>
5:13 pm - Friday April 19, 3168

ህወሃት እንዴት አደብ ይግዛ? (መስከረም አበራ)

ህወሃት እንዴት አደብ ይግዛ?
መስከረም አበራ

በሃያ ሰባት አመታት የህወሃት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርዓት የኖረው የሃገራችን ህዝብ በትግሉ የህወሃትን የበላይነት ከኢትዮጵያም ከኢህአዴግም ትከሻ ማሽቀንጠርን ችሏል፡፡ ስልጣን ሲጥመው የቀረበት ህወሃት ታዲያ እሱ የማይዘውራት ኢትዮጵያ በሰላም ውላ ማደሯን የሚወድ አይመስልም፡፡ በስልጣን ዘመኑ “እኔ ከሌለሁ ሃገር ይፈርሳል” እያለ ሲያስፈራራ ስለኖረ እሱ በሌለበት ሃገር ሰላም ውላ ማደር እንደማትችል ማስመስከር ይፈልጋል፡፡ ህዝብ ለውጡን ለመደገፍ ነቅሎ በወጣበት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር፣ በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚከሰቱ ብጥብጦችን በመቆስቆስ፣ እንደ ኦነግ ያለውን ወዳጅ ጠላት የማይለይን የፖለቲካ ቡድን አይዞህ እያለ በማበጣበጥ ይጠረጠራል-ስልጣን ወዳዱ ህወሃት፡፡

ሳይፈልግ ብቻ ሳይሆን ሳያስብ የለውጥ ማዕበል ያጣለመው ህወሃት ለውጡ ይዞት የመጣውን አመራር ለመቀበል እንደተቸገረ ያስታውቅበታል፡፡አሁን የለውጥ ሃይል ሆኖ ስልጣን የተቆናጡት አካላት (በዋናነት ኦዴፓ እና አዴፓ) ቀድሞ የህወሃት ታማኝ ታዛዥ አገልጋዮቹ የነበሩ መሆናቸው ህወሃት ለራሱ ከሚሰጠው የተጋነነ እና የተሳሳተ ግምት ጋር ሲደመር ያፈጠጠውን እውነት ለመቀበል እንዲቸገር ሳያደርገው አልቀረም፡፡

ህወሃት ሊወድቅ ዘመም ዘመም ሲል ወደ ጀርመን ተጉዘው የህወሃት ደጋፊዎችን ያነጋገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ “ህወሃት በሌላ ይታዘዝ ማለት ነውር ነው” ሲሉ የተናገሩት ንግግር ህወሃቶች ንዑስነታቸውን በማይመጠን ሁኔታ ለራሳቸው የሰጡትን ትልቅ ግምት አመላካች ነው፡፡ እንዲህ ባለ አለቅጥ በተጋነነ የትልቅነት ስነ-ልቦና ውስጥ የቆየው ህወሃት በራሱ አገልጋዮች ተባርሮ መቀሌ መግባቱ ሊቀበለው የማይፈልገው ሃቅ ነው፡፡ ሃቅን መቀበል ባለመቻሉ ሳቢያ በስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ያለው ህወሃት የራሱን ቀውስ ሃገራዊ ቀውስ ለማስመሰል ታጥቆ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በሃገራችን የታየውን የለውጥ ጭላንጭል በማጨለሙ በኩል ህወሃት ቀዳሚው ስጋት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ህወሃት የለውጡ ስጋት መሆኑን የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ የመጀመሪያው እና ዋነኛው በወንበሩ ላይ የተቀመጠውን የለውጥ አመራር እንደመንግስት ለመቀበል መቸገር ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ ከሚገለፅባቸው ሃቆች አንዱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር በወንጀል የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ትግራይ ሰብስቦ ማስቀመጡ ነው፡፡ ጌታቸው አሰፋን የመሰለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በጉያው የያዘው ህወሃት “ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ይዤ ለማእከላዊው መንግስት የሰጠሁት እኔ ነኝ” ሲልም ይደመጣል፡፡ ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተያዙ ሰሞን ወንጀለኞችን ለመያዝ የትግራይ ክልላዊ መንግሰስት ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ የክልሉ መሪ ዶ/ር ደብረፅዮን ተናግርው ነበር፡፡ ይህን ብለው አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ “ወንጀለኞችን ተጠያቂ የሚያደርገው የመንግት አካሄድ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ያለመ ነው” ሲሉ ነገሩን ሁሉ እግር በራስ አድርገውት ቁጭ አሉ፡፡ ይህ አደገኛ አስተሳሰብ የሚመሩት ክልል ህዝብም የሚጋራው እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ሰላማዊ ሰልፍ በማታውቀው ትግራይ ክልል ሰው በቤቱ የቀረ የማይመስልበት ሰልፍ አሰለፉ፡፡

