ከብት ሲያገኙ የሚቀላቀሉ ጎሾች ስላሉ እንሱን እንዳይገድሉ ስምምነት አድርገዉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወያኔ ያጠገበቻቸዉ ፈላታዎቹ በ1986 ዓ.ም. ጎሾቹንም ገድለዉ ሕዝቡ እንዲያቸዉ አደረጉ፡፡ የቋራ ሕዝብ ምንም ዓይነት ጥበቃ እንዳያደርግ በወያኔ ተከልክሏል፡፡
ፈላታዎች ጋምቤላም አካባቢ አልፎ አልፎ ብቅ ይላሉ፡፡ ስለ ጋምቤላ የጸጥታ ሁኔታ የተሠሩ ጥናቶችን ላገላበጠ ይሔንኑ ይረዳል፡፡ ከቋራ ወረዳ በስተደቡብ (ቀድሞ የቋራ አካል የነበረዉ) አሁን “አዉጀሚስ” ተብሎ በሚጠራዉና በመተክል ዞን ሥር በሚገኘዉ ክልላዊ ፓርክ አጠገብም ይገኛሉ፡፡ እዚህ አካባቢ ላይ በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሰፋፊ የእርሻ መሬት የወሰዱ ሰዎች ናቸዉ የሚኖሩት፡፡ ከትግራይ ባለሃብቶቹ ጎን ፈላታዎች ይኖራሉ፡፡
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ዉሥጥ ስለሚኖሩት ፈላታዎች ጉዳይ ልመለስ፡፡ አልጣሽ ፓርክ አጠቃላይ ስፋቱ የአዲስ አበባን አምስት እጥፍ እንደሚሆን እናስታውስ፡፡ የአዲስ አበባ ስፋት 527፤ የአልጣሽ ደግሞ 2665 ስኩየር ኪሎ ሜትር ነዉ፡፡
በአልጣሽ ትይዩ ሱዳን ዉሥጥም ፓርክ አለ-የድንደር ፓርክ፡፡ ፈላታዎቹ ድንደር ፓርክ መግባት አይፈቀድላቸዉም፡፡ ከብቶቻቸዉም አይገቡም፡፡ ከገቡም የገቡት ከብቶች ግማሾቹን በቅጣት መልክ ለሱዳን ይሰጣሉ፤ወይም ይወረሳሉ፡፡
በድንደር በኩል ወደ አልጣሽ መምጣት አይችሉም፡፡ ሱዳኖቹ የራሳቸዉን ፓርክ ስለሚጠብቁ ፈላታዎች ከሱዳን ተነስተዉ ወደ አልጣሽ የሚገቡት ከድንደር በሰሜን አልያም በደቡብ በኩል አድርገዉ ነዉ፡፡ ከድንደር በስተሰሜን በኩል ወደ አልጣሽ የሚገቡት በ”መብትገበያ” ነዉ፡፡ አባቶቻችን መብታቸዉን (ሕይወታቸዉን) ሽጠዉ አገር ስላቀኑ ስለጠበቁ ነዉ ያ ቦታ መብትገበያ መባሉ፡፡ ወያኔ ከገባች በኋላ ፈላታ እንዳሻዉ እንዲገባ ክፍት አደረገችዉ፡፡ ሁለተኛው፣ከድንደር በስተደቡብ አድረገዉ በኦሜድላ በኩል ወደ አልጣሽ ይገባሉ፡፡
አሁን ላይ 410 አካባቢ የሚሆን የፈላታ ቤተሰብ (Household) አልጣሽ ዉሥጥ በቋሚነት ከብት እያረቡ ይኖራሉ፡፡ ይህ 410 ቤተሰብ በስምንት “ገታ” (በእኛ አጠራር ቀበሌ ማለት ይቻላል) ሥር ይተዳደራሉ፡፡ በአማካይ በአንድ ቤተሰብ ዉስጥ አምስት ሰዉ ቢኖር በአጠቃላይ ወደ 2000 ገደማ ፈላታዎች አሉ ማለት ነዉ፡፡ የከብቶቻቸዉ ብዛት ከ800,000 (ስምንት መቶ ሺ) እስከ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ይደርሳል፡፡
የፈላታ ሕዝብ ኢትዮጵያ ዉስጥ እየኖሩ ግብር የሚከፍሉት ግን ለሱዳን መንግሥት ነዉ፡፡
የፈላታ ማኅበረሰብ እስከአፍንጫቸዉ ድረስ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸዉ፡፡ የጦር መሳሪያም ይነግዳሉ፡፡ ስለ ሱዳን ድንበር አካባቢ የመሳሪያ ዝውውር የተሰሩ ጥናቶችም ለዚሁ አብነት ናቸዉ፡፡
ፈላታ የወያኔ (ሕወሃት) መረጃና መሳሪያ አቀባባይም ናቸዉ፡፡
ፈላታዎች ከቤኒሻንጉል/ጉሙዝ በቋራ እስከ መተማ፣ከመተማ እስከ ጎንደር የሚዘልቅ የወንበዴም የሌባም የኮንትሮ ባንድ ነጋዴም ሰንሰለት እንዳላቸዉ ይነገራል፡፡
ፈላታዎች በጋ በሚሆንበት ጊዜ እንኳን በአልጣሽ ደን ዉሥጥ በስፋት የሚገኘዉን ዓመቱን ሙሉ አረንጓ የሚሆነዉን ላሎ የተባለ ዛፍ በመጨፍጨፍ ይህንን የከብት መንጋቸዉን ይመግባሉ፡፡
አሁን ላይ በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ዉስጥ “አቡኒን” በሚባለዉ አካባቢ እየኖሩ ነዉ፡፡
አልጣሽ በፌደራል መንግሥት ሥር ነዉ የሚተዳደረዉ፡፡ አዲስ አበባን አምስት እጥፍ የሚሆን ፓርክ ሃምሳ በማይሞሉ ጥበቃዎች እንዲጠብቁት ነዉ የታሰበዉ፡፡ ከክልሉ ቁጥጥር ዉጭ አድርገዉታል-የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ላይ ሲቋቋም፡፡ ቋረኛዉ ወገኔ አንጀቱ እያረረ ባእዳን ሲወሩት የፌደራል ሁኗል እየተባለ መሬቱን ለናይጀሪያዉያን አስረክቧል፡፡
እንግዲህ ወያኔ ቢመቻት እኮ የፈላታ ሕዝብ የማንነት ይታወቅልኝ፣የልዩ ወረዳ (ዞን) ጥያቄ እቅርቧል ይሰጠዉ ማለቷ አይቀርም ነበር፡፡
የፌደራል መንግሥት እነዚህን የፈላታ ማኅበረሰብ ከዚህ ፓርክ ዉስጥ በስቸኳይ ማስወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ከፈለጉ ከፓርኩ ወጥተዉ ከሌላዉ ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዉ እንዲኖሩ ማድረግ ካልሆነ ደግሞ ግብር ወደሚከፍሉበት ወደ ሱዳን እንዲመለሱ ማድረግ ነዉ፡፡ ካልሆነ ደግሞ ለሙሃመድ ቡሃሪ በመንገር ወደ ናይጀሪያ ይውሰዳቸዉ፡፡
ስለ አልጣሽ ፓርክ በቅርቡ እመለስበታለሁ፡፡
(መረጃ ምንጮቼን በስምምነት ነዉ ስማቸዉን ያልገለጽኩት፤ምስጋናዬ ግን ወደር የለዉም!)