>

ህወሓት የደገፈችው ሁሉ  መጨረሻው አላማር አለሳ!!!  (ዘመድኩን በቀለ)

ህወሓት የደገፈችው ሁሉ  መጨረሻው አላማር አለሳ!!!
 ዘመድኩን በቀለ
* ” Thank you ” ብለው ሰልፍ የወጡለትም አልበሽርም ከዙፋኑ መመነገሉ እየተነገረ ነው። በቀጣይ ማን ይሆን ባለ ሳምንቱ? 
“ህወሓትን” ልቧ ድፍን ሆኖ እንጂ በምድርም በሰማይም፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጬም፣ ምዕራባውያንም ምሥራቃውያንም፣ ሶሻሊስቱም ካፒታሊስቱም ሁሉም እየከዷት መሆኗን መወቅ መረዳት ነበረባት የሚሉ አሉ። እሷ የደገፈችው፣ የጮኸችለት፣ የድጋፍ ሰልፍ የወጣችለት ሁሉ አንዳንዱ እየታሰረ፣ ሌላው እየፈረሰ ነውም ይላሉ። ምርቃቷ እርግማን እየሆነም ተቸግረዋል ወዳጆቿ።
– የሱማሌው አብዲ ኤሌን ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ ቢጮኹለትም ከቂሊንጦ አላዳኑትም። – አላሙዲም በሳኡዲ ቂሊንጦ ነው ያለው።
– ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያጩት ሽፈራው ሽጉጤ እንኳ የአምባሳደርነት ቦታም ተነፍጎ ቢጫዋን ሂሊኮፍተር እየጠበቀ ነውም የሚሉ አሉ።
– የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉልና የአፋር አጋሮቿም በአቢቹ እጃቸውን ተጠምዝዘው ዙፋናቸውን አስረክበዋል። የሐሬሬው እንኳ አልቀረም ወደ ቂሊንጦ ሲወርድ።
ህወሓቶች በምድር ላይ ከቀሯቸው ጥቂት የልብ ወዳጆች መካከል የሳሞራ የኑስ የቅርብ የሥጋ ዘመድ እንደሆነ የሚነገርለትና የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላቷ የሱዳኑ መሪ አልበሽር አንዱና ዋነኛው ነበር። “ከነፍጠኞቹ ዐማሮች የአፄ ዮሐንስ አንገት ቆራጩ አልበሽር በስንት ጣእሙ” የሚል መፈክርም በመቐለ የተሰማው በዚሁ ባሳለፍነው ወር ውስጥ ነበር። በደቡብ ሱዳን ባንዲራ የሰሜን ሱዳኑን መሪ የአቶ አልበሽርን መንግሥት የሚደግፍ የድጋፍ ሰልፍም በመቐለ ከተማ የተወጣውም በዚሁ ባሳለፍነው ወር ውስጥ ነበር። የፈራነው አልቀረም የመቐሌው የአልበሽር የድጋፍ ሰልፍ ወደ እርግማንነት ተቀይሮ ይኸው አልበሽርን ጉድ ሠራው እየተባለ ነው።
አሁን የአልበሽርም የአገዛዝ ዘመኑ አበቃ። አልበሽር ሶርያ ሄዶ የሶርያውን ኣሳድን ጎብኝቶ ከተመለሰ ወዲህ በሀገሩ ሱዳን የተቀሰቀሰው አመጽ ዛሬ ፍጻሜውን ማግኘቱም እየተነገረ ነው። የኩዋታሩ አሚር ዶላር ተሸክመው የአልበሽርን መንግሥት ለመርዳት ካርቱም ድረስ ቢመጡም የአልበሽርን መንግሥት ከመፈረካከስ ሊያድኑት አልቻሉም።
እኔ አሁን የምሰጋው፣ የምፈራውም ህወሓት ሃሳቧን ቀይራ የጠሚዶኮ ዐቢይን መንግሥት ደግፋ ሰልፍ እንዳትወጣ ብቻ ነው። እንዲያ ካደረገች የአቢቹ መንግሥት አለቀለት። በአብዲ ኢሌና በአልበሽር ላይ የደረሰው ዕጣም እንዳይደርሰው እሰጋለሁ። እነሱ ከደገፉት ውስጥ አንድም በረካ የሆነ አለመኖሩን ሳይ ደግሞ ስጋቴ ይጨምራል።
