>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9357

ዞምቢ – የትህነግ የስድብ መንጋ (አብርሀ በላይ)

ዞምቢ – የትህነግ የስድብ መንጋ
አብርሀ በላይ
ትህነግ የሳይበር ተቃዋሚዎችዋን ለማሸማቀቅ ዞምቢን ነው የምታሰማራው። ዞምቢ ደግሞ እንደ ሮቦት የተሰጠውን ትእዛዝ ፈጻሚ ነው። በፌስቡክ ገጽህ ገብቶ የሚሳደባው ዞምቢ፣ ማንነቱን ይደብቃል። የሚገርመውም ነገር እሱ ነው። የህወሃት ደጋፊ (ዞምቢ) ሙቶም ይፈራል። የዞምቢ መደበኛ ሥራ የፀያፍ ስድብ ናዳ መልቀቅ ነው። ዞምቢ ጭንቅላት ያለው መስሎህ፣ ለውይይት ራስህን አታዘጋጅ። ጊዜህን አታጥፋ። አንዴ በስድብ ሶፍትዌር ፕሮግራም ተደርጓል።
ግን የህወሃት የፀያፍ ስድብ አመጣጥ መነሻ አለው?
ትህነግ ተከታዮችዋን ፍጹም ታማኝ አገልጋይ ሁነው እንዲቀሩ የምትቀርፅበት መንገድ ልዩ ልዩ የቅጣት እርምጃዎችን በመውሰድ ነው። አንድ ሰው የትህነግን መመሪያ ከተፈታተነ፣ እንደ ብስለቱ እና ደፋርነቱ ታይቶ ፍርድ ይሰጠዋል። በአቋሙ የፀና፣ በፉጹም እጁን ለነሱ የማይሰጥ፣ ፀረ-ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያውቅ፣ የበሰለ ሰው ከሆነ ምክንያት ፈጥረው በሞት ይቀጡታል። ጥይት፣ መርዝ፣ በመኪና ገጭቶ መግደል፣ እቤቱ ሰብረው ገብተው አንቀው ይገድሉታና ራሱን አጠፋ ለማስባል ሰቅለዉት መሄድ።  በነዚህ  ዜዴዎች የተገደሉ ቤቱ ይቆጠራቸው። የመጨረሻዋ “ቀላል” ቅጣት የምትሰጠው ተጠርጣሪው ሰው ድንጉጥ እና ተሎ የሚመለስ ብለው ካመኑበት ወይም እንደኛ የማያገኙት የዳያስፖራ ሰው ከሆነ “አጥንት በሚሰብር ቃል” ይመቱታል።
የትህነግ ዋና አድራጊ ፈጣሪ የነበረው መለስ ዜናዊ ሰዎችን ቅስም በሚሰብሩ ቃላቶች ማሸማቀቅ ማንም አይደርስበትም ነበር ይባላል። ዱካኩ መለስ ፓርላማ ውስጥ ብዙ ርካሽ ቃላቶች ይጠቀም ስለነበር፣ ይህ የወረደ የዱሩየ ፀባዩ የሰለቻቸው ጀግናው የቅንጅት አመራር አባል የነበሩት ክቡር አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ “አቶ መለስ፣ እንደ እርስዎ ታች ወርደን፣ የርስዎን ቋንቋ መናገር ይከብደናል” ብለው ከል ያለበሱት። እነ መለስ ሌላው የውጭ ሰው ቀርቶ የራሳቸው ሰው ከጠረጠሩት የሚመቱበት መጥፎ ቃል በትግርኛ “ምድሃል፣ ደሃሎ ወይም አርዕዶ” ይሉታል። ቅስሙን ስበረው፣ ግራ አጋባው፣ ፍርሃት ልቀቅበት እንደማለት ነው።
አብነት
መለስ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት በድል መጠናቀቅ ካከሸፈ በኋላ፣ በአገር ክህደት የከሰስቱትን ሰዎች ባዶ እጃቸውን ያባራቸዋል። በህወሃት ህግ ደንብ መሰረት ደግሞ የህወሃት የኦዲት ኮሚቴው ከፍተኛው ብይን ሰጪ አካል ነበር። ታድያ ኦዲት ኮምቴው የሁለቱ የህወሃት ቡድኖች ጉዳይ አጣርቶ መለስ ስህተተኛ መሆኑን ያምንበታል። የኦዲት ሊቀ-መንበር ህሩይ የሚባል ሰው መለስ ቢሮ ጋር ሂዶ “ኦዲት ኮሚቴው አንተን ጥፋተኛ ሁነህ አግኝቶሃል” ይለዋል።
“አንተ ሰገራ!” ይለዋል መለስ። አይኑ አፍጦም፣ “ልጆችህን አታሳድግም!”
