>
4:15 am - Wednesday May 18, 2022

ክሕደት ከፋሺሽት የጣሊያን ወረራ እስከ ባንዳ-ወያኔዎች ፤ በኢትዮጵያ ላይ። (ከዐቢይ ኢትዮጵያዊ....)

ክሕደት ከፋሺሽት የጣሊያን ወረራ እስከ ባንዳ-ወያኔዎች ፤በኢትዮጵያ ላይ።

ከዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ
             ጥበቡ 
መሸሽ መሸሽ የሚል ጥንትም የለመደ፤
በመጫኛም ቢያስሩት ሄደ እየጎመደ።
አገር እሳት ሆኖ ደህና ነኝ የሚለው፤
ከእንቅልፉ ይነቃል ቂጡን ሲያቃጥለው።
ጀግና ግን አይተኛም ጠላቱን ያውቀዋል፤
መቅደም ነው ጥበቡ በሐቁ ያንቀዋል።
    
  «ነፃነት» ለኢትዮጵያ ልዩ መለያ አርማዋ ነው፤ይህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው በክብር መዝገብ የሰፈረው ነፃነታችን፤ በሁሉም አህጉራት ተቀባይነት ያገኘና በአረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የተገለፀ፤ውድ የሕይወት እና የደም-ዋጋ የተከፈለበት የሕዝብ ትግል ውጤት ነው።ክሕደት ወንጀል ነው፤ሸፍጥን ያልፋል፤ከኑፋቄ በላይ ሕይወት ያስገብራል ፣ደም ያፋስሣል፤ስለዚህም የነፃነት ደመኛው ጠላት ነው።
 በተጨማሪም ከነፃነት ባለቤትነቷ በላይ ኢትዮጵያ የምትታወቀው  የሮማን ኢምፓየርን አዋርዳ ያሸነፈች አገር በመሆኗ ነው።እንዲያ በዘመናዊ መሳሪያ እስከአፍንጫው ታጥቆ አገሯን የወረረ የባዕዳን ጦር፤አንዴ ብቻ አይደለም ሁለቱንም ጊዜያት ለአርባ ዓመታት እንደገና ተደራጅቶም ቢመጣ ድባቅ ያስገባች አገር ናት።
  ይህም ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች ከሰው ዘር የተለዩ እንዳልሆኑና ሰው በቆዳው ወይም በሌሎች ነገሮች ልዩነት እንዳይደረግበት፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሊባል እንደማይገባና፣ሁሉም በሰውነቱ በዕኩል እንዲታዩ ያደረገች ሐገር ናት።የጣሊያን መንግሥት ግን ለዘመናት በዘረኝነት ስለኖረና ይህንን ሐቅ ስለማይቀበል ይባስ ማራመድ የጀመረው የፋሺሽዝምን ሥርዓት  በተፃራሪ መንገድ ፈጥሮ ነበር።ያገራችን ፋሺዝም በብሔሮች ሽፋን እንደ እንክብል የተጠቀለለ እንጂ፤በጣልያንኛ ወይም በፈረንሳይኛ የተቋጨ አይደለም።
 
     ፋሺዝም የፖለቲካዊ ርዕዮት ዓለም ሆኖ ሥልጣናዊነትን እና ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን አዋህዶ የያዘ ነው።ከፋሽዝም መገለጫዎች ውስጥ፣ ፈላጭ ቆራጭነትና አምባገነንነት ቀንደኛ መመሪያዎች ሲሆኑ፣በዘረኝነት የሚጎነጎን ተቃራኒ ሐሳቦችንም ሆነ ማሕበረሰቦችን በፍጹም ማፈን፣ኢኮኖሚውንና ማህበረሰቡን ደግሞ ዝንፍ በማይል ሥነ-ሥርዓት ማስተዳደር ከዋና ዋናዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
  የፋሽዝም ኣባት ከሚባሉት አንዱ ደግሞ ደራሲ እና ጋዜጠኛ የነበረው የጣሊያኑ መሪ ቤኔቶ ሞሶሊኒ ግንባር ቀደሙ ነበር።
 ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ቤኒቶ ሙሶሊኒ በትምህርቱ ደካማ ሆኖ በፖለቲከኛነቱ ግን ሲፈጠርም አመፀኛ ነበር።በወቅቱ አገራቸው ጣሊያን በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በተናወጠች ጊዜ ፣ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሃያኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ የፋሺስዝም፣የሶሻሊስትና የሌሎቹን ፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት የተማረው ሙሶሊኒ በሕይወቱ ውጣና ውረድ ውስጥ የፋሺሽዝምን አረመኔ ሥርዓት ሥረ-መሠረት በማጥናት መተግበር ጀመረ።ይህም የቀኝ-ዘመም የፋሺዝም ክላሲካል ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ቅርፆች እየተሰራ በአለም ላይ ተዘራ።በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግርግር ውስጥ የተዘራ መርዝ ነው።
በትለይም ፋሺዝም የፖለቲ እና የኢኮኖሚን ፅንሰ-ሃሳብ ይዞ የተጀመረው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዘረኝነት ላይ ተመሥርቶ ነው።የጣሊያኑ የፋሺሽት ሥርዓት የባሕላዊ ቢመስልም ናዚዝምን  ይጨምራል፤በመሠረቱ ናዚም(ጀርመን በሂትለር የተቋቋመ)ሌላው ዓይነት የፋሺዝም ቅርፅ ሲሆን ዘረኝነትንና ፀረ-ፂዮናዊነትን (racism and antisemitism)ጨምሮ ያራምዳል።ይህንን ሁሉ ዝርዝር ማቅረብ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፋሺዝም በየዘመኑ እንደ እሥስት መልኩን እየቀያየረ፤ እንደባክቴሪያ እየተራባ የእርኩሳን መናፍስት መጋለቢያ ለመሆኑ መረጃዎች ስላሉን ነው።እርባታዎቹም :-
በምዕራብ ኤሮፕ ኒዮ-ፋሺዝም፤
በምዕራብ አፍሪቃ ኢዝላም-ፋሺዝም (ብሪትሽ ፋሺዝም)፤
ሳታቲዝም በጃፓን፤
ቶታሊታሪአንዝም በጥቂቱ በሩሲያ መሰሎች፤
ሒንዱቲቫ በሂንዱዝም የተዋሃደ፤
እንደደቡብ አፍሪቃው የዘረኞች ቡድን  
ሌሎችም ፋሺዝሞች በየታሪካቸው የመዘገቡ ፣ባገራችንም ነጭ ለባሾች ይባሉ የነበሩም አርበኞችን እየጠቆሙ ያሥሰቀሉ ሲሆን፣በዘመናችን ደግሞ የውያኔ-ፋሺሽት(ካድሬዎች) ተብለው ስንቱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያስገደሉ እስከዛሬም ሞልተዋል።
           በነዚያ አርባ አራት ዓመታት የተገደሉና አካለ-ጎደሎ ሆነው የቀሩ በጀግንነት እንዲዘከሩ በምስል ሊመዘገቡ ይገባል።በአንጻሩ ክህደት የፈፀሙባት ባንዳዎች ምስል በአደባባይ ከነሥማቸው ተዘርዝሮ ሊፃፍ ይገባል።ምክንያቱም፣በነዚያ የፈተና ወቅት ኢትዮጵያ የልጆቿን ደም እና አጥንት ገብራ ነፃነቷን ስለአስጠብቀች ነው፤ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ዳር ድንበሯ ያልተደፈረው።በተለይም፤ የሥጋ-ትልን የመሰሉ ሰዎች፣እንዲሉ “ሕውሃት የተባለ ፓርቲ” የአብዮታዊ-ዲሞክራሳዊን ጭምብል ያጠለቀው፣ለኢትዮጵያውያን ፋሺዝምን በራሱ መልክ ቀርጾ ለሌላ አርባ አራት ዓመታት ለማስቀጠል ነበር።ሳይመሻሽ በሕዝብ መስዋዕትነት በፋሺዝም ባህርይው ተጋልጦ ተሰነጣጥቋል እንጂ፤ተመንግሎና ተፈረካክሶ ባያበቃም በሃቁም አባላቱ እየተነቀሉ ይገኛሉ።ከእንግዲህ የሚሆነው ለታሪክ ፋሺሽት-ወያኔ እየተረገመ ለማስተላለፍ:- በጥናት ማነው ይህንን ዕኩይ መሠሪ የፋሺዝም ሥርዓት በአብዮታዊ-ዲሞክርሲ ጭምብል ኢትዮጵያ ላይ ተክሎ የነበረው??? በማለት ሰፊ መረጃ አሰባስቦ ለታሪክ መመዝገብ ይኖርበታል።
   ማጠቃለያ፡በዚህ ጦማር ውስጥ የተገለፀውና ልንዘነጋቸው የማይገቡን ዐቢይ ቁም ነገሮች:- የፋሺዝም ሥርዓት መልኩን እና ቅርፁን እየቀያየረ መምጣቱን፤እናም ስሞቻቸው ቢቀያየርም ያው ሁሉም ተመሳሳይ ባሕርያት እንደአሏቸው መታወቅ  ይኖርበታል።  ጅምላ ግድያ፤በየሰበባ ሰበቡ ግርግር መፍጠር እና ሁሉም-ነገር በዘር ልዩነት ላይ መመሥረቱ፤ሁሉንም በተንኮለኛነት ያስተሳስራል። ይህንን በደምብ ተገንዝበን ወጥመዳቸው ውስጥ እንዳንገባ (ኢትዮጵያዊነት እና ብሔር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅነታቸው ሳይቀር) በዘረኝነት ላይ ልዩ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
Filed in: Amharic