>

"እኔ አማራ ነኝ" " እኔ ኦሮሞ ነኝ" የምንባባለው ኢትዮጵያችንን ለማን ጥለን ነው?!? (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)

“እኔ አማራ ነኝ” ” እኔ ኦሮሞ ነኝ” የምንባባለው ኢትዮጵያችንን ለማን ጥለን ነው?!?
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
“ግንብ በሀሳብ ተፋለሙ” 
“ትጥቅ ለመፍታት አልተስማማንም!”
እነዚህ የግብዣ ቃላት የማን እንደሆኑ የማያውቅ ያለ አይመስለኝም። ክፍት ላለመተው ያህል፥ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። የወያኔ አገዛዝ በሰላም እንዳይታገሉ የከለከላቸው ኢትዮጵያውያን አገር ጥለው ወጥተው በጽሕፈትና በመሣሪያ ሲታገሉ የቆዩ ብዙዎች እንደነበሩ ይታወቃል። አሁን በሰላም ለመታገል ለፈለገ ሁሉ አገሩ ገብቶ ለመታገል  በሩ ክፍት ሆኖለታል። ብዙዎችም ጥሪውን አክብረው ኢትዮጵያ ገብተዋል። ከነዚህ ውስጥ አርበኞች ግንቦት ሰባት፥ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባሮች፥ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግምባር ይገኙበታል። ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባር መሪዎች አንዱ፥ አቶ ዳውድ ኢብሳ፥ “ትጥቅ እንድንፈታ አልተስማማንም” ብለው ነበር። ይህን አባባል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “የአፍ ወለምታ ይሆናል” ብለውታል። ጉዳዩ እንደገና መታየት ያለበት ነው።
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙበት ዕለት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያመጡት ለውጥ ብዛትና ዓይነት የማይታመን ነው። ከሁሉም ይበልጥ የማደንቀው የፖለቲካ እስረኞችን ነፃ አውጥተው እስር ቤቶችን ባዶ ማድረጋቸውና፣ ወያኔዎች ኢትዮጵያን የሸፈኑበትን የፍርሃት መጋረጃ መግፈፋቸው ነው። እድሜ ለዶክተር ዐቢይ፥ አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ የሕወኃት ሰው ሲያይ፥ “ይመታኛል፥ ይገድለኛል፥ ያሳስረኛል” ብሎ ሳይሠጋ በአጠገቡ ያልፋል። አንድ  የሕወኃት የፓርላማ አባል እንደለመደው ሲሞላቀቅ፥ ሌላው አባል መናገር ሲፈቀድለት፥ ይሄ አነጋገር ፓርላማውን “አይመጥንም” ብሎ ሲገሥጸው ሰምተናል። ተገሣጩ ምንም አላደረገው፤ መልስ እንኳን አልሰጠም። ዕለቱን ታሪክ ይመዘግበዋል። ሰው ብቻ ሳይሆን፥  ብዙ ቤቶችም ነፃ ወጥተዋል፤ ባለቤቶቻቸው ወንጀላቸውን ተሸክመው፥ “እግሬ አውጪኝ” ፈርጥጠው ጠፍተዋል። መጥፋት እንኳን አልጠፉም፥ ተሸሽገዋል። ቤቶቹ ግን ነፃ ናቸው ጌታ የላቸውም። ሆኖም፥ ባለሥልጣንን መፍራት ከኢትዮጵያ ፈጽሞ ለማስወገድ ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