ጥይትዋ እንግዲህ “ሰገራ” የምትለዋ ቃል ነች።
ህሩይ ልክ መብረቅ እንደመታው እንጨት ደርቆ ይቀራል። ቀስ ብሎም ኩምሽሽ እንዳለ ብርድ ብርድ እያለው ወደ ቤቱ ይመለሳል። አቶ ኅሩይ በነገታው ከስራው እንደታገደ ይነገረዋል። የመለስ ሰዎች ጋር ሄዶ እያለቀሰ፣ በድያለሁና አንድ እድል ይሰጠኝ ይላል። እነሱም ተገቢ ቅጣቱን እንደተቀበለ አይተው፣ መለስ እግር ስር ወስደው ጣሉት። ጫማውን ስሞ ተነሳ፣ ወደ ሥራውም ተመለሰ። ግን ከዛች ቀን ጀምሮ እንደፈራ ቀረ።
አዎ – “አንተ ሰገራ” ሲል አንድ “የአገር መሪ!” እሱ ነው “ዳሃሎ” ማለት። በጸያፍ ቃል ቅስሙን ስበረው ማለት ነው። ትህነጎች ስድብን እንደ “ፀጥ ማሰኛ” መሳሪያ እንደሚጠቀሙ የምናውቅ ሰዎች  ሲሰድቡን ምንም አይመስለንም። መረጃው ስላለን እናውቃለን። የንሱ ስድብ እኛጋር ደርሶ ይመክናል። (Information is power የሚባለውም ለዚህ ነው)። ነገር ግን ከምዋረድ ብሎ አርፎ እንዲቀመጥ፣ ብሎም እነሱን እንዲለማመጥ ያረጉት ግን ቤቱ ይቁጠረው።
በነገራችን ላይ፣ ወ/ሮ አዜብም የዳሃሎ መሳሪያ ተጠቃሚ ነች።
በስብሰባ መሃል፣ ዘርአይ አስገዶም (የብሮድካስቲንግ ኤጄንሲ ኃላፊ የነበረው) መለስን ለማስደስት ብሎ አባይ ፀሃየን “ወላዋይ” ብሎ ሲያዋርደው ትሰማለች። አዳራሽ ሙሉ ህወሃቶች በተሰበሰቡበት “ዳሃሎ” መጠቀም ፈለገች። ተነሳችና ዘርአይ አስገዶም ማለትኮ “ቱቦ” ማለት ነው። የቁሻሻ ማስተላለፊያ ማለት ነው፣ እያለች በ “ደሃሎ” ረሸነችው። ዘርአይ አስገዶምም የሞት ሞቱን ብድግ ብሎ፣ “ልክ ነው ክብርት ቀዳማዊት እመቤት። እኔ ማለት ቱቦ ነኝ። ይቅርታ ይደረግልኝ” ብሎ ቁጭ አለ (ምንጭ – “የመለስ ትሩፋቶች” – ደራሲ ኤርሚያስ ለገሰ)
እና በፌስ ቡክ የተበተኑት ዞምቢ የስድብ መንጋ ባናውቃቸው ሸሸተን ተደብቀን ነበር። ግን እኛ የትህነግ የሳይበር ዞምቢዎች የምናውቃቸው ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት በነበረው “ትግራይኔት” እና “እትዮፎረም” በተባሉ የኦንላይን የውይይት መድረኮች ላይ ጀምሮ ነው። ማወቅ ግን ኃይል ነው። እና ዞምቢዎች ፀረ እውቀት ናቸው። ጊዜህን ያባክናሉ። እነዚህ ጋር ውይይት ከፍተህ ቁም ነገር ላይ እደርሳለሁ ማለት ዞምቢን አታውቀውም ማለት ነው። ዞምቢ የሚጠፉት መቀሌ መሽገው ያሉት የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ኃይል የጠፉ ጊዜ ነው። ደግሞ ይጠፋሉ!!
Filed in: Amharic