>
4:54 pm - Sunday August 7, 2022

የኦነግ የፖለቲካ አካሄድና ያረበበው ሥጋት (አለማየሁ አምበሴ)

የኦነግ የፖለቲካ አካሄድና ያረበበው ሥጋት

አለማየሁ አምበሴ
የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና መንግስት የገቡበት እሰጣ ገባ በአስቸኳይ በውይይትና በድርድር ሊፈታ ይገባል ያሉት የፓርቲዎች፤ የኦነግ የፖለቲካ አካሄድ ለሀገር ቀጣይ የለውጥ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከተመሠረተ ከ40 አመት በላይ ያስቆጠረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ ከምስረታው ጀምሮ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ሲታገል የቆየ ድርጅት መሆኑን የገለፁት ፖለቲከኞች፤ የህዝቡ ትግል ፍሬ እያፈራ ባለበት በዚህ ወቅት የግንባሩ አመራሮች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገዥ ፓርቲ ኦዴፓ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ምንም የፖለቲካ ትርፍ አያስገኝም ብለዋል፡፡
የኦነግ የፖለቲካ አመራርና ልሂቃንም ሆኑ የኦዴፓ አመራሮች ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ተወያይተው መፍትሔ ካላበጁ፣ ውዝግቡ ለሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ይላሉ – ፖለቲከኞቹ፡፡
በኦነግ እና በኦዴፓ (መንግስት) መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ምክንያቱ ሁለቱም በተደራደሩበት መንገድ ያለ መጓዛቸው ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ “ሶስተኛ ወገን በሌለበት የሚደረጉ ማናቸውም ስምምነቶች እንዲህ ያሉ ችግሮችን መፍጠራቸው እንደማይቀር ይታወቃል” ብለዋል፡፡
ለተፈጠረው ውዝግብ አንዱ መፍትሔ ሁለቱም ወገኖች በአስመራ የተስማሙበትን ጉዳይ በጋራ ተቀምጠው ለህዝብ በዝርዝር ይፋ ማድረግ ነው የሚሉት ፕ/ር መረራ፤ ከዚያም ስምምነታቸውን ሳይጓደልና ሳይሸራረፍ በተግባር ማዋል ይኖርባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ አሁንም ነገሩን ከስሩ ለማጥራት በሁለቱ አካላት መካከል አስመራ ላይ የተፈፀመው ስምምነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ መሆን አለባት ሲሉ የፕ/ር መረራን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የስምምነቱ ነጥቦች ድርጅቶቹ ለቆሙለት ህዝብ በግልጽ መነገሩ ህዝቡ በውዝግቡ እንዳይሳተፍ ለማድረግም ጠቀሜታ እንዳለው ዶ/ር ጫኔ ያሰምሩበታል፡፡
ድርጅቱ አዲስ አበባ በገባ ማግስት ጀምሮ ከመንግስት ጋር ሲያወዛግበው የቆየው የጦር ሰራዊት ጉዳይ አሁንም ዋና አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የኦነግ ሠራዊት እጣ ፈንታን በተመለከተ ሁለቱ አካላት የተስማሙባቸው ነጥቦች መተግበራቸውን የሚከታተል፣ ከሁለቱም ወገን በእኩል የተወከሉበት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመው የነበረ ሲሆን ኮሚቴው ተግባሩን በአግባቡ መወጣት እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡
ከኦዴፓ በኩል የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ሞገስ ኢዴኤ ሰሞኑን በኮሚቴው የእስካሁን ተግባራት ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ከኦነግ በኩል ዳተኝነት በመስተዋሉ ኮሚቴው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡
መግለጫውን የተቃወመው ኦነግ በበኩሉ፤ “አቶ ሞገስ ሪፖርታቸውን ለኮሚቴው የበላዮች ለኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሣና ለኦዴፓ ም/ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሣ ማቅረብ ሲገባቸው፣ ህግ ጥሰው ለሚዲያ ተናግረዋል” ብሏል፡፡
የዚህ ኮሚቴ ተግባርና ሃላፊነት በተመሳሳይ ለህዝቡ አለመገለፁና ውስጥ ለውስጥ መካሄዱ ሌላው የውዝግብ መነሻ ነው ይላሉ – ዶ/ር ጫኔ፡፡
በሁለቱ መካከል በተፈፀመው ስምምነት ላይ የኦሮሞ ህዝብ እስካሁን አስተያየትና ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርብ አለመደረጉ ሌላው ችግር ነው የሚሉት የኢዴፓ ሊቀመንበር፤ ሽፍንፍን ያለ ነገር መብዛቱ የችግሩ መሠረት ባይ ናቸው፡፡
በኦነግ እና በመንግስት መካከል የተፈጠረው ግንኙነት ከመጀመሪያውኑ የተበላሸ ነበር የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (አብኮ) ሊቀ መንበር አቶ ቶሎሣ ተስፋዬ ናቸው፡፡ የኦነግ የሠራዊት ቁጥር፣ የት ቦታ እንደሚገኙና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግልጽነት አልነበረም የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ ከኤርትራ የገባው 1300 ያህል ሠራዊት ብቻ እንደነበር ነው፤ በኋላ ግን ሀገር ውስጥም አለኝ ማለቱ ከመጀመሪያውኑ ሂደቱ ስህተት እንደነበረበት ማስረጃ ነው ይላሉ፡፡
በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ኦነግ ያለው እንቅስቃሴ በግልጽ አይታወቅም ነበር ያሉት አቶ ቶሎሣ፤ “ከመጀመሪያውኑ በሀገር ውስጥ ያለው የኦነግ ቁመና መጠናት ነበረበት” ባይ ናቸው፡፡
