>

ዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ በዐማራ ሕዝብ ላይ ያካሄዱት ጭፍጨፋ ሲታወስ!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ በዐማራ ሕዝብ ላይ ያካሄዱት ጭፍጨፋ ሲታወስ! 
አቻምየለህ ታምሩ
ባለፉት ሀያ ሰባት የፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ ዓመታት ውስጥ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን የሚያወግዙ የውሸት ታሪኮችና የፈጠራ ሐውልቶች እንዳሸን የፈሉበት ዘመን ነበር። ከአኖሌ የተቆረጠ እጅና ጡት ሐውልት እስከ ቱርኩ እንደራሴ አሚር ኑር ሐውልት ድረስ በኢትዮጵያ ምድር ያልቆመ ሐውልት የለም። ፋሽስት ወያኔ የግንባታ ኩባንያዎችን ሐውልት ለሚያቆምላቸው ክልሎች በርካታ ሚሊዮን ብር እያስከፈለ እያስገነባና ዳግማዊ ምኒልክን እያሰየጠነ የኔ የሚላቸውን ዐፄ ዮሐንስን ግን ካለፉት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ በላይ አድርጎ ለኢትዮጵያ ያልተማከለ ስርዓትን በመመስረት ረገድ ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ በመስበክ መልአክ ያደርጋቸዋል።
ሆኖም ግን በጭካኔ ረገድ ወያኔ ባለፈው ሰሞን  በመተማና መቀሌ መታሰቢያ ሐውልት ሊያቆምላቸው የመሰረት ድንጋይ የጣለላቸው ዐፄ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ሙሉ የጥላቻ ሐውልት ከቆመላቸው ምኒልክ ጋር ሲወዳደሩ ጥንባቸውን የጣሉ የጨካኞች ጌታ ሆነው እናገኛቸዋለን። በዚህ ጽሑፍ ላለፉት በርካታ አመታት ያልተነገሩትን የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ከሚገባ ዐፄ ዮሐንስ በዐማራ ሕዝብ ላይ ካካሄዷቸው ጭፍጨፋዎችና ወረራዎች መካከል የተወሰኑትን እናቀርባለን።
የጽሑፋችን የታሪክ ምንጮች «የኢትዮጵያ ታሪክ በአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ» በሚል ርዕስ በዶክተር ሥርግው ገላው ዝግጅትና አርትኦት በ2008 ዓ.ም. ለአንባቢ የቀረበው መጽሀፍ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አዘጋጅተዋቸው ካለፉ ከዘመናት በኋላ እንደገና በ1999 ዓ.ም «ኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል» በሚል ርዕስ የታተመውና በ2009 ዓ.ም . ገበያ ላይ ከማለው «ዋዜማ፡ በማግሥቱ የኢትዮጵያን ነገሥታት የታሪክ በዓል ለማክበር» የተሰኙ የታሪክ ድርሳናት፤ ደብተራ ፍስሃ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊስ «ታሪኽ ኢትዮጵያ» በሚል ጽፈውት 1993 ዓ.ም. እንደገና የታተመ መጽሐፍ፤A Chronicle of Emperor Yohannes IV በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ባይሩ ታፍላ ዝግጅትና አርትኦት በ1970 ዓ.ም. የታተመው የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጥንቅር፤ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ «ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጲያ አንድነት» 1982 ዓ.ም. በሚል ያሳተሙትና ዐፄ ዮሐንስ ለልዑል ራስ ዳርጌ የጻፏቸው ደብዳቤዎች ናቸው።
ዐፄ ዮሐንስ በዐማራ ላይ ካካሄዷቸው ጭፍጨፋዎችና ዝርፊያዎች  መካከል አንዱ በጎጃም ሕዝብ ላይ ሁለት ጊዜ ተመላልሰው ያላሄዱት ጭፍጨፋ በዋናነት ይጠቀሳል። የዐፄ ዮሐንስ የመጨረሻው የጎጃም ወረራ  የተደረገው የመተማ ጦርነት ከመካሄዱ ወራት በፊት ሲሆን  ወረራው በኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሥ ወይንም ንጉሠ ነገሥት ነኝ የሚል አካል ሰማንያ ሺህ ሰራዊት አዝምቶ  ለበርካታ ወራት ሕዝብ  ከዳር ዳር  የተጨፈጨፈበት የአፍሪካ ጥቁር ታሪክ ነው። ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ለማጥፋት የተነሱት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በሣር ውሃ ጦርነት ከደርቡሽ ጋር  ተጋጥመው  በነበረበት ወቅት «አበክሮ (አስቀድሞ) ሳይዋጋ ሸሸ» የሚልና  ንጉሥ ምኒልክ ወደ በጌምድር  ደርቡሽን ለመውጋት  በዘመቱ  ወቅት  ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተገናኝተው   ዶልተውብኛል  በሚል ሰበብ ነበር። «ተከለ ሃይማኖት ሳይዋጋ ብክር ሸሸ»  የሚለውን ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ለመጨፍጨፍ የተጠቀሙበት ሰበብ ከጭፍጨፋው በኋላ ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው ወደ መተማ ሲዘምቱ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከተዋጉበት ስፍራ ከሣር ውኃ  በደረሱ ጊዜ የሰውን አጽም ተከምሮ አይተውት «ሳይዋጋ አስቀድሞ ሸሸ ብላችሁ ያሳማችሁኝ» ብለው እነራስ አሉላን በመቆጣት እንደተሳሳቱ ራሳቸው ስለተናገሩ ጎጃምን ለማጥፋት ላካሄዱት ዘመቻ  እንደ ምክንያት ሲሆን እንደማችይል መናገር ይቻላል።
ወረድ ብለን ዐፄ ዮሐንስ  ያለ ምክንያት በጎጃም ሕዝብ ላይ ያካሄዱት  ጭፍጨፋና ዘረፋ ምን ይመስል እንደነበር  የመረመርነውን ታሪክ እናቀርባለን።  በሣር ውሃው ጦርነት ወቅት ትግራይ የነበረው የዐፄ ዮሐንስ ጦር  የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን በሣር ውሃ ድል መሆን በዐፄ ዮሐንስ ከተማ ወሬው  በተሰማ ጊዜ  ከዚህ በፊት  የደርቡሽን ወላፈን ያልቀመሰው የዐፄ ዮሐንስ  ወታደር ፈንታውን እስቲቀምስ ድረስ የጎጃም ጦር ተጋድሎ ማሽሟጠጥ ጀመረ።  ዐፄ ዮሐንስም  ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን «ሳይዋጋ ሸሸ» ብለው    አሙና ተክለ ሃይማኖትን ለመቅጣት ዝግጅት ጀመሩ። በሣር ውኃ ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር እንዳልተበተነና
ሣር ውኃ ሜዳው ላይ የተዘራ አዝመራ፣
አጫጁ ደርቡሽ ነው ሰብሳቢው አሞራ፤
እንዳልተባለ፤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራሳቸውም  በጭንቅ ተርፈውና  ልጃቸው ተማርካ ተወስዳባቸው ደርቡሽ የድመት ስጋ አርደው ሲያበላት፤
