>

ለሠራዊት እኔው ራሴ ምስክር ነኝ በተለይም በሁለት ጉዳዮች !!!  (ዘመድኩን በቀለ)

ለሠራዊት እኔው ራሴ ምስክር ነኝ በተለይም በሁለት ጉዳዮች !!!  
ዘመድኩን በቀለ
 “…የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥… ዮሐ 3፣ 11
 አንደኛውን ምስክርነት እነሆ ንሱ ተቀበሉኝማ።
የዚህችን ጊዜ የሰጣትን የድንጋይ ሰባሪዋን ቅልና ጮርቃ ክበረ ቢስ ጋጠወጥና አሳዳጊም የበደላት “ሰኞ ጠዋት ዝናብ ዘንቦ ፊት” የመሰለችዋን ደግሞም መረን የለቀቀች፣ ጋዜጠኛ አሰዳቢዋን፣ እንዲሁም ሃይ ባይ ያጣችዋን የ LTV ዋን ቤተልሄም ታፈሰንና፤ ዘመን የከፋበት፣ ቀንም የጣለው፣ ምሳር የበዛበትን የአርቲስት ሠራዊት ፍቅሬን ቃለ መጠይቅ ዓይቼ በፈጸምኩ ጊዜ ይህቺን አጭር ምስክርነት ጻፍኩ። ከምር ሠራዊት አሳዘነኝ። 
ቤቲ ደፋር የጨበጣ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ኦሮሞ መሆኗ እና ዘመኑ የኦሮሞ ነው መባሉ ደግሞ የሌለ ደፋር ሳያደርጋት አይቀርም። ፕሮቴስታንት በመሆኗ ከዚህ ቀደም በፓስተሮቿ ላይ ታሳይ የነበረውን ዕውቀት አልባ ድፍረት የተሞላበትን ጠያቂነቷን ብዙዎች ወድደውላት ስላጨበጨቡላት ጭብጨባው አስክሯት ትይዝ ትጨብጠውን አሳጥቷት በድፍረቷ ቀጥላበታለች።
ለመለስ ዜናዊ ሲሞት ለምን አለቀስክ ? ብሎ የሚጠይቅ ጋዜጠኛ ከቤቲ በቀር በዚህ ዘመን ከወዴት ይገኛል። LTV የኦሮሞው ፓስተር ገመቺስ የግል ንብረትና ፓስተሩም የጠቅላያችን ፓስተር እንደ ንስሃ አባቱ ያለ ሰው ስለሆነ የቴሌቭዥን ጣቢያው የቀድሞው ሥርዓት ደጋፊ ነበሩ የሚባሉትን ሁሉ እየመረጠ ንስሃ የሚያስገባ፤ እንደ ጃዋር ያሉትን ክቦ እንደ የአብኑ ዶር ደሰላኝ እና ሠራዊት ፍቅሬ ያሉትን ደግሞ ለማዋረድና ለማሸማቀቅ የሚጠቀሙበት የማጥቂያ መሣሪያም ሆኗል። ሆሆይ! መለስ ዜናዊ ሲሞት ለቅሶ ደርሰሃል፣ ለቅሶ የሚደርሱትንም አስተባብረሃል ብሎ ጥያቄ ምን ማለት ነው? መጠየቅ ካለበት በመረጃ አስደግፎ ማንጰርጰር ሲቻል በእንጀራው ገብቶ መፈትፈት ነውር ነው።
ሠራዊት የማስታወቂያ ሠራተኛ ነው። አርቲስትም ነው። የፊልም ባለሙያ ነው። ሠራዊትና ሙሉዓለም ለምን አይጋቡም ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በየቤቱ እስኪ ጨነቅላቸው ድረስ በዘመናቸው እጅግ የሚገርም ጥምረት ፈጥረው በሚሠሩት ማስታወቂያ ያስደመሙን ባለሙያዎች ነበሩ። በወቅቱ ሠራዊትና ሙሉዓለም ያሉበትን ማስታወቂያ መመልከት አጭር ድራማ ከማየት እኩል ይቆጠር እንደነበር አስታውሳለሁ።
የማስታወቂያው፣ የድራማና የፊልሙ ዝና ሠራዊትን በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ አደረገው። እናም መንግሥትም ሆነ ድርጅቶች ለሚሠሩት ሥራና ለአቀዱዋቸው ፕሮጀክቶች ከሠራዊት ጋር ቢሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገምተው ሠራዊትን ፈልገው ማሠራታቸውን ቀጠሉ። ሠራዊቱም ጊዜና ዘመን ዕድልም የሰጡትን በአግባቡ ተጠቀመበት። እነሱ ይከፍላሉ፤ እሱ ያስከፍላል። አከተመ ።
