>

ኧረ የመንግሥት ያለህ!!! (ከይኄይስ እውነቱ)

ኧረ የመንግሥት ያለህ!!!

ከይኄይስ እውነቱ

እስቲ ግራ የተጋባውንና መያዣ መጨበጫ የጠፋውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለጊዜው በመተው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ላንሳ፡፡

የዐቢይና የለማ አገዛዝ የአገርና የሕዝብ ውርደት በሆኑ ደናቁርት መንደርተኞች በ4ቱም ማዕዝናት በተወጠሩበት ሰዓት (ከተስፋው ይልቅ ሥጋቱ እያየለ መምጣቱን እያወቅኹ፤ በአገር ፀጥታና በሕዝብ ደኅንነት አያያዝ ያለባቸው ድክመት፣ በዴሞክራሲያዊ ሽግግር፣ በብሔራዊ መግባባት/ፍትሕ፣ ዕርቅና ይቅርታ ጉዳዮች፣ ባጠቃላይ አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ሥልጣን ምን ድረስ እንደሆነ በሚመለከት ያለኝ ተዐቅቦ እንደተጠበቀ ሆኖ) ተጨማሪ ራስ ምታት መሆን የለብንም በሚል የ27 ዓመታት ችግሮቻችንን አዳፍነንና ለጊዜው ዝምታን መርጠን ቆሻሻውን የአገራችንን ፖለቲካ እየታዘብን ተቀምጠን ነበር፡፡ እሊህ ወንድሞቻችን እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እሳት እየተግለበለበባቸው በመሆኑ ከበጎ ምክር ባለፈ ጥያቄዎቻችንን ገታ አድርገን ፋታ መስጠቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት ለአገራችንና ሕዝባችን መልካሙን በሚያስቡ ዜጎች ዘንድ ሲስተዋል ቆይቷል፡፡

አገራችን ከፖለቲካው ውጭ ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዳሉባት እሙን ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ሠራሽና አገዛዝ-ወለድ መሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡

ለዛሬው ማንሳት የፈለግሁት፣ ልንታገሠው የማንችልና ፋታ የማይሰጠን ጉዳይ የውኃና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እጦት ነው፡፡ ይህ ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ እንዳለ ቢገባኝም እኔ ነዋሪ በሆንኩበትና በተግባርም ላለፉት 2 ዐሥርታት ባለማቋረጥ እንደታዘብኩት ለመዲናችን እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን የፈረቃ ጉዳይ ሳይሆን አገልግሎቶቹ በአብዛኛው የከተማው ክፍሎች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም የውኃ አገልግሎት፡፡ አልፎ አልፎ በሚለቀቅበት ጊዜ እንኳን ከሌሊቱ 9 ሰዓት መነሳትን ይጠይቃል፡፡ አገልግሎቱን ባግባቡ ለመስጠት ባልቻሉ፣ የኃላፊነት ስሜት በማይሰማቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች ብልሹ አሠራር ምክንያት አንድ ዜጋ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ተነስቶ (ሊያውም ካለ) ውኃ እንዲቀዳ የሚደረገው ለምንድ ነው? ይህ ችግር ለዓመታት የዘለቀው እውነት የውኃ እጥረት ኖሮ ነው? ያውም በዋና ከተማችን? ገጠር ቢሆን ወራጅ ውኃ ወይም ምንጭ ፍለጋ እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት እነዚህ አገልግሎቶችን ወያኔ ትግሬ (ከአስፈጻሚ አሽከሮቹ ጋር) ሕዝብን ማንበርከኪያ መሣሪያ አድርጓቸው መቆየቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በይሉኝታ ቢሶቹ ቀጭን ትእዛዝ የሚለቀቁና የሚዘጉ አገልግሎቶች ነበሩ፡፡ በሲቪል ሰርቪሱና በመንግሥታዊ ድርጅቶች አካባቢ ነገሮች በአብዛኛው ቀድሞ ባሉበት ሁኔታ ወይም ብሶባቸው ይታያል፡፡ እነ ዐቢይ እነዚህ አካባቢ ጨርሶ የደረሱ አይመስልም፡፡ የኃላፊዎች  ለውጥ እዚህም እዚያም አድርገዋል፡፡ ለውጦቹም በአመዛኙ መናኛ ናቸው፡፡ ተሿሚዎቹ ኢሕአዴግ ወያኔ የሚባል ወንጀለኛ ድርጅት አባሎች ናቸው (ከኢትዮጵያ ምድር ብቃት ያለው ሰው የጠፋ ይመስል)፡፡ ውኃና ኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን ለማስተዳደር ሥልጣንና ተግባር ያላቸው መንግሥታዊ መ/ቤቶችና ድርጅቶች ቀድሞም አሁንም ለሕዝብ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለባቸው አይመስልም፡፡ አብዛኛው ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከተራው ሠራተኛ (አልቅሶ የገባው ጭምር) እስከ ከፍተኛ ኃላፊዎች ሕዝብን በማስለቀስ መጥፎ ስም ያተረፉ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት የሚባክንባቸውና የባከነባቸውም ተቋማት ናቸው፡፡ በንቅዘቱም ረገድ እንደዚያው፡፡ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ጣራ በነካው የኑሮ ውድነት ላይ የውኃና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ከአእምሮው ጋር የሆነ ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ሰዉ ኹሉ ሥራ ፈትቶ፣ ችግር የማይፈቱና ለተገልጋዩም ኅብረተሰብ ክብር የሌላቸው በርካታ የተቋማቱ ሠራተኞችንና ኃላፊዎችን እየተለማመጠ ለዓመታት ደጅ የሚጠናበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር ተሰላችተናል፡፡ ይቅርብን የማንለው ጉዳይ ሆኖብን እንጂ፡፡

በውኑ ፈጣሪን የምትፈሩ፣ ባትፈሩም እንኳን የሙያ ግዴታችሁን ባግባቡ የምትውጡ፣ የአገልግሎት ክፍያና የደመወዛችሁ ምንጭ የሆነውን ግብር የሚከፍለውን ኅብረተሰብ የምታከብሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ካላችሁ በእነዚህ መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚታየውንና ለዘመናት የዘለቀ ችግር ባስቸኳይ የሚፈታበትን መንገድ መፈለጉ ለነገ የማይባል ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

በመጨረሻም ከአውሬ በታች ለሆኑት ሕውሓቶችና እና ተረፈ-ወያኔዎች በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው የእናንተን አገዛዝ ባገራችን ዳግም ከማየት ጦም ማደርን፣ የውኃም ሆነ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን ማጣት እመርጣለሁ፡፡ እናንተው በፈጠራችሁት ችግር ሕዝብ ቢማረርም፣ የናንተ ቅጥ ያጣ ነውረኝነት እንደ ሕዝብ አስመርሯቸው ከመኻላችሁ የወጡት ለማና ዐቢይን የጥፋታችሁ ኹሉ ተሸካሚ ለማድረግ የምታደርጉትን መሠሪ ተግባር በሚገባ ያውቃል፡፡ የናንተን አርቲ ቡርቲ የሚሰማበት ዦሮ የለውም፡፡ ልቡሳነ ሥጋ አጋንንትን ያሰባሰበ ሰይጣናዊ ድርጅታችሁ (ሕወሓት) ከኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚጠፋ አልጠራጠርም፡፡  

Filed in: Amharic