ነብዩ ሲራክ
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ለሀገሩ ያለው ፍቅርና ለቤተሰቡ ያለው ታማኝነት አይዘነጋኝም
የገናው ዋዜማ የቦን ሰማይ የሚያዘንበው ካፊያ በረዶ ጭምር ነው። በዚያ ሰማይ ስር ቦን በነጭ በረዶ ተጀቡና ፤ የራይን ወንዝ ከበረዶው ቀልጦ የሚፈሰውን ውሃ ከዚያና ከዚህ እየተቀበለ ከተማውን ገምሶ ይጓዛል። የኤርትራን ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆንን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ የጀርመን ራዲዮ ጋዜጠኞች የገናው ዋዜማን የሀገረ ቦንን ብርድ ለመከላከል ደራርበን የለበስነው ልብስና ግር እያልን ወደ ሆቴል ስንገባና ስንዎጣ ለከተማዋ እንግዳ ባይተዋሮች መሆናችን ያሳብቃል ። የሁሉም ሀገር ጋዜጠኞች ጀርመን ነዋሪ የሆኑ ባልደረቦቻቸው እየመጡ ይዘዋቸው ይወጣሉ ። ሀገሩንም ያስለምዷቸዋል ። ከእንግዶች እኛን የሀበሻ እንግዶቹን ሀገር ለማሳየትና ለማለማመድ ከእንግዶች መካከል የማይጠፋውስ እሱ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ነበር …
… መሳይ ከጀርመን ራዲዮ በፊት በደቡብ መገናኛ ብዙሃን በሚያቀርባቸው የተደራጁ ሪፖርቶቹ አውቀዋለሁ ። ከሚወደው ሙያው ብቻ ሳይሆን ከሚወዳት ኢትዮጵያና ቤተሰቡ ተገዶ የተሰደደ ትጉህ ጎልማሳ ነው ። መሳይ በሀገረ ጀርመን የጀርመን ራዲዮ ባልደረባ ሆኖ ባሳለፋቸው አጭር ወራት በሰራቸው ጉልበት ባላቸው ዘገባና ዝግጅቱ ይታወቃል ። በወቅቱ የጀርመን ራዲዮ በኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ተጽዕኖ እየደረሰበት ነበርና ራዲዮ ጣቢያው በሽኩቻ በፈዘዘበት ወቅት ጣቢያውን ያነቃቃው መሳይ እንደነበር ዛሬ የሚደበቅ አይሆንም ። መሳይ ድፍረት በተሞላበት የአቀራረብ ስልቱ ብቻ ሳይሆን በመረጃ ምንጩ ምጡቅ ነበርና ይደነቃል ። የጀርመን ራዲዮ የስልጠ ጉብኝት መሳይን በዝና ከማወቅ ባለፈ በአካል እንዳውቀውና እንድንቀራረብ ጊዜው ፈቀደ …
በወቅቱ መሳይ ለሀገረ ጀርመን ሰማይ ምድር አዲስ ነበር ። ቦን በነበረኝ ጉብኝት ምናልባት የመሳይ ቆይታ ከ6 ወር ያለፈ የነበረ አይመስለኝም ። ከመሳይ ጋር በገና ዋዜማ ከሆቴል ወጣ እያልን ገበያውን ፤ ሱቆችንና ዙሪያ ገባውን ፈትሸናል፤ ዘና ብለን መልካም ጊዜን ስናሳልፍ ማታ የፈለገ አምሽቶ ማለዳ ቀድሞ በስራው ይገኝ እንደነበር አይረሳኝም … ከብርቱው ወዳጄ ከጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ጋር በነበረን ቆይታ ሀገር ወዳድ እምነት አክባሪነቱን ፤ ድፍረት እውነቱን ፤ ሙያው አክባሪ ትጋቱን በሚገባ ታዝቤያለሁ ።
