>

ህወሃት ከትከሻ ኦነግም ከአንቀልባ ወርደዋል (መስፍን ማሞ ተሰማ)

ህወሃት ከትከሻ ኦነግም ከአንቀልባ ወርደዋል

መስፍን ማሞ ተሰማ

 

ሠላም ለናንተ ይሁን!

የትግላችንና የመሥዋዕትነታችን የመታሰራችንና የመሰደዳችን ውጤት የሆነው አብያዊው መንግሥት በኢትዮጵያ መንበር ላይ ሲቀመጥ ለ27 ዓመት በምድሪቱ ላይ የሰቆቃና የርኩሰት የጥፋትና የዝርፊያ ሁሉ ቁንጮ የሆነው አሸባሪውና ዘረኛው ህወሃት ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ያለጥርጥር ተመንጭቆ ወርዷል።

የወረደውና የተዋረደው ህወሃት መቀሌ ትግራይ መሽጎ ይንደፋደፋል። በወላለቀ ጥርሱ እየገለፈጠ፤ በተሸበሸበ እጁ እያጨበጨበ በስታዲየምና በአዳራሽ እየተሰበሰበ የቁም ተዝካሩን ያወጣል። ማጋነን የመሰለው በቅርቡ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን ስብሰባ ይመልከት።

በዚያ አዳራሽ የክፉ ሰዎች ስብስብ የሆነው ህወሃት ጣዕረ ሞት ላይ ስለመሆኑ ስብሃት ነጋ በአስረጅነት የቀረበ «አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም» የሚለው ብሂል ማሳያ ነው። 27 ዓመት ዲሞክራሲን ቤተ መንግሥት ሆኖ ሲሰይፍ የኖረው ህወሃት መቀሌ ላይ መሰየፍ ባቃታቸው የጃጁ እጆቹ እያጨበጨበ የፀረ ዲሞክራሲነቱን ተዝካር አውጥቷል።

አሸባሪው ህወሃትና በኢትዮጵያ ምድር በአምሳያው ፈጥሮ የዘራቸው አሜኬላዎች ሁሉ በለውጡ ማዕበል ተጠራርገው የኢትዮጵያ ትንሣዔ ዕውን እንደሚሆን ከቶም አንጠራጠርም። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ህወሃት ከነርኩሰቱና ከነግብረ በላዎቹ መቀመቅ ይወርዳል።

ከህወሃት በተጔዳኝ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እያወከ ያለው ኦነግ ነው። ህወሃት እንደ ድርጅት ከፅንሱ እስከ ውልደቱ፤ ከውልደቱ እስከ ጣዕረ ሞቱ ለኢትዮጵያ ጠንቅ እንደሆነ ሁሉ ኦነግም እንዲሁ ነው። ኦነግ ስለ ኢትዮጵያ መጥፋት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ መኖር አልሞም ሆነ ሰርቶ አያውቅም። ኢትዮጵያውያንን ለመሰየፍና ኢትዮጵያን ለመበተን የሜንጨኛውን ጃዋር እና የለንደኑን የኦነጋውያንን ስብሰባ ፉከራ ዋቢ ማቅረብ ይበቃል። ኢትዮጵያን ማፍረስ እንጂ ማዳን አላማችን አይደለም ያሉትን።

ኢዮባዊ ትዕግሥት የሰፈነበት አብያዊው መንግሥት የኦነግን እኩይነትና በቀል በይቅርታና በንስሃ ለማስተሰረይ በዘረጋለት የሠላም እጅ «ተቀብሎ» ከአስመራ አዲስ አበባ ሲገባ ለኦነግ የተደረገውንና ኦነግ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ያደረገውን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳም። ቡራዩ ይመሰክራልና።

ይህም ሁሉ ሆኖ ለኦነግ «የሳሳ ልብ» የነበረው አብያዊው መንግሥት ባልዋለበት ገድል ጩኸት ያበዛውን ኦነግ በአንቀልባ አዝሎ ሲያባብለው ወራትን አስቆጥሯል። ኦነግ ታዝሎም መዝለሉንና ጀርባ መንከሱን አላቆመም። ኦነግን ያዘለው አብያዊው መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነው። እናም ኦነግ ጀርባዋን እየነከሰ የሚያደማው ሠላም ፈላጊዋን ኢትዮጵያን ነው። ኦነግ ዕብደት ላይ ነው። አብይንና ለማን ወለጋ ላይ አጥምዶ በጥይት ለመጣል ማሴሩን ሰምተናል። አብይ ራሱ በአደባባይ ነግሮናልና። አብይንና ለማን ለመግደል ማቀድ የለየለት ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው።  ኦነግ ታድሶም ሆነ ተሞርዶ ከዕብደቱ ሊድን ከቶም አይችልም።

ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ኦነግንና ኦነጋውያንን አዝላ የምታባብልበት ጀርባ የላትም። መቀሌ ትግራይ እንደ መሸገው አምሳያው ህወሃት ነቀምትና ቄለም ወለጋ ውስጥ የከተመውና በየጉድባው አድፍጦ ህዝብንና ሀገርን የሚያሸብረው ኦነጋዊ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር «መደመር» ከቶም ቢሆን አይችልምና መቀነስ አለበት።

ኦነግን ከታዘለበት አንቀልባ ያወረደውና ክንዱን ሊያነሳ የወሰነው አብያዊው መንግሥት እርምጃው ቢዘገይም ሀገርንና ህዝብን ከኦነግና ኦነጋውያን ጥፋት ለመታደግ አልረፈደምና «ቅነሳው» ይበልጥ ተጠናክሮና ፈርጥሞ ይቀጥል ዘንድ እንጠይቃለን።

ከእንግዲህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኦነግንና ኦነጋውያንን፤ ህወሃትንና ህወሃታውያንን እና መሰል ወዘተርፈዎችን ማዘልም ሆነ መሸከም አንችልም፤ አንገፍግፈውናልና – በቃን በቃን በቃን!!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!

ታህሳስ 2011 ዓ/ም (ዲሴምበር 2018)

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

Filed in: Amharic