የሱዳን ዐመጽ መነሻው በዳቦ ላይ ጥቂት የሳንቲም ጭማሪ መደረጉ እንደሆነ ተነግሯል። ይሄ ህዝብ ለማመጽ እንደመነሻ ምክንያት ነው። መቶሺ ብር ከአቅሙ በላይ ግብር ሲከፍል እየነሰረውም ቢሆን የሚከፍለው ህዝብ ከጠላህና ሊጣላህ ሲፈልግ በዳቦ ላይ አምስት ሳንቲም ተጨመረ ብሎ ቀውጢ በመፍጠር ጉድ ይሠራሃል። የስንዴ ዱቄት መጥፋት ዳቦ ላይ ሳንቲም እንዲጨምር መደረጉ የአልበሽርን መንግሥት አፈር ከደቼ አስግጦታል። ይሄ ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት መሪዎች ከባድ መልእክት ነው የሚያስተላልፈው። በተለይም ለኢትዮጵያችን።
በኢትዮጵያ እስከአሁን የተደረገው አብዮት የነፃነት አብዮት ነበር። የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት ነፃነት እንዲኖር ነበር ብዙዎች የተሰዉት። እሱ ነገር ከሞላ ጎደል እየተሳካ ያለ ይመስላል። ይመስላል ነው ያልኩት። ነው ለማለት አንዳንድ ቦታ አሁንም መደራጀት ክልክል መሆኑን እያየን ነውና ለዚያ ነው መጠራጠሬ። መናገር ፣ መጻፍ፣ መደራጀት መቻል ብቻውን በራሱ ዳቦ አይሆንም። እየጻፍክ፣ እየተደራጀህ፣ በነፃነት እየተናገርክም እቤትህ ስትመለስ ዳቦ ከሌለ ትግሉ ይቀጥላል ማለት ነው። አንተ እየተራብክ አቢቹ ሞዴል መስሎ እየተሽቀረቀረ ቢቀርብ እሱ ምግብ አይሆንህም። የአቢቹ መንግሥት ቢሮውም፣ ራሱ አቢቹም ምን ቢዋቡ፣ ምን ቢሽቀረቀሩ ምግብ አይሆኑም። ውበቱ ለራሱ፣ ለሚስቱና ለልጆቹ ብቻ ነው።
እናም ወዳጄ በቀጣይ የአቢቹ መንግሥትም ከጎረቤት ሱዳን መማር አለበት። በአስቸኳይም የኢኮኖሚ ማሻሻያ ካላደረገ በቀጣይ በመላው ኢትዮጵያ ” የኢኮኖሚ ነፃነት አብዮት” የአቢቹን መንግሥት አሰፍስፎ ይጠብቀዋል። አሁን እንኳ መቐሌ ስንዴ የለም። ዱቄት የለም። 100 ግራም ዳቦ 2 ብር 50 ሳንቲም እየተሸጠ ነው። አዲስ አበባ የሽሮ ዋጋ ጣሪያ መንካቱ እየተነገረ ነው። የዳቦ ሰልፍ፣ የታክሲ ሰልፍም እንደዚያው። ሥራ አጡም የትየለሌ ነው። የቤት ኪራይ ጨራቃ ላይ ወጥቷል። እናም መንግሥት በቶሎ እንዲያስብበት መምከሩ አይከፋም። ይህቺው የተጀመረች የነጻነት ጭላንጭል ድርግም ብላ እንዳትጠፋ ከወሬ፣ ከስብከትና ከፋሽን ሾው ትርኢት፣ ከዲስኩርም ተላቅቆ ኢኮኖሚው ላይ መሥራቱ መልካም ይመስለኛል።
ያም ሆነ ይህ መቐሌዎች አቋሟቸውን ቀይረው የአቢቹን መንግሥት መደገፍ እንዳይጀምሩና እንዳያሟርቱበት መጸለዩም አይከፋም። የደገፉት ሁሉ ትርፉና መጨረሻው መፍረስና ከርቸሌ ከሆነ ባይደግፉት ይሻላል የሚሉም አሉ።
ሻሎም !  ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ታህሳስ 20/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic