>
9:54 am - Sunday November 27, 2022

የአማራው ፖለቲካ መጠለፍና ህወሓት በቀደደው ቦይ የመፍሰስ አደጋ! (መሀመድ አሊ መሀመድ)

የአማራው ፖለቲካ መጠለፍና ህወሓት በቀደደው ቦይ የመፍሰስ አደጋ!
መሀመድ አሊ መሀመድ
ከአማራው ፖለቲካዊ ትርክትና ሥነ-ልቦና አንፃር የዘር/የብሔር አደረጃጀትና አጀንዳዎቹ መገለጫዎቹና ቁመናውን የሚመጥኑ; ብሎም ዘላቂ ጥቅሙን የሚያረጋግጡ አይደሉም። አማራው በዚህ ጠባብ መንገድ ብዙ ርቀት ሊሄድና ሄዶም ብዙ ማትረፍ አይችልም። ይህን መንገድ ህወሓት ሄዶበታል።
የህወሓት መንገድ መጨረሻው ገደል መሆኑን ቀድመው የተገነዘቡት ራሳቸው የድርጅቱ ጠንሳሾች ናቸው። አንዳንዶቹ ቀድመው ድርጅቱን ለቀዋል ወይም ተገፍተው እንዲወጡ ተደርገዋል። ድርጅቱ ያኔ በለጋ ዕድሜው “ነፃ የትግራይ ራፐብሊክን መመሥረት” የሚለው አጀንዳ የተቀለበሰው በድርጅቱ አባላት ባካሄዱት የውስጥ ትግል እንደሆነ ይታመናል። ምናልባትም በወቅቱ የነበረውን ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ከስልት አንፃር አዋጭ ላይሆን ይችላል ከሚል መነሻም ሊሆን ይችላል ብሎም መጠርጠር ይቻላል። ዛሬ ላይ አንዳንዶች የሚመዟት የማስፈራሪያ ካርድ ጥርጣሬውን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ናቸው።
የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ ብሎ የተነሳው ህወሓት የትግል አድማሱን አስፍቶ ለኤርትራ ነፃነትም ከሻዕቢያ ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል። እንዳውም በአንድ ወቅት ሻዕቢያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመደራደር ፍላጎት ሲያሳይ “ከጳጳሱ ቄሱ” እንዲሉ እነመለስ ዜናዊ “የኤርትራ የነፃነት ትግል ሊቀለበስ አይገባም” ከሚል ሙግት በመነሳት መጽሐፍ እስከማሳተም ደርሰዋል። በውጤቱም ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠልና በተለይ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን እንድታጣ ተደርጓል። በአፍሪካ በደም አፋሳሽነቱ ከሚጠቀሰው የነፃነት ትግል ኤርትራውያኑም አትራፊ እንዳልሆኑ ዛሬ ላይ በቁጭት ሲናገሩ ይደመጣል።
ህወሓት ኤርትራ እንድትገነጠል ከማድረግ በመለስ ኢትዮጵያውያን በዘር እንዲደራጁ በማበረታታትና ኢትዮጵያን በግዛተ-ቋንቋ በመሸንሸን ጣሊያኖች ሞክረው ያልተሳካላቸውን የቅኝ አገዛዝ ህልም እውን ማድረግ ችሏል። ለዚህም ይመስላል አንዳንዶች “ባንዳ” ሲሉ የሚፈርጁትና ጥጉን እንዲይዝ (corner) የሚያደርጉት። በመሆኑም ህወሓት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በጠመንጃ ኃይል አንበርክኮ ከመግዛት ባለፈ የህዝብን ልብና ይሁንታ ማግኘት አልቻለም። ለዚህም ተጠያቂ የሚያደርገው የአንድነት ኃይሎችን በተለይም “የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶ ነው” ብሎ የሚወስደውን “የአማራ ብሔርን” ነው።
