አቶ አዲሱ አረጋ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ለሰላማዊ ትግል ወደ ሃገር ውስጥ ከገባ በኋላም በተለያዩ የክልሉ ዞኖች ውስጥ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ ነው ብለዋል የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ።
አቶ አዲሱ ዛሬ ጋዜጠኞች ሰብሰበው በሰጡት መግለጫ፤ በኦነግ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል አሥመራ ላይ የተደረሰው ስምምነት ሆን ተብሎ ዝርዝሩ ከህዝብ ተደብቋል የተባለው ከእውነት የራቀ ነው ያሉ ሲሆን፤ የስምምነቱ ተፈጻሚነትም እንደፈለጉት በፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ ተጉዞ ከኦነግ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።
በርካቶች መንግሥት ከኦነግ ጋር አሥመራ ላይ የደረሰውን ዝርዝር ስምምነት ለህዝብ ይፋ አለደረገም በማለት መንግሥትን ይወቅሳሉ።
የኦነግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳም በቅርቡ ለሃገር ቤት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱ ወገን የተደረሰው ስምምነት ለህዝብ ግልጽ እንዳይሆን እያደረገ ያለው መንግሥት ነው ብለዋል።
በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን እና ከኤርትራ የገቡ የኦነግ ሰራዊቶችን በማሰልጠን እንደየ አስፈላጊነቱ የጸጥታ ኃይሉን እንዲቀላቀሉ ወይም በሌሎች መስኮች እንዲሰማሩ ለማድረግ ከኦነግ ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን ያስታወሱት አቶ አዲሱ፤ በሃገር ውስጥ የሚገኙ የኦነግ ወታደሮችን ከኤርትራ ከተመለሱት ጋር በአንድ ላይ ሰልጠና ለማስጀመር ብንሞክርም በሃገር ውስጥ ያሉት ሳይገኙ ቀርተዋል ይላሉ።
በሃገር ውስጥ የሚገኙ የኦነግ ወታደሮች ስልጠና እንዲጀምሩ ለ15 ቀናት ቢጠበቁም ሳይገኙ በመቅረታቸው ከኤርትራ ለመጡት ብቻ ሰልጠና መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
በመንግሥት እና በኦነግ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለማስፈጻም ከሁለቱም ወገን ተወካዮች በተዋቀረው ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ከስምምነት ይደረሳል፤ ተፈጻሚ ግን አይሆኑም ይላሉ አቶ አዲሱ።
የኦነግ አመራር በጠቅላለው ሰላማዊ ትግልን እንደ አማራጭ አድርጎ መቀበሉ አጠራጥሮናል የሚሉት አቶ አዲሱ፤ የኦነግ አመራር እና በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የጦር አመራሮች የሚሰጡት መግለጫዎች የተለያዩ ናቸው ይላሉ።
”ኦነግ በጉጂ፣ ቄለም፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ እና ኢሉ አባቦራ ዞኖች ውስጥ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ ነው ይህም እጅጉን ያሳስበናል” ብለዋል አቶ አዲሱ።
አቶ አዲሱ ጨምረውም ሕገ-ወጥነት እየተስፋፋ ነው፤ አመራሮቻችንም እየተገደሉ ነው ብለዋል።
ትናንት በነቀምቴ ከተማ ውስጥ የጉቶ ጊዳ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪ የነበሩት ግለሰብ መገደላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ የመንግሥት ባለስልጣናትን መግደል፣ የአስተዳደር ስርዓቱን ማፈራረስ፣ ዘረፋ እና ሚሊሻዎችን ጦር ማስፈታት የመሳሰሉ ወንጀሎች በኦነግ ሥራዊቶች እየተፈጸሙ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ከቀናት በፊት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ የደረሰባቸው ጉዳዮች በመንግሥት እየተጣሱ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ መከበር፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አስከባሪ እና ደህንነት አካል ገለልተኛ እንዲሆን ማድረግ፣ የኦነግ ሠራዊት ወደ መንግሥት ኃይል እንዲካተት ማድረግ ከኦነግ ሠራዊት አንፃር ከመንግሥት ጋር የተስማሙባቸው እንደሆኑ አመልክተው እነዚህ ስምምነቶች ግን በመንግሥት እየተጣሱ ነው ብለው ነበር።