የምትሄዱ ሰዎች የምትሻገሩ፣
ድመት በልታ ሞተች ብላችሁ ንገሩ፤ 
ስትል  መልዕክት እንዳልላከች  የሣር ውኃ ጦርነት  መስዕዋትነትን በማሳነስ፤  በራሳቸው ትዕዛዝ ከተካሄደው ጦርነት የተረፉትን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትት እንኳ   «እንኳን እግዚያብሔር አተረፈህ» ብለው  ሰላምታ  መላኩ ጽድቅ ሁኖ ለኢትዮጵያ መስዕዋትነት የከፈሉትን ዐማሮች  ለመውጋት  “ና ውረድ  ደርቡሽን ውጋ” ብለው ወደ  ሸዋ  ንጉሥ ምኒልክ  ዘንድ ልከው  ጎጃምን ለማጥፋትና ለመዝረፍ   ለዘመቻ ተነሱ። ንጉሥ ምኒልክም  ዐፄ ዮሐንስ ባፄ ቴዎድሮስ ላይ እንዳደረጉት ሳይሆን የንጉሠ ነገሥቱን ጥሪውን ተቀብለው ጦር አስከትተው ወደ ቤገምድር ተጉዘው ጎንደር ሰፈሩ።
ንጉሥ ምኒልክ ወደ መተማ የዘመቱት ከዚህ በፊት ወታደሮቻቸው  ጉልበት እየተሰማቸው  «እንዋጋ ፤ የሰጠው ይስጠው፤ ለትግሬ አንገብር» ቢላቸውን ንጉሥ ምኒልክ ግን የአገር ጉዳይ የጋራ ጉዳይ ነውና ዐፄ ዮሐንስ እንግሊዝን መቅደላ ድረስ እየመሩ፤ ለወራት ቀለብ እየሰፈሩ እንዳደረጉትና ኢትዮጵያን እንደከዷት  ሳይሆን ለናት አገራቸው ሲሉ የፖለቲካ ልዩነታቸውን በጉያቸው አድርገው ባገር ጉዳይ አንድ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ ጥሪ መሰረት ወደ መተማ ዘምተዋል።  ይህ ብቻ ሳይሆን  ዐፄ ዮሐንስ በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ እንዳመጹት ሳይሆን ንጉሥ ምኒልክ ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ግብርም  ሳይቀር ለዘመቻ ከመነሳታቸው በፊት አስቀድመው  በመላክ በጊዜው ገብረዋል።
ጎንደር ሰፍረው ከሰነበቱ በኋላ ግን ጦራቸው ስንቅ በመጨረሱ  ገበሬውን ከማዘረፍ ብለው ጊዜው  እስቲደርስ በደንገል በር ዙረው በገና ወንዝ  ዙሪያ ሰፈሩ። ዐፄ ዮሐንስ «አንገብር እንዋጋ ብሎ ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋራ መክሮ  ከዱ» የሚል ወቀሳ ፈጥረው ጎጃምን ያጠፉትና ወደ ሸዋም  ለመዝመት የተነሱት በዚህ በሳቸው ጥፋት በተፈጠረው የንጉሥ ምኒልክ ሰራዊት ወደ ጎጃም ተሻግሮ ቦታ በመቀየሩ ነው። ዐፄ ዮሐንስ ሁለቱን ንጉሥች የከሰሷቸው «ዐፄ ዮሐንስ መጀመሪያ ወደ ጎጃም የጫነ እንደሆነ ንጉሥ ምኒልክ በቤገምድር መጥቶ በጀርባ ሊወጋ ተማምነው ነበረ። በዚህ ምክር ተባብረው ከተለያዩ በኋላ ግብር ደፍነው ዝም ብለው ተቀመጡ» ብለው  ነበር።
እንግዲህ ዐፄ ዮሐንስ ወደ ጎጃም ለመዝመት ተነሳሁ የሚሉን «የንጉሥ ምኒልክንና የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ክዳት ባወቅሁ  ጊዜ ስለተናደዱ» እንደሆነ ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው አስፍረዋል። ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው በመቀጠል « ጃንሆይ በዚያም  በምጽዋ በኩል ከኢጣልያኖች ጋራ ተሰልፈው  ነበረና ጠባቂ ጦር ከፍለው  በ1880 ዓ.ም. በነሐሴ ወር መጥቶ ወደ ቡዳው አገር ወደ ጎጃም ዘመተ» ይለናል።
የዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ሊቀ መርዓዊ እንደነገሩን ዐፄ ዮሐንስ  ጎጃምን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ በዘመቱበት ወቅት «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» ብለው አዋጅ  አስነግረው ነበር። እንግዲህ ሰማኒያ ሺ የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ወደ ጎጃም የተሰማራው «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይትረፈኝ» የሚለውን ንጉሣዊ ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ነበር። ይህንን እውነት የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጸሐፊም  አልደበቁም። ቀደም ሲል እንደጠቆምነው ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው ሊቀ መርዓዊ የዐፄ ዮሐንስን የጎጃም ዘመቻ ሲገልጹ «ወሖረ ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ሲሉ ነበር የጻፉት። ይህን የዐፄ ዮሐንስ የዘር ማጥፋት ዘመቻና አላማው ወደ አማርኛ ሲመለስ «[ጃንሆይ] ወደ ሰው በላው [ቡዳው] አገር ወደ ጎጃም ዘመተ» ማለት ነው።
ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ከዳር እስከ ዳር ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር እያቃጠሉ፣ ታቦቱን እያወጡ እየጣሉ ካባይ እስከ አባይ ድረስ ያጠፉት በመጀመሪያ ሕዝቡን «ቡዳ» በማለት demonize አድርገው ሰራዊታቸው ሰው ወይንም ሕዝብ  ሳይሆን ቡዳ እየጨፈጨፈ እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ ነበር። የሴቱን ጡት፣ የወንዱን ብልት ቁረጥ ተብሎ በጎጃም ላይ የዘመተው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት በጎጃም ላይ  ያን ያህል ጥፋት ያደረሰውና ካባይ እስከ አባይ  የሬሳ ክምር ያደረገው «ወሖር ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ተብሎ ሰው ወይንም ሕዝብ  ሳይሆን ጎጃምን በሙሉ ቡዳ ነውና መደዳውን ጨፍጭፍ ተብሎ በንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ዘ ኢትዮጵያ አዋጅ ስለተነገረው ነበር። ይህ እኛ እውነት  ተረት ተረት አይደለም፤ ወይንም የተበዳይ ወገን የፈጠረው ውሸት አይደለም፤  በዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል የተመዘገበና  የዘማጁ ወገን  የጻፈው ታሪክ እንጂ። እንዴውም በጎጃም ዜና መዋዕል ጸሐፊዎችም ሆነ በኢትዮጵያ  ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ዐፄ ዮሐንስ ወደ ጎጃም የዘመቱት የወንዱን ብሎት፣ የሴቷን ጡት ለመቁረጥ እንደሆነ እስካሁን የተጻፈ  እምብዛም  ነገር የለም።