ስለሆነም ህወሓቶች በከፍተኛ እልህና ቁጭት ተሞልተው አማራውን ከተሰቀለበት የኢትዮጵያዊነት ከፍታ ወደ ተራ ብሔርተኝነት ለማውረድ በግልፅና በሥውር ብዙ ሠርተዋል። አማራው አያት ቅድመ-አያቶቹ በዱር በገደሉ የተንከራተቱለትን; ከባዕዳን ኃይሎችና ወራሪዎች ጋር አንገት ላንገት ተናንቀው የወደቁለትን; ተነግሮ የማያልቅ መስዋትነት የከፈሉለትን የአንድነት አጀንዳ ጥሎ በጠባብ ብሔርተኝነት አረንቋ ውስጥ ገብቶ እንዲዳክር ሴራ ከመጠንሰስ ባለፈ በረቀቀ ስልት ወደዚያ ጫፍ ተገፍቷል። ዛሬ ህወሓት ወደዳር ተገፍቶ ኢትዮጵያዊነት በመንግሥት ደረጃ በሚቀነቀንበት ወቅት የኢትዮጵያ አንድነት ማዕከል ተደርጎ የሚወሰደው አማራ የጠባብ ብሔርተኝነት አጀንዳ ይዞ በሌሎች ዘንድ “በተገንጣይነት” እንዲሳል መደረጉ የህወሓት ሴራ ውጤት እንጅ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
ህወሓት አማራው በጠባብ ብሔርተኝነት አጀንዳ ዙሪያ እንዲደራጅ ሲገፋው የነበረው በዋነኝነት በአምስት አበይት ምክንያቶች ነው ማለት ይቻላል;
1ኛ/ አማራው ወደጠባብ ብሔርተኝነት ጠርዝ በመግፋት የኢትዮጵያን አንድነት ምሰሶ መነቅነቅና አገሪቱን ማፍረስ ሊሆን ይችላል። በተለይም ህወሓት ያኔ በለጋ ዕድሜው ያቀነቀነውን “ነፃ የትግራይ ሪፐብሊክ መመሥረት” የሚለውን አጀንዳ ለጊዜው የሳበውና (withdraw) አመች ጊዜ ጠብቆ ተግባራዊ ሊያደርገው የሚፈልግ ከሆነ ይኸኛው ምክንያት በቀዳሚነት የሚቀመጥ ይሆናል።
2ኛ/ የሥልጣን ዕድሜውን ከማራዘም ጋር በተያያዘ ህዝብን ከፋፍሎ ለመግዛት ያለመ ነው ማለትም ይቻላል። ከዚህ አንፃር አባላቱና ደጋፊዎቹ ከትግራይ ክልል ውጭ ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ግምት ውስጥ በማስገባት በመላው ሀገሪቱ አንሰራፍተው ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም ተቆጣጥረው ለመቆየት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው መለት ይችላል። ከዚህ አንፃር ካየነው አማራውም እንደሌላው ሁሉ በብሔር የመከፋፈሉ ሴራ ሰለባ ሆኗል ማለት ይቻላል።
3ኛ/ በተለይ አማራውን (በገዥ መደብ ደረጃ?) በጠላትነት ፈርጆ የተነሳው ህወሓት አማራው ከሌሎች ጋር ያለውን ልዩነት የሚያሰፋና ሊታረቅ የማይችል የጠባብ ብሔርተኝነት አጀንዳ ይዞ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። አማራው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠንቅቀው የሚያውቁት ህወሓቶች ሁሉም በጠላትነት እንዳዬው ካላደረጉ እነሱ ብቻቸውን ታግለው ሊነቀንቁት እንደማይችሉ ገና ከጧቱ የተረዱት ይመስላል። ስለሆነም አማራው ከሌሎች መነጠልና ማዶ ለማዶ እየተያዬ ልዩነቶችን ማስፋት ወደሚችልበት የአደረጃጀት ስልት ተገፍቷል ማለት ይቻላል።