ህግ የሚፈልጋቸውን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች የደበቀ ክልል ህገ-መንግስት ይከበር ሲል የዋለበት ሰልፍ የትግራይ ክልል መንግስት ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆኑን ያስመሰከረበት ነው፡፡ ይህን በመሰለው ለተጠረጠረ ወንጀለኛ ጥብቅና የመቆም ሰልፍ ያሁሉ የትግራይ ህዝብ መገኘቱ ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ በጣም የተራራቁ ናቸው ብሎ የሚያስበውን ከትግራይ ውጭ ያለ ሌላው ኢትዮጵያዊ በከፍተኛ ግርምት ውስጥ የከተተ ነበር፡፡

በሰልፉ ሰዓት ከተደረገው የዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር በተጨማሪ እንደ አቶ አስመላሽ ገ/ስላሴ፣ አቶ ስብሃት ነጋ ያሉ የህወሃት አባላትም በትግራይ ቲቪ ብቅ እያሉ የሚናገሩት ንግግር ኢትዮጵያ ከህወሃት ውጭ በሌላ መተዳደሯ እንደማይዋጥላቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡ አልዋጥ ያላቸው ሃቅ ደግሞ ህዝብን አግተልትሎ ሰልፍ ከማስወጣት አልፎ በመላ ሃገሪቱ የሚደረጉ ብጥብጦችን እስከ ማጋፈር የደረሰ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ከመንግስት በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተገለፀ ነው፡፡

የትግራይ ክልላዊ መንግስት ለፌደራሉ መንግስት አልታዘዝም ከማለት አልፎ ራሱን እንደ ሉዓላዊ ግዛት በማሰብ በህገመንግስቱ ያልተፈቀደለትን አካሄድ እንደ መብት በመቁጠር ለኤርትራ መንግስት ደብዳቤዎችን በመፃፍ ግንኙነት ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት በፌደራል መንግስቱ ታዞ ከዛላምበሳ በሚነሳበት ወቅት ያካባቢው ነዋሪ ያለመብቱ ገብቶ ለማዘዝ ሞክሯል፡፡ የክልሉ መንግስት በማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዝ ለስራ ጉዳይ ወደ ትግራይ የሚገቡ ወታደራዊ መኮንኖችን እና ተሸከርካሪዎቻቸውን አግቶ ለወራት በትግራይ አስቀምጧል፡፡ ዶ/ር ደብረፅዮንን፣ አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴን፣ አቶ ጌታቸው ረዳን፣ አቶ አባይ ፀሃይየን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሃት አባል የፓርላማ ተመራጮች ሌላው ቀርቶ ዶ/ር አብይ ፓርላማ በሚገኙባቸው ቀናት እንኳን የፓርላማ ወንበራቸው ላይ አይታዩም፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ፓርላማው ከፍተኛው የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ የፓርላማ አባላት የተባሉ ሰዎች በመርህ ደረጃ ይህን ከፍተኛ ስልጣን የተሸከሙ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስልጣን ደግሞ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው ነገር ነው፡፡ የፓርላማ አባልነትን የመሰለ ክብር ያለው ሃላፊነት የተሸከሙ ሰዎች ከኔ ቢጤው ተራ ህዝብ ላቅ ያለ ህግ የማክበር ስብዕና ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ በእኛ ሃገር በተለይ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የፓርላማ አባላት ላይ እየታየ ያለው ፈለግ ግን ህግ አክባሪነትን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ የህዝብ ድምፅ ይሆናሉ ተብለው በክቡሩ የፓርላማ ወንበር የተሰየሙ አባላት አዘውትረው በፓርላማ ስፍራቸው ሲገኙ አይታይም፡፡