ዐፄ ዮሐንስ «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይትረፈኝ» ብለው  «ወሖረ ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ሲል ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው ያስቀመጠውን ዘመቻ ሲጀምሩ በሣር ውኃ ጦርነት ጦራቸው አልቆባቸው የነበሩት የወቅቱ የጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የቆሰለና የተመናመነ ሰራዊት ይዘው ሰማንያ ሺህ ጦር አዝምተው የመጡትን ዐፄ ዮሐንስን መዋጋት ስለማይችሉ  ስንቃቸውን  አስልተው፤  ዕቃቸውን አሰናድተው  በጅበላና በሙተራ አንባ ገቡ። የወቅቱ ጳጳስ አቡነ ሊቃስ ግን አምባ አልገባም፤  መዋጋት ባልችል ጡት ሊቆርጥ፣ ብልት ሊሰልብ የተሰማራውን የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት አወግዛለሁ ብለው  ጉሊት ማርያም ደብራቸው ተቀመጡ። በቻሉት መጠንም ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን እንዳያጠፉት በመለመንና ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ለማስታረቅ  ሲጥሩ  ከዐፄ ዮሐንስ ዘንድ በመላላክ በዚያው  በጉሊት ከረመ። ሆኖም ግን ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ ዐፄ ዮሐንስም ጎዛምን ላይ ሰፍረው  አምባውን ሊሰብሩ  በጭምትና በማይ አፋፍ መድፍ ጠመዱ።
ዐፄ ዮሐንስ  እንግሊዝ  ኢትዮጵያን  ለመውጋት በመጣ ጊዜ  የተጠቀመበትንና እርሳቸው ለእንግሊዝ  በባንድነት አድረው  ባደረጉት አስተማጽኦ  ምክንያት ናፒየር ጠላቴ ያላቸውን ዐፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት በሩቁ ጠምዶ የመቅደላን ምሽግ ለማፍረስ የተጠቀመበትንና ኋላ ላይ ለዋሉት ውለታ እንግሊዝ  ለርሳቸው ሰጥቷቸው የሄደውን  ኃይለኛ መድፍ   ጠላቴ ባሉት የጎጃም ሕዝብ ላይ ለማዋል  በጭምትና በማይ አፋፍ  ላይ የጠመዱት ጅበላ የገቡትን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትንና በዙሪያው ከለላ የሰጣቸውን ሕዝብ ለመደምሰስ ነበር። ሆኖም ግን መድፉ አላማውን እየሳተ   ጅበላን እያለፈ ከአባይ በረኃ ወደቀ፤ የከሸፈውም ብዙ ሰው ፈጀ። ቀላሉም መድፍ የአምባውን ገደል እየመታ በመፈናጠር ስባሪው ቁጥሩ ተነግሮ የማያልቅ ሕዝብ ወደ ብጥስጣሽ ስጋ ቀየረ።
ያን ጊዜ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የመድፍ ዘመኛ አለቃ ባሻ አስናቀ የሚባል ነበረ። ወደ ዐፄ ዮሐንስ ሕዝብዎን አይፍጁት የሚል ተደጋጋሚ መልዕክት ቢላክም ንጉሠ ነገሥቱ ግን አሻፈረኝ በማለታቸው እንግሊዝ ጠላቴ ባለው ላይ የተጠቀመውንና  ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም  ሕዝብ ላይ የጠመዱትን የእንግሊዝ መድፍ ብዙ ሰው ስለፈጀ ለማምከን  እንቅስቃሴ ተጀመረ።  የተክለ ሃይማኖት የመድፈኛ አለቃ  ባሻ አስናቀ   ጅበላ ላይ ሆኖ ጭምት ላይ የተጠመደውን  ዐፄ ዮሐንስ የጠመዱትን የእንግሊዝ መድፍ ተመልክቶ ቢተኩስ  የመድፉ ዓረር በመድፉ አፍ ገብቶ ከመንኮራኩሩ የኋሊት ገልብጦ ጥሎ  ለጊዜው ዜግነቱ ያልታወቀውን የውጭ አገር ሰው የሆነውን ተኳሹን   ጨምሮ ገደለው። ዐፄ ዮሐንስ ጎጃም ለማጥፋት በዘመቱ ጊዜ ብዙ የውጭ ነፍሰ ገዳይ ቅጥረኞችንም አልፈስ እንደነበር ከመድፍ አስተኳሻቸው ማየት እንችላለን።
 በጭምት ላይ የተጠመደው  የዐፄ ዮሐንስ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ  ሕዝብ የፈጀበት  የእንግሊዝ መድፍ  ከጥቅም ውጭ ከሆነ በኋላ ሰራዊታቸውን አዝዘው  በጎዛምንና በማቻክል የተገኘውን የቤተ ክርስቲያን ሁሉ ሳንቃ እየነቀለ እያመጣ በጭምት አፋፍ የአረር ማብረጃ ተራውን አቁሞ  እንዲማግርና  እየፈለጠ እንዲያነድ አዘዙ። ይህ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ናቸው፤ ለሃይማኖታቸው ሲሉ ሞቱ እየተባለ የሚነገርላቸው ንጉሠ ነገሥት በጎጃም የሚገኘውን ታቦት ሁሉ  ከየመንበሩ እየበረቀሰ በየሜዳው  እንዲጣልና ቤተ ክርስቲያኖች ሳይቀሩ እንዲቃጠሉ አደረጉ። አድማጭ ልብ ማለት ያለበት  ለሃይማኖታቸው ሞቱ እየተባለ የሚነገርላቸው ዐፄ ዮሐንስ ደርቡሽ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልን እርሳቸውም እንዳደረጉት ነው። ከዚህ የምንረዳው በኢትዮጵያ ታሪክ በኢትዮጵያ መንግሥትነት ተሰይሞ ቤተ ክርስቲያን የደፈረው፣ የዘረፈው፤ ያቃጠለውና  ታቦቱን  ሜዳ ላይ የጣለው  የመጀመሪያው ወያኔ እንዳልሆነ ነው። ወያኔ ወደ ኢትዮጵያ መንበገ ሥልጣን ከመምጣቱ አንድ መቶ አመት በፊት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት የተሰየሙት ዐፄ ዮሐንስ ልክ ደርቡሽ ጎንደርና ጎጃም ገብቶ ቤተ ክርስቲያን እንዳቃጠለው ጎጃምን በወረሩበት ወቅት  ቤተ ክርስቲያንን ደፍረዋል፤  ዘርፈዋል፤ አቃጥለዋል፤  ታቦቱን  ሜዳ ላይ ጥለዋል።
የጎጃም ገዢ የነበሩት  ደጃዝማች ተድላ ጓሉ በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ በተደጋጋሚ  አምጸው እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል። ዐፄ ቴዎድሮስም አመጸኛውን ደጃዝማች ለመውጋት ይዘምቱ ነበር።  ደጃዝማች ተድላ ጓሉም የዐፄ ቴዎድሮስን መምጣት በሰሙ ቁጥር  በተደጋጋሚ የውሽ ማርያም እየገቡ ይቀመጢ ነበር። ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስም የአመፀኛውን የደጃዝማች ተድላን የውሽ  ማርያም መግባት በሰሙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኗን ቅጥር ሳይደፍሩ፤ ያመጸባቸውን ተድላን ሳይቀጡ ወደ መጡበት ተመልሰው ይሄዱ ነበር። ዐፄ ዮሐንስ ግን ይህንን የቆየ የኢትዮጵያ የሞራል ስልጣኔ አፈር ድሜ በማስጋጥ ዶልቶብኛ ያሏቸውን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ለመውጋት ዘምተው የጎጃምን ቤተ እምነት ሁሉ ዘረፉት፣ አጠፉት፣ አቃጠሉትም።