የለማ ቡድን አባላት አንድ ጥይት ሳይተኵሱ ኢትዮጵያን ከጅብ መንጋጋ ያወጡት፣ ምን ያህል የረቀቀ ጥበብ ቢኖራቸው ነው!! ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ችሎታ መኵራት ካስፈለጋቸው፣ በዚህ በለማ ቡድን ድርጊት ነው። የወያኔን መቅሠፍት ለመሸሽ አገር ጥሎ የወጣ ሁሉ  ወደ ሀገሩ መመለስ ጀምሯል። ከወያኔ ጋር ተገዳዳይ ጠላቶች የነበሩ ኢሕአፓዎች ሳይቀሩ እየገቡ ነው። በዚህ ባልታሰበ መንገድ በመጣ ለውጥ መገረማችንን እንዳናቆም፥ በየቀኑ አዳዲስ ለውጦች እናያለን። ባሁኑ ሰዓት ጆሮውን ከዜና ምንጮች ላይ ያልተከለ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ሆኖ፥ የምዕራቡ አገር ጋዜጠኞች የዶክተር ዐቢይን ሥራ ሲያደንቁ ስናይማ ድርሰታቸውን ለለውጡ እውነተኛነትና አዎንታዊነት ማስረጃ እናደርገዋለን።
ዘጠኝ ወራት
ዶክተር ዐቢይ ሥልጣን ይዘው ለውጡን ሲያከታትሉት እነሆ ዘጠኝ ወር ሆነናቸው። በግር ግሩ ውስጥ አገርን ሊጎዱ የሚችሉ (ሊሆኑ የማይገባቸው) አንዳንድ ነገሮች ሆነው እንደሆነ የሚል ሥጋት እየተነሣ ነው። ከዐረብ አገሮች ጋር የነበረን ግንኙነት የሻከረ ነበር፤ በምን ተአምር ነው ብዙ ዶለር የሰጡን? ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምክንያት እንደዛተችብን ነበር፣ በምን ተአምር ነው ወዳጃችን የሆነችው? እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ አትራፊ ኩባንያዎች ለምን ይሸጣሉ? እነዚህ ሁሉ ሰዎችን ሲያሠጉ ሰምቻለሁ፤ እኔን ግን አያሠጉኝም። ግብፅ መሥጋቷና ማሥጋቷ አለማሰቧ ነው እንጂ ውሀዋ አይቀነስባትም። ግድቡ የሚፈለገው ለመብራት ኃይል ብቻ መሆኑ ተደጋግሞ ተረጋግጦላታል። የኩባንያዎች መሸጥም በኢኮኖሚስቶች ሳይጠና የተደረገ አይመስለኝም።
እኔ የምሠጋው፣ የሀገሪቱ አንድነት እየተናጋና ሊጠግኑት ከማይቻል ደረጃ የደረሰ ስለሚመስለኝ ነው። ክልሎች እንደጎረቤት አገሮች በድምበር ይጣላሉ። የክልል ሰዎች ስለክልላቸው እንጂ ስለኢትዮጵያ ሲቆረቈሩ አይሰሙም። የኢትዮጵያ የአስተዳደር ሥርዓት ፌዴራል ይባል እንጂ፣ አምሳያው የአሜሪካ ክፍለ ሀገሮች አንድነት (United States) ሳይሆን፥ የአውሮፓ አህጉር አንድነት (European Union) ነው። የሀገሪቱ ፓርላማም የፈለገ ጥሎት የሚወጣውን የአውሮፓን ፓርላማ (European Union) ይመስላል። እያንዳንዱ ክልል ራሱን የቻለ ሀገር ሆኗል። አንዱን ክልል ከሌላው ክልል ጋር የሚያገናኘው ድልድይ አለ ከተባለ፥ በማጕያ መነጽር ቢፈልጉት አይታይም።
የኦሮሞ ክልል
የኦሮሞ ክልል የበለጠ አሥጊ ነው። ከኢትዮጵያ ታላቁን መሬት ቆርጦ ኦሮሚያ ያለው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባር ነው። መላ ኢትዮጵያን እንዳይወስድ ወያኔዎች አለቀቁለትም። ራሱን የቻለ አገር መሆን የሚችል ምድር እንዲወስድ ግን ፈቀዱለት።  ለክልሉ የተሰጠው ስም (ኦሮሚያ) ራሳቸውን ለሚችሉ አገሮች በሚሰጠው መንገድ ነው። የስሙን መጨረሻ ልብ እንበል–ኦሮሚያ፥ ቡልጋሪያ፥ ሀንጋሪያ፥ ሮማኒያ፥ ኢትዮጵያ። የሌሎቹ ክልሎች መሪዎች “ርእሰ መስተዳድር” ሲባሉ፥ “ኦሮሚያ” ያሉት ክልል መሪ  የማዕረግ ስሙ “ፕሬዚዴንት” ነው–ፕሬዚዴንት ለማ መገርሳ። የለማ ቡድን ብዙ ለውጥ ሲያደርግ ይኽንን የወያኔንና የኦነግን ሴራ አጠነከረው እንጂ አልነካውም፤ እንዳለ ተቀብሎታል። አምኖበት ነው? ወይስ ጊዜውን ይጠብቅ ብሎ ነው? አንድ ሰው (ኦሮሞ ነው) “የኦነግን ፍላጎት ለማ መገርሳና ዐቢይ አሕመድ ወርሰው በሥራ ላይ እያዋሉት ነው” ሲል ተሰምቷል። “ኦነጎች የፈለጉት ራሱን የቻለ የኦሮሞ  መንግሥት ተቋቁሞላቸዋል፤ ለማንና ዐቢይን እያመሰገኑ አርፈው ይቀመጡ” ማለቱ ነው።