ይህ ነገር በህወሃት ባለስልጣናት በተለይ ባስ ይላል፡፡ ከላይ በስም የተጠቀሱት የህወሃት ባለስልጣናት የዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በፓርላማ አዘውተረው ሲገኙ አይታይም፡፡ በተመሳሳይ የቀድሞው ጠ/ሚ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ ባላቸው አቶ መለስ ካረፉ ጀምሮ ወደ ፓርላማ ትውር ብለው አያውቁም፡፡ ይብስ የሚገርመው ደግሞ ህግ-ይከበር ብለው ሰልፍ የሚወጡት/የሚያስወጡት እነሱው መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለነዚህ የህወሃት ባለስልጣናት ፓርላ የሚያስቀምጣቸው፣ ሃላፊነቱ የሚጥማቸው፣ ህግ አክባሪ ከእኔ በላይ ላሳር የሚያስብላቸው ሁሉ የተቆራኛቸው የስልጣን ጥም እንጅ ሌላ እንዳልሆነ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ የአዲስ አበባውን ስልጣን ተነጥቀው ወደ መቀሌ በኮበለሉ ማግስት ስለ ህግ አክባሪነታቸው ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ሲመፃደቁ መኖራቸውን ረስተው የፓርላማ ወንበራቸው ላይ እንኳን ያለመገኘት ተራ አመፀኛነት ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡

እነዚህ ባለስልጣናት ፓርላማ አለመገኘታቸውን አስመልክቶ ሃይ የሚላቸው አካል የሌለ መሆኑ ደግሞ ኢህአዴግ መሪ በሆነበት መንግስት ህግ ምን ያህል መቀለጃ እንደሆነ ያሳያል፡፡ መቼም የፓርላማ አባላት ስነ-ምግባር ከፓርላማ ስንት ቀን መቅረት እንደሚያስቀጣ ሳያስቀምጥ አይቀርም፡፡ ፓርላማ ቀርቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ተማሪ ምን ያህሉን የትምህርት ቀን በክፍል ውስጥ መገኘት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ራሳቸውን እንደ ህግ አክባሪ በመቁጠር አትዝረፉ ያላቸውን ሁሉ በህገ-ወጥነት እየከሰሱ የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የነበሩ ግብዝ የህወሃት ባለስልጣናትም ከፓርላማ መቅረት ህጋዊ እንዳልሆነ አያጡትም፡፡ ከፓርላማው የሚያስቀራቸው ጉዳይ ሌላ ነው- የአዲስ አበባውን ወንበራቸውን የማጣት እብድ የሚያደርግ ቁጭት፡፡

ሕወሃት ተበድሏል?

ሳያስቡት ከአዲስ አበባ ተባረው መቀሌ የከተሙት አዛውንት የህወሃት ባለስልጣናት ቁጭታቸውን ተንፈስ ሚያደርግላቸው እጃቸው ላይ የቀረ ነገር ቢኖር ስልጣናቸውን ለቀማቸው አካል ባለመታዘዝ ንቀታቸውን ማሳየት፣ የወንበር ነጣቂያቸውን ሰላም ከሚያደፈርስ ጋር ሁሉ ማህበር መጠጣት ነው፡፡ከኦነግ ጋር ማዕድ ያስቆረሳቸው ይሄው ነው፡፡ ኦነግ በበኩሉ በኦዴፓ በሚመራው አዲሱ የለውጥ አመራር ላይ ቅሬታ አለበት፡፡

የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ዛሬ በኦዴፓ የኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ ተደርገው የሾሙትን ጀነራል ከማል ገልቹን በኤርትራ በረሃ ደማቸውን ሊያፈስ አጥብቆ ይፈልጋቸው የነበረ ደመኛው ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ለውጡን የሚመራው ኦዴፓ “በታሪክ አማራ ኦሮሞን ሲበድል ኖሯል” የሚለውን የዳውድን ኦነግ ፓርቲ ፕሮግራም የማዕዘን ድንጋይ አናግቶበት የሚያላዝንበት ሙሾ አሳጥቶታል፡፡ በኦዴፓ አዲስ እይታ ሳቢያ የአማራ እና ኦሮሞ የጠላትነት ታሪክ ግርግዳ መፍረስ ምናልባትም ከኦነግ በላይ ህወሃትን እብድ በሚያደርግ የፖለቲካ ኪሳራ ላይ የጣለው ነው፡፡ የአብይ/ለማ/ደመቀ/ገዱ ቡድን በህወሃት ላይ ያስመዘገበው አብረቅራቂ ስኬት ጅማሬም ፍፃሜም ይሄው ስልት ነው፡፡ ይህ የለውጡ አመራር ስኬት ደግሞ የዳኦድን ኦነግ እና ህወሃትን እኩል ያከሰረ ስልት ስለሆነ ነው ሁለቱ ከሳሪዎች ግንባር መፍጠራቸው፡፡ በተመሳሳይ የጀነራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ መደረግ የዳኦድን ኦነግ እንዳናደደ ሁሉ የጀነራል አሳምነው ፅጌ የአማራ ክልል የፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ መሆን ደግሞ ህወሃትን ብግን የሚያደርግ የእግር እሳቷ ነው፡፡