ቃላቸውን ተላልፈው ጎጃምን ሲያጠፉ ያዩት የጊዜው የምስሩ ጳጳስ  አቡነ ሉቃስ  ሳይቀሩ ዐፄ ዮሐንስን ተቆጥተው ተናገሩ። «ደርቡሽን አጠፋለሁ ብየ መጣሁ ያልከው ለጎጃም ደርቡሽ አንተ ሆንኸው» ሲሉም የደርቡሽን ውድመት ባዩበት መጠን በጎጃም ላይ ዐፄ ዮሐንስ ያደረሱትን ጥፋት አወገዙ።  ዐፄ ዮሐንስ ግን በዚህም አልተገቱም። የጳጳሱን ተግሳጽ ከመጤፍ ባለመቁጠር  ሰራዊታቸው የሰፈረበትን አምባ  ሰብሮ  እንዲዘርፍ ሌሊት  በጨረቃ ይገባ ዘንድ  ጭፍራ ሰደዱ። የጳጳሱን  ገላጋይነት ተስፋ አድርጎ በየቤቱ ገብቶ የነበረው ሕዝብ ጧት ሲነጋ  ከአምባው ጥግ  በስተጎድን  የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት መውጫ ሲፈልጉ  ባየ ጊዜ ደረቤ ላይ ወጥቶ ቤተ ክርስቲያኑን ከዐፄ ዮሐንስ ጥቃት እንዲታደግ ጥሪ አደረገ። በዚህ  ሕዝቡ ከያለበት ተጠራርቶ በመክተም  ቤተ ክርስቲያን ሊያቃጥል የተሰማራውን የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት በናዳ ተለቀቀው። ከደብረ ማርቆስ ደብር እስከ ውትርን  ጨረቻ ድረስ በተዘረጋው ቦታ በተደረገው ጦርነት  ብዙ  ምዕመን ተጨፈጨፈ።
ደብሩን ለመታደርግ በወጣው ሕዝባዊ ተጋድሎ የተናደዱት ዐፄ ዮሐንስ  በጭካኔያቸውን በመኩራት   ከትግሬ ያዘመቱት ሰራዊትና ጀሌ ሁሉ ጎጃምን ከዓባይ እስከ ዓባይ  ይዘርፍ  ዘንድ አዘዙ። እንዲዘርፍ የታዘዘው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊትም የጎጃምን ዝርዝር እህል እያጨደ ለርኩስ አበላው። እላሙንና በሬውን አንገቱን ሳይባርክ ነቀላውንና ጭኑን፣ ሽንጡን  እየነቀበ እየቆረጥ በላው። ሲናድሩን አቋምጦ  ይዞ በቆላውም በደጋውም ጠል ጠል ሲል በትግሬ ቋንቋ «ዋይለይ ትፍለስ ክነኋት»  እያለ እያስፈራራ ልብስ  ሳይቀር  እያስወለቀ ገፈፈ፤ ቤተ ክርስቲያንን ራቁቷን አስቀሯት።  የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አሽከሮች  ከሆኑት መካከል ጀግኖች አምባ  ያልገቡት እነ ደጃት ወዳጆ  ግን  አምባ ባለመግባታቸው ግራኝ  ያቃጠላትን መርጡለ ማርያምን የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ሊያቃጥል ሲዘምትባት ሊታደጓት ችለዋል።  መርጡለ ማርያምን ለማቃጠል ከተሰማራው የዐፄ ዮሐንስ  ሰራዊት ውስጥ በቅጥሯ ብዙ ወታደር እንደተገደለ ዜና መዋዕሉ ያስረዳል። የጎጃሙ ዜና መዋዕል ጸሐፊ መርጡለ ማርያምን ለማጥፋት ከዘመተው የዐፄ ዮሐንስ ወታደር ውስጥ እነ ደጃች ወዳጆ ብዙውን በስናድር በጥይት እንዳሻሩት ጽፈዋል።
የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕልም በየደብሩ የተሰማራውን ዘራፊ የዐፄ ዮሐንስ  ወታደር «ደገኛ በአምጃው፣ ቆለኛ በክትክታው እየተደበቀ  የአሞራ ቀለብ አደረገው» ሲል ጽፏል። የጎጃሙ ዜና መዋዕል ጸሐፊም  «የቅዱሳን አምላክ እየተራዳ ደብር ሊዘርፍ የተሰማራውን የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት የጎጃም ደገኛ በባዱ እጁ ስናድሩና ጥይሩን ሞሸለቀው።» ሲሉ የነበረውን ትንቅንቅ ያወሳሉ።  ከዚህ በተጨማሪ ዲማ ጊዮርጊስን ሊያጠፋ የተሰማራውን የዐፄ ዮሐንስ ወታደርም የጎጃሙ ዜና መዋዕል ጸሐፊ እንዲህ ሲል  ያነሳል፤  «ያን ጊዜ ደጃት ማሩ የሚባል የዐፄ ዮሐንስ ወታደር ዲማ ጊዮርጊስ ደረሰ። ዋሻውን ሊሰብር ዕቃ ቤቱን ሊበረብር ወረራ አደረገ። ዲሞችም የቤተ ክርስቲያኑን ውድም በሶስት በር ሁሉ ላንቃውን በድንጋይ  ረብረብ ዘግተው ተቀምጠው ነበር። የገጠሩም ዕቃ ብዙ ገብቶ ነበረ። መግቢያ ባጣ ጊዜ በሳንቃው ቀዳዳ አስገብቶ ተኩሶ አንድ ሰው ገደለ።
የዚህን ጊዜ ዲሞች መልክአ ጊዮርጊስን ሰባት ጊዜ ደግመው ረገሙት። ወዲያው ያነን የተኮሰውን የዐፄ ዮሐንስ ቁርጠት ተለቀቀው። ላብ አላበው። ጓደኞች አዝለው ከገበያው አጠገብ ከሰፈር ወስደው ከድንኳኑ አግብተው አስተኙት። ሕማሙ በበረታ ጊዜ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳለ። ሲናድሩንና የወገቡን ጥይት ሰጥቶ ከጸበሉ ጠጥቶ ዳነ። ከዚህ በኋላ ደጃች ማሩ ደነገጠ። ገዳዩ ታቦትዬ እያለ ተደነቀ። ዋሻውን አይቶ ከጸበሉ ጠጥቶ ለዐፄ ዮሐንስ ነግሮ ጥብቅ አሰጠው።» ይህ የሚነግረን ለሃይማኖታቸውና ለታሪካቸው ሲሉ አንገታቸውን ሰጡ እየተባሉ የሚሞካሹትና ሐውልት እንዲቆምላቸው የግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለላቸው ዐፄ ዮሐንስ ልክ እንደ ግራኝ መሐመድና ደርቡሽ የኢትዮጵያን ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና፣ ቅርሶችና ነዋየ ቅዱሳት ይዘርፉ፣ ያቃጥሉና ያወድሙ እንደነበር ነው።
ከጎጃሙ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ባሻገር በወቅቱ በዐፄ ዮሐንስ የጭፍጨፋ ዘመቻ ሰለባ የሆኑት ባላገሮችም ያንን የመከራ ወቅቱ በስነ ቃል የጥፋቱን ልክ ለታሪክ አስቀምጠው አልፈዋል።  ካባይ እስከ ዓባይ ጎጃምን ዝረፍ ተብሎ የተሰማራው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ራቁቷን ያስቀራትና ዘመዶቿን ያሳጣት የጎጃም አልቃሽ የከብቷን  መዘረፍ፣ የዘመዶቿን መፈጀትና  የልብሷ  መገፈፍ በእንጉርጉሮ፤
 በላይኛው ጌታ በባለንጀራዎ፣
በቅዱስ ሚካኤል በጋሻ ጃግሬዎ፣
 በፅላተ ሙሴ በነጭ አበዛዎ፣
 ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ፤ 
በማለት  በዐፄ ዮሐንስ  ዘመቻ የተፈጸመውን ጥፋት  እያለቀሰች   እርሮዋን አሰምታለች። ሰማኒያ ሺህ የሚሆነው የንጉሠ ነገሥት ወታደር  ለወራት ሙሉ እየተዘዋወረ  ከግራሽ ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ  አብያተክርስትያናትን  የመዘበረው፣ ያቃጠለውና ያፈረሰው በዐፄ ዮሐንስ  ዘመነ መንግሥት ነው። እንደ ዐፄ ቴዎድሮሱ ዘመን  መስሎት  ቤተ ክርስቲያ መጠለሉ እንዳይገደልና  ገንዘቡ እንዳይዘረፍ   ያድነኛል ብሎ   የተጠለለው ሕዝብ ሁሉ ሳይቀር   በወራሪው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት እየተመነጠረ የተገደለም የተዘረፈም ቁጥሩ የትየለሌ ነበር።
የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጥፋትና ጉዳት ተዘርዝሮ አያልቅም። ከዐፄ ዮሐንስ ዘመን በፊት  በመንግሥትነት በተሰየመ ብቻ ሳይሆ በተራ ሽፍታ እንኳ ያልተደፈሩ የቤተ ክርስቲያን ክብሮች የተደፈሩት በዐፄ ዮሐንስ ነው። ለዚህም አስረጂ ማቅረብ ይቻላል። ክራሞት በሸፈነው የዐፄ ዮሐንስ የጎጃም ወረራ አንድ ጊዜ በእነሴ ወራፊ ሊኸድ ኮሱ ዝራ ከሚባል አገር ቤተ ክርስቲያን ለመዝረፍ የተሰማሩ የዐፄ ዮሐንስ  ወታደሮች መምጣታቸውን የሰማው አገሬው  ቄሳውስቱን ቀስቅሶ  የመርቆርዮስን ሥዕል  ለማዳን  ቶሎ  ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው  ከመቅደሱ ያወጡት ዘንድ  ከላይ ታች ሲሉ  የዐፄ ዮሐንስ ወታደሮች ግን  በፈረስ እየጋለቡ በመቅደም ቤተ ክርስቲያን ደፍረው ገብተው  ሥዕሉን በዝናርና ካራ ልጠው እንደ ዳውጃና ሸምሎ በፈረሳቸው ላይ ተቀምጠውበት ወሰዱት። የዚህ ጊዜ ዐቃቤይቱ እንዲህ ብላ አለቀሰች፤
እንግዲህ አላምንም ሰማዕታትን፣
በፈረስ ቀደመው መርቆርዮስን፤
በቤተ ክርስቲያንና በሕዝቡ ላይ እየተዘዋወሩ ይህን  ሁሉ ግፍ  ሲፈጸም የተመለከቱት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት «ቢገድሉኝም ይግደሉኝ፤ ቤተ ክርስቲያን ሲወድምና ሕዝቤ ሲያልቅ ዝም ብዬ አላይም» ብለው ከዐፄ ዮሐንስ ዘንድ  ተላክከው  ታረቁ። ወደ ጎጃም የዘመቱት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ከሸዋው ምኒልክ ጋር ዶልታችሁብኛል ብለው ስለነበር ጎጃምን ጨፍጭፈው ከጨረሱ በኋላ  ምኒልክን  ለመውጋት ወደ ሸዋ ለመሄድ ተነሱ። ከዘመቻቸው በፊትም አስቀድመው እንዲህ የሚልክ ግጥም ወደ ሸዋ ላኩ፤
እርሳሱ ብዙ ነው የሐምሌ ቴግብ፣
ድንጋያ መንገስ ነው በዝብዝን ማሰብ፤ 
ይህ  ግጥም በሸዋ በተሰማ  በኋላ አከታትለው  ወደ ኋላ ላይ  የምናቀርበውን  የወቀሳና ዛቻ ደብዳቤ ከዐፄ ዮሐንስ  ወደ ንጉሥ ምኒልክ ይደርስ ዘንድ ወደ ልዑል ራስ ዳርጌ ተላከ።  ንጉሥ ምኒልክም  ይህን በሰሙ ጊዜ በጎጃም የደረሰውን ጥፋት ያውቁ ኖሮ  አገሬን አላዘርፍም ብለው የደብረ ሊባኖስና የዝቋላ መነኮሳትን አስይዘው የሚከተለውን ደብዳቤ ለዐፄ ዮሐንስ  ወደ ደረቋ  ላኩ፤
ይድረስ ከሥዩመ እግዚያብሔር ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ 
የተላከ ከንጉሥ ምኒልክ 
ወደ ራስ ዳርጌ የመጣው የጃንሆይ ደብዳቤ ደረሰኝ። ሰይጣናት በሰው አድረው በእኔና በጃንሆይ መካከል ነቅዕ ስለአገቡብ ደብዳቤውን አይቼ እግጅ አዘንሁ። እኔም ከመሥጋቴ በቀር ከያዝሁት መንግሥት ፈልጌ እንደሆነ ጃንሆይንም ጠልቼ የጃንሆይ መንግሥት እንዲናወጥ አድርጌ እንደሆነ እግዚያብሔር ምስክሬ ነው። ሠራዊትዎ  የሚያወራብኝ ብዙ ነው። ፊት ደርቡሽን አመጡ ተብዬ ነበር። ኋላም ኢጣሊያ ቢመጣ ይህንኑ አለኝ። እኔ ግን ይህ ሁሉ ቢወራ ግን የለም ከጦርነቱና ከሞቱ የተለየ እንደሆነ ያን ጊዜ ሁሉም ይታወቃል ብዬ ሠራዊቴን አስከትቼ ብመጣ ጃንሆን ወደ ደርቡሽ አዘዙኝ።
እኔም ደስ ብሎኝ እግዚያብሔር ኃይል ቢሰጠኝ የክርስቲያንን ደም እመልሳለሁ፣ ብሞትም ሰማዕትነት እቀበላለሁ፣ ብዬ ሄድሁ። በእግዚያብሔር ቸርነት በጃንሆን ሀብት ጠላታችን ሸሽቶ ቢሄድ ታርቀው ሄዱ እያለ ያወራል አሉ።
ዳግመኛ ጃንሆን ባዘዙኝ ቃል ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት መልካም አድርጎ  ቢቀበለኝ  ደስ ብሎኝ ክርስቲያን ለክርስቲያን፣ ወንድም ለወንድሙ፣ መርጠብ ይገባል መስሎኝ ሁለት መድፍና ሁለት መቶ ሃምሳ ጠመንጃ ረጥቤው መጣሁ። ይህ ነውር ሆኖብኝ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ያስከዱ  ንጉሥ ምኒልክ ናቸው ይሉኛል  አሉ። ደግሞ የጃንሆይ ደብዳቤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን አባባላችሁ አስካዳችሁት ይላል።
ከእንግዲህ ወዲህ የዚህን ነገር ብናገር ሀሰብት እንጂ እውነት አይመስልም። ነገሩንም እግዚያብሔር ባወቀ ይግለጸው። «እኔማ ወይሰበክ ወንጌለ መንግሥት ሰማያት ውስተ ኩሉ ዓለም። ከመ ይኩን ስምዓ ላዕለ ኩሉ አሕዛብ» ያለው በጃንሆይ ጊዜ ደርሶ ሊፈፀም ነው ብዬ ሳለሁ የኛን አንድነት ሰይጣናት አፍርሰው የጠላት አላማ በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጸም  ይሆን  ወይ ብዬ አዝኜ ነበርሁ። አሁንም የፈራሁበትን ነገር ከይቅርታዎ ጋራ ላባታችን ለአቡነ ማቴዎስ ነግሬአለሁ። ለራስ ዳርጌም ጽፌአለሁ።
በታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፲፰፹፩ ዓመተ ምሕረት
በእንጦጦ ከተማ ተጻፈ
ንጉሥ ምኒልክ ይህን ደብዳቤ  ከላኩ በኋላ ቀደም ሲል  ለንጉሠ ነገሥቱ ይከፍሉት የነበረው ግብር አስከትለው ላኩ። በዚህ ጊዜ እርቅ ወረደ። ከዚህ በኋላ ዐፄ ዮሐንስ ወደ መተማ ተመለሱ። ወደ መተማ ሲሄዱም  እንደልማዳቸው ጎጃም እየዘረፉ ስለተሻገሩ  በዐፄ ዮሐንስ ወታደር ከብቷን የተቀማች የጎጃም ሴት እንዲህ ስትል አለቀሰች፤
በሬውንም ነዳው የትግሬ  ነፍጠኛ፣ 
ላሚቱንም ነዳት የትግሬ ነፍጠኛ፣
እህሉን  ዘረፈው  በላው ረሃብተኛ፣
ንጉሥ ሆይ ቀረዎ  አንዲት አማርኛ፣ 
ለምን ሆድ አይበሉም አርፈን እንድንተኛ:፤
ከብቶቹን ተረዳን፣ 
እህሉን ተረዳን፣ 
ደግሞ አለብን መርዶ፣ 
ጎጃም ወንዱ ሴቶ በትግሬዎች ታርዶ፤
ዘንድሮ ንጉሡ ደህና ቢመለሱ፣
ምንኛ ጎልድፏል ጎጃሜ ምላሱ፤ 
ጎጃም በአባ በዝብዝ ካሳ  ከዳር እስከ ዳር በጠና  የተጨፈጨፈው  ከመተማ ጦርነት በፊት  በ1870ዎቹ የደርቡሽ ጦርነት በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አሸናፊነት የተጠናቀቀውና ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ያካሄደው ተጋድሎ  ተክዶ ነው። ከመጀመሪያው ጦርነት ሶስት  ዓመታት በኋላ በተደረገ ጦርነት የኢትዮጵያና የደርቡሽ ጦርነት  በንጉስ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር ክፉኛ ተጠቅቶ፣ የንጉሱ ልጅ ሳይቀር ተማርካና የአስራ ሁለት ታላላቅ መኳንንት አንገት ተቆርጦ  ሰራዊቱ ተበትኖ ሳለ  ቀደም ሲል  በደርቡሾች የተጠቃው ጦር   ገና ሳያገግምና     ስንቅም ትጥቅም ማዘጋጀት ተስኖት የነበረውን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን  ጦር ለ3ኛ ግዜ ወደ ደርቡሾች እንዲዘምት  አዝዘውት ከቁስሌ አላገገምሁም ባለ  ደርቡሹ  ያጠፋው ሳያንስ «አበክሮ (አስቀድሞ) ሳይዋጋ ሸሸ» በሚል ዘምተው ደርቡሽ ኢትዮጵያን ካጠፋት በላይ ጎጃምን አጠፉት። ገራሚው ነገር የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነኝ የሚል ንጉሥ  ደርቡሽ ኢትዮጵያን ወሮ ሳለ ቅድሚያ  ወደ ደርቡሾች ከመዝመት ይልቅ ወደ ጎጃም ዘመቱ። ይህ የሚያሳየው ዐፄ ዮሐንስ ጎጃም አጥፍተው እስኪጨርሱ ድረስ ደርቡሽ ኢትዮጵያን ቢያጠፋ ግድ እንዳልነበራቸው ነው።