ሠራዊት ከተናገራቸው ውስጥ ቢያንስ በሁለቱ ክሶቹ ውስጥ እኔም በኮሚቴነት የተሳተፍኩባቸው ስለነበሩ አፌን ሞልቼ እመሰክርለታለሁ። ሰውየው በሌለበት፣ ባልዋለበትም ነገር ሲከሰስ ሳይ ከምር አሳዘነኝ። እኔን ሠራዊት ያውቀኛል እንጂ እኔ ሠራዊትን አላውቀውም። ሠራዊትን እንደማንኛውም ዜጋ በሙያው በቴሌቭዥን መስኮት የማየው ሰው ነው።  አንድ ቀን ሂልተን ሆቴል፣ ሌላ ቀን ደግሞ ቤተ መንግሥት በስብሰባ ምክንያት ከመገናኘታችን በቀር ሠራዊትን አላውቀውም።
የሂልተኑን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። አቶ ሬድዋን ሁሴንን የዘረጠጥኩበትና በሻይ ሰዓት ደበሽ ተመስገንና ሠራዊት ሰውዬውን ሳላውቀው የተናገርኩት መስሏቸው ሊያስረዱኝ የጣሩበትን በብርቱም የደከሙበትን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለዛሬ ግን ሠራዊት ቤተ መንግሥት በነበርን ጊዜ የገጠመውን ገጠመኝ እኔ ዘመዴ ራሴው ምስክር እቆምለታለሁ። ራሴው ነኝ የግድ ሲሉት የማይለቁህ ከሆነ እሺ በላቸው ብዬ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጎን  እንዲቀመጥ የገፋፋሁት።
መድረኩን እንዲመራ የመረጥነው የቶም ቪድዮው ባለቤት አቶ ቶማስን ቢሆንም እኔና ሠራዊት ቁጭ ብለን ሠራዊት ስለ “ግሪሳዎቹ” እየጠየቀኝ ሳለ ድንገት የቤተ መንግሥቱ የፀጥታ ሰዎች መጥተው አስገድደው ባልተዘጋጀበት መድረክ እንዲወጣና መድረኩን እንዲመራ እንዳደረጉት እኔው ራሴው ምስክር ነኝ። በዕለቱ 3 ተኛው ጥያቄ አቅራቢ እኔው ዘመዴ ራሴ ነበርኩ። የተመደበልኝን ደቂቃ ሠራዊት ቢከለክለኝም መለስ ዜናዊ ተወው ይናገር ብሎ ፈቅዶልኝ ነበር የኮፒራይት ብሶቴንና የዘርፉን ችግር ከተመደበው ደቂቃ በላይ ወስጄ እንደልቤ የተነፈስኩት። አቶ መለስም እርስዎ እንዳሉት እኛም በፖሊሶቻችን ሥራ ተቸግረናል። ወንጀለኛ ይዘው ፍርድ ቤት እንዲያደርሱ ስንልካቸው እነርሱ በቦሌና በባሌ እያሸሹ ተቸግረናል የሚል መልስ የሰጠኝም ያንጊዜ ነበር።
ኮሚቴዎቹም ያሬድ ሹመቴ፣ ሰርፀ ፍሬሰንበትና እነ ሃይማኖት ዓለሙን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ባለሙያዎችንም ያካተተም ነበር። ሠራዊት በኮሚቴው ውስጥ አልነበረም። አልተሳተፈምም። በዕለቱም እንደማንኛውም ባለሙያ በስብሰባው ለመሳተፍም ነበር የመጣው። መጥቶም በማያውቀው ጉዳይ በድንገት ብቻ ሳይሆን በግድ መድረኩን እንደመራ የተደረገው። ለዚህ ደግሞ እደግመዋለሁ እኔ ራሴው ምስክር ነኝ።
