>

ብርቱካን የምትባል ሰው! ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም (ቦስተን)

ብርቱካን የምትባል ሰው!

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም  (ቦስተን)

ብርቱካን ሴት የሆነች ሰው ነች፤  ብርቱካን በፍቅር ለፍቅር የወለደች ሰው ነች፤ ብርቱካን በዳኝነት ተሰይማ የፈረደችውን ለማስለወጥ የወያኔ ምክር ቤት በአንድ ቀን ተሰብስቦ አዲስ ሕግ አውጇል፤ አዲሱ ሕግ አንድ የወደቀ ወያኔን መብት ለመጣስ ነበር! የብርቱካን ፍርድ ደግሞ ለወደቀው ወያኔ መብት የቆመ ነበር፤ ለብርቱካን የተከሳሹ ወያኔነት ቁም ነገር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አልነበረም፡፡

ብርቱካን የሔዋን ልጅ ነች፤ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ፈጠረ፤ ከዕጸ በለስ በቀር በገነት ያለውን ሁሉ ብሉ አላቸው፤ ነገር ግን ዕጸ በለስን እንዳይበሉ ከበሉ ግን ክፉና በጎን እንደሚያውቁና ሞትንም እንደሚሞቱ ነገራቸው፤ የብርቱካን መምህር አሰበች፤ ሞት የማወቅ ቅጣት ከሆነ እቀበላለሁ ብላ ወሰነች፤ ዕጸ በለሱን ቅርጥፍ አድርጋ በላች፤ አወቀች! አዳምንም አበላችው፤ አስበላችውም ቢባል ያው ነው፤ አዳምና ሔዋን ዕጸ በለስን በመብላት ክፉና በጎን ለዩ፤ ስለዚህም ሔዋን ለሰው ልጅ የመጀመሪያዋ አብዮታዊ ነበረች ለማለት ይቻላል፤ ይህ በመሆኑ ተረግመው ከገነት ወጡ፤ ብርቱካንን ሳጥናኤል ከዳኝነት ሥራዋ አፈናቀላት፤ ሳጥናኤልም መንበረ ጽልመትን ከጎረቤቱ አፈላልጎ ብርቱካን በጣለችው ሰባራ ወንበር ላይ እስቀምጦታል፡፡

ብዙ የታጠቁ የሳጥናኤል አሽከሮች ብርቱካንን ሲይዙ ወንድ ሆኜ ባላስስጥላትም አብሬአት ነበርሁ፤ እንኳን እሷን ለማስጣል አንድ የተከናነበ መለዮ ለባሽ እኔንም በሰደፍ ፊኛዬን ሲነርተኝ ‹‹አይ ጀግና!›› ከማለት ሌላ ቃል አልወጣኝም፤ ክንብንቡ ደንቆሮ ያመሰገንሁት ሳይመስለው አልቀረም፤ እኔስ በአንድ የሰደፍ ምት ተገላግየዋለሁ፤ በብርቱካን ላይ ግን የጀመሩት ዱላ ስድብ ለዓመታት ቀጠለ፤ ወንድና ሴት፣ ጎበዝና ፈሪ፣ መቼና እንዴት ይለያሉ?

በኢጣልያ የወረራ ዘመን የፋሺስት ወታደሮች ቆንጆ ሴት በመንደር ሲያዩ ‹‹አንቺ! ቼ ኦ ኖን ቼ!›› እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ጥያቄው ‹‹አለ ወይስ የለም፣›› የሚል በመሆኑ ግራ ቢያጋባም ይግባባሉ፤ አንዱ የኔ ዘመድ ውጭ ቁጭ ብሎ ፋሺስቱ ሚስቱን የተለመደውን ሲጠይቃት በተቀመጠበት አጉረመረመ! አይ ባል! በደርግ ዘመን አውቶቡሱን አቁመው ለመፈተሸ ወንዶች ሁሉ ይውረዱ ሲባል አንድ ሽማግሌ ብቻ ቀሩ፤ ሽማግሌው ሲጠየቁ ወንዶችን ውረዱ ተባለ እንጂ እኔን አይደለም! አሉ ይባላል!

እኔን አንዴ በሰደፍ ገጭቶ ብርቱካንን ጭኖ ሲሄድ ምንም አላደረግሁም፤ ወንድነትን ብቻ ሳይሆን ሰው መሆንን አላሳየሁም፤ እስዋ፣ የሔዋን ልጅ ብትሆንስ እኔን ይዘው ሲሄዱ ዝም ትል ነበር? እንጃ!

Filed in: Amharic