በስምምነታቸው ላይም ሁሉም የታጠቀ ሠራዊት ትጥቁን ፈትቶ ወደ ካምፕ የሚገባበት የጊዜ ገደብ በግልጽ መቀመጥ እንደነበረበት ያወሱት የኦብኮ ሊቀመንበር፤ ግልጽነት የሌለው ስምምነት ነው የችግሩ ምንጭ ይላሉ፡፡ ፕ/ር መረራ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በሰነድ ያልተደገፈ (ወረቀት ያልያዘው) መሆኑ ሌላው አስቸጋሪ ገፅታው ነው ይላሉ፡፡
የሁለቱ አካላት ውዝግብ ወደ ህዝቡ መድረክ መምጣት የለበትም የሚሉት ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ መፍትሔው ውይይትና ድርድር ነው ብለዋል፡፡ ህዝቡን በሁለቱም ወገን በኩል እንደ መያዣ መጠቀም ተገቢ አለመሆኑንም ፕ/ር መረራ ይገልፃሉ፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ አባገዳዎችና የህዝብ ተወካዮች በተገኙበት ሁለቱ አካላት ውይይትና ድርድር ቢያደርጉ ለችግሩ እልባት ለማበጀት ይጠቅማል የሚሉት አቶ ቶሎሣ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አካላት ህዝቡ በድጋሚ ወደ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይገባ ልበ ቀናና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከኦነግ ጀርባ እኩይ አላማ ያላቸው ሃይሎች እንዳሉ የሚያስጠረጥሩ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚገልፁት የኦብኮ ሊቀመንበር፤ በተለይ ኦነግ ሀገር ቤት ከገባ በኋላ የመሣሪያ ትጥቅ፣ የወታደራዊ አልባሣት፣ የሠራዊት የእለት ቀለብ፣ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማስኬጃ ገንዘብ ከየት መጣ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ሁኔታም በመንግስትና በኦነግ መካከል ከፍተኛ የእርስ በእርስ አለመተማመን ፈጥሯል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡
የአቶ ቶሎሣን ሃሳብ በከፊል የሚጋሩት የፖለቲካ ተንታኙ ሜ/ጀነራል አበባ ተ/ሃይማኖት፤ የኤርትራ መንግስትና ኦነግ አሁን ያላቸው ግንኙነት ምን ድረስ ነው የሚለው መፈተሽ አለበት ባይ ናቸው፡፡
“የሁለቱ ውዝግብ በተራዘመ ቁጥር በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳርፋል፤ የኦሮሞ ህዝብንም ይጐዳል” የሚሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ህዝቡን ያሳተፈ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል።
በ1983 ዓ.ም ደርግን ከስልጣን ካስወገዱት ሃይሎች አንዱ ኦነግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኦነግ በሽግግሩ ወቅት ብዙም ሳይቆይ ነበር ከህወኃት/ኢህአዴግ ጋር አለመግባባት ውስጥ የገባው፡፡ ወዲያው ከሀገር በመውጣት የትጥቅ ትግል መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ላለፉት 26 አመታትም በዋናነት በኬንያና በኤርትራ መቀመጫውን አድርጐ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲዋጋ ቆይቷል፡፡ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱት ድርጅቶች አንዱ ለመሆን የበቃው ኦነግ፤ አሁን ከመንግስት ጋር የገባው ውዝግብ ወዴት ይወስደው ይሆን?
የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር፤ ኦነግ ጉዳዩን በእርጋታ ካልያዘው ልክ እንደ 1984ቱ ሀገር ጥሎ ሊሸሽ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ይላሉ፡፡ “ሁለቱ አካላት ተወያይተው የማይስማሙ ከሆነ፣ የኦነግ ሠራዊት ዳግም ወደ በረሃ የመመለስ እድል ይኖረዋል፤ ይህ በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡
በአቶ ቶሎሣ ሃሳብ የማይስማሙት ፕ/ር መረራ፤ የ1984 አይነት የአባራሪና ተባራሪ ፖለቲካ ፈጽሞ አይፈጠርም ባይ ናቸው፡፡ “አሁን ፖለቲካው ተቀይሯል” ያሉት ፕ/ር መረራ፤ “ሁለቱ አካላት ረጋ ብለው ህዝቡን መጠቀሚያ ሳያደርጉ ከተወያዩ ችግሩን መፍታት ይችላሉ” የሚል ተስፋ አላቸው፡፡
የቀድሞ የኦነግ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ፤ የኦነግን አካሄድ በተደጋጋሚ  ሲተቹ ቆይተዋል። “ታግሎ ወደ ሀገር ቤት ያመጣንን ወጣትና ህዝብ ማክበር አለብን፤ የድሉ ባለቤት ህዝቡ ነው” ይላሉ – አቶ ሌንጮ፡፡ ታዋቂው አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በበኩሉ፤ ኦነግ ከህዝቡ ጋር መቀላቀልና የህዝቡ ትግል አካል መሆን እንደሚገባው በመጠቆም በኦነግ አካሄድ ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
የኦዴፓ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የእምነት አባቶች በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተው ባከናወኑት የማሸማገልና የማግባባት ስራ በርካታ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፍትተው፣ በሠላማዊ መንገድ ለመታገል በመወሰን ወደ ሠላማዊ መንገድ እየተመለሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ወደ ሠላማዊ መንገድ የሚመለሱ ዜጐችን በአክብሮት ተቀብሎ፣ በፈለጉት የስራ መስክ ተሠማርተው የሚቋቋሙበትን መንገድ ለማመቻቸት መወሰኑን ሃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
Filed in: Amharic