>
10:22 pm - Tuesday July 5, 2022

"ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!" የማይቀየር የህወሃት ሎጂክ! (በያሬድ ደምሴ መኮንን)

“ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!” የማይቀየር የህወሃት ሎጂክ!

(በያሬድ ደምሴ መኮንን)

እንደ ህወሃት ያለ ጅል ድርጅት በዚህ ዓለም ላይ ተፈጥሮ አያዉቅም፡፡ ይህ ጅላጅል ድርጅት ለሃያሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን መግዛቱ ያሳፍራል፡፡ በእዉነት ያሳፍራል፡፡ Shame on Us!! የኢትዮጵየን ህዝብ በምናምንቴ አደንዝዘዉት እንጂ፣ በጤናችን እንዲህ የምንሆን አይመስለኝም፡፡ ሞኝ ምን ብሎ ይረታል? እምቢ ብሎ አሉ! ሞኙ ህወሃትም እምቢ ብሎ፣ ድርቅ ብሎ ዛሬም የኢትዮጵያን ህዝብ ለመርታት እየዳከረ ይገኛል፡፡ ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ብንለዉም አልሰማንም፡፡ ዛሬም እንዳለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በእኛ ላይ እቃቃ መጫወት ይፈልጋል፡፡ ህዝብ ከነቃ የለም ዕቃቃ!!

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በቅርቡ በተካሄደዉ ስብሰባ ላይ አቦይ ስብሃት የተባለ ልጡ የተራሰ፣ መቃብሩ የተማሰ አዛዉንት በለስ በቀደደዉ አፉ እንዲህ ሲል ሰማነዉ፡-

“የኢትዮጵያ ህዝብና አሁን ስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት antagonisitic contradiction ነዉ ያላቸዉ፡፡ የማይታረቅ!! አንዱ አንዱን ካላጠፋ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር አትኖርም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መንግስት ጋር የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ደካማ፣ ጸረ ዲሞክራሲ መንግስት ጋር ያለዉ conflict የተለዬ ነዉ፡፡……” (ኡፋፋፋፋ!!! እንዴት ይሰለቻል!! እነዚህ ጭራቆች ዛሬም መቀሌ ዉስጥ ተሸጉጠዉ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር አትኖርም፣ ትበታተናለች….. እያሉ ሲያላዝኑ መስማት እንዴት ያማል?!! ኧረ ዶ/ር አብይ ፍጠን!!)

ይሄ የአቦይ ስብሃት የተንሸዋረረ ሎጂክ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን የአንድ ነፈዝ ሰዉ ታሪክ አስታወሰኝ፡፡ ይሄ ነፈዝ አንድ ቀን ስለዝምብ መመራመር ጀመረ አሉ፡፡ መጀመሪያ የዝምቧን አንድ ክንፍ ቆረጠዉ፡፡ ከዚያም እጁን እያወናጨፈ፣ ድምጽ አዉጥቶ ዝምቧን “እሽሽሽሸ…..” ማለት ጀመረ፡፡ አንድ ክንፏን ያጣችዉ ዝንብ ወንከር ወንከር፣ ደፍ ደፍ እያለች ለመብረር ሙከራ ማድረግ ጀመረች፡፡ ግን አልቻለችም፡፡ ጅሉ ሳይንስቲት ምርምሩን ቀጠለ፡፡ ሁለተኛዉን ክንፏንም ቆረጠዉ፡፡ አሁንም እንደመጀመሪያዉ እጁን እያቃጣ ዝምቧን “እሽሽሽሽ ይላት ጀመር፡፡ ሁለቱንም ክንፏን ያጣችዉ ያቺ ዝንብ አሁን ከነጭራሹ መብረር አልቻለችም ነበር፡፡ እናም ነፈዙ ተመራማሪ እንዲህ ሲል ደመደመ፡፡ “ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!” እንግዲህ ዝምቧ መብረር ያልቻለችዉ ክንፏ ስለተቆረጠ ሳይሆን እሽሽሽሸ ስትባል ጆሮዋ ባለመስማቱ ነዉ፡፡ ጆሮዋ ቢሰማ ኖሮ እሽሽሽሽሽ ሰትባል ትበር ነበር ነዉ ሎጂኩ፡፡

የአቦይ ስብሃት ድምዳሜም ይሄዉ ነዉ፡፡ ዝምብ ሁለቱም ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም እያሉን ነዉ፡፡ የዶ/ር አብይን ጅምር አስተዳደር ለመደገፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሠልፍ የወጣዉ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከአብይ መንግስት ጋር ቅራኔ ስላለዉ ነዉ ብሎ መደምደም ዝምብ ሁለቱም ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም ብሎ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ የተለዬ አይደለም፡፡ ይሄ አባባል እነዚህ የህወሃት ሰዎች በአእምሮ ልምሻ ከመጠቃት አልፈዉ፣ የለየለት እብደት ዉስጥ መግባታቸዉን የሚያረጋጥ ነዉ፡፡ ህወሃት ላለፉት 27 ዓመታት ሲጠቀምበት ኖረዉ ይሄ ሎጂኩ፣ ዛሬም አብሮት አለ፡፡

