>
9:37 pm - Sunday August 7, 2022

የኦነግ ግንባር (መሳይ መኮንን)

የኦነግ ግንባር
መሳይ መኮንን
በተለያዩ ግለሰቦች የሚመሩት የተለያዩ ኦነጎች አንድ መለያ ምልክትና አንድ መጠሪያ ይዘው እየገቡ ነው። እንደሰማነው የአቶ ገላሳ ዲልቦው ኦነግ የመጨረሻው ይሆናል። በእርግጥ ሌላ አይኖረም ማለት አይቻልም። ለጊዜው ዋና ዋናዎቹ ኦነጎች ሀገር ቤት ገብተዋል። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር ደም አጥንቱን የገበረለትና እነለማ መገርሳን በፊት መሪነት ያወጣው ለውጥ አደጋ ገጥሞታል። አደጋው በዋናነት ለኦሮሞ ህዝብ እታገላለሁ ብሎ ከሚምለው ከአንደኛው የኦነግ ክፋይ የመጣ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል። የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ሃላፊነት በእጁ ላይ የወደቀበት ወሳኝ ዘመን ላይ ይገኛል። እነለማ የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ ተረድተው፡ የሚያሽርና የሚፈውስ ፍቱን መድሃኒት ቀምመው በመጡበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የተረገዘውን ለውጥ የሚያጨናግፍ መስመር ላይ ወጥቶ የሚሸልለውን የዳውድ ኢብሳን ኦነግ አደብ ማስገዛት የሚችለው ከማንም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ነው።
የዳውድ ኢብሳ ኦነግ የገዛ ህዝቡ ላይ ጦርነት አውጇል። የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓን በማፈራረስ የክልሉን መንግስት ለመቆጣጠር በሂደትም በልቡ የተቀበረውንና፡ ለግማሽ ክፍለዘመን የዘመረለትን የኦሮሚያ መንግስት ለመምስረት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ለመሆኑ ምልክቶች ይታያሉ። የኦዴፓን ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አመራሮችን በመግደልና በማፈን ከታች ያለውን መዋቅር የማዳከን ስራውን ለ6ወራት ሲያከናውን እንደነበረ ዘግይቶም ቢሆን ኦዴፓ ይፋ አድርጎታል። አሁንም የዳውድ ኢብሳ ኦነግ የኦዴፓ መዋቅር ላይ ያነጣጠረ ጥቃቱን ቀጥሏል። ሰሞኑን በምዕራብ ጉጂ ዞን ሶስት የወረዳ አመራሮችን አፍኖ ወስዷል።
የኦዴፓ መሪዎች እንደሚሉት ኦነግ በሶስት አከባቢዎች የማሰልጠኛ ካምፖችን በመክፈት ወታደሮችን እያሰለጠነ ነው። የኦሮሞ ወጣቶችን ከግድያ ጀምሮ በተለያዩ ማስፈራራቶች መልምሎ ወደየካምፖቹ እያስገባ እንደሆነም ይነገራል። ከየመንደሩ በአፈናና አስገዳጅ ሁኔታዎች ህጻናት ወታደሮችን ጭምር እንደሚመለምል የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። ከ1ሺህ የማይበልጥ ታጣቂ ይዞ የገባው ኦነግ የመንግስትን ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ተረማምዶበትና ረጋግጦት አደገኛ በሆነ አጥፊ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምዶ የሰራዊቱን ቁጥር በ10ሺዎች ለማሳደግ ተግቶ እየሰራ ነው። ይህ ሰራዊት ስልጠናውን ጨርሶ ሲወጣ የመጀመሪያውን ጥይት የሚተኩሰው ኦዴፓ ላይ መሆኑ እርግጥ ነው። ለውጡን የሚደግፈውን የኦሮሞ ህዝብ ክፍል እየለቀመ የሚያጠፋ ለመሆኑም ምንም ጥርጥር የለውም። አሁንም እያደረገው ነው።
ኦነግ ይህን አጋጣሚ ወርቃማ ብሎታል። ሸልፍ ላይ አዋራ የጠጣውን የከሰረ ፕሮጀክቱን ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ የተመቻቸ እድል ተፈጥሯል ብሎ ያምናል የዳውድ ኢብሳ ኦነግ። አንድ ጥይት ሳይተኩስ በቦሌ የገባው ዳውድ ኢብሳ የቄሮዎችን መስዋዕትነት እየመነዘረ ወደፊት መግፋትን መርጧል። በቅድሚያ ዓላማውን የሚቃወም የገዛ ወገኑን ማጥፋት የኦነግ እቅድ ነው። ከዚያ በኋላ ነው ወደተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ አፈሙዙን የሚያዞረው።  የኦሮሞ ህዝብ ለራሱ ሲል የዳውድ ኢብሳን ኦነግ መጋፈጥ አለበት የሚባለውም ለዚሁ ነው። የኦዴፓው አቶ ታዬ ደንደአ ባለፈው ሳምንት በግልጽ እንዳስቀመጡት የዳውድ ኢብሳ ኦነግ እየረበሸ ነው። ከሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በስምምነት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ታዬ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረን ሸኔ የሚባለው የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ነው ብለዋል። መሀል አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው በመንግስት ቀለብ እየተሰፈረላቸው፡ ለመኝታቸው ባለ5ኮከብ ሆቴል ተይዞላቸው መንግስት ላይ ጦርነት የሚያውጁት አቶ ዳውድ ኢብሳ ብቸኛ መሸሸጊያቸው የኦሮሞ ህዝብ እንደሆነ ይታወቃል። የውጭውን አሟጠው ጨርሰዋል። ቀድሞውኑም የቀረችው ኤርትራ ነበረች። ለኦነግ የሚሆን ቦታ የለኝም ብላ በሯን ዘግታለች። እናም የኦሮሞ ህዝብ በስሙ እየማለ የሚገዘተውንና መልሶ ሊያጠፋው ጦር የሰበቀውን የዳውድ ኢብሳን ኦነግ ፊት የነሳ ዕለት አቶ ዳውድ ምርጫ አይኖራቸውም። ወይ ይደመራሉ፡ አልያም መጨረሻቸው አጓጉል ሆኖ በታሪክ ሲወሱ ይኖራሉ።
ኦዴፓ የዳውድ ኢብሳን ኦነግ ጉዳይ እያስታመመ ያለበት አካሄድ ለብዙዎች የፈሪ መገለጫ ሊሆንላቸው ይችላል። ትዕግስቱ ከልክ አለፈ ብለው በመንግስት የሚማረሩ ጥቂት አይደሉም። ከዚያም አልፈው የለማ ቡድን ኢትዮጵያን ከኦነግ ጋር ተባብሮ እያዳከመ ነው የሚል የሴራ ፖለቲካ የሚተነትኑም አልጠፉም። የዳውድ ኢብሳ ኦነግ የስለት ልጅ ይመስል እሹሩሩ እየተባለ ሀገር እስኪያጠፋ የሚጠበቀው ለምንድን ነው ብለው የሚጠይቁም ድምጻቸው ከፍ ብሏል። ለእኔ የሚሰማኝ ግን ከውዲህ ነው። እነለማ በህወሀት በኩል የተከፈተባቸውን መጠነ ሰፊ የግጭት ግንባር አጠገባቸው አስቀምጠው ኦነግን በሚገባው የጡንቻ ቋንቋ ማናገር ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል። በአፈንጪውና ፈንግጪው አካሄድ ብቻ የኦነግን ጉዳይ መያዝ ድምር ውጤቱ ሀገሪቱን ወደባሰ ቀውስ ይዶላታል። እነለማ አርጩሜና ሰላም ይዘው በጥሩ መንገድ እየተጓዙ ነው። እንደገባኝም አቶ ለማ አራት ስትራቴጂዎችን በአንድ ላይ ጎን ለጎን እያስኬዱ ነው። የመጀመሪያው እሾህን በእሾህ ስትራቴጂ ነው። ኦነግን በኦነግ። አቶ ዳውድን በአቶ ገላሳ።
በገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ መግባቱ ለዳውድ ኢብሳ ጥሩ መልዕክት አይደለም። በዚህ ላይ አቶ ገላሳ ‘’ለውጡ የኦሮሞ ህዝብ የተዋደቀለት በመሆኑ ልንከባከበው ይገባል’’ ማለታቸው ለአቶ ዳውድ የሚቀፍ መልዕክት ሆኗል። የአቶ ገላሳ ዲልቦ ኦነግ የዳውድን ያህል ጦር ባይኖረውም በፖለቲካው አንጻር ጉልበቱ የሚናቅ አይደለም። በሽግግሩ መንግስት ጊዜ የኦነግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ገላሳ በአቶ ዳውድ ለተረጨው መርዝ ማርከሻ መሆናቸውን ኦዴፓዎች የተረዱት ይመስላል። ለቶ ገላሳ ዲልቦ ኦነግ እውቅና በመስጠት በቀጣይም የኦነግ ብቸኛ ተጠሪና ወኪል አቶ ገላሳ ዲልቦ እንዲሆኑ ማድረግ አንደኛ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። የአቶ ዳውድ ኢብሳን ኦነግ በኢትዮጵያ ህግ መጫወቺያ ሜዳ እንዳይኖረው በማድረግ በመጨረሻም እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ መውሰድ ነው። አቶ ገላሳ በኦነግ አንጻር ህጋዊም ታሪካዊም ተቀባይነት ያላቸው እንደሆኑ ይታመናል። የእሳቸውን ኦነግ በአቶ ዳውድ ኢብሳው ኦነግ የመቀየር ስትራቴጂ አንደኛው አዋጭ መንገድ ነው። ጦረኛውን በሰላማዊው ኦነግ መተካት ማለት ነው። አቶ ገላሳ ብቻ አይደሉም። በአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ከፍተኛ የኦነግ አመራር የነበሩ ግለሰቦችም በአቶ ለማ ክልላዊ መንግስትና በዶ/ር አብይ የፌደራል መንግስት ውስጥ ቁልፍ ቦታ መያዛቸው ለአቶ ዳውድ ኢብሳ በብርቱ የሚያሳምም ነገር ነው። እንግዲህ እሾህን በእሾህ ማለት ይኽው ነው። ኦነግን በኦነግ።
ሁለተኛው ስትራቴጂ ማግለል ወይም ነጥሎ ማስቀረት ነው። አቶ ታዬ ደንደአ እንዳሉትም ከዳውድ ኢብሳ ኦነግ በስተቀር ከሌሎቹ ጋር በስምምነት እየተሰራ ነው። ሌሎቹ የኦሮሞ ድርጅቶች የዳውድ ኢብሳን ኦነግ እንዲያውግዙ ማድረግ የኦዴፓ አንደኛው ስልት ነው። ከወዲሁ አንዳንዶች ስም ሳይጠቅሱ ግብሩን እያወገዙ ነው። በሂደት የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ተነጥሎ ይቀራል። ሌሎቹ በግፊትም ይሁን በፍላጎት አንድ መስመር ላይ መውጣታቸው አይቀርም። የአንድነት መንግስት እንዲመሰረት የጠየቀው የዶ/ር መረራ ኦፌኮም ከኦነግ ይልቅ ለኦዴፓ ይቀርባል። የእነለማ ሁለተኛው ስትራቴጂ ኦነግ ተነጥሎ ብቻውን እንዲቀርና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እንዲተፋ ማድረግ ነው። ይህ አካሄድ ውጤት እያመጣ ለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶች አሉ። ከአንጋፋው ፖለቲከኛ ሌንጮ ለታ ከሚመራው ኦዴግ ጀምሮ እስከ ፎርጅዱ ኦብኮ ያሉ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም በቅርቡ እስከገባው የገላሳ ዲልቦ ኦነግ ድረስ ያሉት፡ ለውጡን እንደአይናችን ብሌን እንጠብቀዋለን የሚለው መግለጫ ለዳውድ ኢብሳ የእሬት ያህል የሚመር ነው።  በእርግጥ እነዚህ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የዳውድ ኢብሳን ኦነግ በግልጽ፡ በይፋ፡ በጠንካራ አቋም እንዲያወግዙ ይጠበቃል። መሽኮርመሙን ትቶው፡ በፊት ለፊት ኦነግን ማውገዝና መነጠል ለእነሱም ታሪክ፡ ለህልውናቸውም ዋስትና ይሆናቸዋል።
ሶስተኛው ስትራቴጂ ሽምግልና ነው። አባገዳዎች ጉዳዩን እንደያዙት ተሰምቷል። የሃይማኖት አባቶችም ከዳውድ ኢብሳ ጋር እየተነጋገሩ ነው ተብሏል። ምንም እንኳን የሽምግልናን ዋጋ አርክሰውታል ተብለው ቢታሙም ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅም እጃቸውን አስገብተዋል። አባገዳዎች በዚህ ሳምንት ወደ ወለጋ እንደሚያመሩ ተገልጿል። አቶ ዳውድ በአባገዳዎችና በሃይማኖት አባቶች የተጀመረውን የሽምግልና ሂደት ካጨናገፉትም፡ ከተቀበሉትም ለአቶ ለማ መገርሳ ታላቅ ድል ነው። በሁለቱም አትራፊው የለማ ቡድን ነው። ካጨናገፉት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ልዩ ስፍራ ያለውን የአባ ገዳ ሽምግልናን እንደመናቅ የሚቆጠር በመሆኑ በዚህ በኩል የሚመጣውን ኪሳራ አቶ ዳውድ የሚመርጡት አይመስለኝም። በሁለት ነገሮች ኪሳራው ይመነዘራል። አንደኛው የሰላም እጆችን መርገጥ የሚያመጣው ኪሳራ ሲሆን ይህም ኦነግን ተነጥሎ እንዲመታ ያደርገዋል። ሁለተኛው ለአባገዳዎች ሽምግልና ጀርባን መስጠት በተለይ ከኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ውግዘትን የሚያመጣ ይሆናል። ብቸኛው መደበቂያው በሆነው በኦሮሞ ህዝብ ከተተፋ ደግሞ ህይወት አይኖረውም። ልክ ከባህር እንደወጣ አሳ።
አራተኛው ስትራቴጂ ወታደራዊ እርምጃ ነው። ከስድስት ወራት ትዕግስት በኋላ መንግስት በኦነግ ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። የኦነግ ሰራዊት በዋናነት በሚንቀሳቀስባቸው የወለጋ አከባቢዎች መከላከያ ሰራዊት ተሰማርቷል። ባለፉት ሶስት ሳምንታት ኦነግ የመንግስትን ብርቱ ምት እየቀመሰ ነው። አቶ ዳውድ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው በሚቀልባቸው መንግስት ላይ ጦርነት ያወጁትም ሰራዊታቸው ላይ ከባድ ዱላ ማረፉን ተከትሎ ነው። አባ ቶርባ በሚል ስያሜ ወለጋ ላይ ግድያን በቀጠሮ ሲፈጽሙ የነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች እየተለቀሙ በመታሰር ላይ ናቸው። እስከአሁንም ወደ 20 የሚጠጉት አባ ቶርባዎች ከርቸሌ ወርደዋል። በርካታ የኦነግ ታጣቂዎች መንግስት ማምረሩን አይተው እጅ መስጠት መጀመራቸውም ተሰምቷል። ከባለፈው ሳምንት ወዲህ ከ100 በላይ የኦነግ ታጣቂዎች ኦነግ በቃን ብለው ወጥተዋል። ኦነግን በሚገባው ቋንቋ ማናገሩ ቀጥሏል።
አራቱ ስትራቴጂዎች የየራሳቸው ጥቅምና ጉዳት ሊኖራቸው ይችላል። በአንድ ላይ ጎን ለጎን መሄዳቸው ከሚኖረው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል። ዋናው ነገር በምንም ይሁን በምን ኦነግን መርዙን ማስተፋት ነው። አንድ ጠርዝ ወስዶ መለመላውን ማስቀረት ነው። መንግስት ጊዜ ያለው አይመስለኝም። እስከአሁን የወሰደው ጊዜ ያስከፈለው ዋጋ ቀላል ባለመሆኑ ከእንግዲህ በፍጥነት ይህን አደገኛ ቡድን ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የመንግስት ዋናው የቤት ስራ መሆን አለበት። ጊዜ በተሰጠ ቁጥር ኦነግ እንደአሜባ ሊባዛ የመቻል እድል ያገኛል። በኦነግ በኩል የተከፈተውን ግንባር ሳያጠናቅቁት ሌላኛውን የህወሀትን ግንባር መመከት የሚቻል አይደለም። ህወሀት በዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ በርካታ ግንባሮችን በአንድ ጊዜ በመክፈት እረፍት መንሳትና በሂደትም ማዕከላዊ መንግስትን ማሽመድመድ ዋና ስትራቴጂ አድርጎ ቀን ከሌሊት እየሰራ ነው። ጡረታ የወጡት ሙሰኛ ጄነራሎቹ በትግራይ ውስጥ በሰራዊት ማሰልጠን ተጠምደው የትግራይን ህዝብ ለጦርነት ለመማገድ ተዘጋጅተዋል። መንግስት የኦነግን ግንባር በቶሎ ቋጭቶ ፊቱን ወደ ህወሀት ማዞር ይኖርበታል። የህወሀትን ግንባር በተመለከተ በቀጣዩ ጽሁፍ እመለስበታለሁ።
Filed in: Amharic