ሌላው ህወሃት ተከፋሁበት የሚለው ነገር ሃገር ቆማ እንዳትሄድ አድርጎ ሲዘርፍ የኖረውን ሜቴክን ሲያጋፍሩ የኖሩት ጀነራል ክንፈ ዳኜው ሲያዙ በሃገሪቱ ቴሌቭዥን ቀጥታ መተላፉ፣ እጃቸው ላይ ካቴና ገብቶ መታየቱ፣ ሰውየው ይመሩት የነበረውን ሜቴክን ሁለንተናዊ ሌብነት የሚያሳይ ዲክመንተሪ ፊልም መሰራቱ ነው፡፡ ክንፈ ዳኘው ሊያመልጡ ሲሉ የተያዙበት ሁኔታ ከቦታው በቀጥታ መተለላለፉም ሆነ ሰውየው ሲያዙ እጃቸው ውስጥ ካቴና መግባቱ ምንም ነውር ያለበት ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ማንም ሰው ከህግ ስለማያመልጥ የፍርድቤት ጥሪ ሲደርሰው አክብሮ ህግን መጋፈጥ እንዳለበት፣ መሸሽ እንደማያዋጣ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የጀነራል ክንፈ ጉዳይ በፍርድ ቤት ተይዞ ሳለ ጉዳዩን አስመልክቶ ዶክመንተሪ ፊልም መስራቱ ይልቅ ጥፋት ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን አባዜውን ሊያቆም ይገባዋል፡፡

በተረፈ ተጠርጣሪ ወንጀለኛው እጅ ላይ ለምን ካቴና ገባ የሚለው ነገር ከህወሃት ሲመጣ የሚያስመሰክረው የህወሃትን ድልብ ዘረኝነት ነው፡፡ምክንያቱም ይህን ወንጀል አድርጎ የሚያወራው ህወሃት ራሱ ክስ ፈብርኮ በከሰሳቸው መናኝ መነኮሳት ሰላላ እጅ ውስጥ ካቴና አስገብቶ፣ እንደ በግ አቆራኝቶ አስሮ ሲያንገላታ የኖረ፣ እነ ኡስታዝ አቡበክርን፣ እነ አንዱአለም አራጌን፣ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በካቴና ጠፍንጎ አስሮ በቴሌቭዥን ሲያሳይ የነበረ ግፈኛ መሆኑ ነው፡፡ አሁን የክንፈ ዳኘው ልዩ ሆኖ የታየው ክንፈ ዳኘው “ወርቅ ነው” እያለ ከሚያወራለት ዘር የተገኙ የወንዙ ሰው ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ህወሃት ይሄ እበልጣለሁ ባይነቱ ከዙፋኑ ባፍጢሙ እንደደፋው እስከ ዛሬ እንኳን አለመገንዘቡ ነው፡፡

ሌላው የህወሃት ትልቅ በደል እንደደረሰበት አድርጎ የሚያቀርበው ነገር ፓርቲው ሲያጋፍረው በኖረው የደህንነት መስሪያቤት አዛዥነት በሰው ልጆች ላይ ሲደረግ የኖረው አረመኔያዊ የሰብዐዊ መብት ጥሰት በሃገሪቱ ቴሌቭዥን መጋለጡ፣ ሲጋለጥ ደግሞ ተጎጅዎቹ “የገረፉን ትግርኛ የሚናገሩ ሰዎች ናቸው” ማለታቸውን ነው፡፡ ይህን የሚለው ህወሃት ሃገሪቱን በሚዘውርበት ዘመን የህወሃቱ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተገኝተው የካቢኔ ሹመት ሲያፀድቁ ከእጩዎቹ ስም ቀጥለው የሚጠሩት ዘራቸውን እንደነበር ማንም አያጣውም፡፡ ህወሃት ባዋቀራት ኢትዮጵያ ለመሾም ለመሻር፣ ለመግረፍ ለመገረፍ፣ ነግዶ ለማትረፍ ለመክሰር፣ ለመውጣት ለመግባት ሁሉ ዘር ሳይጠራ አይሆንም፡፡ ስዚህ የገራፊ ዘር ሲጠራ ሰማይ እና ምድር ቦታ የተቀያየሩ ማስመሰሉ ቅን ነገር አይደለም፡፡ የገራፊ እና የተገራፊ ድልድል ለማድረግ ዘር መስፈርት መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ገራፊ ለመሆን ወንበር ላይ የተቀመጠውን ባለጊዜ የልብ የሚያደርስ ዘር ባይፈለግ ኖሮ ገራፊው እና አሳሪው ሁሉ ከአንድ ዘር በልሆነ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ዘር ሳይጠራ ምንም የማይደረግበት ሃገር በራስ እጅ ካበጃጁ በኋላ ለምን የገራፊ ዘር ተጠረራ ብሎ ተበደልኩ ማለት ትርጉም የለውም፡፡