ከመሳይ ጋር በጫዎታ መካከል ሁልጊዜ ቢደጋግም ሲያነሳ የማይሰለቸው ፤ የሚያብሰከስከው ጉዳይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው ። ሀገሩ በክፉ የህዎሃቶች አገዛዝ እጅ ገብታ መታመሟ የዘወትር ህመሙ ነበር። በሀገርና በወገኑ ላይ የሚደርሰውን በደል ይቆጭ ያንገበግበው ነበር ። ከመሳይ ጋር ከኢትዮጵያ ውጭ ወግ ከተጀመረ እኔ ሰለ ከልታማው የሳውዲ ስደተኛ ብሎም ስለሞቀው የሳውዲ ጎጆየና ድክ ድክ ማለት ስለጀመረው የበኸር ልጀ እዮብ አጫውተዋለሁ ። መሳይ ደግሞ ተገፍቶ ከሀገሩ ከመሰደዱ ጥቂት ወራት በፊት ከፈጣሪ ስለተሰጠው የልጅ ፍሬና የትዳር ጓዱ ውድ ባለቤቱ ናፍቆት ሲያወራ ውሎ ቢያድር አይጠገብም ። ከደቡክ ክልል ራዲዮ ወደ ሀገረ ጀርመን ለመጣው መሳይ ከብርዱ እኩል አልለመድ ያለው የሀገርና የቤተሰብ ፍቅሩ እንደነበር ምስክር የመሆን እድል ገጥሞኛል ። እነሆ የገና ዋዜማ ሳስታውስ ወዳጀ ጋዜጠኛ መሳይ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና ለቤተሰቡ ያለው ታማኝነት አይዘነጋኝም !
የክረምቱን ወፋፍራም ብርድ ልብስ ባንደራርብም የሚሞቀን እኔና የሀገረ ኤርትራ የጀርመን ድምጽ ዘጋቢ ጎይቶም ቢሆን ነበርን ። ጎይቶም ከአስመራ ጀርመን ቦን በመገኘቱ ነፍሱ በሃሴት ደምቃለች፡፡ ከኤርትራው የከፋ አገዛዝ ስር ወጥቶ አውሮፓ ጀርመን ቦን መታደሙ ተአምር ነበር ። በእግጥም ከሲኦን ወጥቶ ገነት የመግባት ያህል ሆኖ ማናችንም አስደስቶናል። ነፍሱ ከሶኦል ወደ ገነት በድንገት የተወረወረችና የተረፈች ያህል ነውና ስሜቱ ጋዜጠኛ ጎይቶም ፈጣሪ ደጋግሞ ያመሰግናል፡፡ ጎይቶም ደሰተኛ ነውና ብርዱ ምናምኑ አይሰማውም. . .! እኔ ግን መሳይ ስራ በዝቶበት ከጠፋብኝ ይበርደኛል ። ሲበርደኝና ድብርት ሲወረኝ ደግሞ ከአጠገቤ ያለችውን የጎይቶም ክፍል ኳ ኳ አደርጋለሁ ! ብዙ ጊዜ ደግሞ ጎይቶም አይተኛምና ተያይዘን ወደ ሚያማምሩት የምሽት ክለቦች ውልቅ እንላለን . . . ! እናም በገና ዋዜማ ባንዱ ቢራ ቤት ጎራ ብለን ፉት እያልን ወጋችን እንሰልቀዋለን፡፡ . . .
እኔም ሆንኩ ጎይቶም ከስራ ውጭ ይዞን ከተማዋን የሚያስጎበኘን ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን አልፎ አልፎ ምሽት ላይ ሳይቀላቀለን ሲቀር ይከፋናል ። ያም ሆኖ አመሻሽቶ ሳያየን አያድርም ። መሳይ ምሽት ላይ የመዘግየቱ ምክንያት የጀርመን ራዲዮ ጣቢያን በአዲስ ሃይል ያሟሟቀበት ወቅት ነበርና መዘግየቱ ይገባናል ። ፈጣን ፤ ብርቱና ዝግጅቶችን የማቀነባበርና የማዘገጃጀት ክህሎትን ከተካነው ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ጋር የነበረን የገና ዋዜማ ትዝታ ከቦን እስከ ኮሎኝ የዘለቀ ፍጹም የማይረሳ ውብ ትዝታ ነውና አብሮን እስከ ወዲያኛው ይዘልቃል !
ነቢዩ ሲራክ
ታህሳስ 20 ቀን 2011 ዓም