የዘመቱባቸው ንጉሥ  ተክለሃይማኖት  ንብረታቸውንና መኳንቶቻቸውን ይዘው ጅብላና ሞተራ ገብተው ሲመሽጉ  አንባዎች ላይ መሸጉ ንጉሱን ምንም ነገር  ሳይነኩ   መከላከያ የሌለውን የጎጃም ሕዝብ  ባልተወለደ አንጀታቸው ያለርህራሄ ስቃዩን አሳዩት። ከጭፍጨፋ የተረፈውን ሕዝብ  ለብዙ ወራት   በተደጋጋሚ ጦራቸው  እየዞረ ያለ ርሕራሔ እንዲገድና  እንዲዘርፍ፤ ቋሚና አላቂ የሆነን ንብረት ሁሉ ወደ ትግሬ እንዲያግዝ አዘዙት።  ብዙ ሰው የዐማራ ንብረት እየተነቀለ ወደ ትግራይ መወሰድ የጀመረው በወያኔ ይመስለዋል። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ዐፄ ዮሐንስ ጎጃም በዘመቱ ጊዜ ሰው የለበሰውን ልብስ ሳይቀር አስወልቀው በመዝረፍ ወደ ትግራይ አግዘውታል።  ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን አጥተው መተማ  ላይ ሲሞቱ ፤ ጎረቤት አገር ደም መላሽ ያገኘት የመሰላት የጎጃም አልቃሽ፤
ቤታችን አልጠጣ ቤታችን አልበላ፣
የኛን ደም መለሰ መሃመድ አብደላ፤
ስትል ስሜቷን ገልጻ ነበር። 
ከዚህ በተጨማሪ  በዐፄ ዮሐንስ የተገፈፈው  ድሃው  ከፍ ሲል ከቀረቡት በተጨማሪ  አንድ ተክለ ሃይማኖት በሸሽ መላ ሕዝቡ መከራ ማየቱ ማዘኑን፤
ይገለኛል  ብሎ ይሰቅለኛል ብሎ አንድ ሰው ለሸሸ ፣
መላው የጎጃም ሕዝብ  በትግሬ ሰራዊት እንደ ጭቃ ታሸ፤
ሲል ገልጿል። አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ የተክለ ሃይማኖትን ዱለታ  ለማብረድ  በሚል የጎጃም ገበሬ የሚያርስበትን  በሬ፣ የሚበላው ቅቤና የሚጠጣው ወተት ማሳጣት አለብኝ ብለው   በጎጃም የሚገኝን  የዳልጋ ከብት፣ ላም፣ በሬ፣ የሚጠጣ ወተት ወዘተ. . .  ወደራሱ የጦር ሰፈር እያስነዳ  ልብሷን ሳይቀር ገፈው ወስደው ራቁቷን ያስቀሯት  ጎጃሜ ሴት፤  በየቀኑ ከመከራ ገላግለኝ እያለች እግዜአብሄርን ትማጸን ነበር። ግን እግዚያብሄር መልስ አልመለሰላትም ነበርና እንዲህ ስትል ገጠመች፤
ከሀበሻ ወዲህ ከሀበሻ ወዲያ፣
ሰውን ገረመው እኔንም ገረመኝ፤
ዮሐንስ እግዜርን ገድሎታል መሰለኝ፤ 
ከታሪክ ማስረጃዎች በተጨማሪ በማሕበረሰቡ ዘንድም ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ያካሄዱት ሁለት ዙር ጭፍጨፋና ዘረፋ  በስነ ቃል ደረጃ ብዙ ይገኛል።  ጭፍጨፋውንና ዘረፋውን  በአይኑ ያየውና በተዓምር የተረፈው ቦጋለ አይናበባ የሚባል የጎጃም አልቃሽ ያንን የጎጃም የመከራ ዘምን እንዲህ ሲል ገልጾት ነበር፤
ዮሐንስ ነው ብለው ስንሰማ ባዋጅ፣
ዮሐንስ አይደለም ሳጥናኤል ነው እንጂ፤
ዮሐንስ አጠፋው አደረገው ዱር፣
ጎጃምን የሚያህል ያን ለምለም ምድር፤
በትግሬ ተዘርፈን እንጀራ ፍለጋ ወንዙን ሳንሻገር፣
ድሮ ባገራችን ቡቃያው በጓሮ በጎታ እህል ነበር፤ 
ጎጃም ተቃጠለ ዐባይ እስከ ዐባይ፣
ትግሬ ቅጠል ይዞ ሊያጠፋው ነወይ። 
ከነዚህ በተጨማሪ ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው ጎጃምን እንዳጠፉት በንጉሥ ምኒልክ ማኩረፋቸውን ለልዑል ራስ ዳርጌ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ገልጠላል። የሚከተለው የዐፄ ዮሐንሥ ደብዳቤ ጎጃም እያጠፉ በነበረበት ወቅትና ወደ ሸዋ ለመሻገር ባሰቡ አካባቢ ለንጉሥ ምኒልክ ይደርስ ዘንድ ለልዑል ራስ ዳርጌ የላኩት ነው፤
መልዕክት ዘሥዩመ እግዚአብሔር ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ይድረስ ከራስ ዳርጌ እንዴት ሰነበቱ? እኔ ከሠራዊቴ ጋር እንዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። አስራ አንድ ዓመት ሙሉ በፍቅር ተጸምደን በሃይማኖትና በምግባር አንድ ሁነን መንግሥታችንን አጽንነትን እንኳን የኢትዮጵያ ሰው የወዲያ አገር ነገሥታት እንኳ እየቀኑብነ ከእግዚአብሔርና ከሰው ተስማምተን እስካሁን ተቀመጥነ። አሁን ዲያብሎስ ጽላኤ ሠናያት ነውና የአሕዛብ መሳለቂያ ሊያደርገነ ከሁለታችን ከወንድማማቾች መካከል እንዲህ ያለ ነቅ አገባበነ። ደግሞ ዝምድናችን እንዲፀና እንድንበረታ ብዬ ምንም እንዚአብሔር ቢያሳፍረነ ልጅ ከልጅ አጋባሁ ምክር መከርሁ። ባይማኖት አስተማርሁ። ሥላሴ እንኳን የማያደርጉትን ከመንግሥቴ ከፍዬ ወንድሜን  ለመንግሥት አበቃሁ እንጂ እኔ በንጉሥ ክፉ ያደረግሁ አልመሰለኝም ነበር። አሁንስ በትውልድ አባት ነዎ። በዕድሜ ሽማግሌ ነዎ። ሰይጣን ባልሆኑ ሰዎች አድሮ ነገር ሲያበላሽ እያዩ ምነው ዝም ይላሉ? ምንም ፈቃዱ የእግዚአብሔር ስለሆነ እኔ አሳላፊ ነኝ። ከጎጃም መምጣቴ ነው የሚያሳዝነኝ፤ አህጉረ  ኢትዮጵያን ሁሉ ከፍየ ሰጥቼ ትግሬንና ቤጌምድርን ይዤ ብቀመጥ በቤጌምድር ሹም ሽር ተደረገበት። በትግምሬ የንጉሥ ደብዳቤ አልመጣ እንደሆነ ነው እንጂ የመኳንንቱ ደብዳቤ በሀገሩም በሠፈሩም ያልመጣበት በመልዕክት ያልተባባለ፣ ወርቅ ያልተቀበለ ሰው አይገኝም።
የመጣውንም ደብዳቤ ሎሌ ለጌታው ያየውን የሰማውን አይሰውረውምና ከሰዎቼ እጅ ደብዳቤውን አገኝቼ ነው እንጂ ሳላገኘው በሀሰት አልጻፍኩም። እንግዴህ ግን ደርቡሽ ወጥቶ የክርስቲያን ደም ቢያፈስ ቤተ ክርስቲያን ቢተኩስ የዚህ ፍዳ ንጉሥ ምኒልክ ነው እንጂ እኔን አያገኘኝም። ከልቤ እንኳ ቤቱ ምስጡር ቢኖር ከወንድሜ ከንጉሥ ምኒልክ ሰውሬ የማውቀው አልነበረኝም። በፊትም አብረን ሳለነ እየተባባለ፣ የትግሬ ሁሉ ጦር ሄደ። አሁንም በኋላ አምባጫራ ወርዳችሁ ሳለ በደምቢያም በቤጌምድርም ያለ ሁሉ ደግናውም ፈላሻውም ቤቱም የቀረ የለም እየተባበለ ከናንተ ጋር ባንድ ሄደ።
ሳይጠፋኝ ይህን ሁሉ እየሰማሁ ዝም ብል በመጨረሻ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን አባብላችሁ አስከዳችሁት። ስለከዳ ግን አገሩ ጠፋበት፣ ተጎዳ እንጂ አሁን እግዚያብሔር ምህርት አውርዶ ታርቆ ገባ። ደግሞ እኔ የእግዚአብሔር የትህትና ደካማ ነኝ እንጂ የሰው ደካማ አይደለሁም። የኔን አገር የሚገዛው የለም።
ይህን ሁሉ እያደረገ እናንተንና እኔን ሰይጣን ሆኖ የሚያፋጀውን  መንግሥት ሊያፈርስ የሚጥር የዓለምን ሁሉ ቋንቋ ሲያጠና የሚኖር ነፍስ አባት አይሉት የሰው አገር ሰው ቤጌምድሬ መሸሻ ወርቄ የሚሉት መካር  አበጅታችሁ የተንኮሉ ሁሉ ምንጭ እርሱው ነው እንጂ፣ የንጉሡም የእናንተም ይህን ያህል እንደሌለ አውቃለሁ። አሁንም እኔ ግንድ የለኝም አስተውላችሁ ብትመክሩ ይሻላል። ደብዳቤውን እርስዎ አይተው ወደ ልጅዎ ወደ ንጉሥ ይስደዱት። ተጻህፈ በዳሞት ሰፈር አመ  ፲ወ፰ ለኅዳር በ፲ወ፰፻፹፩ ዓመተ ምሕረት።
ልዑል ራስ ዳርጌም የዐፄ ዮሐንስን ደብዳቤ ባዩ ጊዜ  ነገሩ እጅግ ስላሳሰባቸው በቶሎ ወደ ንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤውን ልከው ንጉሥ  ምኒልክ የዐፄ ዮሐንስን ደብዳቤ ከማቅረባች በፊት ያቀረብነውን ደብዳቤ በልዑል ራስ ዳርጌ በኩል ወደ ዐፄ ዮሐንስ ላኩ። በተለይ «እኔ ከሠራዊቴ ጋር እንዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ» የሚለው የደብዳቤያቸው ክፍል፤
እርሳሱ ብዙ ነው የሐምሌ ቴግብ፣
ድንጋያ መንገስ ነው በዝብዝን ማሰብ፤
ሲሉ የላኩትን ግጥም የሚያጠናክርና ሸዋን ለመውረር የተዘጋጁ ስለመሰላቸው ንጉሥ ምኒልክ በቶሎ ምላሽ እንዲሰጡበት አሳስበው እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል።
ዐፄ ዮሐንስ  በዚህ ለራስ ዳር በጻፉት ደብዳቤ እንዳሰፈሩት ስለጎጃም ሲጽፉ  «ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት  ስለከዳ  አገሩ ጠፋበት» ብለዋል። ዐፄ ዮሐንስ  በዚህ ንግግራቸው «አገሩ ጠፋበት» የሚሉት እሳቸው ራሳቸው እየተዘዋወሩ ሲያጠፉት የከረሙትን ጎጃምን ነው። አንዳንድ የትግራይ ብሔርተኞች ይህንን በመካድ «ስለከዳ ግን አገሩ ጠፋበት» ሲሉ ዐፄ ዮሐንስ ጻፉ እንጂ ጎጃምን አጠፋሁት አላሉም  በማለት ጉንጭ አልፋ ክርክር ይከፍታሉ። ሆኖም ግን የማይዋሽበት ዘመን ነውና የምንኖረው  ጉዳዩ ለአድማጭም  ግልጽ ይሆን ዘንድ ከፍ ሲል ካቀረብነው ደብዳቤ አስተትለው ዐፄ ዮሐንስ ለልዑል ራስ ዳርጌ በጻፉት ደብዳቤ ላይ  ጎጃም ሲያጠፉ እንደከረሙ ያወጉበትን የራሳቸውን ቃል  እንደሚከተለው ከነሙሉ ደብዳቤያቸው እናቀርባለን፤
 መልዕክት ዘሥዩመ እግዚአብሔር ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ይድረስ ከራስ ዳርጌ እንዴት ሰነበቱ? እኔ ከሠራዊቴ ጋር እንዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። አመ ፲ወ፭ ለታኅሣሥ  የተጻፈው የንጉሥ ደብዳቤ ደረሰልኝ። ኢጣሊያ የመምጣቱ ወሬ የመጣልኝ በሐረርጌው በደጃዝማች መኮንን በኩል ነው። ኢጣልያንን ንጉሥ ምኒልክ አመጡ እያሉ በደጅ ይጫወቱ እንደሆነ እንጂ ፊቴ ደፍሮ እንዲህ ያለ ነገር የሚናገር የለም። ከዚህ በኋላም መምጣቱ ከታወቀ ወዲያ ጃንሆን የጦሩ ዕለት እንዳይለይ ያድርጉልኝ የሚል የንጉሥ ቃል በአቡነ ማቴዎድ መጣልኝ። እሺ ብዬ ወደ ንጉሥ ላክሁኝ። ከዚያ ወዲህ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ድል ሆኖ ነበርና ዳግመኛ ሕዝበ ክርስቲያኑን ደርቡሽ ወጥቶ ይፈጀዋል ብዬ ቢያሳዝነኝ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለኢጣልያው እኛ እንበቃዋለን አምባጫራ ላይ ሆኖ እርሱን መጠበቅ ይሻላል ብዬ ወደ ንጉሥ ላክሁኝ። ይህም ሆነ አልቀረም። በምጥዋም በመተመም ያለውን ጠላታችንን እግዚያብሔር አሳፈረው።
ምጉሥ ምኒልክ ከደርቡሽ ጋራ ተላልከዋል ብለው የደምቢያና የቤጌምድር ሰዎች ይጫወቱ እንደሆነ እንጂ ከእኔ መኳንንቶች አፍ እንዲህ ያለ ነገር አይወጣም። እኔም መቅደላ እከርማለሁ ብዬ ሳለሁ ደርቡሽ መጣ ቢሉኝ ከርስቲያኑን ይፈጀዋል ብዬ ወደ ቤጌምድር ወርጄ አሞራ ገደል ሠፍሬ ሳለሁ ንጉሥ ምኒልክና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አሲረው ከድተዋል። ተማምለዋል። ወደ ኢጣሊያም እኛና እናንተ በአንድ ነን ብለው ጽፈው አትመው ሰደዋል፤ ጃንሆይንም ነገሥታቱ ከድተዋቸዋል። በወዲያም ደርቡሽ መትቶባቸዋል እንግዲህ ምን ኃይል አላቸው እያሉ ኢጣልያኖች ይሳለቁብዎታል የሚል ወሬ ሰማሁ። በዚህ ምክንያት ጎጃም ተሻገርሁ።
በእኔም በድኃውም ኃጢአት እንደሆነ አይታወቅም  ጎጃምን ሳጠፋው ከረምሁ። ኋላም    ንጉሥ ተክላ ሃይማኖት ታርቆ ገባ። ከገባ ወዲህ ይህን ቃል እውነት ልካችኋል ወይ? መክዳቱስን እውነት ተማምላችሁ ከድታችሁኛል ወይ? ብለው ከጃንሆይ ጋራ ውጊያ አልዋጋም ብያለሁ እንጂ መሃላውን እሺ ብዬ ምያለሁ ብዬ አልልም ብሎ ነገረኝ። ከዚህ ወዲያ ግን ወደ እርስዎ ደብዳቤ የጻፍሁት ከዚህ የተነሳ ነው።
የመተማመኑ ነገር ግን እኔ አልከዳሁም፤ መሃላ አላፈረስሁም፤ አፍርሼ እንደሆነም ክርስቲያን አልባልም። ዳግመኛስ የምተማመነው የፊቱን ማን አፍርሶት ነው። በእሜን በንጉሥም ፈርሶ እንደሆነ ከዚህ ከእኔ ጋራ ብዙ መኳንንት በወዲያም ብዙ መኳንንት አሉና በያሉበት ሆነው በርምረው እገሌ ከድቷል፤ እገሌ መሃላውን አፍርሷል ይበሉነ። ከዚያ ወዲያም ወደ ቁም ነገራችን እንሄዳለን።
ተጻሕፈ በዳሞት ሰፈር።  አመ  ፭ወ፮ ለኅታኅሣሥ በ፲ወ፰፻፹፩ ዓመተ ምሕረት።
እንግዲህ! በዚህ የዐፄ ዮሐንስ ደብዳቤ በግልጽ እንደተቀመጠው የጎጃም  ድሃ ያለ ጥፋቱ «ሳጠፋው ከረምሁ»  ብለው በራሳቸው አንደበት ነግረውናል። ይህንን በምንም መንገድ  ማስተባበል አይቻልም። እጅግ አስገራሚው ነገር ቢኖር በጎጃም ወረራቸው ወቅት ቤተ ክርስቲያን ሲያቃጥሉና ሲዘርፉ፤ የሕዝበ ክርስቲያኑንም  ደም ሲያፈሱ ከርመው ልክ እንደ ንጹህ ሰው «ደርቡሽ መጣ ቢሉኝ ከርስቲያኑን ይፈጀዋል ብዬ ወደ ቤጌምድር ወርጄ አሞራ ገደል ሠፈርሁ» ማለታቸው ነው። ፋሽስት ወያኔዎችና ተከታዮቻቸው በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ላይ የውሸት ታሪክ እየፈለሰፉና  ያልተፈጸመ  ድርጊት እየፈጠሩ የጥላቻ ሃውልት በየ ጉራንጉሩ ሲያቆሙ የሚውሉት  የፈጠሯቸው  የአኖሌም ሆነ የጨለንቆ ጦሮነቶች ተካሄዱ ከተባለበት ዘመን  በኋላ የኛ የሚሏቸው ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው «ጎጃምን ሳጠፋው ከረምሁ» እያሉ የነገሩንና  «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይትረፈኝ» ብለው የዘመቱበትን  በዐማራ ላይ የተፈጸመ ወደር የማይገኝነት ጭካኔ ደብቀው ነው። ታሪኩ ሲገለጽ፣ ዶሴው ሲወጣ የምናገኘው እውነት ይህ ነው።
በዚህ በምንኖርበት ዘመንም   ከዛሬ ሀያ ሶስት ዓመታት በፊት ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን በጨፈጨፉ ልክ በመቶ ዓመቱ የዐፄ ዮሐንስ የልጅ ልጆች ነን ያሉን ፋሽስት ወያኔዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተቋቋመን የጎጃምን የወባ ማጥፊያ ድርጅት ነቅለው ወደ ትግራይ ስለወሰዱት በመቶ ሺዎች እንደሚቆጠር የሚገመት የጎጃም ሕዝብ እንዲያልቅ አድርገው ነበር። በወቅቱ ከመቶ አመት በፊት ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ተመሳስሎ ከመቶ አመት በኋላ የልጅ ልጆቻቸው ነን ባሉ ወያኔዎች ዘግናኙ ታሪክ መልኩን ቀይሮ ራሱን በጎጃም ላይ ሲደግም፤
ጦማችን ባይሰምር ጸሎታችን ባይደርስ፣
በልጅ ልጅ መጡብ ዐፄ ዮሐንስ፤
ብሎ ነበር ጎጃም።
ቀደም ሲል እንዳነሳነው ፋሽስት ወያኔ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ታሪክ ለማጥፋትና ኢትዮጵያውያንን ለማጋጨት ይጠቅመኛል ያለውን ክፋት ሁሉ አድርጓል፤ በየቦታው በፈጠራ ታሪክ የተዋጁ የተቆረጠ እጅና ጡት ሐውልትን ጨምሮ እልቆ ቢስ ጸረ ምኒልክ ሐውልቶችን አቁሟል። የታሪክ ባለሞያዎቻችን ዝምታ የበጀው ፋሽስት ወያኔ በግፉዓን ምድር፣ ግፍ ሰሪው ራሱ  ታሪኩን በጻፈው ሰብዳቤ በጻፈበት ሁኔታ  የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት መተማ ላይ ይቁምልን እያሉ ነው።  አንድ ነገር እውነት ነው፤  ወያኔዎች የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት መተማ ላይ እንዲቆምላቸው የሚጠይቁት ዐፄ ዮሐንስ ሞቱለት የሚሉንን  አላማ ለማክበር ፈልገው አይደለም።
ወያኔዎች መተማ ላይ ዐፄ ዮሐንስ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሚጠይቁት እነሱ እንደሚሉት ወደቅይለት የሚሉትን የዐፄ ዮሐንስ አላማ በማክበር ቢሆን ኖሮ ዐፄ ዮሐንስ የሞቱለትን የሚሉትን  መሬት እየቆረሱ ለሱዳን አይሰጡም ነበር። እነሱ በዋናነት ለዐፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሚፈልጉት በጊዜ ብዛት የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት የቆመበት ሁሉ የትግራይ መሬት ነው ብለው መሬቱን ወደ ትግራይ ለማጠቅለል እንዲያመቻቸው ነው።
ጽሁፋችንን ከማጠቃለላችን በፊት ግን አንድ ነገር ማንሳት ያስፈልጋል። ከፍ ሲል ባቀረብነው ታሪክ  ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው «ጎጃምን ሳጠፍ ከረምሁ»  ማለታቸውና   ጳጳሱም ሳይቀሩ የጎጃምን ጥፋት አይተው  «በሕዝቤ ላይ  ደርቡሽ ሆንህበት» ማለታቸው   ደርቡሽ  ኢትዮጵያን ያጠፋውን ያህል ዐፄ ዮሐንስ ጎጃም እንዳጠፉት መረዳት ይቻላል።  ይህ ማለት ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ያጠፉት ደርቡሽ እኛን ያጠፋንን ያህል ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የሱዳኑ ደርቡሽ በመተማ ምድር ስላጠፋው ሐውልት ይቁም ከመባሉ በፊት የትግሬው ደርቡሽ ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ስላጠፉት በቅድሚያ ጎጃም ላይ ሐውልት ሊቆም ይገባል ማለት ነው። የሱዳኑ ደርቡሽ መተማ ላይ ሐውልት ይቁም እያሉ ከመተማው ጥፋት በፊት የትግሬው ደርቡሽ ዐፄ ዮሐንስ ጎጃም ስላጠፉት ሐውልት እንዲቆም የማይጠይቅ ቢኖር የሱዳኑ ደርቡሽ መተማ ላይ ስላጠፋው ሐውልት ይቁም የሚለው በሰብአዊነት ስሜት ሳይሆን ለፖለቲካዊ ትርፍ ብቻ ነው። የሰብአዊ ፍጡር መስዕዋትነት ደግሞ ለፖለቲካ አላማ የሚውል ከሆኑ ሰማዕቱን ሁለት ጊዜ መግደል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ በየቦታው ያቆማቸው ጸረ ምኒልክ ሐውልቶች አላማቸው በደልን ታሳቢ ያደረገ ከሆነ በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ያቆማቸውን በትግራይ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተገነቡ የፈጠራ ሐውልቶች አፍርሶ የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ሊቀ መርዓዊ ሳይቀር ለጻፉትና ዐፄ ዮሐንስ በሁለት ዙር «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» እያሉ ዘምተው የቆረጡት የሴት ጡትና የወንድ ብልት ባግባቡ ተጠንቶ ዘመኑን የዋጀ መታሰቢያ ሊቆምና የዐፄ ዮሐንስን የጎጃም ጭፍጨፋ የሚያወግዝ ሐውልት ሊቆም ይገባል እንላለን።
ዐፄ  ዮሐንስ ወደ ጎጃም ዘምተው ሳር ቅጠሉን፣ ከብቱንም ሰውንም እህሉንም ፈጅተው፤ ልክ እንደ ደርቡሽና ግራኝ አሕመድ ቤተ ክርስቲያንን አውድመው፤ የተረፋቸውንና  የሚጓጓዘውን ወደ ትግራይ አግዘው ጨርሰው፤ በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመንም   ከእንግሊዝ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከድተውና  በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ባህረ ነጋሽን ለጥሊያን አሳልፈው ሰጥተው  «ለሀገራቸው ሲሉ በጦር ሜዳ ወድቀዋል» የሚለው ውሃ የማይቋጥር ትረካ ሊቆም ይገባዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዐፄ ዮሐንስ በአዋጅ የጨፈጨፏቸው፣ ምላሳቸውን የቆረጧቸው፣ አፍንጫቸውን የፎነኗቸው፣ ካገራቸው ያሰደዷቸው የወሎ እስላሞችም ሰማዕታቶቻችን ናቸውና ከመተማው ሐውልት በፊት ደሴ ላይ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል። ከባህላችን ባፈነገጠ መልኩ ከማረኳቸው በኋላ ከፍትሕ ነገስቱ በመውጣት ያለ ፍርድ አይናቸውን በጋለ ብረት አፍርጠው፣ በዱልዱም በማረድ በግፍ ለገደሏቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ተክለጊዮርጊስም ወርዒ ማዶ መታሰቢያ ሊቆምላቸው ይገባል!  በዙፋኑ ላይ ያሉት የዳግማዊ ምኒልክን  ዘመን ታሪክ እያሰየጠኑና ዐማራው በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘን እንዲፈናቀል የርዕዮተ ዓለም ጡንቻ እየሆኑ  ዐፄ ዮሐንስ  ብቻ በዘመኑ ሚዛን መዳኘት አለባቸው እየተባለ ለተጨፈጨፏቸው  ንጹሐን  ሐውልት [ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ወዘተ. . . ሊሆን ይችላል] ይቁምላቸው የማይባልበት የሞራልም ሆነ የሕግ አመክንዮ ሊኖር አይችልም። ጤና ይስጥልን!
Filed in: Amharic