አንድ ሰሞን የህወሃት ሰዎች  ህዝብ….ህዝብ ማለት ሲያበዙ ግርም፣ ድንቅ ብሎኝ አንዱ ወዳጄን “ህወሃት ግን ህዝብ የሚለዉ ማንን ነዉ?” ስል ጠየኩት፡፤ ወዳጄም ፈጠን ብሎ “ሆዱን ነዋ! ህወሃት ከሆዱ ሌላ ምን ህዝብ አለዉ!!” ብሎ አንጀቴን አራሰዉ፡፡ እዉነት ነዉ!! ህወሃት ህዝብ የሚለዉ ሆዱን ብቻ ነዉ፡፡ ከአብይ አስተዳደር ጋር ያቆራረጠዉም ይሄዉ ህዝቤ የሚለዉ ሆዱ ነዉ፡፡ እናም ሆዳቸዉን እንደ ህዝብ የቆጠሩት የህወሃት ሰዎች፣ ህዝብና የአብይ አስተዳደር የማይታረቅ ቅራኔ ዉስጥ ገብተዋል ሲሉ የሰማናቸዉ ሆዳቸዉን እንደ ህዝብ በመቁጠራቸዉ ብቻ ነዉ!! በዚህ ስሌት መሰረት ህወሃቶች እዉነት ተናግረዋል ማለት እንችላለን፡፡

ይሁን እንጂ አዛዉንቱ እንዳሉት የአብይ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድም ቅራኔ የለበትም፡፡ ምንአልባት አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ በአብይ አስተዳደር ቅር የሚሰኘዉ እነዚህን እዚህና እዚያ እሳት እየጫሩ ያሉትን ጭራቅና ነብሰ በላ የህወሃት ባለስልጣናት ከያሉበት ለቃቅሞ ራሳቸዉ ከገነቡት እስር ቤት ዉስጥ ባለማጎሩ ብቻ ነዉ፡፡ እነ አቦይ ስብሃት ግን በተለመደዉ ሎጂካቸዉ “ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!” ብለዉ ሊያሳምኑን ይዳክራሉ፡፡

ያገሬ ሰዉ “የጠላ ጥርሰ ነጭ ብሎ ይሳደባል” ብሎ ይተርታል፡፡ ህወሃቶች በጥቂት ሳምንታት ዉስጥ ድባቅ የመታቸዉን የዶ/ር አብይን አስተዳደር፣ የሚነቅሱለት ህጸጽ ቢያጡ  ጥርሰ ነጭ ብለዉ እየሰደቡት ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹን አብዝቶ የሚወደዉና “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ” ብሎ ሰርክ የሚቀድሰዉ ዶ/ር አብይ በህወሃቶች ጸረ ኢትዮጶያዊ ተደርጎ ሲፈረጅ ስንሰማ የጠላ ጥርሰ ነጭ ብሎ የመሳደቡን እዉነታ አረጋግጦልናል፡፡ ኢትዮጵያዉያን የምንመኘዉን መሪ ዛሬ አግኝተናል!!

ቆይ…..ቆይ “ከታሪክ የምንማረዉ ከታሪክ ያለመማራችንን ነዉ” ያለዉ ማን ነበር? ማንም ይበለዉ ማንም አባባሉ ቱባ እዉነት አምቆ ይዟል፡፡ እንደ ህወሃት ያለ ከታሪክ ፈጽሞ መማር የማይችል ጅላጅል ድርጅት ግን ምድር ላይ ተፈልጎ አይገኝም፡፡ ከሌላዉ ታሪክ ያለመማሩ አንድ ነገር ነዉ፡፡እንዴት ሠዉ ከራሱ የዉድቀት ታሪክ መማር ያቅተዋል? ዛሬም ከዉድቀት ታሪካቸዉ ሳይማሩ “ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!” ሲሉ ማላዘን ምን የሚሉት ፈሊጥ ነዉ? ለነገሩ ህወሃት ከታሪክ ለመማር ከረፈደባት ቆይቷል፡፡

ደስ ሚያሰኘዉ ነገር፣ ትናንት በጠመንጃ ሩምታ የሃሳብ ነጻነትን ለመከላከል ስትደክም የኖረችዉ ህወሃት፣ አሁን ደግሞ በመቀሌዉ ስብሰባ ላይ የሃሳብ ነጻነትን በጭብጨባ ሩምታ ለመከላከል ስትሞክር ለመታዘብ በቅተናል፡፡ እርግጥ ነዉ ይህ የህወሃት እመርታ የሚያበረታታ ነዉ፡፡ እነሆ ህወሃትም ጊዜ ከዳትና ከጠበንጃ ሩምታ ወደ ጭብጨባ ሩምታ ተሸጋገረች፡፡ ነገ ደግሞ በጭበጨባና በእልልታ ወደመቃብሯ ታዘግማለች፡፡

ዶ/ር አብይ በትረ ስልጣናቸዉን በጨበጡ በጥቂት ሳምንታት ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፓርላማ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት “የፖለቲከኞቻችን ችግር ነገር ሲሞትና ነገር ሲድን ያለማወቃቸዉ ነዉ!!” ብለዉ መናገራቸዉን አስታዉሳለሁ፡፡

አዎ! የህወሃት ባለስልጣናት ትልቁ ችግራቸዉ ይሄዉ ነዉ፡፡ ነገር ሲሞትና ነገር ሲድን አያዉቁም፡፡ አሁን የህወሃት ነገር ሞቷል!! የቀረዉ ግብአተ መሬቱ ነዉ፡፡ ይሄም በቅርቡ በደማቅ ስነስርአት ይፈጸማል ብለን እናምናለን፡፡ የወጣቱ አምዶም ገብረ ስላሴ ድፍረት የተሞላበት የቅርብ ጊዜ ንግግር፣ በህወሃት መቃብር ላይ አረና የተባለ የወጣቶች ፓርቲ አብቦ በመዉጣት፣ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጥፋት ይታደጋል የሚል ጽኑ እምነት እንዲኖረኝ አስችሏል፡፡ ያኔ እኛም ከህወሃት “ዝምብ ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም!!” ሎጂክ እንገላገላለን፡፡ ብራቮ አምዶም!! ብራቮ!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

Filed in: Amharic