ከላይ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከነሠራዊታቸው ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ፥ “ትጥቅ እንድንፈታ አልተስማማንም” ማለታቸውን አንሥቼ፣ ጉዳዩ እንደገና መታየት ያለበት ነው ብያለሁ። ኦነግና ሕወሐት ለኦሮሞዎች በሰጡት ክልል የሚከሠተውን ልዩ ሁኔታ ላየ፥ ጥሪውን ጋባዥና ተጋባዥ እኩል አልተረዱትም ይል ይሆናል እንጂ፥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንዳሉት፥ “የአፍ ወለምታ” መሆኑን ይጠራጠራል። አቶ ዳውድ ኢብሳ የተባባሉትን መረዳት አያቅታቸውም፤ ሕፃን ልጅ አይደሉም። ኦነግ ኢትዮጵያ ሲገባ መሣሪያውንም እድምበሩ ላይ ለመንግሥት እንዲያስረክብ አልተጠየቀም፤ እንደታጠቀ ነው የገባው። ስለትጥቁ ምንም ሳያወሩ፥ “ና ግባ፤ የታገልክላት ኦሮሚያ ያንተ ናት” ተብለው ይሆናል–አሻሚ ጥሪ።  ዜና አሰራጪዎች እንደሚሉት ከሆነ፥ አቶ ዳውድ አሁን የሚኖሩት በመንግሥት ወጪ ነው። ለመሆኑ፥ ኦነግ ትግሉን በሰላም እንዲያካሂድ የተጋበዘው የትግሉ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑ እየታወቀ ነው? ወይስ ተዘንግቶ? ትግሉ በሰላም ከሆነ፥  ኢትዮጵያን ማፈራረስ ይፈቀዳል ማለት ነው? የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት ይከበራል እንጂ ለድርድር አይቀርብም–ያውም የሀገሪቱን ሥልጣን ይዞ።
የክልል ስርዓትን ማራገፍ
ኢትዮጵያ በተዘረጋባት የክልል ሥርዓት ከቀጠለች፥ ወደፊት ካንዱ ክልል ወደሌላው ክልል ለመሄድ ስንፈልግ መግቢያ መግቢያ ፈቃድ ቢያስፈልግው አይገርምም። አንድ ሀገር ሆና የምትኖርበት መንገድ ግልጽ አይደለም። ብዙነት የአንድነት ተቃራኒ ነው። ራእያችን አገራችንን ገናና ማድረግ ከሆነ፥ የተጫነብንን የክልል ሥርዓት ማራገፍ አለብን። ክልልን የማይፈልገው በሥልጣን ላይ ያለው ፖለቲከኛ (በተለየ አማራው) ብዙ ነው። የተቃውሞ ድምፁን የማያሰማው፣ የለማን ቡድን ፈርቶ ይመስለኛል። ከፍርሃት ገና ሙሉ በሙሉ አልተላቀቅንም።
የሀገራችን ጉዳይ እንዲህ አሥጊ ሆኖ ሳለ፥ ተስፋ እንዳንቈርጥና እንዳይጨልምብን ብዙ ሻማዎች ሲያበሩ ይታዩኛል፤ አንደኛ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክልልን ለማስቀረት ቢፈቀድለት፥ አብዛኛው ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ያስቀረዋል። የተቃዋሚ ቡድኖች ሆይ፥ አሸናፊው አጀንዳችሁ ምን እንደሚሆን ልብ በሉ!! ሁለተኛ፥ ኦጋዴን እንዳትገነጠል  ተደርጓል፤  ሦስተኛ፥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፥ “የኢትዮጵያ ክፍሎች ከዛፍ ላይ እንደሚወድቅ ቅጠል የሚገነጠሉ አይደለም”  ብለዋል። አራተኛ፥ ኦነግ አገር ገብቶ እንዲታገል የተነገረው ቃል አሻሚ ነው። ከነዚህ ሁሉ ይበልጥ ተስፋ የሚሰጠን አምስተኛው ነው፤ ዶክተር ዐቢይ  ኢትዮጵያን ገናና አገር ለማድረግ ታጥቀው ተነሥተዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ልትሆን እንደምትችል የተገነዘቡ ምዕራባውያን Power house ብለዋታል።
ክቡር ዶክተር ዐቢይ (በውድድሩ የሚያሸንፍ ሌላ መሪ ከመጣም) ክልል ያመጣብንን ችግር አስወግደው፥ ኢትዮጵያን ገናና ሀገር የሚያደርጉበትን ዘዴ የኢትዮጵያ አምላክ ያሳያው፤ በቀኝ ያውላቸው። መልካም የልደት በዓል።
Filed in: Amharic