የአማራ ክልል እና የራያ ወጣቶች ወደ ትግራይ የሚሄደውን መንገድ ሲዘጉብን የዶ/ር አብይ መንግስት ዝም ማለቱም አስከፍቶናል ባዮች ናቸው ህወሃታዊያኑ፡፡ መንገድ መዘጋቱን ብቻ ሳይሆን ለምን ተዘጋ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡ የራያ ህዝብ መንገድ የዘጋው ማንነቴ ትግሬ አይደለም በማለቱ ሳቢያ የትግራይ ልዩ ሃይል በጥይት ስለቆላው ነው፡፡ በአማራ ክልል በኩል ያለውን መንገድም እንዲሁ የአማራ ህዝብ በህወሃት ተዘቅዝቆ ሲገረፍ የኖረ በመሆኑ በመሰለው መንገድ ቅሬታውን ማሳየቱ ነው፡፡

በፌሮ ሲገረፍ የኖረ፣ በማንነት ጥያቄው ላይ ሲሾፍበት የኖረ ህዝብ ለተወሰነ ቀን መንገድ መዝጋቱ እሪ ሊያስብል አይገባም፡፡ የሚያዋጣው ስህተትን አምኖ ለበደል ይቅርታ መጠየቅ እንጅ ስገርፍ የኖርኩት ህዝብ ዘንባባ ያንጥፍልኝ የሚል ትዕቢት አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የቆየውን ያህል ቆይቶም መንገዱን ያስከፈተው የዶ/ር አብይ መንግስት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ የዶ/ር አብይ መንግስትም ቢሆን ህዝብ ቅሬታውን ማቅረብ ያለበት መንገድ በመዝጋት እንዳልሆነ ህዝብን ቀርቦ እስኪያስረዳ ቀናት እንደሚያልፉ መገንዘብ ከባድ ነገር አይደለም፡፡ አብይ መንገዱ የተዘጋ የዕለቱ ዕለት ከዙፋኑ ወርዶ ሲገሰግስ አድሮ ለምን በማግስቱ አላስከፈተልንም የሚለውም እበልጣለሁ ባይነትን የተሸከመ ትዕቢት ያለበት ክርክር ስሆነ የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡

ከሁሉም በላይ ህወሃት መንገድ ተዘጋብኝ ብሎ በሚጮህበት ወቅት ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ እሪ የማይሉ ግን ለወራት መንገድ ተዘግቶባቸው ያሉ ወገኖች ነበሩ፤ ወለጋ ላይ በጥይት የሚቆሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ወቅቱ የሽግግር እንደመሆኑ፣ ህወሃት ደግሞ ደህና በመስራት የማይታወቅ ፓርቲ እንደመሆኑ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ባልጠየቀበት ሁኔታም ሁልቀን ፋሲካ መጠበቅ የለበትም፡፡ ህወሃት ራሱ በሰጣት የቤት ስራ ምክንያት እየታመሰች ባለች ሃገር ለምን የኔሰፈር ብቻውን በቸር ውሎ አላደረም ማለት፣ ይህንንም አምርሮ ማራገብ ክፉ ራስ ወዳድነት ነው፡፡