ሠራዊት ከፀጥታ ሰዎቹ ጋር ሲጨቃጨቅ ግድየለም እሺ በላቸው። እገሌ ከእገሌ ቀጥሎ ጠይቅ ማለት አያቅትህም። እሺ በላቸው ብዬ ወረቀቱን አስመጥቼ ለሠራዊት እንዲያጠናው የሰጠሁትም እኔው ራሴ ነበርኩ። አንተ ደግሞ ከመለስ ዜናዊ ኋላ ትቀመጣለህ ብለው ቀጭን ትእዛዝ ከነምቀመጥበት ወንበር ጭምር ወስደው ቀድመው ያሳዩኝም እነዚሁ የጸጥታ ኃላፊዎቹ ነበሩ። ዝርዝር ጉዳዩን በሰፊው በሌላ ቀን የምመጣበት ይሆናል።
በወቅቱ የኢህአዴግም፣ የህወሓትም፣ የኦህዴድና የብአዴን አባል የነበሩ፣ ከኢህአዴግ በላይ ኢህአዴግ የነበሩ፣ ዛሬ ደርሰው ዐብይ ከሰሜን ኮሪያ የመጣ ይመስል ማልያ ቀይረው ሠራዊትን ሊከሱት ሲያሰፈስፉ ሳይ እኔ በበኩሌ  አፈርኩላቸው። በወቅቱ ሁላችንንም ቤተ መንግሥት የሠበሰበን የኮፒ ራይት ጉዳይ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ መፍትሄ ይሰጡን ዘንድ ለአቤቱታም ነበር የሄድነው። ሌላ ምንም ኮተት የለውም።
በወቅቱ የህወሓት ቬሎ ያዥ የነበረና በመደመሩ ሰበብ በአቋራጭ አሁን ሰሞኑን ባለሥልጣን የሆነ ፈጣጣ ሰውም አውቃለሁ። ደርሶ ለመወደድ ሲባል በሃላል ህሊና ባይሸጥ መልካም ነው። ሠራዊት የሚወቀስበት ነገር ካለ እንደማንኛውም ሰው ቢወቀስ ተቃውሞ የለኝም። ሠራዊት እኮ ዐባይ ፀሐዬም አልነበረም፣ አባዱላም አልነበረም። አቦይ ስብሃትም አልነበረም። ስኬታማና ዕድል ፊቷን ያዞረችለት የማስታወቂያ ሠራተኛ ነበር። ነገር ግን ልጁ በተሳካለት ዘመን በስኬቱ ምራቃቸውን ሲውጡና ዓይናቸው ሲቀላ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ደርሰው የለውጡ ሐዋርያ ሆነው ዊኒጥ ዊኒጥ ማለታቸው ሳያንስ እንደ በሬ ልወጠር ባይዋን እንቁራሪቷን ጋጠወጥ ሴት ጋዜጠኛ ተብዬዋን ቤቲን እንደ ፈረስ ተጠቅመው ሰው እየመረጡ ለመጉዳት፣ አንገትም ለማስደፋት የሚራወጡትን ሳይ ግን ይነስረኛል። [ እኔ በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመህ ይቅርታ የምትጠይቅ ከሆነ እንድትጠቀምበት ነው ] እያለች የንስሃ እናት እንድትሆን ይህቺን ሴት መብት የሰጣት ማን ይሆን እልና ወዲያው መልሱን አገኘዋለሁ። #ጌዜ ነው። ጊዜ ጌታ።
ዐቢይና ለማ፣ ደመቀና ገዱ ምን ነበሩ እንዴ? ኦፌኮ፣ ኦብኮ፣ ቅንጅት ወይም መኢአድ እኮ አልነበሩም። ከተቃውሞው ጎራ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙም አልነበሩም። እንዲያውም እነ ደመቀ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዋነኛ አጥማቂ ሐዋርያ የነበሩ እኮ ናቸው። ለዐቢይና ለለማ፣ ለገዱና ለደመቀ፣ ለሙፈሪያትም ይቅርታን ለግሶ ይቅር ያለና ሞቴን ከእናንተ ጋር ያድርገው የሚለው ህዝብ አንድ በሙያው እንጀራ ሲበላ የነበረን ሰው እንዲህ ጠምዶ ይዞ መንዘፍዘፍ የጤናም አይመስልም። ቅናት ክፉ ደዌ ነው። የስኳር ማስታወቂያ ለምን ሠራህ?  ይባልልኛላ !
