ኢትኦጲስ
በአንክሮ ላስተዋለው፣ ጌታቸው አሰፋ ከሥልጣናቸው እስኪነሱ ድረስ፣ ህወሓት በዐቢይ አህመድ መመረጥ ደስተኛ ያልነበረ ቢሆንም፣ ከኢህአዴግ ተነጥሎ የመጓዙ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ የሆዱን በሆዱ አድርጎ፣ ቀስ እያለ የበላይነቱን የማስመለስ ተስፋ ነበረው፡፡ ዕጣ ፋንታው ሆኖ ግን፣ እሱ ዐቢይን ለምሣ ሲያስባቸው፣ ዐቢይ ቀድመው ቁርስ አድርገውት አረፈው፡፡
ከዚህ በኋላ፣ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” ዓይነት ፖለቲካ ነው ይዞ የሚገኘው፡፡ የጌታቸው ውድቀት የህወሓት ውድቀት መሆኑ፣ እነ መለስ ያቆሙት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በኃይል ላይ ያረፈ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ የሥርዓቱ ህልውና ግን፣ በ”ነበር” ብቻ የሚታለፍ ሊሆን አልቻለም፡፡ ሥርዓቱ አዲስ አበባ ላይ የፈረሰ ቢሆንም፣ ትግራይ ላይ ግን እንደቀጠለ ነው፤ ከድሮው የባሰ አደጋ ፈጥሮ ይገኛል፡፡
በአንድ ሀገር ሁለት ሥርዓት፣ ሁለት መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡ በፌድራል ሥርዓት ሁለት ሥርዓትና መንግስታት የሉም፤ ያለው አንድ ሥርዓት፣ አንድ መንግስትና፣ በዚያ ውስጥ የስልጣን እርከንና ክፍፍል ነው፡፡ በፌደራሊዝም የጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መኖር፣ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር ነው፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ሥርዓት ፌድራላዊ አይደለም፤ ወይ ኮንፌዴሬሽን ነው፣ ወይ እንደ ዘመነ – መሳፍንቱ ሥርዓት አልበኝነት ነው፡፡
በመለስ ዜናዊ ዘመን፣ ኢትዮጵያ በተግባር አህዳዊ እንጂ ፌድራላዊ ሥርዓት ውስጥ አልኖረችም፡፡ ይኸው እውነታ፣ በኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን እየተንገዳገደም ቢሆን ቀጥሏል፡፡ አሁን በጀመር ነው የዐቢይ ዘመን ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ከአህዳዊው ወደ ዘመነ – መሳፍንቱ ሥርዓት አልበኝነት የመስፈንጠር አደጋ እያንዣበባት ነው፡፡ በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር፣ ጌታቸው አሰፋን “አሳልፌ አልስም” ብሎ አሻፈረኝ ማለቱ፣ የዚህ አደጋ ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደዚህ የውድቀት መንገድ እንዳትገባ፣ የፌድራል መንግስቱ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቅበታል፡፡
የዐቢይ መንግስት ትልቅ ፈተና ተጋርጦበት እንደሚገኝና፣ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም የሚጠፋው አይደለም፡፡ ለግዜው የመረጡው መንገድ፣ ህወሓትን በከበባ አዳክሞ ማንበርከክ ነው፡፡ በዛላንበሳ በኩል ያለው የኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ተዘግቶ፣ በቡሬ በኩል ክፍት መሆኑ፣ የዚህ ዕቅዱ አንድ መገለጫ ነው፡፡ በዐማራ በኩል ያለው በር ከተዘጋ ሰነባብቷል፡፡ በቅርብ በአፋር ክልላዊ መስተዳደር ከተደረገው ሹም ሽር በኋላም፣ በዚያ በኩል ያለውም በማንኛቸውም ግዜ ሊዘጋ የሚችል ነው፡፡ በሱዳን በኩል ያለውን ለመዝጋት ዱፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ አልባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ፣ ይህ ትልም ስኬት የመሆን ዕድሉን በእጅጉ ያሰፋዋል፡፡
ይህ የከበባ እንቅስቃሴ ህወሓትን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ ጭንቀቱን በስብሃት ነጋ በኩል ሲያስተጋባም፣ “ኢሳያስ አፈወርቂ አሁንም ሽብርተኛ ነው” የሚል ስሞታ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን ላይ እየተደመጠ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ፣ ህወሓትን አንድም ጥይት ሳይተኮስ ለማንበርከክ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፤ ሃሳቡ መጥፎ አይደለም፡፡ ውጤት ለማምጣት ግን፣ ግዜ የሚፈልግ ሆኖ ይታያናል፡፡ እንደ ሀገር፣ ያ ጊዜ አለን ወይ? የሚለው ጥያቄ በእጅጉ ያሳስበናል፡፡
ከዚህ በሻገር፣ በማዕቀብ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻል ቢሆንም፣ ሁሌም የፖለቲካ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል የኩባ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ዚምባብዌ ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ እርግጥ፣ የህወሓት አቅም ከእነ ኩባ ጋር የሚነፃፀር ባሆንም፣ የህወሓት አመራር፣ ሥልጣን ከሚለቅ፣ አፈኖ የያዘውን ህዝብ ስቃይ እንደሚመርጥ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ የህወሓት ችግር በማዕቀብ ብቻ የመፈታት ዕድሉ የጠበበ ነው፡፡
የፌድራል መንግስቱ ከማዕቀብ ባሻገር ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ሁለገብ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል፡፡ በአንፃራዊነት አነስ ያለውን መሰዕዋትነት ፈርቶ፣ ሀገሪቷን ትልቅ ዋጋ ለሚጠይቃት ሥርዓተ አልበኝነት ማመቻቸት የለበትም፡፡ ህወሓት አዲስ አበባ ላይ የወረቀት ነብር ሆኖ እንደተገኘው ሁሉ፣ በትግራይም የተለየ ቁመና የለውም፡፡
ኢትዮጵያን ከሥርዓት አልበኝነት እንታደጋት፡፡