>
1:06 am - Thursday December 1, 2022

 የፖለቲካ ድርጅቶችን ወቅታዊ አካሄድ አስመልክቶ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)

የፖለቲካ ድርጅቶችን ወቅታዊ አካሄድ አስመልክቶ አጭር አስተያየት

አበጋዝ ወንድሙ

በሀገራችን አሁን አየታየ ያለው ለውጥ እንዴት እንደመጣ፣ በለውጡ አማካይነትም የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት፣ ይሄም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ ለሚደረገው ረጅም ጉዞ  መልካም የጥርጊያ መንገድ ሆኖ  የሚያገለግል መሆኑ፣ አሁንም ግን  የበላይነቱን ይዞ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግ መሆኑን ባላገናዘበ በሚመስል መልኩ፣ ከተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ስብስቦችና ተጽአኖ ፈጣሪ ነን ብለው ከሚያስቡ ግለሰቦች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ለመንግስት የሚቀርቡ ጥያቄዎችና አካሄዶች፣ አንዳንዶቹ የሚያስገርሙ ከመሆናቸውም በላይ ለምንመኘው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አሳድሮብኛል  

ትንሽ መለስ ብለን ካየን፣ 1997 ምርጫና የተገኘው የተቃዋሚዎች ያልተጠበቀ አንጻራዊ ድል ያስበረገገው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ብዙ መቶ ዜጎችን ያለርህራሄ በአልሞ ተኳሾች አስገድሎ፣ ብዙ አስር ሺዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በየአስር ቤቶች በማጎር የህዝብን ተቃውሞ ለማፈንና አንገት ለማስደፋት፣ በዚህም የአገዛዝ አድሜውን ለማርዘም ተንቀሳቅሶ እንደነበረና በተወሰነ ደረጃም እንደተሳካለትና ያስከተለውም ጉዳት ይታወቃል።

ሆኖም ምን ያህል ጭቆናና አፈና ቢበረታም፣ ህዝብን መጀመሪያውኑ ለተቃውሞ ያነሳሱ ጉዳዮች እልባት እስካላገኙ ድረስ ፣የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር  ህዝብ ከደረሰበት ጭፍጨፋና የአካልም ሆነ የአአምሮ ጉዳት አገግሞ ወደ ቀጣይ ትግል ማምራቱ አይቀሬ ነው፣ በአገራችንም ያየነው ከዚህ የተለየ አልነበረም።

ይሄ ከደረሰበት መጠነ ሰፊ አፈና አገግሞ የተካሄደውን ዘርፈ ብዙ ህዝባዊ ትግል ታክኮ ነው የዛሬ ዘጠኝ ወር ግድም የለማ ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ መፈንቅለ አመራር በማካሄድ ስልጣኑን ለመቆጣጠር የበቃው።

መጠነ ሰፊውን ህዝባዊ ትግል ተገን አድርጎ መፈንቅለ አመራር በማካሄድ ወደፊት ብቅ ያለውም፣ በአብይ ጠቅላይ ምኒስቴርነት የሚመራው ኦዴፓ መራሹ የኢህአዴግ መንግስት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ካሰበው ፍጥነትና ጥልቀት በበለጠ ረጅም መንገድ በመጓዝ የተወሰኑ  የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስና በዚህም የህዝብን አመኔታና ቅቡልነት ለማግኘት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው

የህዝባዊ ትግል ስኬትም የሚለካው አንድም በተደራጅና በተቀናጀ  መልክ ትግል አካሂዶ ስልጣንን በመያዝ ተጠሪነቱ  ለህዝብ የሆነ መንግስታዊ ስርዓት በመመስረት የህዝብን  ጥያቄዎች በየተራ የማሳካት ሂደት ውስጥ መግባት ሲሆን፣ የተቀናጀና የተደራጀ አመራር ያለው ካልሆነ ደግሞ ሊያደርግ ወይንም ሊያሳካ የሚችለው፣ በሚያደርገው የትግል ግፊት ገዥው ቡድን ላይ ጫና በማሳረፍ፣ ቡድኑ ውስጥ ክፍፍል ፈጥሮ ከመሃላቸው የተሻለው ብቅ አንዲል በማስቻልም ጭምር  በመሆኑ፣ በኢትዮጵያችን ተከስቶ ያየነውም  ይሄንኑ  ነው።

ተቃዋሚ ድርጅቶች እነዚህ በአብይ መንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረግ ጉዞ እጅግ ጠቃሚ የሆኑና ሊበረታቱ የሚገባቸው መሆኑን አውቀው ለዴሞክራሲ ስርዓት በተደላደለ መሰረት መገንባት እንደ  አገር ገና ረጅም ርቀት መጓዝ እንዳለብን ሳይዘነጉና ተጨባጭ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ የትግል ስትራቴጂዎችንና ታክቲኮችን በማውጣት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ዕሙን ነው።

ሆኖም ከነዚህ ተቃዋሚ ነን ከሚሉ ወገኖች ዘንድ በአመዛኙ የሚታየው ግን ይሄንን ያገናዘበ መስሎ አይታየኝም።  የነሸጠው የእብድ ገላጋይ ይመስል፣ አብይ የኢህአዴግን ሕገ መንግሥትና ፓርላማ በአዋጅ እንዲያፈርስ፣ በብሄረሰብ የተደራጁ ፓርቲዎችን አፍርሶ ወደ ሲቪክ ማህበርነት እንዲለውጣቸው ሲመክር፣ ሌላው አብይ ተቃዋሚ የተባሉ የተበታተኑ ቡድኖችን  አስተባብሮ ወደ አንድ ድርጅት እንዲያሻግራቸው ሲለምን  ሌላው አስመራ ከትሞ አልፎ አልፎ መግለጫ ከማውጣት ውጭ አንዳችም ትግል ያካሂድ ያልነበረ ቡድን መንግስት ባመቻቸው መንግድ አውሮፕላን ተልኮለት ቦሌ ሲገባ ለረጅም ዓመት ለተካሄደው የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ክብር ለመስጠት  የመጣውን የህዝብ ብዛት አይቶ፣ ግላዊ ድጋፍ መስሎት ጦር መልምሎ ሀገር ከማመስ በላይ መንግስትን ዳግም  ካልተደራደረን ብሎ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ ሲፎክር ስመለከት ብልጭ ያለው የተስፋ ጭላንጭልን እንዳያጠፉብን ስጋት ጭምር ያሳድርብኛል  

አብዛኛው የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራር አባላት በልዩ ልዩ የግል ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቃለ ምልልስ ከመስጠት ውጭ ፣ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየበት ባለፈው ዘጠኝ ወር ስብሰባ ጠርቶ ሀዝብን ለማወያየት ጋዜጣ ወይንም መጽሄት በማተም ሃሳብን ለህዝብ ለማድረስ ብሎም የሃሳብ የበላይነትን ለማግኘት ያደረጉት ይሄኔ ነው የሚባል ጥረት አለመኖሩ እጅጉን አስገራሚ ነው።

አንዳንዶቹ ድርጅቶች ረጅም አድሜ ያስቆጠሩ ከመሆናቸው አንጻር የተከፈተውን የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ወደ ተግባራዊ  አንቅስቃሴ በመሸጋገር ህዝብ ከማደራጀትና መዋቅራቸውን ከመዘርጋት ይልቅ የዴሞክራሲ ስርዓት መጀመሪያውም መጨረሻውም የምርጫ መካሄድ አለመካሄድ ይመስል ገና የዛሬ ዓመት ተኩል ይካሄዳል ስለሚባለው ምርጫ መራዘም አለመራዘም ሲነታረኩ ይሰማል።

ህዝብን ስለ ማደራጀትና መቀስቀስ ፣አንድ ምሳሌ ብንወስድ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ዘርግቶት በነበረው አስከፊ ስርዓት ውስጥ አንድነት ይባል የነበረው ድርጅት መንግስት በጉልበት ድርጅቱን እስኪያፈርሰው ድረስ በነበረው ትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም ፣አማራጭ ሃሳቡን ለህዝብ ለማሰራጨትና ለማታገል በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚታተም ጋዜጣ እንደነበረውና የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ያካሂድ የነበረውን ሰልፍና ቅስቀሳ እናስታውሳለን።

ዛሬ ላይ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት የፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ግለሰቦች ጋዜጣ ወይንም መጽሄት በማውጣት ሃሳባቸውን በሰፊው ለማሰራጨት በሚታትሩበት ወቅት፣ ለሀገራችን የሚበጅ ከመንግስት የተሻለ ፕሮግራምም ሆነ የፖሊሲ አማራጮች አሉን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው፣ አለን የሚሉትን የተሻለ አማራጭ ወደ ህዝብ በጋዜጣ በመጽሄት ወይንም ማህበራዊ ሚዲያን በስፋት በመጠቀም ማሳመን የሚችሉበት ሥራ እስካልሰሩና ህዝብን እስካላደራጁ ድረስ፣ ምርጫው የዛሬ ዓመት ተካሄደ የዛሬ አምስት ዓመት ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም ብቻ ሳይሆን አንደ ፖለቲካ ስብስብ ፋይዳ ቢስ የመሆን አድላቸው የሰፋ ይሆናልና በጊዜ ሊያስቡበት ይገባል ።

 

                                                                         

 

Filed in: Amharic