ኢህአዴግ እንደድርጅት፣ የኢህአዴግ መሪዎችና የፓርቲው አመራሮችና አባላት ደጋፊዎችም ሁሉ ይቅርታ ሳይጠይቁ ሠራዊት ፍቅሬ ይቅርታ የሚጠይቅበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም። ዛሬ ለአቢቹ የሚያሽቃብጡ አርቲስቶችም ሆኑ ሌሎች ነገ እንዲሁ ቀን ሲከፋ ብድራቱን ትቀበላላችሁና በምትሰፍሩት ቁና ሳይሰፈርባችሁ በፊት አስሬ ለክታችሁ አንዴ ብትቆርጡ መልካም ነው። ብልት ላይ ሃይላንድ ሲያንጠለጥል የነበረን፣ በ1997 ዓም በቅንጅት ሰበብ የአዲስ አበባን ህዝብ በጅምላ የፈጀውን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን የውጭ ጉዳይ አድርጎ ሾሞ በማስታወቂያ ባለሙያነቱ አስከፍሎ እንጀራውን ይበላ የነበረን ሰው ይቅርታ ካልጠየቅክ ብሎ ማስጨነቁ ለእኔ አስገድዶ ከመድፈር ለይቼ አላየውም።
የሠራዊት ” ስለለውጡ ሲናገር ስጮኽለት የነበረው ለውጥ ነው ” ማለቱ ድፍረት ቢሆንም ነገር ግን በውስጠ ታዋቂነት ይጮኽ እንደነበርስ ማን ያውቃል? የዛሬዎቹ የለውጥ ኃይሎች እየተባሉ የሚወደሱት እነ አቢቹና እነ ቲም ለማን ይህን ማዕረግ ከሰጠናቸው ሠራዊትስ የግድ መለፍለፍ ነበረበት ወይ?  ሌላውን ገዳዩን ሁላ ይቅር ብለን በሠራዊት ላይ ሠይፍ መምዘዙም ደግም አይደል። ጊዜ ተለዋዋጭ ነው። የጌዚ እንጂ የሰው ጀግና የለውም። ምናልባትም ነገ ቤቲን ራሷን ነገ ” ማን ጠያቂ አደረገሽ?  ማን ጋዜጠኛ አደረገሽ?  የት ተማርሽ?  እንዴት ጋጠወጥና መረን የለቀቀች ሴት ሆንሽ?  ከጀርባሽ ማን ነበረ?  እናም ባልሽን ለምን ፈታሽ?  የሚላት ዘመን ይመጣ ይሆናል።
በትናንትናው ዝግጅት ግን ሠራዊት ከበቂ በላይ በሆነ ልበ ሙሉነት ከቤቲ ጀርባ የነበሩትን፣ ጥያቄ አውጥተው የሰጧትን፣ የልጁን መውደቅ ይጠባበቁ የነበሩትን ሁሉ በዝረራ አሸንፎ ወጥቷል። በእውነት የሁሉንም አርቲስቶች ጦስ ተሸክሞ የመስዋዕት በግ ሆኖ የቀረበው ሰው ነው አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ።
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፣ እና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ አፉ በሉን። እናንተን የመሰለ የምርመራ ጋዜጠኞችን ባየንበት ዓይናችን አሁን ደግሞ ዊኒጥ ዊኒጥ ባይ ደርሶ የሹም ዶሮ የሆነች ጋዜጠኛ ነኝ ባይ ባለ ጊዜ በዓይናችን ላይ ጢባጢቤ ትጫወትብናለች።
ደግሞም ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ” ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት ።” ዮሐ 8፣7 ሠራዊት ላይ ለመፍረድ መጀመሪያ ይሄን የጌታ ጥያቄ በጽሞና መመለስ በቂ ነው።
ሻሎም !  ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ታህሳስ 18/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic