>
10:37 pm - Tuesday July 5, 2022

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ !!! (መስከረም አበራ)

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ !!!
መስከረም አበራ
 
የኦብነግ ዋና ፀሃፊ ኢሳት ላይ ቀርበው ብዙ ብዙ ተናገሩ፨ መብሰል እንዲህ ነው ! በዘርህ ስትጨቆን በዘር ተደራጅተህ መሳሪያ ነክሰህ ልትታገል ትችላለህ፨ ደህና ቀን ሲመጣ፣ዘመን ሲበስል አብሮ መብሰል ግድ ቢሆንም ሸክም እንጨት ቢነድበትም የማይበስልም ሞልቷል፨ የምስራቅ ፖለቲካ ግን ሙክክ ብሎ በስሏል፨
 
 ኦብነግ ከዚህ በሃላ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሆኖ በመላ ኢትዮጵያ እንደሚንቀሳቀስ ለኢሳት ገልፇዋል፨ ስለ ምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ጠብቆ መደረግ አለመደረግ አስተያየታቸውን ሲጠየቁ “ምርጫ የሚደረገው ለህዝብ ጥቅም ነው ፤ ምርጫ መደረግ ያለበት ህዝብ ተረጋግቶ የሚጠቅመውን የመለየት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፨ መንግስት እንዲህ ያለ አመች ሁኔታ በሃገሪቱ  አለ ብሎ ሲያምን ነው ምርጫው መደረግ ያለበት” ሲሉ በጠዋቱ አስገርመውኛል፨
 
 በዚህ ላይ የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ሙስጠፋ መሃመድ  የዜግነት ፖለቲካ በሃገራችን ቢሰፍን እንደሚወዱ በግልፅ ተናግረው ነበር፤ ይህን ሲሉ የመጀመሪያው የክልል ፕሬዚደንት ናቸው፨ ምስራቅ በስሏል ሰሜን ፣ደቡብ፣ ምዕራብ ተከትለውት ሲበስሉ ዘረኝነት በሰብዐዊነት መተካቱ አይቀሬ ነው!
በሱማሌ ክልል ዘረኝነት አናት አናቱን እየተቀጠቀጠ፣ ለፍቅርና ለአንድነት ቦታውን እየለቀቀ ነው!!
ወንድማገኝ አዲስ
“ክልሎች በሶማሌ ክልል እየሆነ ያለውን በምሳሌነት ወስደው ሀገሪቱን ከሌላ ዙር ቀውስ እና መከፋፈል ይታደጓት ዘንድ አብዝተን ልንጮህ ይገባል።”
ሶማሌ ክልል ደስ በሚል የአንድነት መአዛ  እየታወደች ነው። አብዲ ኢሌ እና የህወሀት ጄነራሎችን አዲዮስ ብላለች። ዘረኝነት አናት አናቱን እየተቀጠቀጠ፣ ለፍቅርና ለአንድነት ቦታውን እየለቀቀ ነው። ዛሬ ጅጅጋ ላይ ወገኖቻችን በማንነታቸው አይሸማቀቁም።ደገሀቡር ላይ ዜጎች ኢትዮጲያዊ ነኝ ለማለት አይፈሩም። ቀብሪደሀር አደባባይ ላይ ስለ አንድነት ጮክ ብሎ ማውራት ይቻላል። የ ርዝራቭ የቀን ጅቦች ሴራ ሁሉ ቆሟል ማለት ባይቻልም ህብለ ሰረሰራቸው ተጎምዶ ነብስ ልትወጣ ስትል ከሚኖረው መንፈራገጥ አይነት የዘለለ አይደለም።
ጄል ኦጋዴን ተከርችሟል። ከንግዲህ ከአንበሳ ጋ የሚታሰር ዜጋ የለም። የህወሀት ምስራቃዊ መረብ ተበጣጥሷል። ከንግዲህ የወያኔ ጄነራሎች የኮንትሮባንድ ዘረፋ አይታሰብም። ሶማሌ ክልል ሶማሌ ያልሆኑ ኢትዮጲያዊያን ሁሉ ሆናለች። ምስራቅ የተፈጥሮ ፀሀይ መውጫ ብቻ ሳትሆን የአንድነት ፀሀይ መፈንጠቂያም ሆናለች።
በአብዲ ኢሌው ሶህዴፓ መቃብር ላይ ፣ ኦብነግ አንድነትን እያቀነቀነ የክቡር ፕሬዝዳንት ሙስጠፋውን ሶህዴፓ ተቀላቅሏል።
ክቡር ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ አማራውን ትምክህተኛ አድርጎ የቀረፀው ትርክት ፍፁም ስህተት እንደነበረ ይህንንም በአማራ ክልል አደባባዮች እንደሚደግሙት ቃል ገብተዋል። ይህ ፍረጃ ለአማራው መጨፍጨፍ ፣መፈናቀል እና እንግልት ምክንያት እንደነበረም አምነዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የአማራ መብት ተቆርቋሪ ነን ባዮች በአማራው ላይ ሲደርስ የነበረው ግፍና ስቃይ መቅረቱ የቆረቆራቸው ይመስላሉ። አማራው በሌሎች የሚጠላበትና የሚጠቃበትን ገቢር 2 ሴራ እየተወኑት ይገኛሉ። ህወሀት አማራው ላይ የለጠፈው ትምክህተኛ የሚለው ታርጋ ትክክል ነበር እስከማለት ደርሰዋል። እነ በረከት ከመንበራቸው ቢጠረጉም ግልገል በረከቶች ተፈልፍለዋል። አረጋውያኑ በረከቶች በጎረምሶቹ በረከቶች እግር ተተክተዋል። ይህ በዚህ ከቀጠለ አዴፓ አጥቂነት ወደ ተከላካይነት ማፈግፈጉ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው። በነዚህ ሀይሎች ጉዳይ የአዴፓ አይን አፋርነት/ፍርሀት በግልፅ የሚነበብ ነው። የአማራውን ማስሜዲያ ሀይጃክ እንደተደረገ በርካታ ማሳያዎች አሉ።
አፍራሽ ሀይሎች በተለይም ዘር ቀመሶች ፊት ከተሰጣቸው ለመራባት ጊዜ አይፈጁም። ጫካውን ለማቃጠል አንድ ክብሪት እንደምትበቃ ሁሉ ሀገራዊ ቀውስንና በህዝብና ህዝብ መሀል እልቂት ለማቀጣጠል ጥቂት ዘረኞች ይበቃሉ።
ኦነግ ሀገሪቱን ለማተራመስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለመግታት ኦዴፓ እያሳዬው ያለው ጥረት በአዴፓም ሊደገም ይገባል። ፌደራል መንግስትም እነዚህ ሀይሎች በለውጡ  ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ደባ ተረድቶ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ  ይገባል። ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም የሚሏት ብሂል እዚህ ላይ ትሰራለች።
ክልሎች በሶማሌ ክልል እየሆነ ያለውን በምሳሌነት ወስደው ሀገሪቱን ከሌላ ዙር ቀውስ እና መከፋፈል ይታደጓት ዘንድ አብዝተን ልንጮህ ይገባል።
Filed in: Amharic