በሙስና እና በሰብዐዊ መብት ጥሰት የተጠየቁ አመራሮች ሁሉ ህወሃቶች ብቻ ናቸው፤ ይህ የሆነው ደግሞ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ነው የሚለው ሌላው ህወሃቶች ተለይተን ተጠቃን የሚሉበት ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር የመጀመሪያው ክርክር በወንጀል መጥሪያ የተቆረጠባቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ህወሃቶች ብቻ አይደሉም፡፡ህወሃቶች ብቻ የሆኑት የፍርድቤት መጥሪያ ተቆርጦባቸው ሳለ ለህግ አንታዘዝም ብለው በትውልድ ቦታቸው የከተሙት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ለተጠርጣሪ ወንጀለኛ የወንዙ ልጆች ዘር ቆጥሮ መጠለያ እየሰጠ ያለውም የትግራይ ክልላዊ መንግት ብቻ ነው፡፡ እነ ያሬድ ዘሪሁን፣ ተስፋየ ኡርጊ፣ ጠና ቁርንዲ ወዘተ ትግሬዎች ያልሆኑ፣ የክልላቸው መንግስትም ዘር ቆጥሮ ያልደበቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በተረፈ ወደፊትም በተጠያቂነቱ ዝርዝር የህወሃት ሰዎች በርከት ብለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ህወሃት ከመባረሩ በፊት መስርቶት የነበረው ስርዓት የወንዝ ልጆች ተጠራርተው፣ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ የሃገሪቱን ሁለመና የመዘወራቸው ነፀብራቅ እንጅ እንደሚያወሩት ትግራይን የማጥቃት ሃራራ ያለበት መንግስት ስለመጣ አይደለም፡፡ የሃገራችን መንግስት ህወሃትን የማንበርከክ ጥማት አለው ቢባል እንኳን ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ጌታቸው አሰፋን የምትፈልገው ትግራይ ተንበርክካ ለማየት ካላት ክፉ ምኞት ሊሆን አይችልም፡፡ ማገናዘብ ደግ ነው!

ህወሃት እንዴት አደብ ይግዛ?

ወንጀለኛ ሰብስቦ የያዘው፣ የፌደራሉን መንግስቱን በግልፅ ሃገር ማስተዳደር የማይችል ነው የሚለው የትግራይ ክልልን የሚመራው የህወሃት አዛውንቶች ስብስብ በሃገር ላይ ሌላ ሃገር መስርቶ የመኖሩ ነገር ሊያበቃ ይገባል፤ በክልሉ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም ከህግ በላይ አለመሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ለውጥ ውስጥ ነኝ ብላ መናገር አትችልም፡፡ ትዕግስት የህግ የበላይነትን ተፈታትኖ፣ አለቃ እና ምንዝር የማይታወቅበት ስድ ፖለቲካ እስኪያመጣ ድረስ ልቅ መሆን የለበትም፡፡

የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ስር እንደመሆኑ መጠን በክልሉ ያሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን እንዲሰጥ መለመን ሳይሆን መታዘዝ ነው ያለበት፡፡ ለወራት ወንጀለኛን ደብቆ ያስቀመጠው የትግራይ ክልል መንግስት ውንጀል ሰርቷልና ከደበቃቸው ወንጀለኞች እኩል መጠየቅ አለበት፡፡ ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት የክልሉ ፕሬዚደንት ዶ/ር ደብረፅዮን በተለይ በግምባር ቀደምነት መጠየቅ አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ እንደ መንግስትም እንደፓርቲም እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡

እንደ መንግስት የትግራይ ክልል መንግስት ተጠርጣሪ ወንጀለኞቹን ለፌደራሉ መንግስት የሚያስረክቡበት የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በጊዜ ገደቡ የማያቀርቡ ከሆነ በሚኒስትሮች ምክርቤት አስወስኖ የዶ/ር ደብረፀዮንን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት በፓርላማ ማስወሰን፡፡ ወንጀለኛ የደበቀ ወንጀለኛ ነውና ደብረፅዮንም ከተፈላጊ ወንጀለኖች ዝርዝር ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ክልሉ ደግሞ በታዳኝ ወንጀለኛ መመራት ስለሌለበት የፌደራል መንግስቱ በደብረፅዮን ለሚመራው የክልሉ መንግስት እውቅና መንፈግ አለበት፡፡ እንደ መንግስት ይህን ካደረጉ በኋላ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ተሰብስቦ ህገ-ደንቡን በተከተለ ሁኔታ በህወሃት ላይ ቅጣት መጣል አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ካልሆነ መንግስት ለክልሉ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እስከ ማቆም የሚሄድ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡

Filed in: Amharic