4ኛ/ የአማራው ማህበራዊ መሠረትና ሥነ-ልቦና የአቃፊነት ባህሪ ያለው መሆኑን ጠንቅቀው የሚገነዘቡት ህወሓቶች አማራው ጠባብ ብሔርተኝነትን ማቀንቀን ሲጀምር እነዚህን መገለጫዎቹንና እሴቶቹን ሊያጣ ይችላል በሚል ስሌትም ወደዚህ አቅጣጫ ሊገፉት ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። አማራው በዘመናት ሂደት ካዳበረው የአብሮነት ሥነ-ልቦናና ከነባር እሴቶቹ ሲያፈነግጥ የተለያዩ ንዑሳን ማንነቶችና ውስጣዊ ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የሚረዳው ህወሓት “አማራው ማህበራዊ ዕረፍት እንዳይኖረው” ለማድረግ የነበረውን ዕቅድ ለማሳካት ሊጠቀምበት እንደሚችል መገመት ይቻላል።
5ኛ/ አማራውን ከተሰቀለበት የሞራል ከፍታ ማውረድና “ማኖ” ማስገባትም ሌላው የህወሓት ግብ ሊሆን ይችላል። በጠባብ ብሔርተኝነቱ ወደዳር ሲገፋና ሲከሰስ የቆዬው ህወሓት ወደፊትም በታሪክ ፊት የሚኖረውን ሥምና ቦታ ሲያስበው ያስበረግገዋል። ይኸን ክስ በዋነኝነት ሊያቀርቡ የሚችሉት በተለይ የአማራው ልሂቃን ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ ህወሓቶች አማራው እነሱ በሄዱበት መንገድ የሚሄድበትን ሁኔታ ፈጥረዋል ማለት ይቻላል። በዚህ መንገድም አማራው በጠባብ ብሔርተኝነት መደራጀት ትክክለኛ መንገድ (justifiable) ስለመሆኑ እንዲሟገትና በታሪክም ተጠያቂነቱን ወያኔ ብቻውን እንዳይሸከም የተዘየደ ፖለቲካዊ ብልሃት እንደሆነ ማሰብ ይቻላል።
ከዚህ አንፃር ህወሓቶች ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል? በዚህ አካሄድስ መድረሻችን የት ይሆን? ምናልባት የማናሸንፈው (አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት) ጦርነት ውስጥ እየገባን ይሆን? ብሔርን መሠረት ባደረገ አደረጃጀት የምናራምዳቸው አጀንዳዎችና የምናሳካቸው ግቦች ምን ምን ናቸው? በረቀቀ ሴራ ተገፍቶና በራሱም ተገፋፍቶ እንደዋዛ መሐሉን እየለቀቀ ያለው አማራ በኋላ ወደነበረበት ቦታ መመለስ (ከሞራል አንፃር) አይቸግረውም ይሆን? በተለይ አሁን ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ (በመንግሥት ደረጃ) በሚቀነቀንበት ወቅት የኢትዮጵያን ብሔረ-መንግሥት (the Ethiopian nation state) በመገንባቱ ሂደት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሚታመነው የአማራው ልሂቅ (elite) ከደረጃው ወርዶ በብሔር መደራጄቱ እስትራቴጂያዊ አንደምታው ምንድነው?
እነዚህ በኔ አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉ ጥያቄዎች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ጉዳዩን ከተለዬ አቅጣጫ (from a different angle) ሊያዩት ይችላሉ። ቢሆንም ልዩነት የጤናማ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገለጫ እንጅ “ለሀገርና ለህዝብ ማሰብ ከኔ ወዲያ ላሳር” ወደሚል አጉል መታበይ የሚወስድ መሆን የለበትም። በዚያ መንገድ ሄደን የትም መድረስ እንደማንችል ከእስካሁኑ ጉዟችን የተሻለ አስረጅ ማቅረብ አይቻልም።
ፈጣሪ-አምላክ ልቦና ይስጠን!
አላህ (ሱ.ወ) ኢትዮጵያን በፍቅሩ ይባርክ; ከክፉም ይጠብቃት!!!
Filed in: Amharic